Pages

Dec 20, 2012

የኢትዮ-ኤርትራን ችግር ለመፍታት የሚረዱ ነጥቦች





ጠቅላይሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ፣ አስመራ ሄደዉ ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ እንደሆኑ ለአልጃዚራ ገልጸዋል።«በአልጀርሱ

ስምምነት ተቋቁሞ የነበረው የድንበር ኮሚሽን የወሰነዉን ዉሳኔ፣ ኢትዮጵያ አክብራ፣ የባድመን ከተማ ጨምሮ
የኤርትራ ናቸው ከተባሉት መሬቶች ሁሉ ለቃ እስካልወጣች ድረስ፣ አልነጋገርም» ሲል የነበረዉ የኤርትራ መንግስት፣
ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም አስተያየት የሰጠው ኦፌሳላዊ ምላሽ ባይኖርም፣ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ ከዚህ በፊት
የነበራቸውን አቋም በማለዘብ ከኢትዮጵያ ጋር ያለዉን ችግር ለመፍታት ፍቃደኛ እንደሆኑም የሚያሳዩ ዘገባዎችን
እያነበብን ነዉ።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝቦች አብረዉ የኖሩ፣ የተዋለዱ፣ በባህል በቋንቋ በሃይማኖት የተዛመዱ ወንድማማች
ሕዝቦች ናቸው። ስር የሰደደ የታሪክ ዝምድና ያላቸው፣ አንድ ወቅትም የአንድ አገር ሕዝብ የነበሩ እንደመሆናቸው፣
በመካከላቸው ያላቸዉን ችግሮች እስከአሁን መፍታት አለመቻላቸው የሚያሳዝን ነዉ። በእዉኑ ያሉን ልዩነቶች ይሄን
ያህል የከረሩ ናቸዉን ? አንዱ አሸናፊ ሌላዉ ተሸናፊ ሳይሆን፣ ሁሉም አሸናፊ የሚሆነበትን መፍትሄ ማግኘት
ያቅተናልን ? እስከመቼስ ኤርትራንና ኢትዮጵያን የሚያካልለዉ ድንበር፣ የልማትና የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚታዩበት
አካባቢ መሆኑ ቀርቶ፣ የፈንጂና የታንክ መናኸሪያ ይሆናል ?
ወደ ኋላ መለስ ብለን ነገሮችን መመዝን ከጀመርን ብዙ ልንባባል እንችላለን። በሁሉም ወገኖች ከዚህ በፊት
የተፈጸሙ ብዙ ስህተቶች አሉ። በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን ከሁለቱም ወገኖቻችን ረግፈዋል። ያ አካባቢ
በደም ርሷል። አሁን ግን ያለፈዉን ትተን ወደፊት ማየት ይኖርብናል። ያለፈውን እያነሳን የምንወጋገዝበትና
የምንካሰስበት ጊዜ አይመስለኝም። ሌሎች አገሮች የትናየት ደርሰዋል። ለልጆቻችን እና ልጅ ልጆቻችን ስንል ፣
ተከባብረን፣ ተስማምተን ፣ ይቅር ተባብለንና ተቻችለን ሁላችንም በጋራ የምናድገበትን ሁኔታ መፍጠር የግድ ነዉ።
ለዚህም ነዉ፣ የጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማሪያም ለዉይይት ዝግጁነትና ፣ አቶ ኢሳያስ ይዘዋል ተብሎ የተዘገበዉን
የአቋም መለሳለስ፣ በሰላም ወዳድ ወገን ሁሉ በአዎንታዊነት ሊታይና ሊበረታታ የሚገባ ነዉ የምለዉ።

በኤርትራና እና በኢትዮጵያ መካከል ያለዉን ችግር ስናይ የምናነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች ይኖራሉ። «ባድመ ለማን
ልትሰጥ ነዉ ? የአሰብስ ጉዳይ ? ከኤርትራ ጋር ነጻ ንግድ ከተጀመረ የብርና የናቅፋ ልዉዉጥ እንዴት ይሆናል ?
ከኤርትራ ተገንጥለው ከኢትዮጵያ መቀላቀል የሚፈልጉት የቀይ ባህር አፋሮችስ ጉዳይ ? …» የመሳሰሉ ጥያቄዎችን
እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
አንድ ነገር ከወዲሁ በግልጽ ላስቀምጥ። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለዉን ችግር የአልጀርሱ ስምምነት፣ ይኸው
ለአሥር አመታት አልፈታዉም። በመሆኑም በዚህ ስምምነት ብዙ ተስፋ ማድረግ ያለብን አይመስለኝም። እንደዉም
ይሄን ስምምነት እንደሌለ እንቁጠረዉ።
ከአልጀርሱ ስምምምነት የተለየ ፣ ችግሮችን ለመፍታት የሚችሉ ሃሳቦች ይኖራሉ። በዚህ ረገድ እኔም ይጠቅማሉ
የምላቸውን አንዳንድ የተጨበጡ የእርቅ ሃሳቦችን በትህትና ለማቅረብ እሞክራለሁ። እነዚህን ሃሳቦች ሳቀርብ
ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ለኢትዮጵያ ብቻ አስቤ ሳይሆን፣ አስመራ የተማርኩ፣ ለኤርትራ ሕዝብ ፍቅር ያለኝ ፣ በመንፈስም
“ኤርትራዊ ነኝ» ብዬ የማምን እንደመሆኔ ፣ ለኤርትራም አስቤ ነዉ።
ከሁሉም በላይ በዋናነት የምደግፈዉና የምመኘው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ነዉ። የአፍሪካ
ሕብረት ለማቋቋም እየተሞከረ አይደለም እንዴ ? በአዉሮፓ አንድ ለመሆነ እየሞከሩ አይደለም እንዴ ? በመከባበርና
በፍቅር ላይ የተመሰረተ አንድነት ቢኖር የበለጠ ያሳድገናል እንጂ አይጎዳንም። የባድመ፣ የአሰብ ፣ እንዲሁም
በመካከላችን ያሉ ሌሎች ችግሮች በሙሉ በአንድ ላይ ተጠቃለው መፍትሄ ያገኙ ነበር። ባድመ የኢትዮጵያም
የኤርትራም ትሆናለች። አሰብም የኢትዮጵያም የኤርትራ ትሆናለች።
የዉህደቱ ጥያቄ በሬፌረንደም እንዲወሰን ማድረግ ይቻላል። ከዚህ በፊት ኤርትራዉያን ብቻ ነበሩ ድምጽ የሰጡት።
አሁን ግን የኤርትራን መቀላቀል ሊቃወሙ የሚችሉ ብዙ ኢትዮጵያዉያን ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም
ዉህደቱን ማጽደቅ ይኖረበታል። እርግጠኛ ነኝ አብሮ የመስራትን ጥቅም እና የታሪክ ትስስራችን በጥልቀት
መመልከት እንዲችሉ ከተደረገ፣ ያለፈዉን የመተዉን ይቅር የመባባል መንፈስ ከሰፈነ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም
ሆነ የኤርትራ ወገናችን ዳግም ለመተቃቀፍ አይኑን ያሻል ብዬ አላስብም። ይሄ ያልተወሳሰበ የሰላምና የእርቅ
መንገድን፣ እቅድ «ሀ» ብዬዋለሁ። ፈረንጆች እንደሚሉት ፕላን ኤ (PLAN A)!
ተስፋ ካደረግነዉና ከገመትነዉ ዉጭ፣ ወይ የኤርትራ ሕዝብ፣ አሊያም የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ወይም ሁለቱም ፈቃደኛ
ሳይሆኑ ቀርቶ፣ ዉህደቱን መፈጸም ካልተቻለ፣ ኤርትራ እንደ አገር እየቀጠለች ፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ በበለጠ ሁኔታ
መልካም ጎሮቤት አገር ሆና እንድትኖር ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህም ሰጥቶ
በመቀበል መርህ፣ የሁሉንም ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ያሉትን ጥያቄዎች መመለስ ይኖርባቸዋል። ይሄ ደግሞ
እቅድ «ለ» ወይንም ፕላን ቢ ( PLAN B) ነዉ።
በአሁኑ ጊዜ አሰብና የደንከል በረሃ፣ ለኤርትራ ይሄን ያህል ጥቅም የሚሰጥ መሬት ነዉ ብዬ አላስብም። ኢትዮጵያ
አሰብን መጠቀም ካቆመችበት ጊዜ ጀመሮ ወደቡ ስራ ላይ ዋለ ማለት ያስቸግራል። መቼም ባጽእ (ምጽዋ) እያለች
ለአስመራና አብዛኛዉ የኤርትራ ግዛት እቃ በአሰብ በኩል ይገባል ማለት ትንሽ ይከብዳል። አሰብን ለኢትዮጵያ
አከራይታ ገንዘብ ካላገኘችበት በስተቀር አሰብ ለኤርትራ አትጠቅማትም።
በቅርበትም ሆነ በጂዮግራፊ አቀማመጥ ካየን ግን፣ አሰብ ለኢትዮጵያ በጣም ትጠቅማለች። ኢትዮጵያ ለጅቢቱ
መንግስት ብቻ በአመት ከ700 ሚሊዮን ብር ታወጣለች። የኢኮኖሚ እድገት የበለጠ ባደገ ቁጥር ለወደብ
የሚከፈለውም ዋጋ እየጨመረ ነዉ የሚሄደው። በኢትዮጵያ ወደብ መኖሩ ትልቅ ብሄራዊና አገብጋቢ ጥያቄ ነዉ።
ለኤርትራ ከሁሉም በላይ የሚጠቅመዉና የሚበጀው፣ አሰብን ይዞ ከመቀመጥ፣ ዘለቄታ ያለዉ ሰላም ከኢትዮጵያ ጋር
መመስረት ነዉ። ብዙም የማይጠቅማትን መሬት ለኢትዮጵያ ሰጥታ፣ ሌሎች የሚጠቅሟትን ነገሮች መቀበል
የምትችልበት ሁኔታ ማመቻቸት የበለጠ ሊረዳት ይችላል። አስተዋይነትም ነዉ። ኢትዮጵያም በበኩሏ አሰብን
ስትቀበል ፣ ለኤርትራን የምትሰጠው ሊኖራት ይገባል።
«ኢትዮጵያ የባህር በር ሊኖራት ይገባል» የሚሉ ኃይላት በብዛት እንደመኖራቸው፣ ይሄም ጥያቄ ደግሞ ትልቅ አገርዊ
ጥያቄ እንደመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ባህር አልባ ሆና አስተማማኝ ሰላም ከኤርትራ ጋር ማድረጉ አስቸጋሪ ነዉ የሚሆነዉ።
ኤርትራ ሁል ጊዜ እንደ ፈራችና ለጦርነት እንደተዘጋጀች ነዉ የምትኖረዉ።
እንግዲህ አሰብን ለኢትዮጵያ መስጠቱ በርግጠኝነት፣ በኤርትራ ሰላምን ለዘለቄታዉ ያረጋግጣል። ኤርትራዉያን
ከጦርነት ስጋት ተላቀዉ፣ በሰላም ይኖራሉ። ሰላም ከማግኘት የበለጠ ደግሞ በረከት የትም አይገኝም። አንድ በሉ።
በአሰብ አካባቢ የሚኖሩ አፋሮች ከአስመራ ይልቅ ልባቸዉና ታማኝነታቸው ለአሳይታና አዲስ አበባ ነዉ። በመሆኑም

ኤርትራ ከኢትዮጵያ የመለየት መብቷ እንደተረጋገጠው፣ አፋሮችም ከኤርትራ የመለየት መብታቸዉ እንዲረጋገጥ
ይጠይቃሉ። ያም መሰረታዊ መብታቸው ካልተከበረ ብረት የማያነሱበት ምክንያት የለም። እነርሱን ለመከላከልና
በአካባቢዉ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን አስመራ ብዙ ዉጭ ማዉጣት ትገደዳለች። ይህ ደግሞ አነሰም በዛም
ኤርትራን የሚጎዳ ነዉ። ሁለት በሉ።
ኤርትራዉያን በታታሪነታቸዉና በጠንካራነታቸዉ ይታወቃሉ። ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ጊዜ በመሃል
አገር ብዙ የተሳካላቸው፣ ትልቅ ደረጃ የደረሱ ወገኖች ናቸዉ። በልጅነቴ ትዝ ይለኛል አንድ በጣም የምንወደው
ብስኩት ነበር። የደቀ መሃሪ ብስኩት ! ደቀ መሃሪ ተመርቶ በመላው ኢትዮጵያ ይሸጥ የነበረ ። ነጻ ንግድ፣ ኢትዮጵያ
ዉስጥ ያለገደብ መስራት …. የመሳሰሉ ሁኔታዎች ቢፈጠሩ ነዉ የበለጠ ኤርትራ በኢኮኖሚ የምትጠቀመዉ። አስመራ
የሚመረቱ ምርቶች በቀላሉ ገዢ ያገኛሉ። ለኤርትራ ባለ ሃብቶች 90 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ደንበኛ ይሆናቸዋል።
የኤሌትሪክ ኃይል በቀላል ዋጋ ወደ አስመራ እንዲገባ ማድረግ ይቻላል። ሶስት በሉ።
በርግጥ በረጋ መንፈስ፣ ከሁሉም አቅጣጫ ሁኔታዉን ቢያስቡት፣ ኤርትራዉያን ከማንም በላይ የሚበጃቸው
ከኢትዮጵያ ጋር መተሳሰር ነዉ።
እንግዲህ ያለፈዉን ሳይሆን የወደፊቱን በማየት፣ የሚከተሉትን ተጨባጭ 7 የእርቅ ነጥቦች (Road Map of
Ethio-Eritrean Peace) አቀርባለሁ፡
1. ከጅቡቲ ድንበር እስከ መርሳ/ፋጥማ ያለዉ፣ አሰብን የሚጨምረዉ፣ የኤርትራ ግዛት ለኢትዮጵያ ይሰጥ።
2. በልዋጩ የባድመ ከተማን ጨምሮ ያወዛግቡ የሰሜን ኢትዮጵያ መሬቶችን ወደ ኤርትራ ይጠቃለሉ።
3. የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ተሻሽሎ፣ ኤርትራዉያን በኤርትራዊ ዜግነታቸው ላይ ደርበዉ፣ ሙሉ
የኢትዮጵያዊነት ዜግነት ይሰጣቸው። ይሄም በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለ አንዳንች ገደብ እንዲነግዱ፣ እንዲማሩ፣
እንዲሰሩ፣ እንዲኖሩ ያደርጋል። ኢትዮጵያዉያንም እንደዚሁ በአስመራ የመኖር መብታቸው ይረጋገጥ።
4. ኤርትራ የኢትዮጵያን ብር እንድትጠቀም ይደረግ። አሊያም የገንዝብ ልዉዉጥን በተመለከተ የጋራ ፖሊሲ
በመንደፍ ሊነሱ የሚችሉ ችግሮች ከወዲሁ ምላሽ ይሰጣቸዉ።
5. አንዱ አገር ሲጠቃ ሌላዉ እንደተጠቃ የሚቆጥር የዉትድርና ስምምነት ይደረግ።
6. በሚደረጉ ስምምነቶች፣ አስመራና አዲስ አባባ ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት በተቻለ አቅም
የተቃዋሚዎቻቸዉን ድጋፍ ለማግኘት ይሞክሩ። ይህ የሰላም መንገድ፣ የሁሉም ማህበረሰብ፣ የፖለቲካ
ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማህበራትን ያሳተፈ ሊሆን ይገባዋል እንጂ አንድ ፓርቲ ብቻ የሚወስነው ሊሆን አይገባም።
7. ፕላን ሃ ካልሰራና ዉህደት ማድረግ አሁን ካልተቻለ፣ ከጥቂት አመታት በኋላ አይቻልም ማለት አይደልም።
ቁስሎች ሲድኑ፣ በሁለቱም ወገኖች የሚኖረዉ መቀራረብ በጨመረ ቁጥር፣ የዉህደት ጥያቄዉ የበለጠ
ተቀባይነት ወደፊት ሊያገኝ ይችላል። በመሆኑ የዉህደቱ ጉዳይ ከአሥር አመታት በኋላ እንደገና እንዲታይ
ይደረግ።
ዉድ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዉያን ወገኖቼ፡
ሰላም ይበጀናል። መረዳዳቱና መደጋገፉ ይሻለናል። ይህ አይነቱን ስምምነት ማድረግ ካልቻልን አማራጩ የከፋ ነዉ
የሚሆንብን። ጦርነት ባልታሰበ ሰዓትና ጊዜ ይቀሰቀሳል። ዛሬ ያሉ መንግስታት ቢስማሙም፣ ነገ የሚመጡ
መንግስታት መካከል ጠብ ሊፈጠር ይችላል። ካለፈው መማር አለብን። ከባድመ ጦርነት በፊት በነበሩት 8 አመታት
አስመራና አዲስ አበባ መልካም ግንኙነት ነበራቸው። ሳይታሰብ ነዉ ድንገት ወዳጅ የነበሩ መንግስታት፣ ጦር
የተማዘዙት። አስተማማኝ ሰላም የሚገኘዉ ፣ ያልተሸፋፈነ፣ በቅንነት ላይ የተመሰረተ፣ መሰረታዊ ጥያቄዎችን
የሚመለስ ስምምነት ሲደረግ እና ሁሉም ሰጥቶ በመቀበል መርህ አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ብቻ ነዉ። እንግዲህ በሁሉቱም
ወገን ላሉ መሪዎች እግዚአብሄር ልቦና ይስጣቸው እላለሁ።

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate