እንደ “ጠቅላይ ሚንስትሩ” አባባል ዋጋ ግሽበቱን ያባባሱት “አዳዲሶቹ ጤፍ በላተኛ” ሃብታሞች ናቸው
ዶ/ር ዘላለም ተክሉ
01/05/2013
01/05/2013
በቅርቡ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች “ጠቅላይ ሚንስትር” ሃይለማርያም ደሳለኝ የሰጡትን ምላሽ በጥሞና አዳምጬው ነበር1:: በዚህ ምላሻቸው ከዳሳሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ስለሃገሪቱ ሁለት አሃዝ ዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አፈጻጸም፣ የኑሮ ውድነት በተለይም የምግብ እህል ዋጋ ግሽበት፣ መራሩን የሃገር ቤት ኑሮ በመሸሽ ወደ ዓረብና አፍሪካ ሃገራት በሚሰደዱ ወገኖቻችን ላይ ስለሚደርሰው ሞትና ዘግናኝ ስቃይ፣ ስለፖለቲካ እስረኞች፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ስላላት ግንኙነት፣ እንዲሁም በቅርቡ በአልጀዚራ ቃለምልልስ አስመራ ድረስ በመሄድ ከኤርትራ ጋር ያለቅድመ ሁኔታ ስለመደራደር ዋና ዋናዎቹ ነበሩ::
በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በውጭ ግንኙነቱ ዘርፍ በአጠቃላይ የሰጡዋቸው ምላሾች “ባለራዕዩ” የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበራቸው ብልጣብልጥነትና ለዛ በስተቀር በይዘታቸው መቶ በመቶ ተመሳሳይ ነበሩ:: ምላሾቹ ባብዘኛው የኢህአዴግ የተለምዶ ማደናበሪያዎች ስለመሆናቸው ከዚህ በፊት በተለያዩ አካላት የተብራሩና ወደፊትም ምላሽ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ:: ለኔ በተለይ ትኩረቴን የሳበው ግን ስለ ዋጋ ግሽበት (Inflation) ትርጓሜና በተለይ የጤፍ ዋጋ እየናረ የመጣበትን ምስጢር በተመለከተ የሰጡት ትምህርት (Lecture) መሳይ ነገር ነበር::
ከሙያ አንጻር ስመለከተው የዋጋ ግሽበቱን በሚመለከት የሰጡት ትርጓሜ በግርድፉ ሲታይ “አማካሪዎቻቸውን” በመያሳማ መልኩ ያስረዱ ይመስላል:: የጤፍ ምርት ዋጋ እየናረ መምጣትንም ከገቢ ማደግ፣ ምርትና ፍጆታ መጨመር ጋር ለማያያዝ መሞከራቸው በግኡዙ(Rubber Stamp) የኢትዮጵያ ፓርላማ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችል ይሆናል ብዬ እገምታለሁ:: ነገር ግን የኑሮ ውድነቱ በየቀኑ እየተባባሰ በመምጣቱ የመራብና የመታረዝ ገፈቱን በተጨባጭ እየቀመሰ ላለው ህዝባችን ይህ ትምህርት (Lecture) ድራማና ስላቅ እንጂ ምንም ተብሎ ሊገለጽ አንደማይችል ላሰምርበት እወዳለሁ:: የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማም ይህንኑ አይን ያወጣ ሽወዳ አይሉት መደናበር ከኔ እይታ ለመፈንጠቅ ነው::
የዋጋ ግሽበት ስለመቀነሱ የተፈጠር ብዥታ
አቶ ሃይለማርያም በመጀመሪያ ሲያስረዱ የሃገሪቱ ከፍተኛ ዋጋ ግሽበት ከወር ወር እየቀነሰ መምጣቱን ከጠቆሙ በኋላ ስለቀመሩ አሰላል ሲያስረዱ የአለፈውን ዓመት ተመሳሳይ ወር ዋጋ ከአሁኑ ዓመት ተመሳሳይ ወር ዋጋ ጋር በማነጻጸር የሚገኝን ልዩነት በማስላት እንደሆነ ገልጸዋል:: በመቀጠልም ይህ ቀመር አጠቃላይ የእርሻና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በአንድ ቅርጫት ውስጥ በማስገባት (Composite Good) እንጂ ለእያንዳንዱ ምርትበተናጠል ማስላት እንደማይቻል ደጋግመው አስረድተዋል:: የ“ጠቅላይ ሚንስትሩ” የትርጉም ግድፈት እንግዲህ የሚጀምረው ለተናጠል ምርቶች የዋጋ ግሽበት ቀመር ማስላት አይቻልም ከሚለው ይሆል:: አይቻልም የሚሉት ስሌት ላይ አጽዕኖት መስጠታቸው ከወር ወር እየቀነሰ መጥቷል ለሚሉት የዋጋ ግሽበት ሪፖርት መከላከያ ግድግዳ (Fire Wall) ለማቆም ፈልገው ነው ብዬ በመከራከር እንደሚከተለው ለማስረዳት እሞክራለሁ::
በአንድ ቅርጫት ውስጥ ሁሉንም ምርቶች በማስገባት ቀመሩን በምናሰላበት ጊዜ የእርሻ፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ምርቶችን እንደ አንድ ምርት (Composite Good) እንዲሁም የእርሻ፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዋጋዎችን እንደ አንድ ዋጋ (Composite Price) ስለምንቆጥራቸው በውስጣቸው ያለውን ልዩነት እንሸፍናቸዋለን:: ይህንን ልዩነት ነጥሎ ለማውጣት እንዲያስችል የገበያና ዋጋ ተንታኞች (Market & Price Analyst) በምርት ዘርፎች የተከፋፈለ የዋጋ ቀመር (Disaggregated Price Index) መስራታቸው የተለመደ አካሄድ (approach) ነው:: በዚህ አካሄድ መሰረት የግብርናውን ምርት በአንድ ቅርጫት ውስጥ፣ የኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ምርቶችን ደግሞ በሌሎች ሁለት ቅርጫቶች ውስጥ በማስገባት የዋጋ ግሽበቶችን በተናጠል ማስላት ዓለም ያወቀውና ፀሃይ የሞቀው እውነታ ነው::
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከወር ወር እየቀነሰ መጥቷል እየተባለ የሚለፈልለትን የዋጋ ግሽበት ከላይ በተገለጸው መልኩ በምርት ዘርፎች በተከፋፈለ መልኩ ተሰልተው ቢቀርቡ ምን ያህል የተጋነነ (spurious) እና የተዛባ (flawed) እንደሆነ ማሳየት ይቻላል:: እስኪ አስቡት የአብዛኛው የግብርና ምርቶች ዋጋ ባለፈው ዓመት አይደለም ካለፉት ጥቂት ወራቶች በፊት እንኳን ከነበረው በላይ እየጨመረ በመጣበት ሁኔታ ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ግሽበት መኖሩ ምን አጠያያቂ ያደርገዋል:: አቶ ሃይለማርያም የጠቀሱት ጤፍ ብቻ ሳይሆን የሽሮ እሆሎቹና ጥራጥሬዎች፣ ለቂጣና ዳቦ የሚሆኑት ስንዴና ገብስ፣ ለማጣፈጫ የሚሆኑት ቅመማ ቅመምና በርበሪ፣ የእንስሳ ምርቶችና ተዋጽኦዎች በሙሉ ዋጋቸው ጨምሯል:: በዚህ ዘርፍ በተናጠል የታየውን የዋጋ ንረት መንግስትም ቢሆን እንደማይክደው እርግጠኛ ነኝ:: አብዛኛዎቹ የኢንዱስትሪ ውጤቶችም ከዓመት ዓመት እየተወደደ በሚመጣው የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው የሚገቡ በመሆናቸው የዋጋ ግሽበቱን የማባባስ አስተዋጽኦዋቸው ከፍተኛ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም:: ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ምናልባት መሰረታዊ ፍላጎት የሆኑት ስኳርና ዘይት ናቸው እንግዲህ ዋጋቸው የቀነሰው:: ያም ለውጥ የታየው በአገር ውስጥ ያሉ አግሮ ኢንዱስትሪዎች ምርት በመጨመሩ ሳይሆን መንግስት ከውጭ አስመጥቶ በተቋማቱ አማካኝነት በአነስተኛ ዋጋ በማከፋፈል በወሰደው የማረጋጋት እርምጃ እንደሆነ ይታወቃል:: ትንሽ የሚታይና የሚጠቀስ ለውጥ የተመዘገበው በአገልግሎት ዘርፉ ላይ ከመጣው ዕድገት ጋር የተያያዘ ነው ብሎ መገመት ይቻላል:: ብዙ ሆቴሎችና መንገዶች በመገንባታቸው፣ ተጨማሪ የስልክና የኤሌክትሪክ መስመሮች እንዲሁም የውሃ ቧምቧዎች በመዘርጋታቸው፣ በየገጠሩ የጤና ጣቢያዎችና ኬላዎች በመከፈታቸው የነዚህ ማህበራዊ አገልግሎቶች ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር ሊወርድ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለኝም::
ነገር ግን አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደድህነቱ ከ 60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን ገቢውን በምግብ ፍጆታ ላይ የሚያጠፋ ከሆነ፣ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ ሲሰላ በአንድ ቅርጫት ውስጥ ከተካተቱት ምርቶች ውስጥ ከ 60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት የምግብ ምርት ውጤቶች ናቸው ማለት ነው:: እንግዲህ አስቡት ከቅርጫት ውስጥ ከተካተቱት ሸቀጦች ውስጥ ከ 2/3ኛ በላይ የሆነው የምግብ ዋጋ መጨመርና 1/3ኛ የሚሆነው የአገልግሎት ኢንዱስትሪ ዋጋ መቀነስን ሁሉም በተስማማበት ሁኔታ እንዴ አድርጎ ነው የአጠቃላይ ምርት ዋጋ ግሽበቱ ቀንሷል ማለት የሚቻለው:: የትምህርት ጥራቱ “እንደሚወራለት ካልወረደ” በስተቀር የ4ኛ ክፍል ተማሪ እንኳን 2/3 ሲደመር -1/3 ይሆናል 1/3 እንጂ -1/3 ብሎ ይሳሳታል ብዬ አልጠረጠርም::
የጤፍ ዋጋ እየናረ መምጣት ሚስጥር
የዋጋ ግሽበት ስሌቱ ከወር ወር ቀንሷል እየተባለ የምግብ ዋጋ ለምን ጨመረ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ጤፍን እንደ ምሳሌነት ተጠቅመዋል:: ከላይ እንደተገለጸው የእያንዳንዱን ምርት የዋጋ ግሽበት ማስላት እንደማይቻል በማከላከል ይህንን መሰረታዊ ጥያቄ ሳይመልሱ አድበስብሰው አልፈውታል:: እርሳቸው እንዳሉት የጤፍ ምርት በብዙ ክልሎች ከ 20 እስከ 30 በመቶ ቢያድግም ዋጋው የበለጠ እየናረ የመጣበት ምክንያት በኢኮኖሚ ዕድገቱ ሳቢያ ገቢያቸው ያደገ ነገር ግን ከዚህ በፊት ጤፍ በልተው የማያውቁ የህብረተሰብ ክፍሎች መመገብ በመጀመራቸው እንደሆነ አስረድተዋል:: ይህ ምላሽ ምንም ስሜት የማይሰጥና አስገራሚ ንጽጽር መስሎ ስለታየኝ የኢኮኖሚክስ ግንዘቤዬን ወደኋለ ሄጄ እንድመረምር ተገደድኩኝ:: ካደረኩት አነስተኛ ምርመራም በጣም ጠቃሚ ምላሽ በማግኘቴ ላካፍላችሁ ወደድኩኝ::
በኢኮኖሚክስ ንድፈሃሳቦች ውስጥ ዋነኛ በሆነው የፍላጎት ህግ (the Law of Demand) መሰረት (ሌሎች ነገሮች ሳይለወጡ Ceteris Paribus) የአንድ ሸቀጥ ዋጋ ሲጨምር ፍላጎት እንደሚቀንስና ዋጋው ሲቀንስም ፍላጎት እንደሚጨምር ይታወቃል:: ይህንን ህግ ከተከተልን እንግዲህ የጤፍ ዋጋ እየጨመረ በመጣበት ባሁኑ ወቅት ፍላጎቱና ፍጆታው መቀነስ ነበረበት:: በሃገራችን የተከሰተው ግን ከፍላጎት ህጉ በተቃራኒው ነው:: ኢኮኖሚስቶች እንደሚያስረዱት ይህን የተለየ ክስተት የሚፈጠረው እየተነጋገርንበት ያለው ሸቀጥ ጊፍን ሸቀጥ(Giffen Good) ሲሆን እንደሆነ ይገልጻሉ:: እነዚህ ጊፍን ሸቀጦች ሁለት ዓይነት ሊሆኑ ይችላሉ:: አንደኛው ዓይነቶች ዕለት ከዕለት በዋናነት አስፈላጊ (Necessary staples) የሆኑ እንደ ዳቦ፣ ስኳር፣ ዘይት፣ የምግብ ዕህሎች (ጤፍ፣ስንዴ፣ ሌሎች)፣ አትክልቶች(ሽንኩርት፣ቃሪያና ሌሎች) እና የመሳሰሉትን የሚያካትት ሲሆን እነዚህን ሸቀጦች ህዝቡ በየቀኑ ማግኘት ስላለበት ዋጋቸው ቢጨምርም እንኳን ሌሎች ፍላጎቶቹን (ልብስ፣ ጤና፣ትምህርት፣መዝናኛና የመሳሰሉት) በማቀብ በከፍተኛ ዋጋም ቢሆን የሚገዛቸው ናቸው:: ሌሎቹ ጊፍን ሸቀጦች ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ ተፈላጊ (Inferior Good) ቁሳቁሶች ሲሆኑ ህብረተሰቡ ገቢው ሲያድግ በሌላ የተሻለ ጥራት ባላቸውና ውድ በሆኑ ሸቀጦች የሚተካቸው ናቸው::
እንግዲህ ከላይ በተዘረዘረው የኢኮኖሚ ንድፈ ሃሳብ መሰረት አቶ ሃይለማሪያም በምሳሌነት የጠቀሱት ጤፍ እንደ ጊፍን ሸቀጥነት መውሰድ ይቻላል:: ጤፍ በአስር ሚሊዮኖች ለሚገመተው የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት የዕለት ከዕለት ምግብ (Necessary Staples) በመሆኑ ዋጋው እየጨመረ ቢመጣም እየገዛ መገበመገቡን የማያቆመው የእህል ዓይነት ነው:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሥርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑና ከዚህ በፊት ጤፍ ተመግበው የማያውቁ ጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎች ቀድሞ ይመገቡት የነበረውን የእህል ዓይነት (Inferior Food) በመተው ወደጤፍ አመጋገብ ተሸጋግረዋል ማለት ነው:: ከሳቸው አባባል በመነሳት እነዚህ በቅርቡ ገቢያቸው የጨመረላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ኑሮዋቸው በመሻሻሉና ለቅንጦት ምግቡ ጤፍ ፍላጎታቸው በመጨመሩ በዋጋ ንረቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ማለት ነው:: ይህ ማለት ደግሞ በአስር ሚሊዮኖች የሚገመቱ ወገኖቻችን ዋና የዕለት ምግባቸውን በከፍተኛ ዋጋ ክፍያ ለማግኘት እየተንገታገቱ ባሉበት ወሳኝ ወቅት ውስጥ ጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎች የዋጋ ንረቱ ሳያስጨንቃቸው ጤፍን እየተመገቡ በደስታና በድሎት እየኖሩ ነው ማለት ነው::
አገዛዙ ካላበቃ ድራማው ይቀጥላል
ከተለያዩ ወገኖች በተደጋጋሚ እንደሚተቸው ወያኔ በፕሮፓጋንዳ እንደሚለፍፈው ሳይሆን ለጥቂት ታጋዮችና የቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ጥቅመኛ ነጋዴዎች፣ የሥርዓቱ ተላላኪዎችና አጎብዳጆች ሃብት ፈጣሪ ቡድን እንደሆነ ይታወቃል:: የ”ጠቅላይ ሚንስትሩ” የፓርላማም ንግግር ይህንኑ የሚያጠናክር ይመስላል:: በአስር ሚሊዮኖች የሚገመተው ጤፍን በዋና የዕለት ምግብነት የሚጠቀመው ህዝባችን የዋጋ ግሽበቱ መከራውን እያበላው ባለበት ባሁኑ ወቅት፣ እንደቅንጦት ምግብነት በውድ ዋጋ ገዝተው የሚመጋቡ ጥቂት አዲስ ሃብታሞች መፈጠራቸውን አብስረውናል:: መቼስ በየቀኑ በኢትዮጵያ የሚሰማው ጉድ ማለቂያ የለውም:: ነገ ደግሞ የምንሰማው ተአምር ምን ይሆን? መቼም ይህ አገዛዝ የሚያበቃበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ድራማው መቀጠሉ አይቀሬ ነው!
No comments:
Post a Comment