Dec 30, 2012
ፓትርያርክ በዕጣ
ከወገንተኛነት የተላቀቀ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ መስዋእት ለመክፈል የተዘጋጀ፣ ሰውን የማይፈራ፣ ለከንቱ ረብ
ከአዘጋጁ፡ ይህን የethiopianchurch.org ር ዕስ አንቀጽ የድረ
ገጹ አዘጋጆች የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች ይደረሳቸው በሚል የላኩልን
መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አቡን ፍሬምናጦስ የተሰኘ የሊባኖስ
ተወላጅ ነው። ሹማ የላከችው የእስክንድርያ ግብጽ ቤተክርስቲያን
ስትሆን፣ ዘመኑም 330 ዓ.ም ነው። እስክንድሪያ በጠቅላላው 111
ግብጻውያን ሊቃነ ጳጳሳትን አከታትላ ወደ አገራችን ልካለች።
የመጨረሻው ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በጣልያን ወረራ ዘመን መንጋውን
በትነው ካይሮ ስለ ቀሩ፣ ነጻነት ሲመለስ በአጼ ኃይለሥላሴ ከፍተኛ
ጥረት የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ፣ በ1943 አቡነ ባስልዮስ
የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሊቀጳጳስ ሆነው ተሾሙ። ባስልዮስ
በስድሳ ሁለት አርፈው በስድሳ ሦስት ቴዎፍሎስ ተኩአቸው። በስድሳ
ስድስት የአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ፈረሰ። በስድሳ ስምንት
ቴዎፍሎስ ታሠሩ። ቴዎፍሎስ እስር ላይ እያሉ ተክለሃይማኖት
ሦስተኛ ፓትርያርክ ሆነው በመንግሥት ተሾሙ። ተክለሃይማኖት
በሰማንያ ድንገት ሞተው፣ መርቆሬዎስ በዚያው ዓመት አራተኛ
ፓትርያርክ ሆኑ። በሰማንያ ሦስት መንግሥት ፈረሰ፤ መርቆሬዎስ ከሥልጣን ወርደው ተሰደዱ። በሰማንያ አራት አቡነ
ጳውሎስ አምስተኛ ፓትርያርክ ተብለው በመንግሥት ተሰየሙ። ጳውሎስ ነሐሴ 2004 ሳይታሰብ ሞቱ። ጳውሎስን
ማን ይተካ እየተባለ ነው።
በእኛ አስተያየት፣ ትክክለኛው ጥያቄ ጳውሎስን ማን ይተካ ሳይሆን፣ የፓትርያርክ ምርጫ እንዴት ይካሄድ የሚለው
ነው፤ ከ1943 ጀምሮ የመንግሥት እጅ ሳይገባበት የተካሄደ ምርጫ አንድም የለምና። ከስድሳ ስድስት ወዲህ
እንዲያውም፣ የተሰየመው ሳይሞት በላዩ ሌላ የመሾም ጉዳይ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቋሚ ችግሮቿ አምስት ናቸው። የመጀመሪያው ከመንግሥት ተጽዕኖ ተላቅቃ ራሷን በራሷ
ለማስተዳደር አለመብቃቷ ሲሆን። ሁለተኛው፣ ምዕመኑ የክርስቶስን ወንጌል እንደሚገባ እንዲያውቅና እንዲያነብ
አለመደረጉ ነው። “ማርያም አዳኝ ነች፤ ያለርሷ አማላጅነት ዓለም አይድንም” የሚለው የስሕተት ትምህርት እምነትን
እንደሚገባ ካለማወቅ የሚመነጭ ሲሆን፣ በክርስቶስ ያመኑና ያላመኑትን ለይቶ አለማወቅ ሌላኛው አሳሳቢ ችግር ነው
[1ጢሞ 2፡5፤ የሐዋ.ሥ 4፡12፤ ሮሜ 10፡9]። ሦስተኛ፣ ወንጌል ማንበብና መጸለይ ያበዙ ልጆቿን “ጴንጤ”
“መናፍቃውያን” በማለት ማባረሯና፤ ይህም ሁኔታ ቀርበው ሊቀላቀሉ የሚያስቡትን ጭምር ማራቁ ነው። አራተኛ፣
የክርስቶስን ሳይሆን የየራሳቸውን የርዕዮት፣ የምቾችና የጎሳ ፖለቲካ በሚያራምዱ ቡድኖች መከፋፈሏ ነው። አምስተኛ፣
ማንም ግለሰብና ቡድን ከያለበት አሳቡን በቴክኖሎጂ ማስተላለፍ መቻሉ፣ ለእርምት በማያመች አኳኋን
የቤተክርስቲያንን አስተምህሮና ህልውና እየተቀናቀነ መምጣቱ ነው።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን “ዲሞክራሲያዊ” የሢመት ሥርዓት የላትም አንልም። “ዲሞክራሲያዊ” አሠራር ግን
መሪዎች በግልና በቡድን ከሚያራምዱት የሥልጣን አጀንዳ አንጻር የሚያስማማና አስተማማኝ ነው ማለት አይደለም።
ሰሞኑን የተጠናቀቀውና ብዙዎችን ያነካከሰ የአንግሊካን ማህበራት መሪ ምርጫ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ይሆነናል። ወቅቱ
ወሳኝነትና ቅንነትን የሚጠይቅ ወቅት ነው። ከተለምዶው የወጣ ምርጫ የሚጠይቅ ወቅት ነው። የሚቀጥለው
የቤተክርስቲያን አባት የተበተነውንና የተጎሳቆለውን መንጋ የሚሰበስብ፣ በፍርሃትና በጥርጣሬ የሚተያየውን
የሚያረጋጋ፣ የሚያውከውን ለመገሠጽ የሚበቃ፣ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ እንጂ የማንም እንዳይደለች የተረዳ፣
የማይሳሳ የእምነት ሰው መሆን ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰማንያ አምስት በመቶ ያህሉ ከአርባ ዓመት በታች ነው። ዘመኑም 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ
መሆኑ፣ የአዲሱን ትውልድ ጥያቄ በማይለወጥ የወንጌል እውነት ማነጋገርንና የሚስማማ አሠራር የመተግበርን
አስፈላጊነት አጉልቶታል። አንዱም አሠራር በቀደሙ አባቶች ዓይነተኛ አስተዋጽዖ ላይ መገንባት ነው። አቡነ ጳውሎስ
ተዘግቶ የኖረውን መንፈሳዊ ኮሌጅ እንደገና መክፈታቸው፣ የተቀደሰና ነገን አሳቢ ተግባር ብቻ ሳይሆን፣ ብቃት ያላቸው
መሪዎችን ለማፍራት መሠረቱ ነው። የአቡነ ተክለሃይማኖት የሕይወት ዓይነት ደግሞ ሰዓቱ የሚፈልገው ነው።
ብጹእነታቸው ለሕዝቡ ለመጸለይና የጉስቁልናው ተካፋይ ለመሆን የራሳቸውን ምቾት ወደ ጎን ማድረጋቸው፣
ተንሠራፍቶ ለምናየው ሙስና፣ ዓለማዊነትና የበዛ ድፍረት ምላሽ ይሆናል እንላለን።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከመንግሥትና የራሳቸውን አጀንዳ ከሚያራምዱ ቡድኖች ተጽዕኖ ነጻ ትሆናለች ማለት
ከቅርቡ ታሪክ አለመማር ነው። ከየፊናው የምንሰማው ይህንኑ አመልካች ነው። ለዚህ አንዱ መፍትሔ እግዚአብሔር
ሙሴን እንዳዘዘው ማድረግ ነው። በሕዝበ እስራኤል ዘንድ ብዙ ማጉረምረም ነበረና፤ ያን ሊቆርጥ እግዚአብሔር
የእያንዳንዱ ነገድ ስም ያለበትን አሥራ ሁለት በትር “እኔ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ
በምስክሩ ፊት አኑራቸው” አለ ይላል [ዘኁልቁ 17]። በዚያም መካከል የአሮን ስም የተጻፈበትን በትር አኖሩ።
እግዚአብሔር የመረጠውን በምልክት ያሳይ ዘንድ የአሮን በትር አቆጠቆጠች፣ የሌሎቹ ግን አላቆጠቆጠችም።
እግዚአብሔርም የሰው እጅ ያልገባበትን ሥራ ሠርቶ አሳየ። እንግዲህ የሁሉም ፍላጎት እግዚአብሔር የፈቀደውን
ሲያደርግ ማየት እስከሆነ፣ የመንፈስ ቅዱስን ምሪት መፈለግና መከተል አሁን ለሚታየው አለመተማመን፣ ጥላቻና
መከፋፈል ምላሽ ይሆናል እንላለን።
እስቲ አንዴ ለእግዚአብሔር መንገድ እንልቀቅለትና የሚያደርገውን እንይ። የሚያስደንቀንን ሳያደርግ ይቅርና
እንታዘበው። ሐዋርያት፣ ይሁዳ በተዋት አገልግሎት ምክንያት፦ “የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ፥ ይሁዳ ወደ
ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ስፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ
ከሁለቱ አንዱን ሹመው አሉ። ዕጣም ተጣጣሉላቸው፥ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር
ተቈጠረ” እንዲል፣ ጸሎትና ዕጣ መጣል ከ“ዲሞክራሲያዊ” አሠራር የሚቀድም የጥንታዊት ቤተክርስቲያን ሥርዓትና
ወግ ነው [የሐዋርያት ሥራ 1፡24-26]። ዛሬም እንደ ጥንቱ እግዚአብሔር አይሠራም ያለ ማነው?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከእስክንድርያ ሥልጣን ሥር ወጥታ ራሷን ቻለች ማለት ከእስክንድርያ
የምታስቀረው ሥርዓት የለም ማለት አይደለም። ባለፈው ሳምንት፣ ከስምንት ወር በፊት በሞቱት በአቡነ ሸኑዳ እግር
ዳግማዊ ታዋድሮስ [ቴዎድሮስ] ሲመረጡ፣ ዓይኑን የታሠረ ሕጻን ከቀረቡት ሦስት ተመራጮች መካከል ዕጣ
እንዲያወጣ ሲደረግ አይተናል። ነብዩ ኢሳይያስ፣ “በአንድነት ያርፋሉ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል” እንዳለው ማለት
ነው [11፡6]። ነገሩ፣ ከሰው እጅ፣ የእግዚአብሔር እጅ ይበልጣል ነው። ከምድራዊ መንግሥት ይልቅ የሰማይ
መንግሥት ይምረጥ ነው። በሰው ከመታመን በእግዚአብሔር መታመን ይበልጣልና። እግዚአብሔር ይምረጥልን፣
ሰላምና እረፍት ያውርድልን ነው። እግዚአብሔር ይናገር፤ ፍጥረት ዝም ይበል ነው። “ዕጣ በጕያ ይጣላል፤ መደብዋ
ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” [ምሳሌ 16፡33]። ከውጭና ከውስጥ መተማመን እንዲኖር፣ ማንም
የሚያመካኘው እንዳይኖረው፣ ለዚህ ወቅት ከተለምዶው በወጣ አኳኋን ምርጫው በዕጣ ይሁን የምንለው ለዚሁ ነው።
ይህም ትሕትናን ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ሕዝብ መራራትን፣ ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን መፍራትን አመልካች
ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ በያለበት የንስሃ ጾም ይጹም፣ ይጸልይ። በኃይሉና በጥበቡ ወደር የሌለው፣
የቤተክርስቲያኑ ጌታና እረኛ ሕያው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የቤቱ ቅንዓት ግድ ይበለው።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment