Pages

Jan 7, 2013

የሙስሊም ሓበሾች የነጻነት ትግል ከግንቦት20 እስከ ግንቦት 20

የሙስሊም ሓበሾች የነጻነት ትግል ከግንቦት20 እስከ ግንቦት 20
አቡ ዘኪያ
ከምድረ-አናቶሊያ
“እስላም እሚያርድ እንጅ እሚወድ አይመጣም፣
የፈራህ ሰው ውጣ እኔ መልስ አላጣም
ይዘገያል እንጅ ሰው የጁን አያጣም”ሸህ ሑሴን ጂብሪል
እነሆ እስልምናና ሀገረ-ሐበሻ ከተዋወቁ አስራ አራት ክፍለ ዘመናት ተቆጠሩ::በነዚህ ዘመናት ዉስጥ  ሙስሊም
ሐበሾችን ያስደሰቱና ያሳዘኑ  ብዙ መስዋዕትም ያስከፈሉ በዚች አጭር ጦማር  ተዘርዝረው የማያልቁ በርካታ
ክስተቶች ተከስተዋል:: በዛሬው ጽሑፌ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሙስሊም
ሐበሾች ላይ የተጋረጡ  ዋና ዋና ጋሬጣዎችንና እነሱን ለማስወገድ የተደረገውን ትግል አጠር አድርጌ ለመዳሰስ
እሞክራለሁ::
በወርኃ የካቲት 1847  ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ በረዥሙ የሀገራችን ታሪክ ዉስጥ ዘመነ መሳፍንት በመባል
የሚታወቀውን ነገሥታት የተዳከሙበትንና መሳፍንታት የገነኑበትን ዘመን ፍጻሜ  በማብሰር ራሳቸውን ዳግማዊ
አፄ ቴዎድሮስ  ብለው አወጁ::በጎጥ ተከፋፍላ ያገኟትን ኢትዮጵያን ማዋሀድ ከአፄ ቴዎድሮስ ርዕዮች አንዱና
ዋነኛው ነበር::ኃይማኖታዊ አንድነት የሀገራዊ ዉህደት አንዱ መሰረት ነው በሚልም በእሳቸው ቁጥጥር በነበረው
የሰሜን ኢትዮጵያ ግዛት ዉስጥ ይኖሩ የነበሩ ሙስሊሞችን እንደ ባላንጣ በማየት ለአስከፊ ስቃይ ዳርገዋቸው
እንደ ነበር ይታወሳል::
ግንቦት 20 ቀን 1870...
ግንቦት 20 ቀን 1870 በሙስሊም ሐበሾች ታሪክ ዉስጥ ልዩ ስፍራ ይዞ የሚገኝ እለት ነው::አፄ ቴዎድሮስ
ራሳቸውን መቅደላ አምባ ላይ በገደሉ በአራተኛ ዓመታቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው የነገሡት አፄ
ዮሐንስ አራተኛ የአፄ ቴዎድሮስን ኃይማኖታዊ መሰረት ያለው ሀገራዊ አንድነት ግንባታ መርህ እጅግ በከፋ
መልኩ የተገበሩ ንጉሥ ነበሩ::የዚህ ፖሊሲያቸው ሰለባም የሰሜን ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ነበሩ::
ግንቦት 20 ቀን 1870 በኢትዮጵያ ክርስቲያናት መካከል ለዘመናት ለዘለቀው(ቅባት፣ጸጋና ካራ ቡድኖችን
ያስታውሷል) ቀኖናዊ ዉዝግብ  እልባት ለመስጠትና ሙስሊሞችን ለማጥመቅ ከደሴ ከተማ በስተሰሜን 10 ኪሎ
ሜትር  ርቀት ላይ በሚገኘው ቀለም ሜዳ(ቦሩ ሜዳ)በአፄ ዮሐንስ  ዋና ወምበርነት አንድ ኃይማኖታዊ የክርክር
መድረክ ተከፈተ::ያ ለቀናት የዘለቀና የሸዋውን ንጉሥ ምኒሊክንና ሌሎች ስመጥር መኳንንትና ካህናትን ያሳተፈ
ስብሰባ  የተረቱ ክርስቲያን ሊቃውንትን  እግር፣እጅና ምላስን በማስቆረጥና የሐበሻ ሙስሊሞች ህልውናን አደጋ
ላይ የሚጥል አስደንጋጭ ዉሳኔን በማሳለፍ ነበር የተጠናቀቀው::
የሰሜን ኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንዲጠመቁ ወይም ሀገር እንዲለቁ በይፋ ተነገራቸው::ተጠመቅ ወይ አገር
ልቀቅ የሚለው የአፄ ዮሐንስ አዋጅ ለኃይማኖታቸው ቀናዒ ለነበሩት የሰሜን ኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚዋጥ
አልነበረም::እርግጥ ነው ከመሞት መሰንበት ያሉ ከእምነት ይልቅ ሹመትን የመረጡ የኢማምሙሐመድ ዓሊ

ወይም ራስ ሚካኤል(በኋላ ንጉሥ ሚካኤል)ዓይነት ግለሰቦችም ነበሩ::እስኪያልፍ ያለፋል እንዲሉ አንዳንዶችም
ለይስሙላ በመጠመቅ ቀን ቀን ክርስቲያን ማታ  ማታ ሙስሊም መሆንን መርጠው ነበር::ሌሎች
ተሰደዱ::እምነቴን ወይ ሞቴን ያሉ ደግሞ ጂሐድ አወጁ::
ጂሐዱ ሁለት መልክ ነበረው ማለት ይቻላል::ሰላማዊና ብረታዊ ::ሰላማዊ ዘርፉ እምቢተኝነትን በሰላማዊ መልክ
በግጥምና በእንጉርጉሮ  መግለጽ ላይ ያተኮረ ነበር::የሰላማዊው ዘርፍ  ዋና መሪ  በዘመን ተሻጋሪ አስደማሚ
ግጥሞቻቸውሙስሊሞችን ሲያበረታቱና አፄ ዮሐንስን ሲመክሩና ሲያስጠነቅቁ የነበሩት ኢትዮጵያዊው
ኖስትራዳመስ ሸህ ሑሴን ጂብሪል ነበሩ::ዛሬም ድረስ በሙስሊም አምሐራዎች ዘንድ በስፋት የሚታወሱትና
የሰላማዊው ጂሐድ ስንቅና ትጥቅ ከነበሩት የሸህ ሑሴን ጂብሪል ግጥሞች  ዉስጥ እንዲህ የሚሉ ይገኙባቸው
ነበር:-
ዓባይ በጣና ላይ መሄዱ ለምን ነው?
ትንሹ ሲያጠፋ ትልቁ ሊችል ነው፣
ቢያከፋም ቢያበጅም ዓባይ ማለፉ ነው
ሰውን በግዴታ የሚገዛው ማነው?
ከምክር በስተቀር የቀረው ከንቱ ነው::
ማረዱ ከፋ እንጅ ጀግንነት አያጣም
እስላም እሚያርድ እንጅ እሚወድ አይመጣም፣
የፈራህ ሰው ውጣ እኔ መልስ አላጣም
ይዘገያል እንጅ ሰው የጁን አያጣም
መተማ ከሄደ ተመልሶ አይመጣም::
አንተም እድሜህ አጭር ወይ ዘርህ አይገዛ
ጎርፍ ደርሶ አይወስድም አለቅጥ ካልበዛ
እንጨት ከደረቀ ቢቀቡት አይወዛ
ሐበሻ ክፉ ነው አይምሰልህ ዋዛ
መተማ እስቲጠራህ በብልሃት ግዛ::
እመክርህ ነበረ መች እሺ ትላለህ
ሀሳብህ ብዙ ነው መንገድ ታበዛለህ
መተማ ለመዝመት አሁን ትሄዳለህ

መመልስክን እንጃ እዛው ትቀራለህ
በድርቡሽ ጎራዴ ራስህን ታጣለህ::
አንድ ዓመት ሲቀረው ምኒልክ ሊነግሥ
አላህ መተማ ላይ ይስላል መቀስ
በደም አጨማልቃ የምትቆራርስ
እራስ የምትቆርጥ ያውም የንጉሥ
አንደዜ ተመታች የማታላውስ::
በወቅቱ ከፍ ያለ ተሰሚነት በነበራቸው ሸህ ሑሴን ጂብሪል ይነገሩ የነበሩት መሳጭና ተስፋ ሰጭ ዜማዊ
መልእክቶች ጋራ ሸንተረሩን ተሻግረው ከጎጥ ጎጥ  በፍጥነት ይደርሱ እንደነበር አበው ይተርካሉ::እነዚህ ዉብ
ስንኞች ሕዝበሙስሊሙ ተስፋ ሰንቆ በእምነቱ ጸንቶ እንዲቆይ የተጫወቱት ሚና ቀላል አልነበረም::
ከላይ እንደ ተጠቀሰው ሁለተኛው የትግል ግንባር ወታደራዊ ጂሐድ ነበር::የጂሐዱም መሪዎች በሕብረተሰቡ
ለሕብረተሰቡ የተመረጡ የኃይማኖት መሪዎች ነበሩ::ወታደራዊው ጂሐድ በርካታ መሪዎች ነበሩት::ከግንባር
ቀደም ወታደራዊ አዛዦች አንዱ ሸህ ዓሊ አደም  ነበሩ::ሸህ ዓሊ አደም በአሁኗ የደሴ ከተማ ደቡባዊ ጫፍ
የሚገኘውና  ልዩ ስሙ ቢለን የሚባለው መንደር  ተወላጅ ነበሩ::ቤተሰቦቻቸው ከጂሩ-መንዝ የፈለሱ
በመሆናቸው ሸህ ዓሊ ጅሩም ተብለው ይጠራሉ::
ሸህ ዓሊ አደም የአፄ ዮሐንስን ጦር ለመጀመሪያ ጊዜ ግንባር ለግንባር የተጋፈጡትሙጃሒዲኖች መሪ
ነበሩ::የመጀመሪያው ታሪካዊ ዉጊያም የተካሄደው  በቀለም ሜዳው አዋጅ  ማግስት ከዛሬዋ ሀይቅ ከተማ
በስተሰሜን ምዕራብ ዋሄሎ በተሰኘ ቦታ ላይ ነበር::በውጊያውም የሸህ ዓሊ ጦር ለሽንፈት ሲዳረግ ሸህ ዓሊም
በውጊያው ላይ ተሰው::በውቅቱ ዋሄሎ ላይ አርፎ የነበረው የሸህ ዓሊ አስከሬን ከስድስት ዓመት በኋላ ወደ
ትውልድ ቦታቸው ቢለን የተዛወረ ሲሆን ቀብራቸውም  የጎብኝዎች መስህብ የሆነ ታሪካዊ ቦታ ለመሆን በቅቷል::
ሌላው የወታደራዊ ጂሐድ ዝነኛ መሪ የአርጎባው ተወላጅ ሸህ ጠልሃ ቢን ጃዕፈር ነበሩ::ሸህ ጠልሃ የአፄ ዮሐንስንና
የሸዋው ንጉሥ ምኒሊክን ጣምራ ጦር ለዓመታት በመመከት አይበገሬነታቸውን አስመስክረዋል::ሸህ ጠልሃ
በባላንጦቻቸው ሳይቀር:-
ጠላት ማወደስ እንዳይሆን እንጅ
ማንም አያህለው ጠለሃ ሐጅ
ተብሎ የተገጠመላቸው ድንቅ የጦር ሰው ነበሩ::ወታደራዊው ጂሐድ ደቡብና ሰሜን ወሎን፤ሰሜን ሸዋንና ደቡብ
ትግራይን ያካለለ የአምሐራ ፣አርጎባ ፣አፋር ፣ኦሮሞና ትግራይ ተወላጆችን ያሳተፈ ህብረ-ብሐራዊ የነጻነት
ተጋድሎ ነበር::ጂሐዱ ለዓመታት የዘለቀና ብዙ መስዋዕትነትም የተከፈለበት ነበር::

የአፄ ዮሐንስን መተማ ላይ መቀላት ተከትሎ የንጉሠ ነገሥትነቱን ስልጣን የተቆጣጠሩት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ
ከአፄ ዮሐንስ ስህተት የተማሩ ይመስላሉ:: "አመልክን በጉያ ስንቅህን በአህያ"  ተብሎ በሚታወቀው የኃይማኖት
ፖሊሲያቸው መሰረት ከኦሮቶዶክስ ኃይማኖት ዉጭ ላሉ ዜጎቻቸው መለስተኛ የእምነት ነጻነት መፍቀዳቸው
ለዚህ ዓይነተኛ ማስረጃ ነው::
አፄ ምኒሊክን የተኩትና ተራማጅ ርዕያቸው በልጅነት የተቀጨባቸው ልጅ ኢያሱ በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ
ሙስሊሞችን ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር እኩል ለማድረግ የጣሩ ብቸኛ ተራማጅ መሪ ነበሩ::ድህረ-ኢያሱ
ኢትዮጵያን መጀመሪያ በአልጋወራሽነት  በኋላም በንጉሠ ነገሥትነት የመሯት ቀዳማዊ ኃይለ  ሥላሴ በሙስሊም
ሐበሾች ዘንድ በበጎ ዓይን ከማይታዩ ነገሥታት ወገን ይመደባሉ::በተለይም ከ1909 እስከ  1928 በነበረው የግዛት
ዘመናቸውሙስሊሞችን በጣም መጫናቸው ይታወሳል::ከ1928 እስከ 1933 በነበሩት ዓመታት ሀገራችን ወሮ
ፋሽስታዊ ስርዓት መስርቶ የነበረውሙሶሎኒ ለከፋፍለህ ግዛ አላማው ይረዳው ዘንድ ለሐበሻ ሙስሊሞች
ከአብዛሃኞቹ ሰለሞናዊያን ንጉሦቻቸው ሻል ያለ የእምነት መብት ሰጥቶ ነበር::
ከስደት መልስ አፄ ኃይለ ሥላሴ የጣሊያንን እርምጃ ከግንዛቤ ዉስጥ በማስገባትሙስሊም ዜጎቻቸውን
አስመልክቶ ከወትሮ ሻል ያለ ፖሊሲ ስራ ላይ ለማዋል ሞክረዋል::በ1936 በንጉሠ ነገሥቱ የታወጀው የናኢባና
ሸሪዓ ፍርድ ቤት አዋጅ ለዚህ እንደማስረጃ ሊጠቀስ ይችላል::ኤሪትሪያ በ1944 ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን
መጣመሯና በኋላም የኢትዮጵያ አንድ ጠቅላይ ግዛት ሆና መጠቃለሏም ንጉሠ ነገሥቱ ሙስሊሞችን
አስመልክቶ አንዳንድ አዎንታዊ እርምጃዎች እንዲወስዱ የራሱን ተጽእኖ አስድሯል::በ1960ዎቹ አካባቢ ሁለት
ሙስሊም ሚኒስትሮች መሾማቸውም የዚህ ተጽእኖ ውጤት ነበር::
ትግሉ ቀጥሏል..."በኢትዮጵያ የሚገኙ ሙስሊሞች"በመባል በሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ይታዩ የነበሩትሙስሊሞች
በየካቲት 1966 አብዮት ፍንዳታ ማግሥት ማለትም ሚያዝያ 12 ቀን 1966 "የዜግነት መብቶቻችን
ይጠበቁ..."በማለት 300,000 ራሳቸውን ሆነው በአዲስ አበባ ግዙፍ ታሪካው ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ::ይሁን እንጅ
የአፄ ኃይለ ሥላሴ ስርዓት የሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ ሳይመልስ ተገረሰሰ::
መስከረም 2 ቀን 1967 ንጉሠ ነገሥቱን ከዙፋን አውርዶ ጊዜያዊ መንግሥት ያቋቋመው ግራ ዘመም ወታደራዊ
ጁንታ  ስልጣን በያዘ በማግስቱሙስሊሞች "በኢትዮጵያ የሚገኙ ሙስሊሞች" መባላቸው ቀርቶ
"ኢትዮጵያዊያንሙስሊሞች"እንዲባሉ ፣የዒድ አልፍጥር፣ ዒድ አል አድሀ(አረፋ)እና መውሊድ በዓላት
በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበሩና ሙስሊሞች ኃይማኖታዊ ጉዳዮቻቸውን የሚከውኑበት "የኢትዮጵያ እስልምና
ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባዔ"የተሰኘ መሪ ድርጅት እንዲያቋቁሙበመፍቀድ የሙስሊም ሐበሾችን ቀልብ በተወሰነ
ደረጃ መሳብ ያስቻሉ ታሪካዊ  እርምጃዎችን ወሰደ::
ግንቦት 20 ቀን 1983...
የአስራ ሰባት ዓመታት የጭቆና ቀንበር በሕዝባዊ ትግል ተሰባብሮ አዲስ ምእራፍ ተጀመረ::በሰኔ 1983
የተመሰረተው የሽግግር መንግሥትም ዜጎች የእምነትና የመደራጀት መብት እንዳላቸው በይፋ ደነገገ::ይህን
ተከትሎም በዘመነ ደርግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲሙስሊም ተማሪዎች ተጠንስሶ የነበረው የኢትዮጵያሙስሊም
ወጣቶች ድርጅት(ኢ.ሙ.ወ.ድ.) እና ሌሎች እስላማዊ ማሕበራት በሕጋዊ መልክ ተመዝግበው እንቅስቃሴ

ጀመሩ::የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባዔም(መጅሊስ)በአዲስ መልክ ማንሰራራት ጀመረ:: ከጥቅምት
5 እስከ ጥቅምት ስምንት 1985 ለአራት ቀናት በተደረገ  ጉባዔም መጅሊሱ በአዲስ መልክ ተዋቀረ::ሳይውል
ሳያድርም የስልጣን ሽኩቻው ተጀመረ::ያ ዉስጣዊ ትርምስም ለየካቲት 14 ቀን 1987 ትራዤዲ መንገድ ጠረገ..
የካቲት 14 ቀን 1987 በአንዋር መስጅድ በግለሰቦችመሀል በተፈጠረ ግርግር ፖሊስ 10 ሙስሊሞችን መስጅዱ
ዉስጥ ገደለ::የአስር ሰዎች ደምና የሚሊዮኖች እምባ ፈሰሰ::ኢ.ሙ.ወ.ድ. እና መሰል እስላማዊ ማሕበራት
ከሰሙ::የሙስሊም ኢትዮጵያዊያን መሪ ድርጅት የነበረው መጅሊስም ፈረሰ::ከዚያች እለት ጀምሮ መጅሊሱ
ከሙስሊሞች ወኪልነት ወደ  የኢሕአዴግ "እስላማዊ"ክንፍነት ተሸጋገረ::ግንቦት
ሃያዊያንና(ኢሕአዴግና)ሙስሊም ኢትዮጵያዊያንም ሆድና ጀርባ ሆኑ::
ታኅሳስ 24 ቀን 2004...
ልክ የዛሬ ዓመት በዚች እለት "ድምጻችን ይሰማ"የሚል  ድምጽ በኢትዮጵያዋ ታህሪር አደባባይ ማለትም አወሊያ
ቅጥር ግቢ ተሰማ::የጩኸቱም  ምክኒያት  ከሰኔ 2003 ጀምሮ መጅሊሱን የተቆጣጠረው ሊባኖስ በቀል አህባሽ
የተሰኘ አንጃ ታሪካዊው የአወሊያ መድረሳ ላይ እጁን ማሳረፉ ነበር::የአወሊያ ተማሪዎች ተቃውሞም ተዳፍኖ
የነበረውን የሙስሊሙን ብሶት ለአደባባይ አበቃው::አወሊያን ማእከል ያደረገው ሕዝባዊ እንቅስቃሴም በፍጥነት
በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ መስጂዶችን አዳረሰ::የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ተቋቋመ::በሕዝበሙስሊሙ  ለሕዝበ
ሙስሊሙ  የተቋቋመ መጅሊስ እንሻለን፣ መንግሥት ሕዝብ ሙስሊሙላይ የአህባሽን አንጃ በግድ ለመጫን
የሚያደርገውን ትግል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ያቁም እና አወሊያ በሕዝበሙስሊሙበተመረጡ ክህሎቱ
ባላቸው የቦርድ አባላት ይተዳደር የሚሉ ሦስት አበይት ጥያቄዎችም  ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት
ቀረቡ::
በሰላማዊ መልክ ለቀረበው የመብት ጥያቄ በመንግሥት በኩል የተሰጠውና እየተሰጠ ያለው ምላሽ ባያስገርምም
አሳዛኝ ነው::በሕዝባዊ እንቅስቃሴውና መሪዎቹ ላይ  የተለያዩ ታርጋዎችን በመለጠፍ ኢ-ሰብዓዊ እርምጃዎችን
በመውሰድ ላይ ይገኛል::በሚያዝያ 19 ቀን 2004  አርሲ አሳሳ ላይ የተካሄደውን ጭፍጨፋ፣በወርኃ ሐምሌ
የመፍትሄ አፈላላጊውን ኮሚቴ አባላት ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ታፍሰው የታሰሩ ሙስሊሞችን
ጉዳይና በጥቅምት 10 ቀን 2005 በገርባ ከተማ የተካሄደውን ጭፍጨፋ ለአብነት ያህል ማንሳት ይቻላል::
ወደ ግንቦት 20 ቀን 1870 እየተጓዝን ይሆን?ወደ ኋላ መለስ ብለን ግንቦት ሃያዊያንን.:-
ሰውን በግዴታ የሚገዛው ማነው?
ከምክር በስተቀር የቀረው ከንቱ ነው::
የምትለዋን ዘመን ተሻጋሪ የሸህ ሑሴን ጂብሪልን መልእክት ልናስታውሳቸው እንወዳለን::አዎ!በእርግጫ ሕዝብን
ለዘመናት ለመግዛት ማሰብ እንደነ ጋዳፊ በሕዝባዊ ጡጫ መዋረድን ማስከተሉ አይቀሬ ነው::እናም
እንደማመጥ::ለመደመጥ ማዳመጥ ፤ለመሰማት መስማት የግድ ነው::መሰማማትና መስማማት  አለብን
...እንመካከር "ከምክር በስተቀር የቀረው ከንቱ ነው::"አበቃሁ::

ትግሉ ይቀጥላል...
ታኅሳስ 24 ቀን 2006 በሰላማዊቷና ዴሞክራሲያዊቷ ኢትዮጵያ በሰላም ለመገናኘት ያብቃን!

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate