Pages

Dec 30, 2012

ሰንበት ምሳ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች ደቡብ አፍሪካ ምን አላቸው!?


ዛሬም “ለአዲስ ታይምስ” (ፍትህ) አዲሳባ ተልካ የነበረችቱን ወግ ለሰንበት ምሳ እዚህ ተለጥፋለች፤ ይቋደሱልኝ እውነት ግን የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች ደቡብ አፍሪካ ምን አላቸው!?
ሰላም ወዳጄ እንዴት ሰነበቱ…
የመንገድ ቁፋሮው ነገር እንዴት አድርጎታል? በአሁኑ ሰዓት አዲሳባ ውስጥ ትራንስፖርት ከማግኘት “ፖርት” ማግኘት ይቀላል ሲሉ የሚያሽሟጥጡ ሰዎች መበራከታቸውን እየሰማን ነው።
ኧረ “ፖርት” ብል ጊዜ ምን ትዝ አለኝ፤ ኢትዮጵያ ለጅቡቲ አዲስ ወደብ ግንባታ እያደረገችላት መሆኑን ሰምተን ደስታችን ጨምሯል። እሰይ እንዲህ ነው እንጂ ልግስና! በዚሁ አይነት ፤ ሌሎቹ ጎረቤቶቻችንም እንዳይቀየሙ ብንገነባላቸው ምን አለበት…? ለነ ሱዳን ፤ለነ ሱማሌ ኤርትራዬ እና ኬኒያስ ቢሆኑ ካለኛ ማን አላቸው…? እና ይታሰብበት… “ያስቀኛል ገንፎ ከራቴ ላይ ተርፎ” አሉ አበው!
እና ታድያ የትራንስፖርቱ ነገር እንዴት አደርጎታል? እንደውም እንደሰማሁት ከሆነማ “ፒያሳ መሀሙድጋ ጠብቂኝ” ከሚለው የታላቁ ወዳጃችን መሃመድ ሰልማን መፅሐፍ በኋላ “ቦሌ ፒኮክ ጋ ጠብቂኝ” “መርካቶ ምዕራብ ሆቴል ጋ ጠብቂኝ” የሚሉ ተደጋጋሚ የቀጠሮ ፅሁፎች ሲወጡ የነበረውን ያህል… አሁን በቅርቡ ከወዳጆቻችን እንደ አንዱ የሆነው በሀይሉ ገብረ እግዚአብሔር “የትም አትጠብቂኝ” ብሎ መፃፉን ሰምተናል።
ወዳጃችን ይህንን ሲፅፍ እንደሌሎቹ መቀጣጠሪያ ቦታ አጥቶ ሳይሆን፤ ብቀጥራት በምን ትራንስፖርት ትመጣለች? ብሎ ይመስለኛል። እርግጥ ይሄ የኔ ግምት ነው እንጂ፤ ሙሉ ፅሁፉን ገና አላነበብኩትም። (የት አግኝቼው…)
የምር ግን የትራንስፖርቱ ነገር “የትም አትጠብቂኝ” የሚያስብል መሆኑን ብዙ ወዳጆቼ እያማረሩ ነግረውኛል። እኔ የምለው ግን መንገድ ገንቢው አካል ገንቢ አስተያየቶችን ለምን አይቀበልም? መንገዶቹን እስኪሰሩ ድረስ ወይ አማራጭ መንገድ መስራት ወይ ደግሞ የስራ ማቆም አድማ መጥራት አለበትኮ! አለበለዛ ሰዉ ከአለቃውና ከቀጠራት ጋር እየተጣላ ከተማዋ የድብድብ “ሪንግ” እንዳትሆን ያሰጋል…!
ለማንኛውም ወዳጄ ዛሬም ኬኒያ እንሄዳለን… ሻንጣዎትን መያዝ አይጠበቅብዎም እንደው ደረስ ብለን መለስ ነው የምንለው።
በነገራችን ላይ ከአዲሳባ ኬኒያ አንድ ሰዓት ከሃምሳ ደቂቃ የበረራ ሰዓት ብቻ ነው የሚወስደው። በአሁኑ ሰዓት ከሽሮሜዳ ቦሌ ለመድረስ እንኳ ስንት ሰዓት ይፈጃል? አሁን አሁንማ ምን ሰዓት “ሰው ነው የሚፈጀው እንጂ!” ብለው በጣም አያማሩ…
እንደምንም ብለው ቦሌ ይድረሱ። ከዛም አንድ ሰአት ከሃምሳ ደቂቃ በሰማይ ላይ ተንሳፈው፤ ናይሮቢ ኬኒያ እንኳን ደህና መጡ ብላ ትቀበልዎታለች።
በኬኒያ በተናጠል ከሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በአንድ ጊዜ አርባ ሰላሳ እየሆኑ እየተቧደኑ የሚሰደዱ የደበብ ኢትዮጵያ ልጆችን ማየት በጣም የተለመደ ነገር ነው። እነዚህ “ደቡቤዎች” ኬኒያ የሚመጡት ካናዳ፣ አሜሪካ፣ እና አውሮፓን ናፍቀው አይደለም። ወይ ደግሞ ፖለቲካን ነክተው መንግስት “ንኩት” (ውጡልኝ ከዚህ ቤት) ብሏቸውም አይደለም።
በቃ ከሆነ ጊዜ በኋላ በደቡብ ኢትዮጵያ የመጣ አንድ ፋሽን አለ። አንድ ሰው ጎርመስ ካለ፤ “ደርሷል ይባላል” ለአቅመ አዳም አይደለም። ለአቅመ ስራም አይደለም። ለአቅመ ጉዞ ደበብ አፍሪካ እንጂ…!
አንድ ሰሞን ግራ ገብቶኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች ደቡብ አፍሪካ ምን አላቸው? ብዬ አንድ ወዳጄን ጠይቄው ነበር።
እርሱም ሲነግረኝ፤ በአንድ ወቅት አንድ የደቡብ ክልል ሰውዬ ስማቸው ጠፋኝ (በቅንፍ እርሳቸውም ጠፍተዋል መሰለኝ። (በሌላ ቅንፍ ዘንድሮ አንደሆነ እግር ኳስ ተጫዋች ሳይሆን እንደወጣ የሚቀረው የመንግስት ባለስልጣን ሆኗል። ሁለቱም ቅንፋችን ዘግተን ስንወጣ))
እናልዎ እኒህ የደቡቤ ባለስልጣን በደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ተደርገው ተሹመው ነበር አሉ። ታድያ ያኔ ሰውዬው በርካታ ዘመዶቻቸውን ከደቡብ ክልል ወደ ደቡብ አፍሪካ ማስወጣት ጀመሩ። ዘመዶቻቸው ደግሞ በ “ሳውዝ” እንደምንም ብለው ተፍጨርጭረው ውጤት ላይ ሲደርሱ ሌላ ዘመዳቸውን መጥራት ጀመሩ። ከዛ እያለ እያለ አሁን አሁን የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች ታላቅ የተስፋ ምድር አድርገው የሚያዩዋት ደቡብ አፍሪካ ሆነች።
ወደዛ ለመድረስ ደግሞ ኬኒያን መርገጥ፤ በኬኒያም መረገጥ ግድ ነው። እንዴት የሚለው ብዙ ነው… ዛሬ እንደው መንደርደሪያውን እንቃመሰውና እንቀጥልበታለን…
አብዛኛዎቹ የደቡቤ ስደተኞች የሚመጡት በግሩፕ ነው ተባብለን የለ! ኬኒያ ድረስ በእግርም በአውቶብስም በምንም በምንም ተብሎ ይገባል። ከዛ በኬኒያ አንድ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለው አርባ ወይም ሰላሳ እስኪሞሉ ይጠባበቃሉ። ምክንያቱም ለቀጣዩ የደቡብ አፍሪካ ጉዞ ትራንስፖርታቸውም የትልልቅ መኪና እቃ ማጠራቀሚያ “ኮንቴይነር” ነው። “ኮንቴይነሩ” ከሰላሳ እስከ አርባ የሚሆኑ ሰዎችን በአንዴ ይይዛል። ዋጋውም ከሌሎች መጓጓዣዎች ቀነስ ያደርጋል። ስለዚህ ብዙዎች ይመርጡታል።
በኮንቴይነር ሲጓዙ ታድያ፤ ዋጋው ብቻ ሳይሆን ስቃዩም እርካሽ ነው። ሞቱም በሽ ነው። ምነው እንኳ ባለፈው ኬኒያን አልፈው ታንዛንያ ሲደርሱ ስንት ወጣቶች ናቸው አየር አጥሯቸው በኮንቴይነር ውስጥ የሞቱት…? እረሱት እንዴ፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሁሉ ዜናውን ሰምተን አልነበር እንዴ! (ወይስ እርስዎ ያኔም ዲሽ ገዝተው ነበር…!? ትንሽ ኢቲቪን ሏሽሟጥ ብዬ እንጂ ዜናው በአለም አቀፍ ማሰራጫዎችም ተሰራጭቶ ነበር። እና በርግጠኝነት ሰምተውታል)
ኬኒያ ቁጭ ካሉ ደግሞ እንደዚህ አይነት ዜና ብርቅ አይደለም። በተለይ ታንዛንያ ላይ በርካታ ወገኖቻችን በታጨቁበት ኮንቴይነር ውስጥ ፍፃሜያቸው ሆኗል።
ነገር ግን እንዲህም ሆኖ ጉዞው አያቋርጥም። መጓጓዣውም አይቀየርም። ኬኒያ ለ12 አመታት የኖረው አዲስ እንደነገረኝ ከሆነ “እነኳን ሌላው ቀርቶ አጠገባቸው ጓደኞቻቸው በኮንቴይነር ውስጥ አየር አጥሯቸው ሞተው በእግዜር ታምር ተርፈው ደቡብ አፍሪካ የገቡ ሰዎች ራሳቸው፤ ሌላ ዘመዳቸውን የሚያስመጡት በኮንቴይነር ነው።” ብሎኛል።
ደቡቤ ወዳጆቻችንም እንትና ሞተ የሚለውን ወሬ ቢሰሙትም ከልባቸው አይፅፉትም። በጣም ያስገረመችኝን አንድ ወሬ ቀጥሎ ልንገርዎትማ፤
በደቡብ ኢትዮጵያ በተለይ ከንባታ እና ሃድያ አካባቢ የተለያዩ ቪዲዮ ቤቶች አሉ። ቪዲዮ ቤቶቹ ፊልም ያሳያሉ። የሚያሳዩት ፊልም የ “ጄኪ ቻን” ካራቴ እንዳይመስልዎ… የ “ጆቴ ጃና ህይወት በደቡብ አፍሪካ” የሚል ነው።
እንግዲህ “ጆቴ” በአካባቢው የሚታወቅ የደቡብ ልጅ ነው አሉ። (ስሙ አፌ ላይ መጥቶ ነው አንጂ ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ያለው እውነተኛው ስም አይደለም) እና ከደቡብ ሲወጣ “ስንጥር ነበር የሚያክለው ቀጫጫ፤ አሁን ወፍሮ ባላባት መስሏል። እቤቱ ሶፋ ላይ ሲቀመጥ፣ በሪሞት ቴሌቪዥኑን ሲያበራ እና ሲያጠፋ፤ የሆነች ነጭ የምታምር መኪና ተደግፎ፣ ደግሞ ሌላ ቀይ መኪና ውስጥ ቁጭ ብሎ “ሾፌር” ሆኖ… ብቻ በጥቅሉ የአካባቢው ወጣቶች በቅርብ የሚያውቁት “ጆቴ ጃና” ሆኗል የሚያስቀና…!
ይህንን ቪዲዮ የአካባቢው ወጣቶች ከፍለው ነው የሚያዩት። ከዛ የስቃይ እና የሞት ወሬ ትዝ አይላቸውም። ቁጭ ብለው ያስባሉ እንደ “ጆቴ ጃና” መሆን የሚቻለው እንዴት ነው? ብዙውን ጊዜ ቪዲዮውን የሚያሳየው ሰውዬ ራሱ አማካሪ ነው። እንደውም ሳስበው ቪዲዮውን ካሳያቸው በኋላ “እንደ ጆቴ ጃና መሆን ይፈልጋሉ… እንግዲያስ መላው ቀላል ነው!” ብሎ ማስታወቂያ ሳይሰራ አይቀርም።
ታድያ የድለላ ስራ ይራና ጠርቀምቀም ያሉ ጎረምሶችን ከመንገድ መሪ ጋር አድርጎ ኬኒያ ያደርሳቸዋል። ከኬኒያ ደግሞ ጠርቀምቀም ሲሉ በኮንቴይነር መኪና ውስጥ ተጭነው በሰላም ከገቡ “ጆቴ ጃና” ደቡብ አፍሪካ ይቀበላቸዋል።
“መሃሉ አይነገርም” እንዲል ሰባኪው መሃሉ ግን ብዙ ጣጣ አለው። በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ መሃል ካሉት የመሃል ላይ አበሳዎች አንዱ ኬኒያ ውስጥ ያለው አበሳ ነው… በሚቀጥለው ጊዜ ቅንጭብጫቢ አበሳዎችን እናነሳለን!
ለዛሬ ይብቃን…
እስቲ አማን ያሰንብተን!

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate