Pages

Dec 29, 2012

የሙስሊሙ ብስለት፣ የመንግስት ክስረት፣ የኢቲቪ ቅጥፈት

ነብዩ ኃይሉ
የአዲስ አበባ አየር ከጨፈገገ ሰነባብቷል፤
የክረምቱ ቅዝቃዜ የፀሀይን ወራት የሚያስናፍቅ
ነው፡፡ ፖለቲካው ግን ቀድሞ የፀሀይን ወራት
የናፈቀ ይመስላል፤ የፖለቲካው ነፋስ የክረምቱን
ድባቴ ገለል እያደረገ ድንገቴ ክስተቶችን በማንፈስ
የፖለቲካው ክረምት እየጠራረገው ይመስላል፡
፡ የፖለቲካው ውጥረትና ግለትም ከጊዜ ወደ
ጊዜ በመናር ላይ ይገኛል፡፡ ከክረምቱ ድንገቴዎች
መካከል ለሰባት ወራት የቀጠለው የሙስሊሙ ተቃውሞ “ከመጅሊስ ወደ መለስ” እየዞረ መምጣት፣
የአቶ መለስ አልጋ ላይ መዋልና እሱንም ተከትሎ
በኢህአዴግ ውስጥ የተጀመረው የስልጣን ሽሚያ
(power struggle)  የክረምቱ የፖለቲካ ግለቶች
ሆነዋል፡፡
የአቶ መለስ መንግስት የአለቃውን ህመም
ተከትሎ የገባበት ውጥረት ላይ የተጨመረው
የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተቃውሞ የስልጣኑን
መሰረት እንዳያሳጣው የሰጋ ይመስላል፡፡ ወራትን
ባስቆጠረው የመንግስትና የሙስሊሙ ህብረተሰብ
አለመግባባት፣ በሙስሊሙ አካባቢ የነበረውን
የድጋፍ መሰረት ቀስበቀስ ተንዶበታል፡፡
ከታሪካዊው የታህሪር የአደባባይ ተቃውሞ
ወዲህ በአፍሪካ በርካታ ሰዎችን የያዘና የተደራጀ
ታላቅ ትእይንተ ህዝብ ሲደረግ የሰሞኑ የአዲስ
አበባ የሙስሊሞች ተቃውሞ የመጀመሪያው ነው፡
፡ በተለይም በዘንድሮው የረመዳን ፆም የመጀመሪያ
አርብ ሐምሌ 13  በአንዋር መስጂድና አካባቢው

በተደረገው ድምፅ አልባ የተቃውሞ ትዕይንት
የተሳተፈው በግምት ከአምስት መቶ ሺ በላይ
የሚሆነው ህዝብ በፍፁም ጨዋነት የተቃውሞው
መልዕክቱን አስተላልፎ በሰላም መበተኑ
የሙስሊሙን ህብረተሰብ የብስለት ደረጃ በግልፅ
የሚያሳይ ነው፡፡ ከአሁን አሁን ተበጠበጠ፣ ከአሁን
አሁን ድንጋይ ተወረወረ ብለው ሲጠባበቁ የነበሩት
የመንግስት ሃይሎች በእጅ ምልክት የታጀበውን
የተቃውሞ ትእይንት እንደ ቲያትር ለመመልከት
ተገደዋል፡፡
ይህ አይነቱ ሰላማዊ የተቃውሞ መንገድ
ከማህተመ ጋንዲም ሆነ ከማርቲን ሉተር ኪንግ
ጁኒየር የሰላማዊ ትግል ስልቶች የላቀና የረቀ
መሆኑ፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚወደስበት ጊዜ
ሩቅ አይሆንም፡፡ ይህ አይነቱ ተግባራዊ የተቃውሞ
ስልት ሰላማዊ ትግልን መግለጫ በመስጠት ብቻ
ገድበው ለተቀመጡት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙ
ሊያስተምር የሚችል መሆኑ አንድና ሁለት
የለውም፡፡
የተቃውሞ እንቅስቃሴው መሪዎች
እንደሚታሰሩ ባስ ካለም በመብት ጥያቄ ትግላቸው

ሕይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ አስቀድመው
ተረድተዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል የእነሱን መታሰር
ብሎም ሕይወትን ማጣት ተከትሎ ህዝቡ ወደ
ግብታዊ የሀይል እርምጃ እንዳገባ አስቀድመው
መቀስቀሳቸው፡፡ ሌላው ብስለት የተሞላው
እንቅስቃሴ የመንግስት ሚዲያዎች የተቃውሞ
እንቅስቃሴው በሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ላይ
ስጋት እንዲፈጥር የተሰሩትን የህዝብ ግንኙነት
ስራዎች በማክሸፍና የሙስሊሙን ጥያቄ በቀና
ልቦና እንዲወስደው ብሎም ከጎናቸው እንዲሰለፍ
ለማድረግ ያደረጉት የተሳካ የማግባባት ስራ
በሂደት ለውጥ እያመጣ መሄዱ የሚያጠራጥር
አይመስልም፡፡      
የሙስሊሙ ተቃውሞ ከመጅሊስ ወደ መለስ
እንዲዞር እያደረጉ ካሉ አጋጣሚዎች መሀከል
የኢቲቪ ቅጥፈት ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ ጣቢያው
የስርአቱ ዋንኛ የፕሮፓጋንዳ ማሽን እንደመሆኑ
መጠን የገዢዎቹን ጥቅም ለማስከበር  “ጋግሮ”
የሚያሰራጫቸው መረጃዎች ህዝቡ ዘንድ መዘባበቻ
አድርገውታል፡፡ እንደተለመደው የሙስሊሙን
መሰረታዊ ጥያቄ በተንሸዋረረ መነፅር በማሳየትና
የጥያቄውን መንፈስ ፖለቲካዊ ይዘት በማላበስ
የጋገረውና እየጋገረ ያለው መረጃ መንግስት
በሙስሊሙ ላይ ያለውን አቋም በአንድም ሆነ
በሌላ የሚገልፅ ይመስላል፡፡
በተለይም በቅርቡ እስከ ግጭት ለደረሰው
አለመግባባት ትልቁን ሚና የተጫወተው በቅርቡ
“ብዙ ሃይማኖት አንዲት ሀገር” በሚል ርዕስ በኢቲቪ
የቀረበው ዘጋቢ ፊልም እና በተለያዩ የሀገሪቱ
ክልሎች  “ተቃውሞውን በመቃወም”  የተደረጉ
ሰልፎች ሰፊ የዜና ሽፋን በመስጠት የውግዘት መአት
ማውረዱ ነው፡፡ ጣቢያው የሙስሊሙን እንቅስቃሴ
ፖለቲካዊ ታፔላ በመስጠት ሙስሊሙም ሆነ
ክርስቲያኑ እንቅስቃሴውን የጎሪጥ እንዲመለከተው
የተለያዩ የፕሮፖጋንዳ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
ኢቲቪ መረጃውን ጋርሮ ሳይጨርስ ህዝበ
ሙስሊሙ ክስተቶችን ወዲያውኑ በፌስ ቡክና
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ለህዝብ ያዳርሳሉ፡
፡ ኢቲቪ ከብዙልፋት በኋላ የሚያሰራጨው መረጃ
የማደናገር አቅም የሚኖረው ለቴክኖሎጂ ቅርበት
የሌለውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ነው ማለት
ነው፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚቀርቡትን
መረጃዎች ሳይመረምሩ ለመቀበል የሚከብድ
መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ማህበራዊ ሚዲያዎቹ
እውነተኛውን መረጃ ከምስል ማስረጃ ጋር
ማቅረባቸው ኢቲቪ የሚያቀርባቸው መረጃዎች
ተፋልሶ ቁጣን እንዲቀሰቅስ አድርጎታል፡፡
በኢቲቪ እና ክስተቱን እየተከታተሉ በማህበራዊ
ሚዲያዎች በሚዘግቡ መካከል የሚተላለፈው
መረጃ ያለው ሰፊ የመረጃ ልዩነት አስገራሚ ነው፡
፡ ለማሳያት ያክልም ቅዳሜ የተከሰተውን ግጭት
ተከትሎ ፖሊሶች ምዕመናኑን ሲያሳድዱና ሲደበድቡ
የሚያሳዩት የቪዲዮና የፎቶግራፍ ምስሎች
በማህበራዊ ሚዲያዎች ተሰራጭተው ምዕመናኑ
ላይ የደረሰውን በደል ሲያሳዩ፤በሌላ በኩል ደግሞ
ኢቲቪ ቅዳሜ ማታ ባሰራጨው ዜና “አክራሪዎች”
ሙስሊሙን በአንዋር መስጂድ አግተው እንደነበር
በማተት የእንቅስቃሴውን ህገ ወጥነት ተናገረ፤
በግጭቱ የወደሙ ንብረቶችንም አሳየ፡፡ ሆኖም
ጣቢያው ምእመናኑ ድንጋይ ሲወረውሩ እንጂ
ፖሊሶቹ ድብደባ ሲፈፅሙ አላሳየም፡፡ የግጭቱንም
እውነተኛ መንስኤ ለማመላከት አልደፈረም፡
፡ የተቃውሞው እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥም ሆነ
በአለም አቀፍ ሚዲዎች በቂ ሽፋን አለማግኘቱ
የእንቅስቃሴውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና በሀገሪቱ
ፖለቲካ ላይ የሚኖረውን በጎም ሆነ አሉታዊ
ተፅእኖ በጉልህ እንዳይታይ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡
መንግስት ከሙስሊሞች እንቅስቃሴ ጋር
ተያይዞ የተለያዩ ኪሳራዎችን ለማስተናገድ የተገደደ
ይመስላል፡፡ ተቃውሞው ፖለቲካዊ ገፅታ እንዲይዝ
ያደረገው ጥረትም ሆነ እንቅስቃሴውን ከህዝቡ
ለመነጠል ያደረገው ጥረት የሰመረ አይመስልም፡
፡ መንግስትን ትዝብት ላይ ከጣሉት አጋጣሚዎች
መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው ከሳምንታት በፊት
በኢቲቪ ባስተላለፈው  “ብዙ ሃይማኖት አንዲት
ሀገር”  በሚለው ዘጋቢ ፊልም ላይ የሃይማኖት
ምሁራን በሚል ያቀረባቸውን ግለሰቦች በሳምንት
ጊዜ ውስጥ አሸባሪ በማለት አፋፍሶ ማሰሩ ነው፡፡
የታሰሩት ግለሰቦች የተቃውሞ እንቅስቃሴውን
ለሰባት ወራት ሲመሩ ቆይተው አሁን የፖለቲካው
ውጥረት ሲያይል መታሰራቸው ከኢህአዴግ
የተለመደ ባህሪ አንፃር የእስሩን ፖለቲካዊ አንድምታ
የሚሰጥ ነው፡፡ የተቃውሞ እንቅስቃሴው መሪዎች
ህዝቡ በየትኛውም ምክንያት ወደ ስሜታዊ
እንቅስቃሴ እንዳይገባ መቀስቀሳቸው፣ የመንግስትን
ውንጀላ ከንቱነት ያረጋገጠ ይመስላል፡፡
መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ የሚያደርገው
ጣልቃ ገብነት በሙስሊሙ ላይ ብቻ ባይሆንም
የተቀሩት ሃይማኖት ተከታዮች ተቃውሟቸውን
ወደ አደባባይ ለማውጣት የደፈሩ አይመስሉም፡፡
በወቅታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥረት
ውስጥ የጎላ ድርሻ ያበረከተው የሙስሊሞች
የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወዴት እንደሚያመራ
ለመገመት አስቸጋሪ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሰላማዊ
የተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሰፈረው አሻራ ግን
ለዘመናት አይረሴ ሆኖ ቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate