መደማመጥና መነጋገር ከቻልን የማንፈታቸው ልዩነቶች የሉም!!!
January 13, 2012 In ርእሰ አንቀጽ
አገራችን እና ሕዝቧ በአንድ ጠባብ ዘረኛ ቡድን መዳፍ ውስጥ ናቸው። በአገራችን የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የግለሰብም ሆነ የቡድን መብቶቻቸው ተረግጠው በባርነት እየተገዙ፤ ጉልበታቸውና ሃብታቸው እየተመዘበረ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የምገኝ ዜጎችና ማኅበረሰቦች ሁሉ እጣ ፈንታችን ተሳስሯል። ሁላችንም ነፃ ካልወጣን በስተቀር ማናችንም በተናጠል የነፃነት አየር መተንፈስ አይቻለንም። ስለሆነም ለራሳችን የግልም የሆነ የቡድን ጥቅም ስንል እያንዳንዳችን ስለሁላችን ማሰብና መጨነቅ ግዴታችን ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከሁሉም የዲሞክራሲና የነፃነት ኃይሎች ጋር ተባብሮ ለመሥራት የሚያደርገው ጥረት ፍሬ እያፈራ ቢሆንም አሁንም የንቅናቄዓችንን አቋም በትክክል ያልተገነዘቡ ወገኖች እንዳሉ እንገነዘባለን።
ስለሆነም በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያለንን አቋም ደጋግመን ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።
1. ሥልጣንን በተመለከተ
ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥልጣን ምንጭ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆን ይገባዋል ብሎ ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል። ሁሉም የአስተዳደር እርከኖች አንድ ዜጋ አንድ ድምጽ ኖሮት በሚካሄድ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ብቻ የሚሾሙ መሆን ይኖርባቸዋል ብሎ ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል።
ግንቦት 7፣ ኢትዮጵያ የተለያዩ ማኅበረሰቦችና የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች አገር መሆኗን ያውቃል። ለእንዲህ ዓይነቱ አገር ያልተማከለ ፌደራላዊ የመንግሥት አወቃቀር የተሻለ ነው ብሎ ያምናል። በእያንዳንዱ ፌደራላዊ መንግሥት ውስጥም የዲሞክራሲ መሠረት የሆነው የአንድ ሰው አንድ ድምጽ መርህ መከበር አለበት ብሎ ያምናል።
ይህ መንገድ ነው በብዙሃን የሚደገፉ መሪዎችን ወደ ሥልጣን የሚያወጣልን።
2. መብቶችን በተመለከተ
ግንቦት 7፣ የግለሰብና የቡድን መብቶች መከበር ይኖርባቸዋል ብሎ ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል።
የቡድን መብቶችን ሰጥቶ የግለሰብ መብቶችን መንሳት ምንም አለመስጠት መሆኑ በተግባር ከመለስ ዜናዊ አገዛዝ የምናየው ነው። መለስ ዜናዊ ለብሄር፣ ብሄረሰቦች የክልል መንግሥታዊ መዋቅርን፣ አርማን፣ መዝሙርን፤ በቋንቋ መማርና መዳኘትን እና የመሳሰሉትን መስጠቱ ዘወትር የሚነግረን ጉዳይ ነው። እነዚህ ሁሉ ዋጋ ያላቸው ነገሮች የሚሆኑት ከግለሰብ ነፃነት መከበር ሆነው ቢሆን ነበር። ሰው የሰውነት ብሎም የዜግነት መብቱ ካልተከበረ የቡድን መብቱ መከበሩ ምን ትርጉም ይሰጠዋል? ፍትህ ሳይኖር በቋንቋው መዳኘቱ ተበዳይን ምን ይጠቅመዋል? የመረጠውን ሰው መሾም፤ የማይስማማውን መሻር የማይችል ከሆነ በስሙ የሚጠራ መንግሥት መኖሩ ምን ይፈይድለታል?
በሌላ በኩል ደግሞ ግንቦት 7፣ የግለሰብ መብቶች ብቻቸው በቂ ናቸው ብሎ አያምንም። እንደ ኢትዮጵያ ላለ ውስብስብ ታሪክ ላላት አገር የቡድን ፍላጎቶችና ስሜቶች በቸልታ ማለፍ አይቻልም። በግለሰብ ነፃነት ሥም የቡድን መብቶችን መደፍጠጥም ኢፍትሃዊ ነው ብሎ ግንቦት 7 ያምናል። በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ሃይማኖቶች ጠንካራ የቡድን ስሜትና ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል ይገነዘባል።
በዚህም ምክንያት ግንቦት 7 ለሁለቱም የመብት ዓይነቶች እውቅና የሚሰጥ ድርጅት ነው።
3. ትብብርን በተመለከተ
ግንቦት 7 የትብብር ጥሪ ሲያደርግ ሁላችንም በአገር ማዳን ስሜት እንነሳ በሚል ብቻ አይደለም። የተለያዩ ርዕዮቶች እና አስተሳሰቦች ባላቸው ቡድኖች መካከልም ትብብር ሊኖር እንሚችል ግንቦት 7 ያምናል። በአንድ ድርጅት ውስጥ እንኳን የተለያዩ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ቡድኖች ቢኖሩ ከእያንዳንዱ ጋር መተባበር ይቻላል ብሎ ያምናል።
ግንቦት 7፣ የአንድ ወገን እውነት የሁሉም ወገን እውነት ላይሆን እንደሚችል ይገነዘባል። ለመደማመጥ ዝግጁዎች ከሆንን የጋራ ችግሮቻችን በርካታ ናቸውና በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ ተመርኩዘን ትግላችን ማጎልበት ይገባል ብሎ በጽኑ ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል።
ግንቦት 7 ከዲሞክራሲና የነፃነት ኃይሎች ጋር መተባበር የሚፈልገው ዛሬ ተባብረን መታገላችን ለዘላቂው አብሮነታችን መሠረት ይጥላል ብሎ ስለሚያምን ነው።
መደማመጥ፣ መሰማማትና መነጋገር ከቻልን የማንፈታቸው ልዩነቶች የሉም።
No comments:
Post a Comment