Pages

Jan 6, 2013

የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በድረ-መለስ ኢትዮጵያ፣ አይዲዮሎጂካል እና ስትራተጂካዊ ሁኔታዎች በጋሻው አለሙ

የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በድረ-መለስ ኢትዮጵያ፣ አይዲዮሎጂካል እና ስትራተጂካዊ ሁኔታዎች
1. መግቢያ
የጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊን ህልፈተ-ህይወት ተከትሎ በኢህአዴግ እና በተቃዋሚ
ኃይሎች የሚታየው የመረበሽና ትርምስምስ በመሰረታዊነት ምንጮቹ ፖለቲካዊ፣
ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ቢሮክራሲያዊ ስልጣኖችን በአጠቃለለ ሁኔታ ጠ/ሚ መለስ
በእጃቸው ማስገባታቸውና በእሳቸው ህልፈተ-ህይወት ምክንያት የተከፈተውን የስልጣን
ክፈተት የሚሞላ ተቋማዊ አቅም አለመገንባቱና ሁለተኛ ግለሰብ በስርአቱ ውስጥ አለመኖር
ናቸው:: ስለዚህም በእርሳቸው ህልፈተ-ህይወት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት በሚደረግ
ሂደት ውስጥ በሁለተኛው የኢትዮጵያ ሪፐብሊክ ውስጥ የነበረውን የሃይል አሰላለፍ
የሚያፋልስና፤ ይህም የስልጣን ሽግግር አይዲዮሎጂካልና ስትራተጂካዊ አመክንዮችን
የሚላበስ ነው::  ለመልካምም ይሁን ለመጥፎ ምክንያት፣ ጠ/ሚ መለስ የሁለተኛው
የኢትዮጵያ ሪፐብሊክ መስረታ ሂደትን በበላይነት የመሩ፣ የስርአቱን አይዲዮሎጂካዊና
ስትራተጂካዊ ንድፈ-ሃሳቦች በመቅረጹ ሂደት ላይ ወሳኝ ድርሻ የተጫወቱ ናቸው:: ስለዚህም
የእርሳቸው አለመኖር በገዢው ሃይል ውስጥ የሚከፍተው ክፍተት በአጭር ጊዜ ውስጥ
ሊሞላ የሚችልና ውስጣዊ የስልጣን ሽግግሩ በቀላሉ ሊካሄድ የሚችል አይደለም::
በሌላ በኩል ጠ/ሚ መለስ የተቀዋሚ ሃይሎችን የቀን-ተቀን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን
በአግባቡ በመከታተል የተቃዋሚ ሃይሎችን አይዲዮሎጂካዊና ስትራተጂካዊ አጀንዳዎች
አስቀድሞ በመቀየስ እንዲሁም የተቃዋሚ ሃይሎች ህዝባዊ ይሁንታ ያገኙባቸውን ፖለቲካዊ
አጀንዳዎችን በመውሰድና ኢህአዴጋዊነትን እያላበሱ በመተግበር የተቃዋሚ ሃይሎችን
አይዲዮሎጂካዊና ስትራተጂካዊ መሰረቶች ለማጥበብ ችለው ነበር::  ይህም ከተቃዋሚ
ሃይሎች ቁመናና አሰላለፍ ጋር ተዳምሮ የተቃውሞ ፖለቲካው በሀገር አቀፍ እንዲሁም
በዲስፖራው ውስጥ ተቋማዊ ገጽታው በትናንሽ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሞላ እንዲሆን
አድርጎታል:: ብዙዎች የገዢው ሃይል ሁሉን አቀፍ ተጽእኖ ለትናንሽ ፖለቲካ ፓርቲዎች
መመስረት እንደምክንያትነት ይጠቅሳሉ:: ነገር ግን፣ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ወረራ በራሱ

የድክመት ማሳያ ሲሆን በወረራ ተሸናፊነት ምንጩ ደግሞ ውስጣዊ ድክመት ነው:: የገዢው
ኃይል ተጽእኖ ውጤታማነት ምንጩ የተቃማዊ ኃይሎች ውስጣዊ ድክመት ነውና::
የተቃማዊ ኃይሎች ውስጣዊ ድክመት ሁሉን አቀፍ ድክመት ነው:: በአሁኑ ጊዜ ተቃማዊ
ኃይሎች አይዲዮሎጂካዊ፣ ስትራተጂካዊ፣ ተቋማዊ እና ዕቅዶችን ገቢራዊ የማድረግ
ድክመቶች አለባቸው::  እነዚህም ድክመቶች ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ    በስፋት የተቃማዊ
ኃይሎች መሰረታዊ የህዝብ ድጋፍ እያሳጣቸው እንደሆነ እየታየ ነው:: የተቃማዊ ኃይሎች
ልሂቃን ለምሳሌ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም፣ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አሁን
ያለውን ስርአት ለመታገል የአሁኑ ትውልድ ሃገራዊ ፍቅርም ሆነ ወኔ ያንሰዋል የሚል
የመከራከሪያ ሃሳብ እያቀረቡ ናቸው:: የአሁኑ ወይስ የትላንቱ ትውልድ ይበልጥ ሀገራዊ
ፍቅር አለው የሚለውን ክርክር ወደ ጎን እንተወውና፣ መሰረታዊ በሆኑ የተቃውሞን
እንቅስቃሴ    እየጎዱ ባሉና አሁን ካለው ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሊስተካከሉና
እንደገና ሊታዩ የሚገቡ አይዲዮሎጂካዊና ስትራተጂካዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው::
የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማው በተቃማዊ ሃይሎች ውስጥ ያለውን አይዲዮሎጂካዊና
ስትራተጂካዊ ጉዳዮች በድረ-መለስ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር
ለመዳሰስ ነው:: ምንም እንኳን የድረ-መለስ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሁሉን አቀፍ ትንተና
ለማድረግና የወደፊቱን ለመተንበይ ጊዜው ገና ቢሆንም፣ ከተቃማዊ ኃይሎች የሃይል
አሰላለፍ፣ ተቋማዊ ገጽታና ከገዢው ኃይል ተቋማዊ ባህል አንጻር መመልከት የሚቻልበት
ዕድል ሰፊ ነው:: የታላቁ እስክንድሪያ አባባል በመዋስ፣ ኢህአዴጎች የሚፈሩት በበግ የሚመራ
የአንበሶች ተቃውሞ ሳይሆን በአንበሳ የሚመራ የበጎችን ተቃውሞ ነው:: ስለዚህም ይህ
ጹሁፍ ተቃዋሚ ኃይሎች ላይ ትኩረት የሚያደርግና ተቃማዊ ኃይሎች የተጋፈጡባቸውን
አይዲዮሎጂካዊና ስትራተጂካዊ ጉዳዮች ከሀገራዊና አለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች
አንጻር እንደሚከተለው ለመዳሰስ ሞክሯል::
2. አይዲዮሎጂካዊና ስትራተጂያዊ ጉዳዮች
2.1 አጠቃላይ የትግሉን አላማና ስልት ስለመወስን
አሁን በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል ያለው ልዩነት አሁን ያለውን ስርአት ለመቀየር በሚደረግ
ትግል    አስፈላጊ መሆኑ ወይም አለመሆኑ ላይ አይደለም:: በአጠቃላይ በትግሉ አላማና
ስልት ላይ እንጂ:: በአንድ ወቅት ዶ/ር ብርሃኑ የአሁኑን ትግል ከ 1970ዎቹ ትግል ያለው
ልዩነት የገለጸው፤ያለፈው ትግል ሲካሄድ የነበረው የመጨረሻ እውነትን ለማግኘትና
እውነተኛ ህዝባዊና ሶሻሊስታዊ ስርአት ለመገንባት ነበር:: የአሁኑ ትግል በባህሪ ደረጃ ግን

በሂደት ላይ የተመሰረተ የመጨረሻ እውነትን ሳይሆን ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች
የሚያስማማ አማካይ ቦታ የመፈለግና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባት ነው:: ነገር
ግን ዶ/ር ብርሃኑ እንደሚያስበው ሳይሆን በሁለቱም ትግሎች በመሰረታዊ አስተሳሰብ ደረጃ
በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል ያለው ልዩነት እምብዛም ነው:: ሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች
የሚያነጣጥሩት ስርአት ስለመቀየር እንጂ በምንመልኩ መሬት ላይ ያለውን ፖለቲካዊ
ስርአትና ባህል በመሰረታዊነት ስለመለወጥ አይደለም::
ሁሉም የፖለቲካ ስርአቶች ሊሻሻሉ የሚችሉ አይደሉም:: ለምሳሌ የአጼውም ሆነ የደርግ
ስርአት በባህሪያቸው ሊሻሻሉ የሚችሉ አልነበሩም:: በጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን እንዚህ
ስርአቶች መወገድ ያለባቸው በመሰረታዊ ለውጦች ነበር:: የሆነውም እንደዛ ነበር:: ነገር ግን፣
ደርግ የአጼውን ቢሮክራሲያዊ፣ ወታደራዊና የደህንነት መዋቅሮች በመውረስ የህልውናው
መሰረቶች እንዲሆኑ ይበልጥ አጠናክሯቸው ነበር:: እንዚህ ተቋሞችና መዋቅሮች በባህሪቸው
ህዝባዊ ሳይሆኑ የህዝቡን የዕለት-ተዕለት ተግባሮች መንግስት የሚቆጣጠርባቸው የጭቆና
ቀንበሮች ነበሩ:: ኢህአዴግም የደርግን ቢሮክራሲያዊ፣ ደህንነት እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሮችን
ከሞላ ጎደለ ከተወሰነ ቅርጻዊ መሻሻሎች ጋር ሲያስቀጥላቸው የደርግን ወታደራዊ ኃይል
በራሱ ኃይል ተክቷል:: ስለዚህም በኢህአዴግ ዘመንም መንግስታዊና ቢሮክራሲያዊ
መዋቅሮች ህዝባዊነት የተላበሱ፣ የሀገሪቷንና የህዝቦቿን ፍላጎትና አንድነት የሚያስጠብቁ
ሳይሆን የገዢውን ቡድን ስልጣን የሚያስጠብቁ ናቸው::
ተቃዋሚ ሃይሎች በአሁኑም ወቅት በዚህ የትግል ልማዳዊ አስተሳሰብ ውስጥ ነው
የሚገኙት:: ተቃማዊ ኃይሎች ከዚህ የትግል አስተሳሰብ ውስጥ መውጣት አለባቸው:: የዚህ
ዝግ አስተሳሰብ ዋነኛ ምንጩ የ1960ዎቹ እና 70ዎቹ ግራ ዘመም እና የዜሮ ድምር
የፖለቲካ ስትራተጂ ናቸው:: ስለዚህም ካለፈው የፖለቲካ ትግል ልምድ ብቻ ሳይሆን
ያለፈውን ትግል በአግባቡ ገምግመው ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ አጠናክረው ደካማ ጎኖችን
ለመቅረፍና ለማሻሻል መትጋት አለባቸው:: ትግል ሂደት ቢሆንም ሂደቱን መረዳትና
የሂደቱን አቅጣጫ መተለም ግን ቁልፍ ጉዳይ ነው ለአንድ ትግል ውጤታማነት::
የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የተቃዋሚዎችን አይዲዮሎጂካዊና ስትራተጂያዊ ጉዳዮች ላይ
የበላይነት ብቻ ሳይሆን ይዘው የነበሩት፣ ተቋማዊና ውስጣዊ ድክመቶቻቸውን አብጠርጥረው
ለይተው በአስፈላጊው ቦታ ተስማሚውን የፖለቲካ ካርድ እያወጡ አንድም ተቃዋሚዎች
የሃሳብ የበላይነት እንዳይዙ ሁለትም ተቃዋሚዎች ሲጠንክሩ እጅ በመዘርጋት ማለትም
በጥቅማ ጥቅሞች በመደለል እንዲሁም እጅ በመጠምዘዝ ይቆጣጠሯቸው ነበር:: ስለዚህም
የተቃዋሚዎች ውስጣዊ ድክመቶችና የገዢው ቡድን ሁለንተናዊ የበላይነት ጋር ተዳምሮ

ተቃዋሚዎች በመርህ ላይ የተመሰረተ የጋራ አጀንዳና ትብብር መፍጠር እንዳይችሉ
አድርጓቸዋል:: በመሆኑም የተቃውሞ ትግሉ ወደፊት መራመድ እንዳይችልና እስካሁን
ከተከፈለበት መስዋእትነት አንጣር ውጤታማነት እንዳይኖረው ሆኗል::
ስለዚህም አጠቃላይ የትግሉ አላማ መሆን የሚገባው አንዱን ስርአት ጥሎ በሌላ ስርአት
መተካት ሳይሆን፤ ስርአት የመተካቱ ሂደት በባህሪው ዴሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ
መሰረታዊ ለውጥን ሊላበስ ይገባዋል::  ለዚህም፣ ግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ፣ በትላንት
ቅራኔዎች የተተበተበ፣ በበቀል የተሞላ፣ በጭፍን አስተሳሰብ የተደገፈ የተቃውሞ እንቅስቃሴ
ውጤት እንደማያመጣ መገንዘብና የውጩን መልካም ዕድልና ፈተናዎች በአግባቡ
ለመጠቀም ውስጣዊ ብቃት ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል::
መሰረታዊ የትግል ስልት ሊመራ የሚገባው በሰላማዊና ህጋዊ ማዕቀፍ ሊሆን ይገባል::
ብዙዎች ወታደራዊ አመጽን እንደ ዋነኛ የትግል ስልት የሚወስዱ አሉ:: ነገር ግን በጠመንጃ
አፈሙዝ አንድትን፣ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊነትንና ነጻነትን ማግኘት የሚቻልበት መንገድ
በጣም ጠባብና እጅግ አደገኛ ነው:: ትሬር ካረቭር የተባለው ፖለቲካ ሳይንቲስት “Dictatorship in History and Theory: Bonapartism, Caesarism, and Totalitarianism”
ብሎ በሰየመው መጽሃፉ እንደሚሟገተው ምንኛውም ትግል የሃይል እንቅስቃሴን በይበልጥ
የሚጠቀም ከሆን ዴሞክራሲያዊ የመሆን እድሉ በዛው ልክ በጣም አናሳ ነው::  በእርሱ
ቃሎች እንደሚከተለው ይገልጸዋል::
“There has been a good deal of violence, terrorism, armed struggle,
civil war, and worse in the history of the foundation and defense of
democratic regimes. By definition, none of them emerged through democratic process, and the close any struggle comes to force of arms, the
less democratic it is bound to become (Terrell Carver 2004: 107)”
የአጠቃላይ የትግል አላማውም ሆነ ግቡ ለሁሉም እኩል የሆነች፣ ነጻነትና እኩልነት
የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህና የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ መሰረታዊ የብሔር
ብሔረሰቦች ጥያቄዎች የተመለሰባት ዴሞክራሲዊያት ኢትዮጵያን መፍጠር እስከሆነ ድረስ
የትግል ስልቱም እነዚህን ጉዳዮች ይበልጥ ሊያሳካ በሚችልበት አኳኋን መሆን አለበት::
ለዚህም፣ የመጨረሻ ውጤቱ የውጤቱን መንስኤ ይገልጸዋል፤ ወይም ደግሞ የውጤቱ
መንስኤ የመጨረሻ ውጤቱን ይገልጸዋል የሚለው ከሁለት አንዱ አስተሳሰብ ሳይሆን
ለአጠቃላይ የትግሉ አላማ ስኬት የሚስፈልገው ሁለቱንም አስተሳሰቦች ያማከለ መሆን
ይገባዋል::  የትግል ስልቱም የመጨረሻ ውጤቱን ታሳቢ ያደረገ፣ የውጤቱን መንስኤዎች

ከጠቃላይ የትግሉ አላማ ጋር እያዛመዱና መንስኤዎችን ወደውጤት የመቀየር ሂደቱን
ሁሉን አሳታፊና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን ማስቻልን የሚጠይቅ ነው::
2.2  የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ በተመለከተ
የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ የያ ትውልድ እንዲሁም የአሁኑንም ትግል ማዕከላዊ አጀንዳ
ነው::  ይህ ጥያቄ በሶሻሊስታዊ በተለይ ደግሞ በሌኒኒስታዊ-ስታሊኒናዊ ዕይታ እንዲታይ
ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተውና ፈረ-ቀዳጅ የሆነው የዋለልኝ ጹሁፍ ነው::  ይህን ጥያቄ
ከራሱ ታሪካዊ ዳራና ትርጉም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው::  የገዢው ቡድን ይህን ጥያቄ
ከአማራ ገዢ መደብ በተለይ ከሸዋ-አማራ የበላይነት አንጻር ሲያዩት፣ የተወሰኑ ምሁራን
የዋለልኝን ጹሁፍ ጨምሮ ይህን ጥያቄ ከአማራ-ትግራይ የበላይነት አንጻር ሲመለከቱት፣
እንደ ጆህን ማርካኪስ “Ethiopia: The Last Two Frontiers” የመሳሰሉ ሙሁራን ደግሞ
የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ከመሃል ሃገር-ዳር አካባቢ ባሉ የህዝቦች ግንኙነት አንጻር
ይመለከቱታል::  እንደ ዶ/ር መራራ ያሉ ደግሞ ይህንኑ ጥያቄ ከአማራ፣ትግራይና ኦሮሞ
ልሂቃን መካከል በሚደረግ የስልጣን ሹኩቻ አንጻር ያዩታል::  በሌላ በኩል ደግሞ እንደ
ሮደሪገር ኮርፍ የመሳሰሉ የፖለቲካል ሶሾዮሎጂ ሳይንስ ሙሁራን የብሔረሰብ ጉዳይን
ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሚታ አንጻር ሲመለከቱት በዚህም ላይ የሚመሰረት ግንኙነትን
በመሰረታዊነት አንድን ቡድን ያገለለ የጥቅም ግንኙነት እንደሆነ ይገልጹታል:: ይህም ማለት
የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ በጣም ውስብስብና በአመክንዮ ላይ የተመሰረተ መልስ
የሚያስፈልገው ነው::
ይህ ጥያቄ ለተቃዋሚ ኃይሎች የበለጠ ውስብስብ የሚሆነው ከኢህአዴግ አቋም አንጻር ነው::
በአሁኑ ጊዜ ያሉ ተቃዋሚ ኃይሎች የተወሰኑት የበለጠ ስልጣንና መብት ለብሔር
ብሔረሰቦች መሰጠት አለበት የሚል አቋም ሲያራምዱ፤ የተቀሩት ደግሞ አሁን ከተሰጠው
ለብሔር ብሔረሰቦች ስልጣንና መብት ተቀንሶ ለማዕከላዊ መንግስት ይሁን የሚሉ ናቸው::
በዚህም ምክንያት ገዢው ግንባር በዚህ ጥያቄ ላይ ያለው መልስ አማካይ የሆነ የሚመስል
ነው::  በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ያለው የፌደራል አወቃቀር የበለጠ የተቃማዊ ኃይሎችን
በብሔረ ፖለቲካ የተጠመዱ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል::  እንደ አብነትም ያህል በአሁኑ ጊዜ
ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አብዛኞቹ በብሔር ላይ የተመሰረቱ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው::  እንደዚሁም በብሔር ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎችና ህብረ-
ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረጉት የጥምረትና ቅንጅት እንቅስቃሴዎች በአጠቃላይ
ሊባል በሚችል መልኩ ፍሬ አልባ ነበሩ:: ወይም ደግሞ ፍሬ አልባ ናቸው::

በንድፈ-ሃሳባዊ የፖለቲካ ውይይት ዕይታ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ የሚወድቀው
በግለሰብና የቡድን መብቶች ቅድም ተከተል ላይ የቱ ቅድሚያ መውሰድ አለበት በሚል ነው::
በፖለቲካ ፍልስፍና ታሪክ እንደሚታወቀው በግለሰብ መብቶች ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ዕይታ
በደንብ ተጠናክሮ የወጣው በሶሻል ኮንትራስቸዋሊስት (social contractualists)  ተብለው
በሚታወቁት ሆብስ፣ ሩሶው፣ ሞንተስኪውና ሎኬ ስራዎች ነው::  ሆኖም ግን በነዚህ
ፈላስፋዎች ስራዎች እንደተመለከተው የግለሰብ መብቶች ራሳቸውን ችለው የሚቆሙ
ሳይሆን ከሌሎች ግለሰቦች መብቶች፣ ግዴታዎችና ፍላጎቶች ጋር በተያያዘ መልኩ
ማህበረሰባዊ ስምምነቶች ሲኖሩ ብቻ ነው::
ከላይ የተጠቀሰውን በአውሮፓ ተጨባጭ የህይወት አውድ ላይ የተመሰረተውን ንደፈ-ሃሳባዊ
ዕይታ በበለጠ መልኩ ወደ አፍሪካ አምጥቶ መመልከቱ ተገቢ ነው::  በአውሮፓውያን
ፍላስፍና አድማስ እኔ ማለት እኔ ነኝ (I am because I am)  ሲሆን፣ በአፍሪካውን
ፍልስፍና ደግሞ እኔ ማለት እኛ (I am becasue we are)  ማለት ነው::  ይህ ልዩነት
መሰረታዊ የሚሆነው የአውሮፓውያንን የማህበረሰብ አወቃቀርና እዚያ ላይ የተመሰረተውን
ፍልስፍናቸውን ለመረዳት በሚደረግ ጥረት ውስጥና እንዲሁም የአፍሪካውያንን የማህበረሰብ
አወቃቀር ጋር ለማስተያየት በሚሞከርበት ጊዜ ነው::  በተጨባጭ በአገራችን ኢትዮጵያ
የተለያዩ የየራሳቸው ቋንቋ፣ ማንነት፣ ባህልና ትውፊት ያላቸው የብሔር ብሔረሰቦች፣
ሃይማኖቶች፣ ልምዶችና ባህሎች የሚገኙባት ናት::  ከዚህም በላይ፣ በዘመናዊት ኢትዮጵያ
የግንባታ ሂደት ውስጥ የተደረጉ የብሔር ብሔረሰቦችን መብትና ባህሎች የሚጋፉና
በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎችም ህልውናቸውን በሚፈታተን መልኩ የተደረገ ነበር::
ስለዚህም የብሔር ብሔረሰቦች መብቶችን ከግለሰቦች መብት ጋር አጣምሮ ማክበር
የሚቻልበት ዕድል ዝግ አይደለም::  መሆን የሚገባውም የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሀገራዊና
ታሪካው ሁኔታዎች ያገናዘበ፤ የተዛነፍን የህዝቦች ግንኙነት በሚያድስና የነገን አብሮነትና
አንድነት በሚያጠናክር መልኩ አይዲዮሎጂካዊና ስትራተጂካዊ ቅርጽ መያዝ አለበት::
ተቃዋሚ ኃይሎችና ልሂቃን ኢትዮጵያዊነትንና የብሔር ብሔርተኝነትን እንደ ሁለት
የተለያዩ ማንነቶች ሳይሆን ተያይዘው በአንድነት ሊከበሩና ሊገለጹ የሚችሉ የአብሮነታችን
ሁለትም አንድም፣ አንድም ሁለትም የሆኑ መብቶች ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ
መስራት አለባቸው:: ይህም የገዢው ግንባር በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም ስርአትን
እንደ ቋንቋ፣ ኢኮኖሚዊ ትስስር፣ ለአስተዳደር አመቺነትና የመሳሰሉ መስፈርቶች ላይ
የተመሰረተና የህዝቦች በግባባት ላይ የቆመ የፌደራል ስርአት መዘርጋትን እንደ ግብ
መያዝን የሚጠይቅ ነው::

2.3  የእርቅና የመታደስ አስፈላጊነት
የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ከሞላ ጎደል የውስጥና የውጭ ጦርነቶች የበዛበት ታሪክ
ነው::የውጩን ጦርነቶች እንኳን ብንተው፣ የውስጥ ጦርነቶች የሚፈጥሩት ኢኮኖሚያዊ ፣
ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጫናዎችን ወደ ጎን ብንተው፣ በህዝቦች ላይ ያደረሰውን ስነ-ልቦናዊ
ችግሮችን ወደ ጎን የማያስደርገን ደረጃ ለይ ደርሰናል::ይህ የጦርነት ታሪክ ይበልጥ ውስብስብ
የሚሆነው የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ አስተዳደር ማለትም ፊዊዳላዊ፣ ወታደራዊና አምባገነናዊ
አገዛዝ የስልጣን መደላድሎችንና ስልጣናቸውን የሚያስጠብቁበት መንገድ በህዝብ ውስጥ
ፍርሃትን የሚያነግስ በመሆኑ ጭምር ነው::  በጦርነቶች የመጨረሻ ውጤት የአንድ ወገን
አሸናፊነትና የሌላ ወገን ተሸናፊነት ሲሆን ይህም አሸናፊው በአሸናፊነት ሊቀጥል የሚችለው
ተሸናፊው እንደገና እንዳያንሰራራ በሚያደረግ መልኩ ሲጫነው ሲሆን ተሸናፊውም
ተሸናፊነቱን አምኖ የሚቀበለው እራሱን እንደገና እስኪያንሰራራ ድረስ ነው:: ይህም ሁኔታ
የጦርነት አዙሪትን ይፈጥራል:: በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ በእርግጥም ይሄው ነው::
ይህንን የጦርነት አዙሪት ለመስበር፣ አሸናፊው ሁሉንም ይወስዳል አስተሳሰብ ለመላቀቅና
ሁሉም ወገን አሸናፊ ሊሆን የሚችልበትን ስርአት ለመገንባት ሁሉም ኃይል የዕርቅና
የመታደስ ሂደት ውስጥ ማለፍ ይገባቸዋል::  አለም አቀፉ የዴሞክራሲና የምርጫ ድጋፍ
ተቋም የዕርቅና የመታደስ ሂደትን እንደሚከተለው ይፈታዋል:: [It is] a process through
which society moves from a divided past to shared future (IDEA Handbook
2003: 12).  በዚህ ፍቺ መሰረት የዕርቅና የመታደስ ሂደት ዋና አላማም አንዱ ይቅርታ
ሰጪ ሌላው ተቀባይ አሊያም ደግሞ በባለፈው ጥፋቶች ላይ ለመወቃቀስ ሳይሆን፤ ዋናው
አላማው አንድን ማህበረሰብ ከተከፋፈለ ግንኙነት ወደ የጋራ አንድነትና ብልጽግና መውሰድ
ነው::
የኛም ማህበረሰብ በፖለቲካ ቅራኔ የተወጠረ ማህበረሰብ ነው::  ለምሳሌ፣ በሁለት የተለያዩ
የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ኖሮን አያቅም:: በኢህአፓና
መኤሶን መካከል የነበረው የጥላቻ ፖለቲካ መሰረቱ ግለሰባዊ ፉክክር ቢሆንም፣ የጥላቻ
ፖለቲካውን ወደ ግልጽ የመጠፋፋት ግንኙነት የቀየረው ግን ፖለቲካዊ ልዩነቶች ሳይሆኑ
ማህበራዊ ቁርሾዎች ናቸው::  በነዚህ አንጋፋ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የነበረው
ግንኙነት ከነሱ በኋላ ለተፈጠሩትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በእርስ የጥላቻ  ግንኙነቶች
መንገድ ከፋች ሆኖ ነው የቀረው::  ይህ የጥላቻ ፖለቲካ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ብቻ
ሳይሆን በአንጋፋ የፖለቲካ ልሂቃንና መሪዎች መካከል ያለ ጭምር ነው:: በፖለቲካ

ፓርቲዎች መካከል ብቻ ሳይሆን ዛሬ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውስጥ ቅራኔዎችና
የስልጣን ሽኩቻዎች እየታመሱ ናቸው::
በጥላቻ ፖለቲካ በሚመራ የፓለቲካ ስርአት ውስጥ ሁሉንም ሊያስማሙ የሚችሉ ተቋማትና
ተቋማቱ ሊመሩባቸው የሚችሉ የህግ ማዕቀፎች ሊኖር አይችልም:: ለዚህም ሁሉም ኃይሎች
መጀመሪያ ራሳቸውን ማደስና ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መዘርጋት አለባቸው::
የተቀዋሚ ኃይሎች ውስጣዊ ጥንካሬ ከሌላቸው ምንም ያህል ውጫዊ አጋጣሚዎች
ቢኖራቸው በውጤታማነት ሊጠቀሙበት አይችሉም:: ለዚህም እንደምሳሌ እንዴት ደርግ
ስልጣን እንደያዘ ማስታወስ ተገቢ ነው:: ውስጣዊ መታደስ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ
መጀመሪያ መካሄድ ያለበት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው:: እራሱን ያላደሰ፣ እራሱን ከውስጣዊ
የስልጣን ሹኩቻ ያላወጣ፣ በጥላቻ ፖለቲካ ጽንፍ የያዘ በምንም ታምር ሁሉን አቀፍ
የይቅርታ መድረክ ላይ በውጤታማ ሁኔታ ሊሳተፍ አይችልም::
የፖለቲካ መሪዎች በተማሪነት ዘመናቸው አሊያም ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል
በነበረ ግንኙነት ያዳበሩትን ጽንፍ የወጣ በጥላቻ የታፈነ የእርስ በእርስ ግንኑነት ማስወገድ
ያለባቸው በስልጣን ላይ ያለውን ስርአት ለመቀየር ለሚደረገው ትግል ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ
ለሚመሰረተው ሁሉን-አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረትም ስለሆነ ጭምር ነው::
ውስጣዊ መታደስ እንግዲህ ግቡ ስልጣን ላይ ለመውጣት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን
የፖለቲካ ባህል በመሰረታዊነት ለመቀየር ጭምር ነው::  ባልተቀየረ ፖለቲካዊ ባህል ላይ
ሊተካ የሚችልው ቀድሞ የነበረውን ስርአት ከተወሰነ ኮስሞቲክስና ግለሰቦች ለውጥ ነው::
ባልተቀየረ ፖለቲካዊ ባህል ላይ ተመስርቶ መሰረታዊ መንግስታዊና ብሮክራሲያዊ
የአወቃቀር ለውጥ ሊመጣ አይችልም:: ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል በማለት ብቻ ብሔራዊ
እርቅ ሊኖር አይችልም:: ላለፉት 20  ዓመታት ብዙ ሙሁራኖችና የፖለቲካ ኃይሎች
ብሔራዊ ዕርቅ እያሉ ቢለፉም አንድም ጠብ ያለ ነገር የለም:: ይህም ውስጣዊ መታደስን
ሳያስቀድሙ በመቅረታቸው ነው:: ለዚህም ካለፈው በመማር መጀመሪያ ውስጣዊ መታደስን
በማምጣት ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ውስጣዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለጋራ አላማ
መሳካት በአንድነት ሊቆሙ የሚችሉት::
2.4 ውስጣዊ አቅምን በተመለከተ
የተቃማዊ ኃይሎች ካለባቸው ሁለንተናዊ ድክመቶች ውስጥ አንዱ ውስጣዊ አቅም አለመኖር
ነው:: ውስጣዊ አቅም ሲባል ተቃዋሚ ኃይሎች ድርጅታዊ አደረጃጀት፣ ድርጅታዊ ስርአትና
የሰው ኃይልን የሚመለከት ነው:: አደረጃጀት ከስርአት መቅደም አለበት አሊያም ስርአት
ከአደረጃጀት ይቀድማል የሚለው የስትረተጂክ ማኔጅመንት ንደፈ-ሃሳባዊ ክርክር በራሱ ብዙ

የሚያስብል ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎችና ልሂቃኖች ልምድ ስንነሳ ግን
በአብዛኛው የመናገኘው አስተሳሰብ ማደራጀት፣ ማስታጠቅና ማታገል የሚለውን ንድፈ-ሃሳባዊ
ሃዲድ ነው:: በመሰረቱ ይሄ የአስተሳሰብ ሂደት የሚመነጨው ከማርክስ፣ ሌኒንና ማኦ
ፍልስፍናዎች ናቸው::
ትናንሽ የተቃማዊ ኃይሎች አደረጃጀት የተበጣጠሰ አሰራርና የተወሰነ የሰው ኃይል
ስለሚይዝ የህዝብ ተደራሽነትን የማያጎናጽፍ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት
አቻችሎና አጣጥም ወደ ሁሉን-አቀፍ አላማ (common objective)  የማያሸጋግርና
ለተቋማዊ ልህቀት ማለትም የፖለሲ ጥራት፣ የነጠረ ራዕይና የፖሊሲና ዕቅድ አፈጻጸም
አቅም ውስኑነት የሚዳርግ ነው:: በሌላ በኩልም የኢትዮጵያን ፖለቲካ በገዢው ግንባር
ውስጥም ሆነ በተቃማዊ ጎራ ሆነው የሚመሩት በተመሳሳይ መልኩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን
ተቋማዊ አቅም የሚለኩባቸውም ሆነ የሚመኩባቸው መስፈርቶች በአመዛኙ የሌኒዚምና
ስታሊኒዝም አሰተሳሰቦች ላይ የተመሰረቱና የአሁኑን ተጨባጭ ሁኔታዎች ያላገናዘቡ
ናቸው:: የገዢው ግንባር የተቋማዊ አቅም አስተሳሰብ የሚንጠለጠልባቸው ነገሮች በዋናነት
የፋይናስና የማቴሪያል አቅርቦቶች፣ ሁሉን አቀፍ ቁጥጥርና የህዝብ አደረጃጀቶች ናቸው::
በተመሳሳይ መልኩ የተቃዋሚ ኃይሎች ጊው ግንባር ጋር የመገዳደር አቅማቸውን
የሚለኩባቸው መስፈርቶች ሃሳባዊ የህዝብ ተቀባይነት፣ የገዢው ኃይል አምባገነንነትና
የነርሱ ዴሞክራሲያዊነትና ኢትዮጵያዊነት ናቸው::
ከላይ የተመለከቱት ተቋማዊ መስፈርቶች አንድም ተቋማዊ ኃይሎች አንድነታቸውንና
መስተጋብራቸውን እንዳያጠናክሩ የትኛው ኃይል ይበልጥ በገዢው መደብ ተበድሏል፣
ተጨቁኗል በሚል የተሸናፊነት ስነ-ልቦና ጋር በመዳበሉ ምክንያት በኢትዮጵያ ፖለቲካ
የሚሳተፉ የፖለቲካ ሊህቃኖች ከፊታቸው የተደቀነውን ትግልና የሃይል መዛለፍ ካለመረዳት
ጋር ተዳምሮ በአሁኑ ሰአት የተቃዋሚ ኃይሎች በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው የተቀባይነት
ደረጃ ከምርጫ 1997  ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ነው:: ደካማ ተቋማዊ ብቃት ህብረተሰባዊ
ተቀባይነትን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካ ኃይሎች የሚከተሉንትን የፖለቲካ ስልት ጭምር
ይወስነዋል:: ለምስሌ፣ በምርጫ 1997  ይብዛም ይነስም የተቃማዊ ኃይሎች የነበራቸው
አቀራረብ ከዜሮ-ድምርና እንካ-ሰላንቲያ ፖለቲካ ወጣ ያለና ገዢውን ኃይል በወሳኝ ሀገራዊ
ጉዳዮች ላይ የሞገቱበትና አማራጭ ሃሳቦች ያቀረቡበት ነበር:: ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ
ፖለቲካ አንዴ ብቻ ፈንጥቆ የጠፋ ጉዳይ ነው::
ውስጣዊ አቅሙን የገነባ የተቃዋሚ ኃይል ለመቃወም ብቻ የሚቃወም የፖለቲካ ኃይል
ሳይሆን የሚሆነው የገዢው መደብን ድክመቶችና ጥፋቶች እያመላከተ አማራጭ ሃሳብ

የሚያቀርብ፤ተቋማዊ ቅርጹ ከግለሰቦች ስብእና የላቀና የሌሎችን የፖለቲካ ኃይሎች አማራጭ
የሚረዳና ሁሉን አቀፍ አጀንዳዎች ላይ በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ እየተስማማና የሃሳብ
ልዩነትን እንደተፈጥሮአዊ ህግ የሚቀበል ነው የሚሆነው:: በሀገራችና በሁሉም የፖለቲካ
ኃይሎች ላይ የሚስተዋለው ዋናው ችግር ግለሰባዊ ስብዕና ከፓርቲዎች ህብረተሰባዊ
ተቀባይነት በላይ የሆነና፣ በዚህም ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደግለሰባዊ ንብረትነት
የሚታይበት አስተሳሰብ እያየለ ነው:: ይህም በፖለቲካ ኃይሎች ውስጥ የሃሳብ ልዩነት
ሳይሆን የግለሰቦች ግላዊ ጥላቻዎች በልጠው እንዲታዩ አድርጓል:: በዚህም ሳቢያ የተበታተነ
የተቃውሞ ኃይሎች እንዲፈጠሩና በተመሳሳይ መልኩ እርስ በርሳቸው በጠላትነት
መተያየታቸው በትንሹ እንኳን የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚለው መርህ እንኳን ላይ
የተመሰረተ ጊዜያዊና ታክቲካዊ ትብብር መመስረት ተስኗቸዋል::
ይህ የተቀውሞ ተቃዋሚነትን ያለመረዳት ችግር በመሰረታዊነት የፖለቲካ ኃይሎችን
ህብረተሰባዊ ተቀባይነትንና መሰረትን እያሳጣቸው ይገኛል:: ይህም የፖለቲካ ኃይሎች ወደ
ህብረተሰቡ ውስጥ በመግባትና ህብረተሰቡን በማንቃት የተጠናና በደንብ የተመራ መሰረታዊ
ስርነቀል   ለውጥ ለማምጣት የሚችሉበትን እድል ከመዝጋቱም በላይ እራሳቸው የተቃማዊ
ኃይል ልሂቃኖች የተጣለባቸውን ሃላፊነት በወጉ የተረዱ አይመስሉም:: ለምሳሌ ያህል
በቅርቡ ዶ/ር ነጋሶ በጻፉት ጹሁፍ ላይ “ህብረተሰባችን ብሶተኛና የሚያጉረመርም እንጂ ይህ
ስሜቱ ወደ ህበረተሰባዊ ንዴት አልተለወጠም” ብለዋል:: ይህ አባባል በመሰረታዊነት
የሚነሳው ህዝቡ በመጀመሪያ ደረጃ በሥልጣን ላይ ያለውን ሃይል ለማውረድ አደባባይ
መውጣት አለበት ከዚያ የፖለቲካ ልሂቃኖቹ ወደስልጣን እንምጣ ከሚለው አስተሳሰብ ነው::
ለፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኝ ከሆነው ፖለቲካዊ ስራዎች ወሳኙ ህብረተሰቡን የማንቃትና
የማደራጀት ስራ ነው:: ይህን የቤት ስራ ሳይሰሩ የህበረተሰቡን የንቃት ደረጃ
እንደምክንያትነት ማቅረብ ተገቢ አለመሆን ሳይሆን ለፖለቲካ ፓርቲዎች ውድቀት ጭምር
ነው::
3. እንደማጠቃለያ
የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ባህልና የተቃውሞ አደረጃጀት ታሪክ እንደሚያሳየው ከሆነ በወዳጅና
ጠላት ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ነው:: ይህ ክፍፍል በፓለቲካ ተዋናዮች መካከል
በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳይፈጥሩ ብቻ ሳይሆን ያደረጋቸው፣ በተቃማዊ
ኃይሎች መካከልም ጭምር አንድነት እንዳይኖሯቸው አድርጓል:: ይህ የጥላቻ ፖለቲካዊ
ባህል ስር የሰደደና ተቋማዊ ቅርጽ የተላበሰ ሆኗል:: በሌላ በኩልም፣ የገዢው ኃይል
ልሂቃኖች እውቀት ላይም ሆነ ጉልበት ላይ የተመሰረተ በተቃዋሚዎቻቸው ላይ የበላይነት

ነበራቸው በጊዜ የተወሰነም ቢሆን:: አጼ ኃይለስላሴ፣ ጓድ መንግስቱና ጠ/ሚ
በተቃዋሚዎቻቸው ላይ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የበላይነት ነበራቸው:: ለዚህም አንዱ
ምክንያት የኢትዮጵያ መሪዎች ተቃዋሚዎቻቸውን ለማጥፋት መንግስታዊ ተቋማትን
ጭምር መጠቀማቸው ነው:: በሌላ በኩል ግን፣ ተቃዋሚዎች እራሳቸው አንድነት መፍጠር
አለመቻላቸው ነው::
ይህ ከላይ የተመለከተው የፖለቲካ ድህነት አዙሪት አሁንም በኢትዮጰያ ፖለቲካ ውስጥ
ጉልህ ሥፍራ መያዙ ነው:: ይህ አዙሪት ሳይወገድና በመሰረታዊነት የኢትዮጵያ ፖለቲካ
ባህል ሳይለወጥ፣ ዴሞክራሲያዊት    ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገው ትግል የመጨረሻ
ውጤቱ አሁን ያለውን አገዛዝ በባሰ አገዛዝ መተካት ይሆናል:: ይህ እንዳይሆን የፖለቲካ
ሃይሎች ተቋማዊ አቅም በመገንባት፣ ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ ባህል በማስፈን እራሳቸውን
መዳስ ይገባቸዋል:: በዚህም በገዢው ሃይል ተይዞባቸው የነበረውን አይዲዮሎጂካዊና
ስትራተጂካዊ የበላይነት በመቀልበስ የሃይል አሰላለፉን መቀየር ይችላሉ::

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate