ኢሳት ዜና:-ከስኳር ልማት ጋር በተያያዘ በአፋር አካባቢ የሚደርሰው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መጨመሩን የአካባቢው ተወላጆች ተናግረዋል።
ህዳር 20 ቀን 2005 ዓም በዱብቲ ወረዳ ቀይ አፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ፋጡማ ኡህመድ ገዶ የተባለች የ11 አመት ልጅ ተደፍራ መሞቷን የልጂቱ አጎት ለኢሳት ገልጸዋል። ልጂቷን የደፈሩት ሰዎች መንግስት ለስኳር ልማት ስራ ብሎ ያመጣቸው ሰራተኞ ች ይሁኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለማወቅ እንዳልቻሉ የልጂቷ አጎት ገልጸው፣ ይሁን እንጅ የአፋር ተወላጆች እንዲህ አይነት ድርጊት እንዳልፈጸሙ በእርግጠኝነት ተናግረዋል። የአካባቢው ባለስልጣናት ጉዳዩን ይፋ ቢያወጡ እርምጃ እንደሚወስዱባቸው እንደዛቱባቸው የልጂቷ አጎት ገልጸው፣ በድርጊቱ የተበሳጩ የጎሳው አባላት ተቃውሞ እንዳያሰሙ የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው እንዲሰፍር መደረጉን ተናግረዋል።
በአካባቢው ምንም ሰላም እንደሌለ የተናገሩት ነዋሪዎች ፣ ለስኳር ልማቱ ቤታቸውን እንዲያፈርሱ ተጠይቀው ፈቃደኛ ያልሆኑ በርካታ ሰዎች ወደ እስር ቤት መጓዛቸውንም ገልጸዋል።
በቅርቡ ደግሞ ሩቢ ኢብራሂም አሊ የተባለች የ8 አመት ህጻን በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍራ ወደ አዲስ አበባ ጦር ሀይሎች ሆስፒታል መላኩዋን እስካሁን ድረስ ሊሻላት እንዳልቻለ አንድ በአፋር ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ እናት ተናግረዋል። ግለሰቡዋ ኢሳት ችግራቸውን ለመዘገብ ስለደረሰላቸውም ምስጋና አቅርበዋል
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአፋር ሰብአዊ መብቶች ድርጅት ሃለፊ የሆኑት አቶ ገአስ አህመድ ለኢሳት እንደተናገሩት ከስኳር ልማት ጋር በተያያዘ በአካባቢው ያለው ችግር እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸዋል።
በክልሉ ያለውን ችግር ለአለማቀፍ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ድርጅታቸው እየሰራ መሆኑንም አቶ ገአስ ገልጸዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ የአፋር ገድሌ እየተባለ የሚጠራው ታጣቂ ሀይል በአፋር አካባቢ መንቀሳቀሱ መሰማቱን ተከትሎ ዞን 1 እዳር ወረዳ አካባቢ ያለው ሰራዊት ተንቀሳቅሶ ህዝቡ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ እና ታጣቂው ሀይሉን እንዳይቀላቀል ኬላዎች መዘርጋታቸውን የአፋር ጋድሌ ወታደራዊ ጉዳይ ዋና አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል መሀመድ አህመድ ተናግረዋል
No comments:
Post a Comment