Pages

Feb 22, 2013

መርዝ ከውጭ ይረጫል ወይም ከውስጥ ይመነጫል

ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

መርዝ ከውጭ ይረጫል ወይም ከውስጥ ይመነጫልበአለፉት ሠላሳ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ችግሮችን መፈልፈያ መሣሪያ ሆናለች፤ ለብዙ ምዕተ-ዓመታት ይዘናቸው (ምናልባትም አቅፈናቸው ማለት ይሻል ይሆናል) ስንንከባለል የቆዩ ችግሮች ሞልተውናል፤ እያሰብን እነዚያን የቆዩ ችግሮቻችንን በመፍታት ፋንታ ሌሎች አዳዲስ ችግሮችን እየፈለፈልን የተቆላለፉና የተወሳሰቡ፣ ውላቸው የጠፋ ችግሮችን ፈጥረናል፤ እየፈጠርንም ነው፤ አሁን በመፈጠር ላይ ያለው አዲስ ችግር እስላማዊ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚል ነው፤ እስቲ እንመልከተው፡፡
በሩቁ እንጀምር፤ እስላማዊ መንግሥታት ያቋቋሙ አገሮች አሉ፤ አንዳቸውም ሰላም የላቸውም፤ እስላማዊ ቡድኖች በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን የያዙ አሉ፤ ለምሳሌ በቅርቡ በአረብ አገሮች በተጀመረው የፖሊቲካ እድገት ለውጥ በቱኒስያና በግብጽ እስላማዊ ቡድኖች አሸንፈው ሥልጣን ይዘዋል፤ በዚህም ምክንያት በቱኒስያና በግብጽ የለውጥ ጥያቄ አገርሽቶ አንደገና ሰዎች እየሞቱ ነው፤ በነዚህና በሌሎችም አገሮች የሚገኙት ወጣቶች የሚፈልጉት የሰው ልጆች ሁሉ መብቶች የሚከበሩባቸውና በሙሉ የግለሰብ ነጻነት የተረጋገጡባቸው አገሮች እንዲኖራቸውና በእኩልነት ኩሩ ዜጎች ሆነው እንዲኖሩ ነው፤ የአንድ አገር ዜጎች የተለያየ ዘር፣ የተለያየ የቆዳ ቀለም፣ የተለያየ ቁመትና ውፍረት፣ የተለያየ ጾታና ዕድሜ፣ የተለያየ ቋንቋ፣ የተለያየ ሃይማኖት፣ የተለያየ የፖሊቲካ አመለካከት፣ የተለያየ ትምህርት፣ የተለያየ ሙያና የተለያየ ገቢ ሊኖራቸው ይችላል፤ የጋራ ማንነታቸው ዜግነት ነው፤ እኩልነታቸው በዜግነታቸው ነው፤ አንድነታቸው በዜግነታቸው ነው፤ እኩልነታቸውንና አንድነታቸውን የሚያረጋግጥላቸውና ሚዛኑን የሚጠብቅላቸው ከበላይ ሆኖ ሁሉንም የሚገዛው ሕግ ነው፡፡
በቡድን ወይም በጅምላ የሚያስቡ ሰዎች የሕግን ባሕርይ አያውቁትም፤ ‹‹ክርስቲያኖች እስላሞችን እንጨርሳለን›› አሉ፤ ወይም እስላሞች ክርስቲያኖችን እንጨርሳለን›› አሉ፤ በሚል አሉባልታ ላይ ክስ ተመሥርቶ ሕጋዊ ፍርድ መጠበቅ አይቻልም፤ በየትም ሆነ በማንኛውም ጊዜ ጽንፈኛ እምነትና አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ይገኛሉ፤ እነዚህ ግለሰቦች ሕልማቸውንም ሆነ ቅዠታቸውን በስውርም ሆነ በአደባባይ ይገልጻሉ፤ ለምሳሌ በአሜሪካ ጥቁሮችንና ይሁዲዎችን ከአገሩ ጠራርገን እናወጣና ንጹሕ የነጮች አገር እንፈጥራለን የሚሉ ግለሰቦች አሉ፤ ይህ እምነት ለአሜሪካ ማኅበረሰብ መርዝ ነው፤ አሜሪካ የነጻነት አገር ነው፤ የነጭ ዘረኞቹ መርዛቸውን ለመንዛት መብት አላቸው፤ የዘረኞቹን መብት ለማፈን የሚወሰድ የጡንቻ እርምጃ ሁሉ አሜሪካ የነጻነት አገር መሆኑን ይሽራል፤ ከዚያም በላይ የአሜሪካ መንግሥት በሚከተለው ዘዴ ከነጭ ዘረኞቹ የተሻለ አይሆንም ነበር፤ ስለዚህም ነጭ ዘረኞችን ለመቋቋም የሚወሰደው አርምጃ አሜሪካ የነጻነት አገር መሆኑን ሳይሽርና ነጭ ዘረኞቹም እምነታቸውን የመግለጽ መብታቸው ሳይደፈጠጥ መሆን አለበት፤ የነጻነት ትርጉሙ ይህ ብቻ ነው፡፡
በሥልጣን ወንበር ላይ ስለተቀመጡ ብቻ አንድ ዓይነት የፖሊቲካ እምነት ብቻ ይዞ ሌላውን መደፍጠጥ፣ መንግሥት የባረከውን አንድ ዓይነት የኦርቶዶከስ ሃይማኖት ብቻ ማደርጀትና ሌላውን ማፈን፣ መንግሥት የባረከውን አንድ ዓይነት የእስልምና ሃይማኖት ብቻ ማደርጀትና ሌላውን ማፈን ልማድና የአሠራር ባህል እየሆነ ሲሄድ ሁሉንም ነገር አንድ ዓይነት ብቻ ለማድረግ የሚታየው ጥረት የኢትዮጵያን ጉራማይሌ ባሕርይ የሚቃረን በመሆኑ ስር አይኖረውም፤ ይህ ሁሉም ሰው ሊያስብበት የሚገባው አንዱ ነገር ነው፤ ሁለተኛው አንድ ወይም ጥቂት ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እስላማዊ መንግሥት እናቋቁማለን ቢሉ አገር የሚሸበርበት ምንም ምክንያት የለም፤ ኢትዮጵያን የኦርቶዶክስ ክርስቲያን አገር ለማድረግ የሚመኙም አሉ፤ ኢትዮጵያን ሃይማኖት-አልባ የጉግማንጉግ አገር ለማድረግ የሚፈልጉ አሉ፤ ኢትዮጵያ በአንድ አጋጣሚ ወንበሩ ላይ የወጣ ጉልበተኛ የሚያትምባትን እምነትም ሆነ ሃይማኖት የማትቀበል አገር መሆንዋ ተደጋግሞ የታየ ነው፤ ኢትዮጵያን የይሁዲ አገር ለማድረግ ተሞክሮአል፤ ኢትዮጵያን የክርስቲያን አገር ለማድረግም ተሞክሮአል፤ ኢትዮጵያን የእስላም አገር ለማድረግም ተሞክሮአል፤ ሁሉም አልሆነም፤ ኢትዮጵያ የሁሉም አገር ሆና ዘልቃለች፤ ይህንን በማክሸፍ ለማንም ምንም ጥቅም አይገኝም፤ በአንጻሩ ደግሞ የሥልጣን ወንበሩ ላይ የወጡ ጉልበተኞች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀውን የነጻነት ጮራ እያዳፈኑ የነጻነትን፣ የእኩልነትንና የሕግ የበላይነትን ዓላማ ለማክሸፍ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው፡፡
የነጻነትና የሕጋዊነት መክሸፍ የሰላም ጠንቅ ነው፤ የሰላም መክሸፍ የልማት ጠንቅ ነው፤ የልማት መክሸፍ ደሀነት ነው፤ ደሀነት የሞት አፋፍ ነው፤ ይህንን ለመገንዘብ የሚያዳግተው ሃያ አንድ ዓመት የሞላው ሰው አለ? ኢትዮጵያን ለመምራት የሚደናበሩት ሰዎች ሁሉ ሃያ አንድ ዓመት አልፎአቸዋል፤ ነገር ግን ከላይ የተገለጸው የመክሸፍ ጉዞ ጭራሽ አይታያቸውም፤የሚታየውም ሲነግራቸው የተበለጡ ስለሚመስላቸው አይሰሙትም፤ ስለዚህም የሚታየውን ሳያዩ፣ የሚሰማውን ሳይሰሙ ጊዜ የሚበላውን ጉልበታቸውን ብቻ ተማምነው በጭፍን እንምራችሁ የሚሉትን ተከትለን ለእኛ በሚታየንና ለእነሱ በተሰወረባቸው ገደል ውስጥ ለምን አብረን እንግባ? አብረን ገደል በመግባት አንድነታችንን የምንጠብቅ የሚመስላቸው ሰዎች በሁለት በኩል ይሳሳታሉ፤ አንደኛ ከአገዛዙ መሪዎች ዘንድ የሎሌ ተከታይነትን እንጂ የአኩልነት አንድነትን አያገኙም፤ እኩልነት በሌለበት አንድነት አይፈጠርም፤ ሁለተኛ ወደገደል የሚጨምር አንድነትን መምረጥ ሕይወትን ትቶ ሞትን መምረጥ ነው፡፡
በሃያ አንድ ዓመት ውስጥ መክተፍ-መከታተፍ ሙያ ሆነ፤ ብዙ ሰዎችና ድርጅቶች ሠለጠኑበት፤ መክተፍ-መከታተፍ አብሮ የመኖር ጸር ነው፤ አብሮ የመኖር ጸር የሚሆነው በፍቅር ፋንታ ጥላቻን፣ በሰላም ፋንታ ጠብን፣ በመረዳዳት ፋንታ መጋጨትን፣ በልማት ፋንታ ጦርነትን በመንዛት ነው፤ አንዳንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በግልጽም ሆነ በስውር እንደጠላት መቁጠርና በእነሱ ላይ ቂምን እንዲቋጥሩ ማድረጉ የማንንም የፖሊቲካ ቡድን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብም ይጎዳል እንጂ አይረዳም፡፡
አሁን ደግሞ በአንድ በኩል በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ በየገዳማቱና ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትና በሊቀ ጳጳሳት ምርጫው ላይ አገዛዙ እያሳየ ያለው ጣልቃ-ገብነት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችን እያስቀየመና እያስኮረፈ ነው፤ በሌላ በኩል በእስልምና ሃይማኖት ላይም የሚታየውን ጣልቃ-ገብነት ተከታዮቹ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በርትተው በመቋቋማቸው እየደረሰባቸው ያለው ግፍ ለጆሮ እየቀፈፈና በጣም አሳፋሪ እየሆነ ነው፡፡
ይህ በሃይማኖቶች ላይ የተጀመረው ዘመቻ ውጤት ይኖረዋል፤ ውጤቱ በአገዛዙ የውስጥም ሆነ የውጭ አመራሩ ላይ ከባድ ተጽእኖ ይኖረዋል፤ የሃይማኖቶቹ ጉዳይ እንደጎሣዎች መከታተፍ በኑሮ ላይ ብቻ ጫናውን የሚያሳርፍና በምድር የሚንከላወስ አይደለም፤ ወደሰማይ ያርጋል፤ የሰማይ ሠራዊትን ይጠራል፤ ያንን ኃይል እንኳን የኢትዮጵያ የጦር ኃይልና የአሜሪካውም አይችለውም፤ ዓይን ያለው ያያል፤ ጆሮ ያለው ይሰማል፤ ልብ ያለው ያስተውላል፤ ዶላር ነፍስን አይገዛም፤ ክብርን አይገዛም፤ ወዳጅንም አይገዛም፡፡
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም፤ የካቲት 2005

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate