ሰንበት ምሳ፤ ኢትዮጵያ መድሃኒያለም እና ኤርትራ ኪዳነምህረት በኬኒያ
ከአቤ ቶክቻው
ይህ ፅሁፍ ለአዲሳባዋ ፍትህ/አዲስ ታይምስ ተልኮ ነበር። እነሆ ለርሶም፤
ዛሬም ኬኒያ ነን። አንድ ጊዜ “ኬኒያን በደርበቡ” ካልኩዎት በኋላ ክፍል ሁለት ክፍል ሶስት እያልኩ ከማደክምዎ ይልቅ በተለያየ ርዕስ ብቅ ብል ይሻላል ብዬ ነው ይህንን ርዕስ የሰጠሁት፤ ሌላም ምክንያት አለኝ…
ደሞስ እስከመቼ በድርበቡ እንላታለን! አንዳንዴም የፈጀውን ይፍጅ ብለን ገባ ብለን እናያታለን አንጂ… ደሞ ለኬኒያ!
ጀመርን!
ባለፈው ጊዜ በዚች አዲስ ታይምስ ላይ የወጣች ጨዋታችንን በውጪ ሀገር ለሚገኙ ወዳጆችም ትድረስ ብዬ በኢንተርኔት አስተላልፊያት ነበር። ምነው እንኳ በኬኒያ ስለ “ኬዝ” ጋገራ የምታወራው… እ…! ታድያልዎ አንዳንድ ወዳጆቻችን በፅሁፏ ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል። የተቃውሞው መነሾ አንድም፤ “ይህንን ጨዋታ ፈረንጆቹ ቢያገኙት ወይም በስሚ ስሚ ቢሰሙት በየበረሃው በስደት የሚጉላላውን ኢትዮጵያዊ ላይ ጭራሽ ይጨክኑበታል።” የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ፤ “የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች… አሉ” … “ወንድ ከሆን… አንተ ራስህ ምን “ኬዝ” እንዳስጋገርክ አታወራም…? “አንተ ምንትስ አንተ ቅብርጥስ አንተ… ወዘተ…!” በሚል ልክ ልኬን (ልክ ልኬን አንኳ አይደለም አብዛኛዎቹ ጠበውኛልም አጥረውኛልም…!) ብቻ ግን ነግረውኛል!
የሆነው ሆኖ ግን እንደኔ እምነት አንድ “የሚፅፍ” ግለሰብ ያየውን የሰማውን ሳይደብቅ ቢያወራ ሃላፊነቱን በአግባቡ ተወጣ ነው የሚባለው። እኔም ያደረግሁት እርሱኑ ነው። “ህይወትን ከነቡግሯ መሳል” እንዲል፤ ጋሽ ስብሐት ለአብ! ዋናው እውነት መሆኑ ነው እንጂ! ምንም ነገር ቢሆን ከመፃፍ አያመልጥም ብዬ አስባለሁ።
ለነገሩ እኛ ያወጋነው ወግ ያን ያህል የሚስተዛዝብም የሚያበሳጭም አልነበረም። (ሰይጣን በመሀላችን ካልገባ በስተቀረ..!)
በኬኒያ ያለው ስደተኛ ሁለት አይነት እንደሆነ ይታወቃል። “ይታወቃል” ስል በእኔም ዘንድ በወዳጆቼም ዘንድ በኤምባሲዎች እና በግብረሰናይ ድርጅቶች ዘንድ በእግዜሩም ዘንድ! ማለቴ ነው።
አንድ ጋዜጠኛ ወዳጅ አለኝ በሀገሪቱ ውስጥ ከነበሩ ዋና ጋዜጦች መካከል በአንዱ ከፍተኛ አዘጋጅ ሆኖ ይሰራ ነበር። እንደ በርካቶቹ ጋዜጠኞች “ከምገባ ብወጣ ይሻለል” ብሎ ያመለጠ ነው። ይህ ወዳጄ በዛም ሰዓት፤ በስደት ሀገሩ የአቅሙን ያህል ሀሳቡን በመግለፅ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኝ ነበር።
ታድያ ያኔ በነበረባት ኬኒያ አንድ ሰው ይተዋወቃል። ከዛም በወሬ በወሬ ከየት ነህ እንዴት ነህ..? መባባል ሲጀምሩ ገደኛዬ ያጋጠመው ሰው ከአዲሳባ ከተማ በሞያሌ አድርጎ ወደኬኒያ መምጣቱን ይነግረዋል። ጓደኛዬም በሁኔታው አዝኖ፤ “በረሃው መቼም ከባድ ነው… ለመሆኑ ምን ሆነህ ተሰደድክ?” ብሎ ቢጠይቀው ጊዜ፤ “ጋዜጠኛ ነበርኩ አላሰራ አሉኝ ወጣሁ!” አለው። ይሄን ጊዜ ወዳጄ የሙያ አጋር በማግኘቱ እየተደሰተ፤ “አይዞህ” ብሎ ካፅናናው በኋላ “የት ጋዜጣ ላይ ነበር የምትሰራው?” ሲል ድንገት ጠየቀው። ይሄኔ ሰውዬው ሆዬ በአዲሳባ ዋና ከሚባሉ ጋዜጦች መካከል አንዱን ጠራለት። ጓደኛችን ደነገጠ። ይሄ ጋዜጣ እርሱ በከፍተኛ አዘጋጅነት ሲሰራበት የነበረ ጋዜጣ ነው። ይህንን ሰው ቀርቶ እርሱን የሚመስል ሰው እዛ ቤት ስሰራ አይቶ አያውቅም… ግራ ተጋባ…!
ቢገርምዎትም ይግረምዎ ወዳጄ ይህ ጋዜጠኛ ያልሆነ “ጋዜጠኛ” “ለደህንነቱ አመቺ ቦታ” ተብሎ ከኬኒያ ወደ ሌላ ሀገር ሲዛወር ይሄ ትክክለኛው የጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ ግን ከአሁን አሁን ምን ይፈጠር ይሆን ብሎ በስጋት ኬኒያ ይኖር ነበር።
በነገራችን ላይ በኬኒያ በርካታ መንግስት አይናችሁ ላፈር ያላቸው ወዳጆቻችን አሁንም ጭምር የስጋት ኑሮ እየኖሩ ነው። በተለይም በአካባቢያቸው አዲስ አበሻ ባዩ ቁጥር አፍኖ ሊወስደኝ ይሆን እያሉ የሚደነግጡ በርካታ ወዳጆች አሉኝ። ይህንን ድንጋጤ ከሚጋሩት መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ…!
ቆይ እንደውም እዚህ ጋ ካልተወራች በስተቀር ሌላ ቦታ የሚገኝላት ያልመሰለችኝን አንድ ገጠመኝ ልንገርዎትማ…
አንድ ጊዜ ሰፈሬ ከምትገኝ በኤርትራዊው ሳሚ “ማናጀርነት” በኢትዮጵያዊቷ አሚዳ አብሳይነት እና በኬኒያዊቷ ካትሪን ረዳትነት የአካባቢውን ሀበሻ በሙሉ ቀጥ አድርጋ የምትመግብ ደሳሳ ምግብ ቤት ገብቼ መረቅ ያለው ቀይ ጥብስ አዝዤ እየበላሁ ነበር… (አታስጎምጀኝ… አሉኝ እንዴ…? አረ ራሴም ምግቡ በአይኔ ላይ እየሄደ ነው።) እናልዎ… ሁለት ከዚህ በፊት አይቻቸው የማላውቅ ጎረምሶች! ምግብ ቤት ውስጥ የሞቀ ክርክራቸውን ሳያቋርጡ ገቡ እና ቡና አዘዙ።
በሀሳቤ እነዚህ ደግሞ ከየት ይሆኑ…!? ብዬ መጨነቅ ጀመርኩኝ… እውነቱን ለመናገር፤ ኬኒያ ላይ ያለ የኢትዮጵያን መንግስትን ፈርቶ የወጣ ስደተኛ አርፎ ቤቱ ቢተኛ ይሻለዋለዋል። ምክንያቱም ማን… መቼ መጥቶ ምን እንደሚያደርገው አይታወቅም። አንዳንድ ግዜ ትላንት ያየነው ሰውዬ ከነገ ወዲያ “ተገደለ” ሲባል ልንሰማ አንችላለን። ወይ ደግሞ “ታፍኖ ተወሰደ” ሲባል ይሰማል። ስለዚህም ሁልግዜም ይህን ሰውዬ እኔ ላለመሆን በትጋት መፀለይ እና በትጋት መደባበቅ ያስፈልጋል።
በርዕሴ ላይ ያሉትን ቤተ ክርስቲያኖችንም ያየኋቸው ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ስል ነበር። ቆይማ ወደሱ እንመለሳለን፤
ሰንበት ምሳ፤ ኢትዮጵያ መድሃኒያለም እና ኤርትራ ኪዳነምህረት በኬኒያ
እናልዎ በምግብ ቤቱ ውስጥ ልጆቹ ሲገቡ ብመለከት ጊዜ አዲስነታቸውን አይቼ፤ እነዚህማ የሆነ ተልኮ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ብዬ በሆዴ ማንሰላሰል ጀመርኩ። ልክ ይሄን ጊዜ የእኔን ስም እያነሱ አንዳች ክርክር ጀመሩ። ለካስ እስካሁንም የሚጨቃጨቁት በኔው የነተሳ ነበር። “የሆነውን ፅሁፍ አንስተው ሀገር ቤት እያለ ነው ውጪ ከወጣ በኋላ ነው የፃፈው” እያሉ ይከራከራሉ። የምበላው ምግብ ከጉሮሮዬ እንዴት ይውረድ። በጣም ደንጋጣ መሆኔን ካረጋገጥኩባቸው ጊዜያቶች አምስተኛው ይሁን አስረኛው ይሄው ነው። (በቅንፍም ደንጋጣ መሆኔን ብዙ ግዜ አረጋግጫለሁ ማለቴ ነው)
ታድያልዎ በቃ አለቀልኝ ብዬ አንገቴን አቀርቅሬ ሮጬ ላምልጥ? ወይስ እግራቸው ላይ ወድቄ የምታወሩት ሰውዬ እኔ ነኝ አፈር ስሆን በልጆቻችሁ በምትወዱት ይሁንባችሁ ምንም አታድርጉኝ…! ብዬ ልለምናቸው እያልኩ እያንሰላሰልኩ ሳለ፤ ያዘዟትን ቡና ከምኔው ፉት እንዳሏት እንጃ እኔን እስከመኖሬም ሳያዩኝ ወጡ። ከሁሉ ያሳቀኝ አጠገባቸው ያለሁትን ሰውዬ “አሁን አሜሪካ ስለሆነ እንደልቡ ይፃፍ እንጂ…” እያሉ አድናቆት አይሉት ቁጭት ሲናገሩ መስማቴ ነው።
እንግዲህ ባለፈው ጊዜ እንደነገርኩዎ በስደት ላይ ያለ ሰው ሁለት አይነት ነው። አንደኛው በትክክል የሆነውን ሆኖ ከሀገሩ የወጣ እና ሌላው ደግሞ ያልሆነውን ሆኛለሁ ብሎ ከሀገሩ የወጣ። ሁለቱም ግን ምስኪን ስደተኞች ናቸው። ልዩነታቸው ይሄ በተለይ የፖለቲካ “ድቁሳት” ደርሶበት ከሀገሩ የወጣው ስደተኛ በየመንገዱ ሲሄድ ገልመጥ ገልመጥ እያለ እያንዳንዷን እርምጃ የሚሄደው በጥርጣሬ ሲሆን፤ የኢኮኖሚ “ድቁሳት” ደርሶበት የተሰደደው ደግሞ ከኬኒያ ፖሊስ በስተቀረ ሌላው ሳያሳስበው በሰላም የሚውልበት ውሎ ወደቤቱ ይገባል።
ወደ ርዕሳችን ስንመጣበት፤ ኬኒያ ሁለት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኖች አሉ። አንደኛው ላይ በአማርኛ፤ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንመ የመድሃኒያለም ቤተ ክርስቲያን” ተብሎ የተፃፈ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ በትግርኛ ቋንቋ፤ “በኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን” ተብሎበታል።
በኢትዮጵያው መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን ውስጥ በርካታ የኤንባሲው ሰዎች በየጊዜው ጎራ ይላሉ። ጎራ ብለውም ፀሎትም ስለላም አድርገው ይመለሳሉ። ስለላው ማን መጣ? ለምን መጣ? ከየት መጣ? እንዴት መጣ…? የሚል ሲሆን ፀሎቱ ግን ስለምን አንደሆን እንጃ!
ስለዚህ እንደኔ ላለው ፈሬ ተሳላሚ በተለይ ሰው በሚበዛበት ዕለተ ሰንበት እና በዓላት ቀን የኢትዮጵያውን መድሃኒያለም በሩቁ “ሃይ” ብሎ ዝርዝሩን ሄዶ ለኤርትራዋ ኪዳነምህረት መንገር ጥሩ አማራጭ ነው።
ባለፈው ጊዜ ጀመር አድርጌ ተውኩት አንጂ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዊያን እዚህ ኬኒያ ውስጥ ስንንኖር ክላሽና ካርታው ማለት ነን አንዳችን ያለ አንደኛችን የማይሆንልን የማንለያይ ወዳጃማቾች።
የኢትዮጵያው መድሃኒያለም አና የኤርትራዋ ኪዳነምህረትም ብዙም አይረራቁም። ቅርብ ለቅርብ ናቸው። ብዙ ጊዜ በተለይ እኛ ሰፈር የሚኖሩ ኤርትራዊያን እና ኢትዮጵያውያን ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ቤተ መሸታ አብረው ነው የሚታደሙት።
ታድያ መድሃኒያለምን ብቻ ወይም ኪዳነ ምህረትን ብቻ ተሳልመው አይመለሱም። ኢትዮጵያ መድሃኒያለም የጀመሩትን ፀሎት ብዙ ጊዜ፤ ኤርትራ ኪዳነ ምህረት ሄደው ነው የሚጨርሱት።
ዛሬ ይህንን ርዕስ የተጠቀምኩበት ዋና ምክንያት፤ ሰሞኑን ጠቅላይሚንስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከኤርትራ ጋር ያስታራቂ ያለ እያሉ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም አንዲሁ ከሁለት ጎራ ተከፍሎ የነበረ አካሏን ለማጋጠም ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
ስለዚህ ሁለቱንም ቢሆን እኛን ነው ማየት ብዬ ፍቅር እንቁልልጭ ልላቸው እፈልጋለሁ!
ወዳጄ ለዛሬው እዚህ ላይ ላቁም!
በመጨረሻም
አማን ያሰንብተን!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment