Pages

Dec 12, 2012

የመድረክ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ዲያስፖራው እርስዎን ለምን አይወድም? በሚል በሃገር ቤት በሚታተመው ሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበላቸው

የመድረክ
ከፍተኛ
አመራር
የሆኑት
ፕሮፌሰር በየነ
ጴጥሮስ
ዲያስፖራው
እርስዎን
ለምን
አይወድም?
በሚል በሃገር
ቤት
በሚታተመው
ሰንደቅ ጋዜጣ
ለቀረበላቸው
ጥያቄ “ዲያስፖራው 50 ዶላር ከፍሎ በዛች 50 ዶላር መንግስት ለምን አትገለብጡም ይላል” ሲሉ ምላሽ ሰጡ።
ፕሮፌሰር በየነ ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት አብዛኛው ምላሽ አነጋጋሪ ነው። ያንብቡትና የ እርስዎን አስተያየት ያካፍሉን።
በነገራችን ላይ ሚኒሶታን ጨምሮ ለወራት በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የከረሙት ፕ/ር በየነ አንድም ህዝባዊ ስብሰባ
ከሕዝብ ጋር አላደረጉም። የየከተማው የመድረክ የድጋፍ ሰጪ ቻፕተሮችም ከሕዝብ ጋር እንዲነጋገሩ ሁኔታዎችን
እንዳላመቻቹላቸው ልብ ይሏል።
በዘሪሁን ሙሉጌታ
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የአራት ፓርቲዎች “ግንባር” የሆነው የመድረክ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው። ፕሮፌሰር በየነ
የግንባሩ የህዝብ ግንኙነት ቢሆኑም ከ2002ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ በኋላ የሚዲያ ተደራሽነታቸው ቀንሷል። በተለይ
ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እሳቸውን በተመለከተ ከተፃፉ ፅሁፎች ጋር በተያያዘ በመጠኑ ሻክሮ ቆይቶ
ነበር። ያም ሆኖ የተከሰቱ ችግሮችን በመተውና ለአንባቢዎቻችን ክብር በመስጠት ለቃለ-ምልልስ ተባብረውናል።
ለዚህም የፕሮፌሰር በየነ ተነሳሽነትና አርቆ አሳቢነት ሰንደቅ ጋዜጣ ትልቅ ክብርና እውቅና ትሰጣለች።
ባልደረባችን ዘሪሁን ሙሉጌታ በወቅታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካ እና በተያያዥ ጉዳዮች ከፕሮፌሰር በየነ ጋር አራት ኪሎ
በሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ፋክልቲ ፅ/ቤታቸው አግኝቶ ከአንድ ሰዓት በላይ ቆይታ አድርጓል።
የቆይታቸውም ውጤት የሚከተለውን ይመስላል።
ሰንደቅ፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ጊዜ በሚዲያ አይታዩም ምክንያቱ ምንድነው
ፕሮፌሰር በየነ፡- ሚዲያው እኔ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንዲያስተዋውቀኝ ወይም (promote) እንዲያደርገኝ ወይም
ያልተሟላ አጀንዳ ያለኝ ሰው አይደለሁም። ሊያናግረኝ የፈለገ ሚዲያ መጥቶ ያባረርኩት ሚዲያ የለም። ከዚህ ባለፈ
ግን በግድ ስሙኝ ብዬ የሚዲያዎቹን በር እያንኳኳሁ ቃለ-መጠይቅ አድርጉኝ የምል ሰው አይደለሁም። ስለዚህ
ከሚዲያ ሆን ብዬ የጠፋሁበት ምክንያት የለም። ምንአልባት የጠፋሁ የሚያስመስለው ከሰኔ ወር መጨረሻ አንስቶ
እስከ መስከረም መግቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበርኩም በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታመሙ፣ ሞቱ፣ አሉ፣ የሉም
በሚባልበትና በኋላም በለቅሶው ጊዜ እዚህ ሀገር አልነበርኩም። ለዚህ ነው ከሚዲያው ላልታይ የቻልኩት።
ሰንደቅ፡- በነገራችን ላይ ቢዘገይም በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት ምን ተሰማዎት
ፕሮፌሰር በየነ፡- እንደማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ሲሞቱ ማዘን ያለ ነው። መቼም በጦር ሜዳ ለመሞት እኔ ልቅደም፣
እኔ ልቅደም ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰብአዊ ፍጡር ተፈጥሮአዊ ሞት ሲሞት የሚደሰትበት ወይም የሚፈነድቅበት
ሁኔታ አይኖርም። እና እኔም እንደማንኛውም ዜጋ አዝኛለሁ። በተለይ በሽግግሩ ቻርተር ጊዜ አንስቶ ከማንኛው
የተቀዋሚ ፓርቲ አመራር በበለጠ የማወቃቸው ሰው ናቸው። ብዙ ጊዜ ፊት ለፊት ተነጋግረን እናውቃለን። ስለዚህ
የአካሄድና የአላማ ልዩነት ቢኖረንም የእሳቸውን ህልፈተ- ሕይወት እየተመኘሁና እየፀለይኩ የነበርኩ ሰው
አይደለሁም። 57 ዓመት አፍላ ዕድሜ ነበር ብዙ ቢቆዩ ጥሩ ነበር።
ሰንደቅ፡- ድንገት “መለስ ሞቱ” ሲባል ደንግጠው ነበር? በቀጣይስ ሀገሪቱ ምን ትሆናለች ሲሉ አሰቡ
ፕሮፌሰር በየነ፡- እንደማንኛውም ሰው የሚያስደነግጥ ነገር ሊኖር ይችላል። ሀገሪቱ ምን ትሆናለች ለሚለው
ኢህአዴጎች የተፈጠረውን ክፍተት ተሰካክተውም ቢሆን እሳቸው የቀየሱትን መስመር ተከትለው እንደሚሄዱ እምነቱ
ነበረኝ። ከዚህ ውጪ የፖለቲካ ክፍተት (Political Vacuum) ይፈጠራል የሚል ነገር በአዕምሮዬ አልነበረም።
ለዚህ ደግሞ የኢህአዴግን ፖለቲካ ስለማውቀው ነው። አቶ መለስ አብዛኛውን የቤት ሥራ ሰርተውታል። በላመ መሬት
ላይ የተዘራውን መሰብሰብ አዳጋች አይሆንም። “ፈለጋቸውን እንከተላለን” እያሉ እየተሽቀደዳደሙ ያሉትስ ለዚሁ
አይደል? ማን ለመለስ ባለሙዋል ይሆናል እያሉ ሽሚያ ላይ ያሉ ነው የሚመስለው። የእኔም ግምት ይሄው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ለዚሁ ዓላማ እንዳዘጋጁዋቸውም አውቅ ነበር። ነገር ግን ኢህአዴግ እሳቸው (አቶ
መለስ) ካስቀመጡት መስመር ከወጣ ገን ቀውጢን መጥራት ነው። ሕገ-መንግስቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሉ
ምክትሉ ተክቶ ይሰራል ስለሚል በዛው ቀጥለዋል። ከሕገ-መንግስቱም ባሻገር የአቶ መለስን ኀሳብ እንደወረደ
ከማስቀጠል ሌላ አማራጭ ያላቸው አይመስለኝም።
ሰንደቅ፡- አቶ መለስ አቶ ኃይለማርያም ተተኪአቸው እንዲሆኑ የፈለጉበትን ፖለቲካዊ እንደምታ ሊገልፁልኝ ይችላሉ
ፕሮፌሰር በየነ፡- መቼም የሰውዬውን አዕምሮ ጨርሶ ማንበብ አይቻልም። አቶ መለስ ግን አቶ ኃይለማርያም
የዓይናቸው ቀለም ስላማራቸው ብቻ ለሹመት አጭተዋቸዋል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል። በእኔ ግምት አቶ ኃይለማርያም
በጣም ውስብስብ በሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያደጉ አይደሉም። እሳቸው የቀለም ሰው ናቸው። እኛ በተማሪ
እንቅስቃሴ ያሳለፍነውን የማርክሲዝም፣ ሌኒኒዝምና የተራማጅ ፖለቲካ አቀንቃኝ አይመስሉኝም። ስለዚህ አቶ
ኃይለማርያም በአቶ መለስ ዙሪያ ካሉት በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ አልፈን መጥተናል ከሚሉት፣ በርዕዮተ ዓለሙም ግትር
ከሆኑት ታጋዮች የተሻለ አዳማጭ ይሆናሉ፣ የተማሩም በመሆኑ ለሚሰጣቸው አዳዲስ ኀሳቦችና ቀና አመለካከት
ይኖራቸዋል ብሎ መገመት ይቻላል። ነገር ግን የተከበቡት “ከማን አንሼ” በሚሉ የህወሓት ታጋዮች ነው። “ማንም
ከማን አባቱ ይበልጣል” የሚል አባባል ታጋይ ነበርን ከሚሉ ሰዎች ይታያል። እና አቶ መለስ በቀላሉ ከማይወርፍ ሰው
ጋር መስራት መርጠው ሊሆን ይችላል። ኃይለማርያምን ለስልጣን ያጩአቸው የፖለቲካ ድርቅና በሚያራምዱና ታጋይ
ነን በሚሉ ኃይሎች ተሰላችተውም ሊሆን ይችላል አቶ ኃይለማርያምን ከፊት ያመጣቸው በእርግጥ ይሄንን ስል ልሳሳት
እችላለሁ። ነገር ግን እንደ አንድ ታሳቢ ሊወሰድ ይችላል።
ሰንደቅ፡- አቶ ኃይለማርያም የተሰጣቸውን ከማስፈፀም ባለፈ ግልፅ የፖለቲካ ስልጣን የላቸውም የሚሉ ትችቶች
ሲሰጡ ይታያል። እርስዎም ይሄንን ትችት ይጋራሉ
ፕሮፌሰር በየነ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ከጅምሩ አስፈፃሚ ነው። አቶ መለስ ግን ከአስፈፃሚነት አልፈው ብዙ ነገር
ተቆጣጥረው ነበር። አሁንም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሳቸው ይህኑ ማለት ነው? ኢህአዴጎች ደጋግመው
እንዳሉት አመራራቸው ቡድናዊ አመራር ብለው ነበር። አሁን ግን የሁሉም ነገር አድራጊና ፈጣሪ አቶ መለስ ነበሩ
ብለውናል። ከትንሿ ተራ ሰነድ እስከ ትልቁ ዓላማ የነደፉት አቶ መለስ ናቸው ብለውናል።
የትብብር አመራር ሲሉ አንድ ነገር ሁሌ ትዝ ይለኛል። በሽግግሩ መንግስት ጊዜ እኔ የትምህርት ሚኒስትር በነበርኩበት
ጊዜ አንድ የአቶ መለስ ዋርድያ (ጠባቂ) ያለኝ ነገር እስከአሁን ድረስ አልዘነጋውም። እኔ ወደ እሳቸው ቢሮ ስሄድ
“ወዴት ነው የምትሄደው?” አለኝ። ወደ ክቡር ፕሬዝዳንት መለስ ጋር ነው (በዛን ጊዜ ፕሬዝዳንት ነበሩ) “ለምንድ
ነው?” ሲለኝ ቀጠሮ አለኝ አልኩት። በእውነቱ በወቅቱ እኔ ወደውጪ ሀገር ለመሄድ ተልዕኮ ስለነበረኝ ከእሳቸው ጋር
አንዳንድ ኀሳቦች ለመለዋወጥ ነበር። እና ያ ዋርድያ “ቁም” አለና ስማቸውን መጣራት ጀመረ። እንዴ … “አንተ
“የሀገርን መሪ እንዴት በራፍ ላይ ሆነህ ትጣራለህ” አልኩት። “እሱም ቢሆን የተሰጠውን ስራ ይሰራል፤ እኔም
የተሰጠኝን ኃላፊነት እወጣለሁ” አለኝ። በዛ ጊዜ እውነትም የጋራ አመራር አለ ይሆን? በሚል ለማስመሰል ይሞከራል።
ሁሉም የየራሱን የስራ ድርሻ በመወጣት እኩል ይመስለን ነበር። በተማረውም ሆነ ባልተማረው ታጋይ መካከል
የእኩልነት ምልክቶች ያሉ ይመስል ነበር። አሁን ግን በእሳቸው ስም ብቻ ሲማል ስናይ በሚባለውና በሚሰራው
መካከል ልዩነት መኖሩን ያመለክታል።
የሆነ ሆኖ አቶ ኃይለማርያምን ስልጣን ይኖራቸዋል ላልከኝ መቼም የስልጣን ክፍፍል አለ ይባል የለ? የተሰጣቸውን
የስልጣን ድርሻ ይጠቀሙበታል ብለን እንገምታለን። ይህ ሲባል ግን ጥርጣሬ ሊኖር ይችላል። የህወሓት ካድሬዎች
የጠቅላይ ሚኒስትሩን መስመር ለማዝለቅ ሲሉ ከዚህ መስመር እንዳይወጡ ከበው ይከላከሉዋቸዋል ብሎ መገመትም
ይቻላል።
ሰንደቅ፡- ከሰሞኑ ተጨማሪ ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተሹመዋል፤ ይሄንንስ እንዴት ያዩታል
ፕሮፌሰር በየነ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የመሾማቸው ምስጢር
በህወሓት ካድሬዎች የመከበባቸው ምስጢር ሊሆን ይችላል። አቶ ኃይለማርያም የሁለቱን ምክትል ጠቅላይ
ሚኒስትሮች ሲያሾሙ በሕገ-መንግስቱ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራና ተግባራት መካከል የእኔ ድርሻ ያሉት አንድ
ሦስቱን ብቻ ነው። የቀረውን ደግሞ በክላስተር ነው … በምናምን ብለው አሳልፈው ሰጥተዋል። ይህም ማለት ጠቅላይ
ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ብቻቸውን ሲሰሩት የነበረውን ስራ ለአራት ተካፍለውታል። ይህም ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ነው።
ከዚህ ቀደም የቀድሞ የፓርላማ አባል በነበርኩበት ዘመን ይህ አሰራር ተግባራዊ ሲደረግ ተቃውመናል። ሹመቱ
ኢህአዴግ በራሱ ተነሳሽነትና በማንአለብኝነት የሚሰጠው በመሆኑ “በሕግ አምላክ” ስንል ተቃውመናል።
ሕገ-መንግስቱ አንድ ጠቅላይ ሚኒሰትር ነው የሚለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ነገር ቢሆኑ፤ ‘‘ተክተው ይሰራሉ’’
ሳይሆን ‘‘ተክቶ ይሰራል’’ ነው የሚለው። ይህም ከሕገ-መንግስቱ አንፃር አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሾም
ያመለክታል “ሕገ-መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው። ማንኛውም ሕግና ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግስት
አካል ወይም የባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ-መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት የለውም” በሕገ-መንግስቱ
አንቀፅ ዘጠኝ ንዑስ አንቀፅ አንድ ላይ ሰፍሮ ይገኛል። በንዑስ አንቀፅ ሦስት ደግሞ ከዚህ ሕገ-መንግስት ከተደነገገው
ውጩ በማንኛውም አኳሃን የመንግስት ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው ይላል። በተጨማሪም በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ
75 ላይ ስለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በሚዘረዝረው ድንጋጌ ላይ “ሚኒስትር” እንጂ “ሚኒስትሮቹ” በሚል
ብዙሕነትን አያሳይም። ለምሳሌ በዚሁ አንቀፅ “ሀ” ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይተው
የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል ይላል እንጂ “ያከናውናሉ” አይልም በ“ለ” ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሰራሉ
አይልም። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው ይላል እንጂ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ
አይልም። ሌላው በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 36 ላይ የሚኒስትሮችና ምክር ቤት ማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምክትል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሚኒስትሮች በሕግ በሚወሰነው መሠረት ሌሎች የሚገኙበት ምክር ቤት ነው ይላል። ስለዚህ ሕገ-
መንግስቱ ተጥሷል። የሚገርመው “በሚኒስትር ማዕረግ” እያሉ ፓርላማው ያላፀደቀላቸው ከአራት በላይ ሰዎች አሉ።
“ሚኒስትር” ብለው ወደ ፓርላማው አያመጡም። ይሄ ደግሞ ኢ-ህገመንግስታዊነት ነው። አሁንም ይሄ ሁሉ የምክትል
ጠቅላይ ሚኒስትር ጋጋታ ምን የሚሉት ነገር ነው? እነዚህ የተሾሙት ሰዎች በሕገ-መንግስቱ መሠረት ተጠያቂ ናቸው?
እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አንድ ነገር ቢሆኑስ ማን ነው የሚተካቸው? ሦስቱም በአንድ ጊዜ ጠቅላይ
ሚኒስትር ሊሆኑ ነው ወይስ ምንድነው? ሕገ-መንግስቱ በአማርኛ ነው የተፃፈው “ነው” እና “ናቸው” ‘‘ሚኒስትሮች’’
እና ‘‘ሚኒስትሩን’’ አናውቅም እንዴ?
ሰንደቅ፡- ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የተሾመበት ምክኒያት ስራን ለማከፋፈልና ለማፋጠን ነው ተብሏል።
በሌላ ወገን ደግሞ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ስልጣንን የማጋራት ይመስላልና የእርስዎስ ኀሳብ ምንድ ነው
ፕሮፌሰር በየነ፡- ገዢው ፓርቲ የሰከነና የበሰለ ቢሆን በአደባባይ እንደሚናገሩት እምነት ኖሮአቸው በጠቅላይ
ሚኒስትርነት ያስቀመጡትን ሰው ማገዝ ነበረባቸው። አሁን ግን ስልጣንን በኮታ የተከፋፈሉት ነው የሚመስለው።
ከተማው ውስጥ፤ ስልጣን ለአማራ፣ ለትግሬ፣ ለኦሮሞና ለደቡብ እያለ እንደሚያወራው ነው እነሱም የተከፋፈሉት።
ሰው እንኳ የሚያወራው ጊዜ ለማሳለፊያ ቢሆንም፤ እነሱም ወሬውን ሰምተውና ተከትለው ለወሬው ምላሽ የሰጡ ነው
የሚመስለው። ይሄ ደግሞ በጣም የሚያሳፍር ነው። ሰውዬውን (አቶ ኃይለማርያም) በተለየ ሁኔታ መደገፍ ሲገባቸው
ስልጣንን እንደ ፀበል ነው የተራጩት “ክላስተር” የሚል ነገር ደንቅረው ተራው ሰው የማይገባውን ነገር እየከተቱ
የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማአት ያዥጎደጎዱት በመካከላቸው መተማመን ባለመኖሩ ነው። ይሄ ደግሞ በኢህአዴግ
አመራር ውስጥ መተማመን የለም የሚለውን ስነ-ልቦና የሚያሰርፅ ነው።
ሌላው “ታላቁ መሪ” በሚል የተጀመረው ነገር ነው። ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን የራስዎት ሰው
ይሁኑ ብያለሁ። አሁን ግን በቻይና ፖለቲካ የቀረውን የመሪን ተክለሰብዕና የመገንባትን ጉደይ በሰፊው ተያየዘውታል።
በዕርግጥ አቶ መለስ እያሉ በ2002ቱ ምርጫ ወቅት እኛ ለምርጫ ቅስቀሳ እንዳየነው፤ ምስላቸው ደቡብ ኦሞ ድረስ
ጫቃ ላይ ሁሉ ተሰቅሎ ነበር። እሳቸው ይወዳደሩ የነበረው እዛ ሰሜን አድዋ ሆኖ እያለ ደቡብ ኦሞ ምስላቸው
በየጫካውና በእየሾሁ ላይ በዛፍ ግንድ ላይ ሳይቀር ተሰቅሎ ነበር። እኛ አድዋ ላይ ምስላችንን ብንሰቅል ግን ሕገ-ወጥ
ብለው ያስሩን ነበር። አሁን ደግሞ ለይቶለታል። ቻይናዎች የማኦሴቱንግን የግል አምልኮ እራሳቸው በኮሚኒስት ፓርቲ
ውስጥ የታገሉት በእኛ ግን “ኸረ አበዛችሁት” የሚል ነው የጠፋው። አንድ ሰሞን አቶ ስብሃት ነጋ አቶ መለስ በህይወት
አሉ ወይስ የሉም ሲባል “አቶ መለስ በግለሰብነት ቢኖርም ባይኖርም ፓርቲው ይቀጥላል” ያሉትን አሁን መድገም
አቅቷቸዋል። አሁን “ታላቁ መሪ” የሚለው ጫጫታ ሲበዛባቸው አስተያየት መስጠት አቁመዋል። ዞሮ ዞሮ ይሄ ጠቃሚ
እንዳልሆነ የዓለም ታሪክ ያሳያል። ከቻይናም ይሄንንም ሊማሩ በተገባ ነበር።
ኢህአዴጎች በራሳቸው ስለማይተማመኑ ሁሉም ነገር በአቶ መለስ ዙሪያ ያደረጉት የፖለቲካ መስመሩን በመንደፉ፣
ለውይይት የሚበቃ ሰነድ በማዘጋጀቱም ሆነ በሌላ በልማት ዙሪያ እራሳቸውን ያላዘጋጁ መሆኑን ያሳያል። ፈረንጆቹ
እንደሚሉት የቀሩት ኢህአዴጎች Foot Soldier ወይም ለመሰማራት የተዘጋጁ እንጂ የሚያስቡ የሚያጠኑ ወይም
የሚመራመሩ አልነበሩም ማለት ነው። በተቀደደ ቦይ የመፍሰስ ነገር ነው።
ሰንደቅ፡- ቀድሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ህልፈት በኋላ በቀጣይ ዓመታት በኢህአዴግ ውስጥ የኀሳብ ልዩነት
ተፈጥሮ በኬኒያ እንደታየው ሁለት ተቀናቃኝ ኃይል ሊፈጠር እንደሚችል የሚገምቱ ወገኖች አሉ፤ ይህ አካሄድ
በኢህአዴግ ውስጥ ምን ያህል ርቀት ይጓዛል
ፕሮፌሰር በየነ፡- የኬኒያን ምሳሌ እንዴት ታመጣለህ? ኢህአዴግ እኮ መነሻው እንደ አለሎ ድንጋይ የጠጠረ
ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም፣ ማኦሴቱንግ የወጣ ቡድን ነው። የእነ መለስ የርዕዮተ ዓለም መተክላቸውና ያደጉበት ጠጣር
አቋም አላቸው። የኬኒያ ግን ፖለቲከኞች ገንዘብ ሲያገኙ እኔ ከእገሌ እለያለሁ የሚሉ ገራገር ፖለቲከኞች ናቸው።
ገንዘብ ሲያገኙ እኔ ከእገሌ አለያለሁ የሚሉ እንጂ ጠጣር አይደሉም። ኢህአዴግ እኔ ያልኩት ካልሆነ በመቃብሬ ላይ
የሚል ኃይል ነው። ኢህአዴግ ግትር ነው አይታጠፍም። አጥፈዋለሁ ብትል ይሰበር ይሆናል እንጂ አይታጠፍም።
ፈረንጅንም እንዴት ማታለል እንደሚችሉ ተክነውበታል። እኛ እኮ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር አለ ለማለት’ኮ
ተቸግረናል።
ሰንደቅ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሕልፈትና ያንንም ተከትሎ በመጣው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተቃዋሚዎች ተጠቃሚ
የሚሆኑበት ዕድል አለ
ፕሮፌሰር በየነ፡- በሰው ህይወት ውስጥ ለውጥ እንደሚመጣ ባላሰብክበት ጊዜ ሁሉ በፖለቲካ ህይወት ውስጥም
ለውጦች ሊመጡ ይችላሉ። በምን አጋጣሚና ሁኔታ የሚለው ቁርጥ አድርጎ መተንበይ አስቸጋሪ ቢሆንም ተቃዋሚ
ድርጅቶች አደረጃጀታቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
ሰንደቅ፡- ተቃዋሚዎች ባለፉት 21 አመታት ኢህአዴግን አልቻላችሁትም እኮ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- እያስጨረስናቸው ነው። ማለቴ ሁልጊዜ ምርጫ ሲሉ ሂደቱን እናግዛለን በማለት የተቃዋሚ ካምፕ
በተለይ ሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሰው እንደሁኔታው የሚቀያየር ነው። በአንድ ሁኔታ ተስፋ ቆርጦ ቤቱ የሚገባ
አይደለም። ይሄንን ስርዓት እስከተቻለ ድረስ እየተነቀነቀ መቆየት አለበት። ተቃዋሚ ዝም ብሎ ስልጣን መያዝ ብቻ
አይደለም። በሂደት ሕዝብ ያነቃል ያስተምራል ያለውንም ስርዓት ያጋልጣል።
ሰንደቅ፡- ሃያ አንድ አመት ሕዝብን ለማንቃትና ለማስተማር በቂ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ’ኮ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- በእኔ እምነት ትእግስት የሚያሳጣን ምክንያት የለም። ሌላ ቀርቶ በዲሞክራሲ አምስት መቶ አመት
ሞልቶአቸዋል በሚባሉ አገሮች እንኳ 40 እና 50 አመት ከታገሉ በኋላ ወደ ስልጣን የመጡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች
አሉ። ለምሳሌ የሜክሲኮ ፓርቲ 70 አመት ሙሉ አንደ ፓርቲ ነው ሲገዛ የኖረው። በዚህ ጊዜ ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች
የሉም ማለት አይደለም። ፈረንሳይ ሀገር ሶሻሊስት ፓርቲ ከ40 አመት በኋላ ነው ስልጣን ላይ የወጣው። የፖለቲካ
ስርዓቱ እንደኛ ሀገር ፅንፍ የረገጠ በማይሆንበት ሁኔታ ስልጣን ላይ ባይወጡም በሂደት ልዩነት ያመጣሉ።
ሰንደቅ፡- ይሁን እንጂ የፖለቲካ ስርዓቱ አልተስተካከለም እያላችሁ ባለበት ሁኔታ አሁን ካለው ትግል ይልቅ እጅን
አጣጥፎ መቀመጥ ይሻላል የሚሉ አሉ። እናንተም ቢሆን በከንቱ ከምትደክሙ አርፋችሁ ብታስተምሩ ይሻላል የሚል
ክርክር አለ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- የለም… የለም… አሁን ለምሳሌ በጃፓን እንኳ ሶሻሊስት ፓርቲ ነበር። ስልጣን ላይ ወጥቶ የማያውቅ
ነገር ግን ሁልጊዜ ፓርላማ ውስጥ ይገባል። በገዥው ፓርቲ ላይ ውጥረት ይፈጥራል። እንዲህ እያለ ሕዝቡ ችግር ላይ
እንዳይወድቅ እየተከታተለ የሚቀጥል ፓርቲ አለ። የእኛ ሀገር ከዚህ ለየት የሚልበት ገዥው ፓርቲ ጨርሶ ለማዳመጥ
ፈቃደኛነቱ የሌለው መሆኑ፣ ጠርዝ የረገጠ አመለካከት የሚከተል በመሆኑ ነው። ክፋት፣ ቂም በቀለኛ እና ጨካኝ
በመሆኑ ነው።
ሰንደቅ፡- በእናንተ በኩል ችግር አለ። ሕዝብ ማደራጀት አልቻላችሁም የሚል ኀሳብ አለ። ሕዝብ ሳትይዙ ገዥውን
ፓርቲ ማንበርከክ አትችሉም እየተባለ ነው?
ፕሮፌሰር በየነ፡- ሕዝቡን ከዚህ በላይ እንዴት እንያዝ? ሕዝብ ላለመያዛችን ምን ማስረጃ አለ? ኢህአዴግ ሕዝብ
አልያዙም ብሎ ካሰበ ለምነ የምርጫውን መድረክ ክፍት እያደርግም? ሕዝቡን ለምን አንድ ለአምስት አደራጅቶ ድምፅ
እንዲሰጡት ያደርጋል? እኛ ሕዝብ የመያዝ ጉዳይ ችግራችን አይደለም። የማያውቁ ሰዎች ግን ሕዝብ አልያዙም ብለው
ሊያወሩ ይችላሉ። ተቃዋሚዎች ደካማ ናቸው ይሉናል። ደካማ ከሆንን ኢህአዴግ ለምን ይፈራናል? ስጋቱስ ከየት
መጣ? በ1997 ትንሽ በሩ ገርበብ ሲደረግ ሮጠን ስንገባ ኢህአዴግ ደነገጠ። እና ተቃዋሚዎች ደካማ ናቸው የሚለው
አልባሌ ወሬ ነው።
ሰንደቅ፡- መድረክ ከእነችግሩም ቢሆን ለምን የስነ ምግባር ደንቡን በመፈረም የተዘጋውን የድርድር በር አይከፍትም?
ፕሮፌሰር በየነ፡- የእነሱን እልህ ለመወጣት ብለን በሚሆነውም በማይሆነውም ይፈረማል እንዴ? እነ በረከት
እንደሚያውቁት ድርጅቴን በመምራት ብዙ ጊዜ ተፈራርመናል። ነገር ግን ፊርማው ከተፈረመበት ወረቀት ዋጋ የሌለው
ነገር እየሆነብን ነው የተቸገርነው። አቶ በረከት እንደ ሀገር መሪ በቁም ነገር ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል። በየነን
አንበርክኬ አስፈረምኩት ማለት ምን ዋጋ አለው። አቶ በረከት በመፅሐፋቸው ላይ ‘‘አቶ መለስ ይሄንንማ እነ በየነ እሺ
ብለው አይፈርሙም’’ እያሉኝ እንደምንም እጃቸውን ጠምዝዤ አስፈረምኩ ማለታቸው ነውረኝነት ነው። በ1997
ቀውጢ ወቅት ሰላም ፍለጋ ላይ በነበርንበት ወቅት፤ አመፀኛ ከምትሏቸው ጋር እነርሱም ስላሉ ሳይሆን ምንም አይነት
ድርጅታዊ ቁርኝት የለንም ብለን ፈርመን ነበር። ያ ደግሞ የእውነታችን ነው። እኛ በነውጥና ጉልበት ለውጥ ላምጣ
ከሚለው አካል ጋር ውል የለንም። አሁንም የለንም። ይሄንን ይዘው እጃቸውን ጠምዝዤ አስፈረምኩ አሉ። አቶ በረከት
ገና በረቂቅ ላይ ለመነጋገር የተቀመጠውን ነገርና በመጨረሻ ይሄ ይግባ ይሄ ይውጣ ብለን የፈረምነውን ሳይለዩ
በመፃፋቸው ነው የፃፉት። ይሄ ደግሞ በጣም የሚያሳፍር ነው። የሀገር መሪ ሆነው የመንደር ልጆች አይነት ሽወዳ
መውረድ ደረጃችንን አይመጥንም።
የስነ ምግባር ደንቡ በተመለከተም አንደኛ ሕግ አድርገውታል። ሕግ አክባሪ ድርጅቶች ስለሆነ እናከብራለን።
ኢህአዴጐች የተባሉት (የተሸወዱት) የስነ ምግባር ደንቡን ወስደው በፓርላማቸው ሕግ ማድረጋቸው ነው። ሕግ
ባያደርጉ ኖሮ አሁን የሚሉትን ነገር ማንሳት ይችሉ ነበር። ነገር ግን አሁን ሕግ ሆኗል። የቀረው ነገር የእነበረከት እልህ
ነው። እና የበረከትን እልህ ለማርካት ስል ሄጄ ተንበርክኬ አልፈርምም። ይሄንን ዕድል ዕድሜ ልክ አያገኙትም። ምን
ሊያደርግልን?
ሰንደቅ፡- ኢህአዴግ የአመራር መተካካት ሲያደርግ በተቃዋሚ ጎራ በተለይም የእርሶ ፓርቲ እርሶዎን በሌላ አመራር
መተካት አልቻለም የሚል ወቀሳ ሲቀርብብዎ ይደመጣልና ስለዚህ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- እኔ የድንጋይ ዳቦ ዘመን ሰው አይደለሁም። 60 ገብቼአለሁ። ነገር ግን የስራ ፈት ወሬ ነው። አቶ
መለስም የተፈጥሮ ሞት ስለወሰዳቸው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር አየን እንጂ ምኑን ነው የተተካኩት። ማን በማን ነው
የተተካው? የመለመሏቸው ካድሬዎች ገና ወጣቶች ናቸው። የቀሩት ደግሞ አንጋሽ (king maker) ሆነው ከበው
ነው ያሉት። አሁን አንጋሾቹ ባለሙሉ ስልጣን ሆነው፣ የሀገሩን ኢኮኖሚ ተቆጣጥረው ማንን ነው የተኩት? ይህን ወሬ
የሚያስወሩት ኢህአዴግን ጠንቅቀው የሚያውቁትን የተቃዋሚ አመራሮች በምላሳቸው በመተንኮስ ካባረሩ በኋላ
የቀረውን በልምጭ እንነዳዋለን የሚል ፍላጎት ስላላቸው ነው። እኛ ከተማሪ ንቅናቄ ጀምሮ የህወሓት አባላት እነማን
እንደሆኑ እናውቃለን። እና ተቃዋሚውን በልምጭ እንነዳዋለን ብለው ነው ይሄንን የሚያስጮሁት። ይሄ ነገር ከሆነ
ቦታ ቱስ ያደርጉና እንደ ቄንጥ ‘‘መተካካት’’ እያሉ እንደ ባዶ በርሜል ይጮሃሉ። የእኛ ችግር የዕድሜ አይደለም እስቲ
የፖለቲካ ምህዳሩን ክፍት ያድርጉና የሚዳደር ወጣት እንጣ? በተማሪ እንቅስቃሴ ያለፈው ትውልድ የሚከበር ነው።
በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በርካታ ታሪክ የፈፀመ ትውልድ ነው። እስካሁንም ድረስ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለ
ወገን ነው እንጂ እንደማንም ዝም ብሎ ሆዳም አይደለም። ፎቅ እየካበ ሀብት እያካበተ የተቀመጠ አይደለም። ያ
ትውልድ አድር ባይ አይደለም። ገንዘብ የለመደ፣ አየር ባየር ነጋዴ ሳይሆን ሕይወቱንና ጊዜውን ለትግል የሰው ናቸው።
እና ‘‘መተካካት’’ እያሉ የእኛን ስም መስማት የመይፈልጉ ከሆነ እኛ ምን እናድርጋቸው ታዲያ?
ሰንደቅ፡- በአብዛኛ ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራ) እርሶዎን የማይወዱዎት ለምን ይሆን?
ፕሮፌሰር በየነ፡- በመጀመሪያ ዲያስፖራውን አንተ ማወቅ አለብህ። ዲያስፖራውን ካላወቅክ ለምንድነው የሚለው
አይገባህም። እኔ በእርግጥ የራሴ ሰው ነኝ። አንዳንዶቹ የድርጅቶችን ነፃነት የሚጋፉ ናቸው። አንድ ስብሰባ ላይ መጥቶ
50 ዶላር ከፍሎ በዛች 50 ዶላር መንግስት ለምን አትገለብጡም ይላል። ያለው ኢህአዴግ ደግሞ የማይፈለጥ አለት
ነው። ዛሬ የተቃዋሚ አባል መሆን ፈተና ነው። ነገሩ የሂደት ጉዳይ ነው። ባለን አቅም ነው የምንገፋው። ቤቱን ሸጦ
ተቃዋሚ ፓርቲ እያንቀሳቀሰ ያለ የፓርቲ አመራር በመሀከላችን አለ።
ሰንደቅ፡- በተጨባጭ ቤቱን የሸጠ ሰው አለ?
ፕሮፌሰር በየነ፡- ይሄን በእርግጥ ግለሰቡ ሊናገረው ይችላል። ቢያንስ እኔ ስለማውቅ ነው። ቤታችሁ አትገቡም ወይ
ከምንባላውስጥ ቤት የሌላቸውን ስለማውቅ ነው። እና ወደ ዲያስፖራው ስመለስ ጯሂውን ከሰከነው መለየት
ያስፈልጋል። እና እኔ የጯሂው ዲያስፖራ ተላላኪ መሆን አልችልም። ነገር ግን ተባብሬ መስራት ግን እፈልጋለሁ። እና
አንተም የጯሂውን ድምፅ ነው የሰማኸው። ብዙ ግን የሰከኑ ኢትዮጵያውያን አሉ። ይሄ የፖለቲካ መልከኛ መሆን
የሚፈልገውን ጯሂውን ዲያስፖራ መተው ነው።
ሰንደቅ፡- ባለፉት 21 አመታት ብዙ ሰው ሲታሰር እርሶዎና ዶ/ር መረራ ታስረው አያውቁም የሚል ይባላልና…?
ፕሮፌሰር በየነ፡- እኛ በግ ነን እንዴ ኢህአዴግ በፈለገ ጊዜ የሚያስረን? ይሄ ደግሞ ካልተዋጠላቸው ሄደው ኢህአዴግን
ይጠይቁት። ኢህአዴግ ለእኛ የሚላላኩትን ታጋይ ልጆቻችንን እያሰረ አይደለም እንዴ? ይሄ ሁሉ አላዋቂነት ነው።
ሕዝብ ስላገለገልን መታሰር ያለብን አይመስለኝም።

1 comment:

  1. The professor has also said ,there are good people in the diaspora.So ,i dont know why the writer wants to focuse on the "bad diaspora" stuff.And the professor is right when he said " some in diaspora wants a quick result".Its true that ,some in the diaspora wants a quick fix for the complicated problem of ethiopia.Struggle is a process and needs a longer organized struggle.Leave the professor alone or atleast be fair in your criticism.

    ReplyDelete

Total Pageviews

Translate