Pages

Dec 26, 2012

ኢትዮጵያውያን ሴቶች ወደ ዱባይ ለሥራ እንዳይሄዱ በህግ ታገዱ


ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት  ሴቶች ወደተባበሩት አረብ ኢምሬት(ዱባይ) ለሥራ  እንዳይሄዱ በህግ ማገዱን አስታወቀ።ህገ-ወጥ ጉዞው ግን እንደቀጠለ ነው አለ።
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ ፥ በጉብኘትና በግል ቪዛ በቤት ሰራተኛነት ለመቀጠር ወደ ዱባይ የሚያደረገው ጉዞ እንዲቆም የተደረገው ራስን ለከፋ ችግር የሚዳርግ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ዜጎች ህጋዊ ጥቅሞቻቸውና መብቶቻቸው ተጠብቀውላቸው እንዲሰሩ የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ ሀገራት ጋር የንግድ የሰራተኛ ቅጥርና የተለያዩ ውሎች  ስምምነት አለው  ያሉት ዳይሬክተሩ፤ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ ስምምነት የተፈራረመችው ከሳውዲ አረቢያና ከኩዌት ጋር ሲሆን ፥ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋርም ተመሳሳይ ስምምነት ላይ ለመድረስ  ገና በሂደት ላይ  ትገኛለች ብለዋል።
<<ወደ ዱባይ   የሚደረግ ጉዞ ለዜጎች ደህነነት ሲባል ቢከለከልም፤ በህገ ወጥ መንገድ የሚደረገው  ጉዞ ግን  አሁንም አልቀረም።>>ብለዋል-አቶ ግርማ።
መንግስት ወደ ዱባይ ለቤት ሰራተኝነት የሚደረገው ጉዞ እንዲቆም ያደረገው ፥ በዚህ ጉዞ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለከፋ እንግልት የሚዳርጉ ውስብስብ ችግሮችን ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግስት ጋር በመመካከር ለመፍታት ነው ሲሉም አክለዋል።
ዜጎች ከሁሉም በላይ በሀገራቸው ባለው የስራ አማራጭ ለመጠቀም መጣር አለባቸው ያሉት አቶ ግርማ ፥ ጉዞ ካስፈለገም ህጋዊ መንገድን ተከትሎ ብቻ በመሄድ መስራት እንደሚገባ መናገራቸውን የፋና ዘገባ ያመለክታል።
ይሁንና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነት ያለው  ከሳዑዲ አረቢያና ከኩዌት መንግስታት ጋር ነው ቢሉም፤  አለ የሚሉት ውልና ስምምነት  በተጠቀሱት አገሮች  ያሉትን ኢትዮጵያውያን ከመከራ ሊታደጋቸው አልቻለም።
በሳዑዲና በኩዌት  በሚገኙ  በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይም  ከዱባይ ባልተናነሰ መልኩ በተደጋጋሚ ዘግናኝ በደልና ግፍ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate