የመድረክ ከፍተኛ አመራር አባል ዶ/ር መረራ ጉዲና ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ
እርሳቸውና ድርጅታቸው ስልጣን ላይ ቢወጡ በቅድሚያ ለዜጎች የምግብ ዋስትና እንደሚሰጡ አስታወቁ። የፖለቲካ ሳይንስ
ምሁሩ ዶ/ር መረራ በአባይ ጉዳይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው “በእኔ እይታ ጉዳዩን ስመለከተው
ግብጾች ጦርነት ውስጥ ይገባሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሌሎች ብዙ አማራጮች አሏቸው፡፡ ግድቡ ተሰርቶ እንዳያልቅ ሊያደርጉ
የሚያስችሉ የተሻሉ መንገዶች አሏቸው፡፡” ብለዋል። ቃለ ምልልሱ ለግንዛቤዎ ይጠቅማል ብለን ስላሰብን እንደወረደ
አስተናግደነዋል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲም ሊሆን ይችላል እንደ ተራ
ኢትዮጵያዊ ወይንም ዜጋ ከግብጽ የምንማረው ነገር አለ፡፡ ግብጾች የቱንም
ያህል መንግሥታቸውን አምርረው ቢጠሉ በሀገር ጉዳይ ግን ምንጊዜም
አንድ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በዓባይ ላይ ያላቸው አቋም የተለየ ነው፡፡
ይሄንንም በቀጥታ ከተላለፈው የቴሌቪዥናቸው ስርጭት መረዳት
እንችላለን፡፡ ወዲህ ወደ እኛ ሀገር ስንመለስ ግን በአባይ ላይ እንኳን አንድ
መሆን አልቻልንም፡፡ በእዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር መረራ፡- እኔ ከምንም በላይ የምለው ኳሱ ያለው በኢህአዴግ ሜዳ
ላይ ነው፡፡ በኢጣሊያ ዘመን ያየነው ነገር ነው፡፡ በእዚያ ዘመን የኢጣሊያን
ባንዳ ሆነው ፔሮል ላይ ሳይቀር የሰፈሩና ያገለገሉ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ኃይለሥላሴ ሌላ ኢትዮጵያ ሌላ ብለው ከእሥር ቤት
ወጥተው የተዋጉ እንደ ባልቻ አባነፍሶ ያሉ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ከእዚህ
የምንማረው ምንድን ነው፣ መንግሥት ስትሆን ቀዳዳ እንዳይከፈት
ማድረግ አለብህ፡፡ በሀገር ፖለቲካ ላይ ብሔራዊ መግባባት ካልፈጠርክ ግብጾች ነገም ሆነ ከነገ ወዲያ የውጭን ኃይል ሊጠቀሙ
ይችላሉ፡፡
ላለፉት 150 ዓመታት ያለውን የኢትዮጵያን ታሪክ ስናየው ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከውጭ እጅ ነፃ የሆነ አይደለም፡፡ ከአጼ
ቴዎድሮስ ጀምሮ አሁን እስካለው የኢህአዴግ መንግሥት ድረስ ያለው እውነታ የሚያስረዳው ይሄንን ነው፡፡
መንግሥት በሀገር ጉዳይ ላይ ተቃዋሚዎችን በሙሉ ልብ እንዲሳተፉ ካላደረገ ከእኔ ጋር አልተሳተፉም ብሎ ጧትና ማታ መጮሁ
ዋጋ አይኖረውም፡፡ ተቃዋሚውም በማይሆን መንገድ በሀገር ጉዳይ ላይ መደራደር የለበትም፤ ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡
መንግሥትም ቢሆን ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ነገር መፈጸም የለበትም፡፡ ስለዚህ በሁለቱም ወገን ጉዳዩ
መታያት አለበት፡፡ ኢህአዴግ በሀገር ጉዳይ ላይ ከተቃዋሚዎች ጋር ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና ወደ ውጪ እንዳያዩ ማድረግ
ካልቻለ ዋናው ጥፋተኛ መንግሥት ነው የሚሆነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው ክርክር የሚያስኬድ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በእዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ መንግሥት በአባይ ዙሪያ ምን ማድረግ አለበት ነው የሚሉት?
ዶክተር መረራ፡- እኔ አሁን ኢህአዴግ በገባበት ደረጃ የተሻለውን የሚያውቀው እራሱ ኢህአዴግ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዲፕሎማሲው ይቀጥል ማለትዎ ነው?
ዶክተር መረራ፡- ይሄ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው ለዲፕሎማሲ ነው፡፡ በእኔ እይታ ጉዳዩን ስመለከተው
ግብጾች ጦርነት ውስጥ ይገባሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሌሎች ብዙ አማራጮች አሏቸው፡፡ ግድቡ ተሰርቶ እንዳያልቅ ሊያደርጉ
የሚያስችሉ የተሻሉ መንገዶች አሏቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ እንዴት ዓይነት?
ዶክተር መረራ፡- ቀዳዳዎችን በመጠቀም ሊሆን ይችላል፡፡ ሶማሊያ አለች፤ ለአልሸባብ የፈለጉትን ማቀበልም አለ፤ ጂቡቲንም
ማባበል ይኖራል፤ እኔ እዚህ ጨዋታ ውስጥ አትገባም ብዬ የማስበው ኬንያን ብቻ ነው፡፡ እርሷም ብትሆን አንዳንድ ጊዜ አይታ
እንዳላየች የምትሆነው ነገር አላት፡፡
ስለዚህ የዲፕሎማሲው መንገድ ካልሰራላት ግብፅ የምትከተለው መንገድ ይሄ ነው የሚሆነው፡፡ ግድቡ እዚያ አይደርስም እንጂ
ተሰርቶ ካለቀ ግን የግድቡን ደህንነት የምትጠብቀው እራሷ ግብፅ ነው የምትሆነው፡፡ ምክንያቱም ግድቡ አንድ ነገር ከሆነ ውሃው
ጠራርጎ ይዞ የሚሄደው ግብፅን እንጂ ኢትዮጵያን አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያም በዲፕሎ ማሲው መግፋት እንዳለ ሆኖ እስከዚያው
ራሷን ማደራጀት አለባት፡፡
ግብፅ ሠራዊቷን ልካ ኢትዮጵያን ትወራለች የሚል እምነት የለኝም፡፡ ከእዚያ ይልቅ መንግሥትን ሊያዳክሙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ
የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭንም ብቻ ሳይሆን የውስጡንም የቤት ሥራ መስራት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተራበ ግብፅ
የተሻለ እየተመገበች መቀጠል አይኖርብንም፡፡ በመሆኑም የራስህን ጥቅም አሳልፈህ በማይሰጥ መልኩ መደራደር ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለመጨረሻ ጊዜ ልጠይቅዎት፡፡ በእርስዎ ግምት የግድቡ ግንባታ ይሳካል ብለው ያምናሉ? እርስዎስ እንደ አንድ
ኢትዮጵያዊም ሆነ የመንግሥት ሠራተኛ ለግደቡ ቦንድ ገዝተዋል?
ዶክተር መረራ፡- ግድቡ ያልቃል የሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ምክንያቱም በዜሮ ባጀት እየተሠራ ያለ ፕሮጀከት ነውና፡፡
እስካሁን የተሰበሰበው ብርም ከ10 በመቶ በላይ ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለዚህ የሀገሪቷን ሀብትና ባጀት ሁሉ ወደ ፕሮጀከቱ ማዞር
ነው ያለው አማራጭ፡፡ ይሄ ደግሞ የራሱ ችግር አለው፡፡ ስለዚህ በቀላሉ ያልቃል ብዬ አላምንም፡፡ የውጭ ጣጣ ሲጨመርበት
ደግሞ ችግሩ በዚያው ልክ ይጨምራል፡፡ የቦንድ ግዥን በተመለከተ ወደድንም ጠላንም ዩኒቨርሲቲው የአንድ ወር ደመወዛችንን
በዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ ብሎ ወስዷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ተስማምተዋል?
ዶክተር መረራ፡- እኔ በእውነቱ አልተጠየኩም፤ በግድ ነው የተወሰደብኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሦስት አራት ሰው አነጋግሮ ሠራተኛው
ወስኗል ማለቱ አግባብ አይደለም፡፡ ይሄንንም በግልጽ በደብዳቤ ጋዜጣ ላይ የጻፉ አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ እርስዎ ልመለስና፣ እርስዎ ቢሮዎ ለግድቡ አስተዋፅኦ ያድርጉ የሚል ደብዳቤ ወይንም ቅጽ ቢመጣልዎት
ይፈርማሉ?
ዶክተር መረራ፡- እርሱን እንኳ ያን ጊዜ ምን እንደማደርግ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን በፈቃደኝነት ፈርሙ ቢባል ብዙ ሰው
አይፈርምም የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጥሩ መንግሥት ተከዜን በአራት ቢሊዮን ብር፣ ጣና በለስን በሰባት ቢሊዮን ብር በራሱ ወጪ ሰርቶ አሳይቷል፡፡
አሁንም ጊቤ ሦስተኛን በራሱ ወጪ እያሠራ ነው፡፡ እንደው እነዚህን ነገሮች ሲመለከቱ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሰርቶ
ይጨርሰዋል የሚል ጥርጣሬ አያጭርብዎትም?
ዶክተር መረራ፡- ሁለቱ ግድቦች የነበረባቸው ችግር የገንዘብ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ግድብ ግን ችግሩ የገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ የውጭ
አይኖች ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ እንዲሆን ያደረገ ፕሮጀክት ነው፡፡ የአረቡ ዓለምንም በኢትዮጵያ ላይ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ከውስጥም
ከውጭም በቂ ድጋፍ ሳይኖርህ ጠንከር ያለ የውጭ ዓለምም ተቃውሞ እየገጠመህ በቀላሉ የምታሳካው ፕሮጀክት አይደለም፡፡
ግድቡ እስኪያልቅ ድረስ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ሁሉ ልታጥፍ፣ ግሽበት ውስጥ ሁሉ ልትገባ ትችላለህ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስኪ ወደ ሌላ ሃሳብ ልውሰድዎት፡፡ ግብጾች በተደጋጋሚ የሚያነሷ ቸው የ1929 እና የ1959 ስምምነቶችን
ነው፡፡ አሁን ደግሞ የተፋሰሱ የላይኛው አገሮች የተፈራረሙት የኢንቴቤው ስምምነት አለ፡፡ እነዚህን ስምምነቶች እንዴት
ያዩዋቸዋል?
ዶክተር መረራ፡- ይሄ ምንም የሚያነጋግር ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ላልፈረመችበት ሕግ የምትገደድበት ምክንያት የለም፡፡ ያ
የቅኝ ግዛት ሕግ መቀየር አለበት፡፡ 86 በመቶ የሚያመነጭ አገር እንዴት አንድ ሊትር ውሃ እንኳን አይሰጠውም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንደ ግለሰብ ወይንም በፓርቲዎ ደረጃ መንግሥት ቢሆኑ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ፕሮጀክቶች ምን ምን
ይሆናሉ?
ዶክተር መረራ፡- እኔ ለምግብ ዋስትና ቅድሚያ እሰጣለሁ፡፡ በእዚህ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይሄስ ቀላል የሚሆን ይመስልዎታል፣ ግብጾችስ ዝም የሚሉ ይመስልዎታል?
ዶክተር መረራ፡- አልኩህ እኮ ግብጾች ሊቃወሙ ይችላሉ፡፡ ትንንሽ ፕሮጀክቶችን እየተጠቀምክ ግን አቅምህን ታዳብራለህ፡፡
በመጨረሻ ይጠቅማል ከተባለ ከ30 ወይንም ከ40 ዓመት በኋላ ወደ አባይ ልትሄድ ትችላለህ፡፡ ያን ጊዜ ግብጾችም ሊያግዙህ
ይችላሉ፡፡ ግብጾችም ብዙ ውሃ እንዲመነጭ የኢትዮጵያን ደን በማልማት በኩል እንዲገቡ አደርጋለሁ፡፡ እነርሱ ዛሬ የሚያስቡት
ኢትዮጵያን ማልማት ሳይሆን ውሃውን ወደ ሲና በረሃ አሻግረው ለእስራኤል መስጠትን ነው፡፡
ሌላው ኢህአዴግ ለሚለው የገጠር ልማትና ኢንዱስትሪ ቅድሚያ እሰጣለሁ፡፡ ኢህአዴግ እኮ ዝም ብሎ ይጮሃል እንጂ በገጠር
ልማት ላይ አልሠራም፡፡ ገና ብዙ ሥራዎች ገበሬው ላይ አልተሰሩም፡፡ አሁንም ድረስ ገበሬው የሚጠቀመው የ13ኛው ክፍለ
ዘመን አስተራረስን ነው፡፡ ይሄንን ካልቀየርክ ለውጥ አታመጣም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ዶክተር ምርታማነት ጨምሯል?
ዶክተር መረራ፡- ይሄንን እኮ ኢህአዴግ በባህርዳሩ ጉባኤው አምኗል፡፡ ካድሬው ለምቷል፡፡ ገበሬው ግን ገና ነው፡፡ በሚፈለገው
መጠን አልለማም፡፡ ስለዚህ ለመስኖ ትኩረት መስጠትና የግብርና አብዮት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የኢንዱስትሪ
ጥያቄ መምጣት ያለበት፡፡ የኢንዱስትሪ አብዮት ካላመጣህ ደግሞ ኢትዮጵያን የትም ማድረስ አትችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዶክተር ለሰጡኝ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ምናልባት የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ መጥቼ
አስተያየትዎን እወስድ ይሆናል…
ዶክተር መረራ፡- (ከረጅም ሳቅ በኋላ) ምንም ችግር የለውም፡፡ ለእዚያ ያብቃን፡፡ ያን ጊዜ መወቃቀስም መሞጋገስም ይቻላል፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment