ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ውሀና ፍሳሽ ተቋም ለኮንትራክተሮች ሰጥቶ ለፍሳሽ ማስወገጃ በተቆፈረው ከ 70 ደረጃ ወደ አፍንጮ በር በሚያስወጣው ጠባብ መንገድ ላይ በቁፋሮ ስራ ላይ የነበሩ የቀን ሰራተኞች ከ7 ሜትር ጥልቅት በላይ የሚቆፍሩት መሬት ተደርምሶ አራቱን ሰራተኞች እዛው እንደቀበራቸው የተናገሩት የስራ ባልደረቦቻቸው ሲሆኑ፣ ሁለቱ ሰራተኞች ግን የአካባቢው ወጣቶች ተሰባስበው ለህይወታቸው ሳይሳሱ በገመድ በመጎተት እና የተጫናቸውን ናዳ በቁፋሮ በማስለቀቅ በህይወት ታድገዋቸዋል።
የፌደራል የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ኤጀንሲ ከቀኑ 7 ሰአት ላይ አደጋው እንደተከሰተ ቢደርስም ገመድ ከማቀበልና መሰላል ከመዘርጋት የዘለለ ተግባር አላከናወነም ሲሉ የተቹት ሰራተኞች ፣ የአካባቢው ወጣቶች እና ነዋሪዎች ርህራሄ የተሞላበት ትብብር በማድረጋቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በጠዋቱ ፈረቃ ጀምረው በትጋት ሲሰሩ ነበር ስትል ለዘጋቢያችን የገለጸች የአካባቢው ነዋሪ ፣ 7፡30 አካባቢ መሬት ተደርምሶ አደጋው ቢደርስም በቦታው ፈጥነው የደረሱት የእሳት አደጋ ሰራተኞች ፣ በርካታ ፌደራል ፖሊሶች እና የአዲስ አበባ ፖሊሶች ህዝቡን ከማገድ በስተቀር የሰሩት ስራ አልነበረም ስትል ወቀሳ አቅርባለች። የአካባቢው ወጣቶች ተፍጨርጨረው ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ አንደኛውን ቀን ሰራተኛ ያወጡት ሲሆን ከወገቡ በታች በጥልቀት የተያዘውን ሰራተኛ ደግሞ ከቀኑ 11፡15 ላይ ወገቡን በገመድ አስረው በትብብር መንፈስ ሊያትረፉት ችለዋል።
ከዚህ በሁዋላ የፌደራል ፖሊስ አባላት የመቆፈሪያ መሳሪያዎችን በመጠቀም የሌሎችን አስከሬኖች አውጥተዋል።
No comments:
Post a Comment