ሰላም! ሰላም! መብራትና መጥፋት እንዴት እያደረጋችሁ ነው? ምን ይደረግ ዘንድሮ ከውኃ እስከ መብራት ከሀብት እስከ ድህነት በርቶ የማይጠፋ ጠፍቶ የማይበራ የለም! ዓይን ከማየት ጆሮ ከመስማት አይጠግብ የማናየው የማንሰማው የለም።
ድሮስ ለመሥራት እንጂ ለመስማትና ለማየትማ ማን ብሎን? አትሉኝም?! እውነቴን እኮ ነው! ትንሽ የሰሞኑ የመብራት ደም ማነስ አትሉት ደም ግፊት እያሰቃየ በጊዜ ያስተኛን ወሬያችንን ያቋርጠን ጀምሮ ነው እንጂ፣ ሁሉም ነገር እንደጉድ በየመንገዱ ተበትኖላችሁ ሳያዩና ሳያሙ ማለፍ አላስችል ብሏል እኮ። እኔምለው ግን ‘ኔትወርክ’ እየጠፋ አማሮናል የሚለው ማመልከቻችን ደርሶ መፍትሔ ሳይሰጠው ደግሞ መብራት ኃይል ላይ መጮህ ልንጀምር ነው? ምነው ባልበላ አንጀታችን በየአቅጣጫው ባያስጮሁን ግን?! የእኛ ነገር ያው መጮህ ነው ልምዳችን ብዬ እኮ ነው።
ባሻዬ እሪ ስንል ከርመን የማንደመጠው ነገር ሲታሰባቸው፣ ‹‹እኔማ አሁን አሁን እግዜሩ ለኢትዮጵያዊው አዳም ለይቶ በ‘ጥረህ ግረህ ብላ’ ፈንታ ‘ጮኸህ ጮኸህ ቅር’ ኑር ብሎት ይሆን?›› ይሉኛል ከእሳቸው በላይ እኔ የቅዱሱ መጽሐፍ ሊቅ እመስል። ታዲያ ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ምን ሲለኝ ነበር መሰላችሁ? እንዲያው ነገርን በነገር ማንሳት ስንችልበት እኮ! ‹‹አንበርብር እነዚህ ግብፆች በዓባይ አወዛግበውን ቆቃን ናዱት እንዴ?›› አይለኝ መሰላችሁ። የመሠረተ ልማቱ ሥራ በሙሉ ፖለቲካ የሆነባት አገር ብዬ በሆዴ፣ በአፌ ሌላ ነገር ሳልመልስ በፈገግታ ሸኘሁት። አሁን አሁን ሳስበው ‘በጥርሷ ሸኝታኝ አለችኝ ደህና እደር’ ብሎ ነፍሱን ይማረውና ጥላሁን የተጫወተው ጣፋጭ ዜማ ለእንዲህ ያለው አነካኪ ጨዋታ መዋል የሚችል ነው። መቼም ዘንድሮ በክፉም በደጉም ሳይነካኩ መኖር ከባድ ነው። አስቡት እስኪ መኖር በከበደበት ዘመን የአኗኗር ስልቱ ሲከብድ? በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አትሉም!
ያው እንደምታውቁት በአንዱ ላይ አንዱ ችግራችን ሲደረብ የማንቆጥረው ጉድለት የለም። በዚህ እልም ድርግም እያለ መብራት በሚረብሸን ሰሞን ነው። ከአንድ ‹‹ቪትዝ›› መኪና አስመጪ ወዳጄ ጋር በሥራ ጉዳይ ተገናኝተናል። እኔም ‹‹ቪትዝ›› ፈላጊ ሲመጣ ሲያጋጥመኝ እዚህ ወዳጄ ጋ ነው የምሮጠው። ይገርማችኋል የእኛ አገር ቢዝነስ ጥሎበት ነው መሰል ተመሳሳይ ነው። አሁንማ አገር ምድሩ ‘ቪትዝ’ በሚባል መኪና ተለክፎ እሱን ስናከራይ፣ ስናሻሽጥና ስናስለውጥ መዋል ሆኗል ሥራችን። (‘ቪትዝ ጄነሬሽን’ ተብሏል አሉ) ያው እንግዲህ በየነገሩ ኮሚክ አይጠፋም አይደል? አንዱ ምን አለ ሲባል ሰማሁ፣ ‹‹የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ የምንደርሰው በፋብሪካ መሆኑ ቀርቶ በቪትስ ሆነ እንዴ?›› አለ አሉ። ሳቁንስ ሳቅነው። ከሳቁ በኋላ ያለው ደረቅ የኑሮ እውነታ ባያቃጥለን ነበራ። እንግዲህ ይኼውላችሁ ጨዋታ ነው ብዬ ቀስ በቀስ ራሴን በነገር ሳጠላልፍ የጀመርኩላችሁን የወዳጄን ጨዋታ ስረሳው። ‘ሞት ይርሳኝ’ አልል ነገር የዘንድሮ ሞት የቁም ጭምር ሆኖ ከአንዱ ብንድን ከአንደኛው አንሽርም። የቸገረ ነገር እኮ ነው!
እናላችሁ ከመኪና ነጋዴ ወዳጄ ጋር ስለአገርና ስለሥራ ስንጨዋወት ቆየንና፣ ‹‹አንተማ ምን አለብህ በደህናው ጊዜ አግብተህ፤›› ብሎ የትዳር ጨዋታ አስጀመረኝ። በነገራችን ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የካፌ ስብሰባዎች ከፖለቲካ ስብሰባዎች እኩል እየሆኑ መምጣታቸው ምክንያቱ ትዳር ፍለጋ ነው ሲሉ የሠፈሬ ልጆች የሠሩት ‹‹ሪሰርች›› ጠቁሞኛል። ታዲያ የዘንድሮ ዩኒቨርሲቲዎች ከቁም እንቅልፋቸው አልነቁምና ስለዕለት ተዕለት አኗኗራችን በጥናት የተደገፈ መረጃ ሲያምረን የት እንሂድ? ‹‹አንተ ደግሞ ይኼን ያህል ጊዜ ሥራ ሥራህን ስታይ ቆይተህ አሁን ነው ትዳር ትዝ የሚልህ?›› አልኩት እኔም አንስቶልኝ የማያውቀውን ወሬ ሲያወራኝ። ‹‹አይ አንበርብር አንዳንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራችንን ትረሳዋለህ ልበል? እኔ የሰሞኑ መብራት እንዳሻው መጥፋት ብቸኝነቴን ባይጠቁመኝ አሁንስ ቢሆን የት አስታውሼው?›› ሲለኝ የምለው ጠፍቶኝ ጭጭ አልኩ። አስቡት በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነቱን ነገር የሚነግራችሁ ሰው ሲገኝ። ‘የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር’ ማለት ታዲያ ይኼኔ ነው!
መኪና መግዛት የፈለገው ደንበኛዬ መጥቶ የፈለጋትን ዓይነት መርጦ እስኪያሳውቀን ድረስ ከዚሁ ወዳጄ ጋር ጨዋታችን ደራ። ‹‹አሁን አንተን የመሰለ የልጅ ሀብታም ማግባት አልቻልኩም ብለህ ስታወራ ትንሽ አታፍርም? ኧረ እንዲያው እንዴት ያለችዋ ናት አንተን እንቢ የምትለው?›› ስለው፣ ‹‹አይ አንበርብር! ገንዘብ መስሎህ ነው ቁም ነገሩ? በጨበጣ አገባህ ተርፎህ አገባህ ዋናው እኮ የምታገባት ሴት ባህሪ ነው፤›› ሲለኝ ይኼ ነገረኛ አዕምሮዬ ወዲያው ምን አሰበ መሰላችሁ? ውስጥ ውስጡን ከኑሮ ውድነት እኩል የትዳር ውድነት እንዲህ ሥር ሰዷል ማለት ነው? ስል አሰብኩ። በሎሚ ጠበሳ በሚሪንዳ ጅንጀና ድሮ ቀረ እንላለን እንጂ በመኪና ቁልፍና በስደት ቪዛም ለካ አልሆን ያለው ብዙ አለ?! ጉድ ነው ዘንድሮ። (የዘንድሮ ጉድ ግን አልበዛም?)
ለዚህ ይሆን ታዲያ በትዳር ላይ የዝሙት ሙስና ከገንዘቡ ሙስና ሲበልጥ እያየን ያለነው? ምን ይታወቃል። ለነገሩ ቢታወቅም ዕውቀትና አዋቂ የተናቁበት ዘመን ስለሆነ ዋጋ የለውም። ‹‹እንዲያው ብቻ የዚህ የቁጠባ ቤቱ፣ የባቡሩ፣ የህዳሴው ግድብ የመሳሰለው ተስፋ ሰጪ ማነቃቂያ የልማት ሥራ ሲመጣ ሰው ፍቅሩ እየጨመረ ሲሄድ ማየት ነበረብን፤›› የባሻዬ ልጅ ያለኝ ትዝ አለኝ። ልክ እኮ ነው ታዲያ። ሰው ከሰው ጋር መተባበበር፣ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ለጋራ ለሕዝብ ጥቅም መሥራት፣ ተቃዋሚዎችና መንግሥት በሕዝብ አጀንዳ ላይ መጣመር ሲገባቸው ራስ ወዳድ መሆን በእውነቱ ደስ አይልም። ‹‹ትልቁ ችግራችን ይኼ አይደል ታዲያ? አይተነው የማናውቀውን የእንቅስቃሴና የለውጥ ዘመን እኮ ነው እያየን ያለው። ምነው ተመስገን ብናውቅ?›› ስትለኝ የሰነበተችው ማንጠግቦሽ ናት። ይኼን የውዷን ባለቤቴን ማንጠግቦሽን ማስተዋል ገዥው እስኪመጣ እየተቁነጠነጠ ለሚጠብቀው መኪና ሻጭ ወዳጄ ስነግረው አንድ ገጠመኙን አጫወተኝ። ሦስተኛው ዓለም ላይ ሲኖሩ ገጠመኝ መቼ ያልቅና?!
‹‹ባለፈው ሰሞን ሁለት አፍላ ፍቅረኛሞች ሲሆኑ ያየሁትን ልንገርህማ። እንግዲህ መጀመርያ እኔ ዘንድ መጥታ መኪና መግዛት እንደምትፈልግ ነግራኝ የተዋወቀችኝ እሷ ናት። ኋላ የምትፈልገውን የቀለም ዓይነትና ሞዴል መርጣ ክፍያ ላይ ስንደርስ እሱ መጣ። ከዚያማ ዞር ብለን እንነጋገር ሳይሉ ፊት ለፊቴ የሆድ የሆዳቸውን ይነጋገሩልህ ጀመር። እሱ ‘አሁን መኪና ምን ያስፈልገናል ለቤት አንቆጥብም ወይ?’ ሲላት እሷ፣ ‘ይኼ መኪና እየተከራየ የሚያመጣው ገቢ ለቁጠባ አይበቃንም ወይ? አንድም ንብረት ነው ሌላም ገቢ ይኖረዋል፤' ትለዋለች። እኔ ይህንን ስሰማና ሳይ አንድም ሰው ስለተሻለ ሥራና ኑሮ ማሰብ መቻሉ በራሱ ለዚህች በደም ስትጨማለቅ ለኖረች አገር ትልቅ ነገር መሆኑ ታየኝ። በአንፃሩ ደግሞ አሁንም የዕለት ጉርሱን አጥቶ መንገድ የወደቀው ዜጋ እየታሰበኝ የመደብ ልዩነት የማይኖርባት፣ ሕዝቦቿ እኩል ያሰኛቸውን ጠይቀውና አግኝተው ሠርተውና ፈጥረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ናፈቀችኝ፤›› ብሎ ሲያጫውተኝ፣ የእሱ ማስተዋል የብዙኅኑ እንዲሆን ተመኘሁ። ምኞት አይከለከልምና!
እንደ መብራቱ ሄድ መለስ የሚለው የደላላ ሥራ ሰሞኑን ደግሞ በአከራይና ተከራይ ደምቆ ነው የሰነበተው። የሚከራይ ቤት ስፈልግ የሚከራይ የኮንስትራክሽን መኪናና ማሽን ሳጣራ ነበር የሰነበትኩት። በአጠቃላይ ማን የማይከራይ ማን የማያከራይ አለ ብላችሁ ነው? ‹‹አንተ አገሩ በሙሉ ኪራይ ሰብሳቢ ሆነ ቢባል ታዲያ ምን ይገርማል? እንዲህ ውጣ ውረድ የሌለበት የሰነፍ ሥራ ለምዶ?›› ያለኝ የሚያካልበኝን ጉዳይ በአጫወትኩት ቁጥር የሚያዋየኝ የባሻዬ ልጅ ነው። እሱ ደግሞ ነገር ማጠጋጋት ይወዳል፡፡ ነገሩን ወዴት እንደወሰደው ተመልከቱ። ታዲያ ካነሳነው አይቃር አንድ ጨዋታ ላጫውታችሁ። (መቼም ለቤት እንጂ ለወሬ ቁጠባ የለውም) ባለፈው ከወዳጆቼ ጋር ለሰኔ ውርጭ እጅ ላለመስጠት ‹‹ዋን ዋን›› እያልን ተሰብስበን ስንጫወት፣ ‹‹ምነው ሙሰኛ ማደኑ የአንድ ሰሞን ዜና ሆኖ ቀረ?›› ብሎ ከመሀላችን አንዱ ይጠይቃል። ‹‹አብደሃል እንዴ? ለመኖርያ ቤት የምንቆጥበው አንሶ ደግሞ ለእስር ቤቶች እንድንቆጥብ አማረህ?›› ሲል ሌላው ይመልስለታል። ‹‹ኧረ ንገርልኝ! አላወቀም አገር ምድሩ ወጣት አዛውንቱ እልም ያለ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኑን። ማን ይተርፍና?›› ይላል ሌላው። ኋላ ይኼን ጨዋታ ያመጣው ወዳጃችን ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹‘ላይጋግሩ ምጣድ ማሟሸት’ ታዲያ ምን አስፈለገ?›› ሲል የተመካከርን ይመስል፣ ‹‹እሱን አብረን እንጠይቃለን አልነዋ፤›› አይገርማችሁም ግን?! አሁን የኢሕአዴግ ‘ወጤ ከጣፈጠ ጠላዬ ቢቀጥን’ አካሄድ ጠፍቶት ነው? ተናግሮ ሊያናግረን እንጂ!
በሉማ እንሰነባበት። የ40/60 የቁጠባ ቤቶች ሙሉ በሙሉ የከፈለ ቅድሚያ ይሰጠዋል አሠራር የባሻዬን ልጅ አበሳጭቶት ሲያገኘኝ የሚያወራኝ ስለዚሁ ሆኗል። ‹‹ቆጥቡ ብሎ መሸጥ? ቁጠባ ሌላ ግዥ ሌላ! እንዴት ያለ ነገር ነው?›› ይለኛል ባገኘኝ ቁጥር። ይኼን ጊዜ የዚህን የቤት ፕሮግራም መጨረሻ አይቼው እያልኩ በሆዴ ከተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ተቀምጠን ከግራ ከቀኝ የሚባለውን አዳምጣለሁ። ገሚሱ፣ ‹‹ሀብታምም ዜጋ ነው! ኢትዮጵያ ያላቸውም የሌላቸውም ናት። እኛን የሚያሳስበን እንዴት አድርገው አገኙት? የሚለው ብቻ ነው፤›› ሲል እሰማለሁ። ገሚሱ፣ ‹‹ደርሶ ሁሉን ነገር መቃወም። መንግሥትስ ከየት አምጥቶ ይሠራዋል? እንዲህ ያለውን አማራጭ የማይጠቀም ካልሆነ? ኤድያ! ደርሶ በረባ ባረባው እንደ አገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቃቂር ማውጣት ስንወድ፤›› ይላል። ‹‹ተው! ተው! የተቃዋሚዎችን ነገር አታንሳብን። እንዴ፣ አሁንማ'ኮ ከሕዝብ ፍላጎት፣ ሐሳብ፣ ከአገራዊ የልማት አጀንዳዎች ወጥተው አንደኛውን ‘ፖለቲካን በጨበጣ’ ተያያዙት እኮ!›› ሲል ከወዲያ ሌላው ይመልሳል። ሌላው ከወዲያ፣ ‹‹ኧረ ከተቃዋሚዎች ራስ ላይ ውረዱ፡፡ ኢሕአዴግ ዙሪያውን ዘጋግቶባቸው አላሠራ ያላቸው አንሶ የምን መሟዘዝ ነው?›› ሲል ሰማነው፡፡ ‹‹እንነጋገር ከተባለማ የጨበጣ ፖለቲካ ያለውማ እከሌ ከእከሌ ሳይባል ሁሉም ዘንድ ነው፤›› እያለ ከማዶ በኩል አንዱ ሲናገር ግሮሰሪያችን በሕዝብ ያልተወከሉ የፓርላማ አባላት የተሰባሰቡባት መሰለች፡፡ ሒሳብ ከፍለን ከባሻዬ ልጅ ጋር እስክንለያይ ድረስ ‘ፖለቲካን በጨበጣ!’ ያሉዋት አገላለጽ በልቤ ውስጥ ቀረች። መልካም ሰንበት! ደላላው ዘሪፖርተ
ር
ር
No comments:
Post a Comment