የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን
ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ (ሚኒስትር)
ከእንጀራ ልጆችዎ
ክቡር ሚኒስትር አቶ በረከት ሆይ
ልብ ብለው ይስሙን፡፡ እባክዎትን አንድ ጊዜ
ጆሮዎትን ያውሱን፡፡ ምነው ልብዎት በእኛ
ጨከነሳ? ይህ የእንጀራ ልጅን የማግለል ሥራ
ውጤቱ ጥሩ የሚሆን ይመስልዎታልን? እንዴት
ነው ነገሩ?
ክቡር አቶ በረከት፡- እኛ ለእርስዎ ልዩ ክብርና አድናቆት አለን፡፡ የኮሙዩኒኬሽን ድ/ቤትን መምራት ከጀመሩበት
ጊዜ ጀምሮ በዋናነት በእርስዎ አመንጭነትና አስፈፃሚነት የተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎች በአገራችን ለዘመናት
የነበረውን የኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለማሻሻል ጥሩና አበረታች ጅምር ያሳዩ ናቸው፡፡ ይህን
እናምናለን፡፡ በእርስዎ አንቀሳቃሽነት እየመጡ ያሉ መሠረታዊ ለውጦችን ሁላችን በየመስሪያ ቤታችን እያየንና
እየተደሰትን ነው፡፡ ድካምዎት ሁሉ ለአገራችን ሁለንተናዊ ለውጥ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ ታላቅ አስተዋጽኦ
እንዳለው በመገንዘብና ለአገራችን መልካም ገጽታ መገንባት ከልብ በማሰብ ነው ብለንም እናምናለን፡፡
እርስዎ በጽ/ቤትዎት እያመጡት ካለው ለውጥ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰውም በየጊዜው የሚሰጠው የአቅም
ግንባታ ሥልጠና ነው፡፡ ልዩ የኮሙዩኒኬሽን ሥልጠናው፡፡ በተለይም በደንብ በተጠናና ተከታታይነት ባለው
መልኩ ቢሆን ኖሮ፡፡ የኮሙዩኒኬሽን ሥልጠናው የተሰጠበት መንገድ ማለትም የሠልጣኞች አመላመል ችግር
እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ለኮሙዩኒኬተርነት የማይበቁ ብዙ ኮሙዩኒኬተሮች ሥልጠናውን ቢወስዱም ኮሙዩኒኬተር
መሆን እንዳልቻሉ እርስዎም እያዩት ይመስለናል፡፡ የዚህ ችግር ዋናው መነሻ ደግሞ የኮሙዩኒኬተሮች አመላመል
ነበር፡፡ የተፈጥሮ ሳይንስ ምሩቃን፣ የሒሳብና ፊዚክስ መምህራን ኮሙዩኒኬተር ሁኑ ሲባሉ ችግር ባይገጥም ነበር
የሚገርመው፡፡
የሆነው ሆኖ ግን እስከመሠረታዊ ችግሮቹም ቢሆን ኮሙዩኒኬተሮችን በአቅም ለመገንባት የተሰጡ ሥልጠናዎች
አበረታች ለውጥ እያሳዩ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በየፌዴራል መስሪያ ቤቱ ኮሙዩኒኬተር መኖሩ በራሱ ጥሩ ነገር
ነው፡፡ ይህ ግን ብቻውን ትርጉም ያለው ለውጥ አያመጣም፡፡ በተለይ በድ/ቤትዎ በኩል በአሁኑ ሰዓት
ለኮሙዩኒኬተሮች እየተሰጠ ያለው የትኩረት ማነስና አድሎ የተሞላበት መከፋፈል ከፊት ለፊቱ ትልቅ ስጋትን
ደቅኗል፡፡ በየፌደራል መስሪያ ቤቱ የተገለልን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጉዳይ በአስቸኳይ መፍትሔ
ካልተሰጠው ወደ ከፋና አስቀያሚ ችግር ያመራል፡፡ አይጠራጠሩ፡፡
ይህን የምንልዎት ከመሬት ተነስተን አይደለም፡፡ እጅግ ተጨባጭ ማስረጃዎችና ማሳያዎች አሉን ምን አልባት
አይደርስዎት እንደሆነ እንጅ የጽ/ቤትዎ ኮሙዩኒኬተሮች/አስተባባሪዎች በተለይ/ በየመስሪያ ቤታችን መጥተው
ችግሩን በመረጃ አስረድተናቸው አምነውበታል፡፡ ፊርማ አሰባሰበን ማመልከቻም አስገብተናል፡፡ በተለያዩ
ጊዜያትም ችግሩ መፍትሔ እንደሚሰጠው ተዋሽቶልናል፡፡ ሁል ጊዜ ውሸትና የማይፈፀም ቃል ግን ይሰለቻል፡፡
ለማንኛውም የጽ/ቤትዎን ችግር ወይም የእርስዎን ክፍተት ለዛሬ ጥቂቶቹን ብቻ እናንሳ፡፡
1ኛ/ የአቅም ግንባታ ችግር፡- ይህ ጉዳይ ስትራቴጅካዊ ችግር ነው፡፡ አሁን በየፌዴራል መስሪያ ቤቶች ያለን
ኮሙዩኒኬተሮች ከፍተኛ የሆነ የአቅም ክፍተት አለብን፡፡ ካሁን በፊት የተሰጡ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች
ለተወሰኑ ኮሙዩኒኬተሮች ብቻ ነበር፡፡ የተወሰኑት ለ2ኛና 3ኛ ዙር በተደጋጋሚ ሲስለጥኑ ሌሎቻችን ግን
ሥልጠናው አይመለከታችሁም ተብለናል፡፡ የአብዛኞቻችን የአቅም ክፍተት መንጩ ይኽው አድሎአዊና የተወሰኑ
ግለሰቦችን ብቻ መሠረት ያደረገ ሥልጠና አሠጣጥ ነው፡፡ ግን ለምን? እኛ ኢትዮጵያዊያን አይደለንም?
የአገራችን ለውጥ እኛን አይመለከተንም? ሥልጠናውን ለማግኘት ምን መስፈርት ነው ማሟላት ያለብን?
ከ50% በላይ የምንሆን ባለሙያዎች እኮ ሥልጠና አልወሰድንም፡፡
ብዙ ጊዜ የኮሙዩኒኬሽን ሥልጠና የሚሰጠው ለኢህአዴግ ታማኝ አባላት ነው የሚል ግምት ነበረን፡፡
በተጨባጭ ከየመስሪያ ቤቱ ያለን የእንጀራ ልጅ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በግል ተሰባስበን ስንነጋገር ግን
ይህ አይደለም እውነቱ፡፡ እንዲያውም እንዳንድ ፀረ ዴሞክራሲያዊና ፀረ ልማታዊ የሆኑ በሥልጠናው ሲጠቀሙ
እጅግ ጠንካራ የድርጅቱ ልጆች ግን እስካሁን ተገለዋል፡፡ በጣም የሚገርመው በአብዛኛው ፌደራል መስሪያ
ቤቶች ያሉና ሥልጠናውን የወሰዱ ኮሙዩኒኬተሮች የነበራቸው የትምህርት ዝግጅት የተፈጥሮ ሳይንስ በመሆኑና
አሁንም ለመለወጥ ዝግጁ ስላይደሉ ሥልጠናውን ደጋግመው ቢወስዱም እንኳን በስም እንጅ በግብር
ኮሙዩኒኬተር መሆን አልቻሉም፡፡ በአንፃሩ ግን በፖለቲካል ሳይንስ፣ በቋንቋ፣ በደርናሊዝምና ኮሙዩኒኬሽን
ተመርቀን ሥራውን በአግባቡ እየሰራን ያለን ባለሙያዎች ሥልጠናውም አልተሰጠንም፣ የኮሙዩኒኬተርነት
ማዕረግም የለንም፡፡
የስልጠና መስፈርቱ ምን ይሆን? ለምንስ የአቅም ግንባታ ሥልጠናው ቆመ? “የክቡር አቶ በረከት መልካም
ፈቃድ ስለሚያስፈልግ ነው” የሚለው የእርስዎ ባለሙያዎች መልስ እውነት ነው? እውነት ከሆነ እኛ ምን
አጥፍተን ነው የእርስዎን መልካም ፈቃድ ማግኘት ያልቻልነው? ሥልጠናውን ብንወስድ ምን ይጎዳዎታል?
እባክዎትን ያስቡበት፡፡ ይህ ማግለል አገርን ይጎዳል ለሥራዎም እንቅፋት ይፈጥራል፡፡ እኛም በኢትዮጵያ ጉዳይ
ያገባናል፡፡ በሥልጠናው አቅማችንን ገንብተን ለአገራችን ሕዳሴ የራሳችንን ድርሻ መወጣት እንፈልጋለን፡፡
እባክዎትን ያሰልጥኑን! የሰለጠነ አይጎዳም- ይጠቅማል አንጅ!
2ኛ/የቡድንተኝነት መንፈስ፡-
ይህ መጥፎ የሆነ የቡድንተኝነት መንፈስ በአብዛኞቹ ፌደራል መስሪያ ቤት ኮሙዩኒኬተሮች ዘንድ በግልፅ
ይታያል፡፡ የእንጀራ ልጅ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ከየመስሪያ ቤቱ በግል ተሰባስበን በተወያየንበት ወቅት
በግልፅ እንደተረዳነው ይህ የቡድንተኝነት መንፈስ በሥራ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ
ከየመስሪያ ቤቱ ወጥቶ ይሄው ሀገራዊ እየሆነ ነው፡፡ ሥልጠናውን የወሰዱና የኮሙዩኒኬተርነት ማዕረግ
የተሰጣቸው ሥልጠና ያልወሰድን ባለሙያዎችን እያገለገሉን ነው፡፡ በሆነ ባልሆነው ኮሙዩኒኬተር
አለመሆናችንንና ከሕዝብ ግንኙነት ሥራም ልንባረር እንደምንችል ይነገረናል፡፡ ይህ ሁሉ ዛቻና ማግለል ከፍተኛ
የሆነ የሞራል ውድቀት እያስከተለብን ነው፡፡ እስከመቼ እንደዚህ ሆነን እንኖራለን? በፌዴራል መስሪያ ቤቶች
እኮ ከ5ዐ% በላይ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሥልጠና አልወሰድንም፡፡ ታዲያ ይህን ክፍል ያገለለ ሥራ
ውጤታማ ይሆናል ብለው ያስባሉ?
በጣም በሚገርመው በሁለቱ ቡድኖች ማለትም በሠለጠኑ እና ባለሠለጠኑ ኮሙዩኒኬተሮች መካከል መረጃ
የመደባበቅ ሁኔታው ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ የሠለጠኑ ኮሙዩኒኬተሮች ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/
ቤትም ሆነ ከሌላ የሚደርሳቸውን መረጃ ለራሳቸው ብቻ ይጠቀሙበታል፡፡ ለነገሩ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/
ቤትም ቢሆን መረጃ የሚልከው ለሠለጠኑትብቻ ነው፡፡ እርስዎም ይህን ያውቃሉ ብለን እናምናለን፡፡ የእኛን ኢ-
ሜይል /E-mail/ አድራሻ እኮ ጽ/ቤትዎ አያውቀውም፡፡ምንም መረጃም ደርሶን አያውቅም፡፡ ምክንያቱም
የእንጀራ ልጆች ነና፡፡ ይህ ግን የአገሪቱን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ምን ያህል እንደሚጎዳ ታስቦበት ነው እንዲህ
የሚደረገው? እርስዎ ያሰቡትን ያህል ለውጥ እየመጣ ያልሆነው እኮ በዚህ ምክንያትም ነው፡፡ እርግጠኞች ነን
መረጃዎቹ ምሥጢራዊ አይደሉም፡፡ እኛ እንዳናውቅ የምንደረግበት ምክንያት ግን ግልፅ አይደለም፡፡ እባክዎትን
ይህ ጉዳይ አገር ይገድላልና ያስቡበት፡፡
3ኛ/ከፍተኛ የሆነ የደመወዝና የጥቅማጥቅም ልዩነት፡-
ክቡር ሚኒስትር አቶ በረከት፡- ይህ መቼም ከእርስዎ የተደበቀ አይደለም፡፡ እያወቁ ለምን እንዲህ እንዲሆን
እንደፈቀዱ ግን ለማንም ግልፅ አይደለም፡፡ በደመወዝ እንጀምር፡፡ አንድ ልዩ ሥልጠና ወስዶ (የ15 ቀናት
ሥልጠና) የእርስዎ ክቡር ፊርማ ያረፈበት የመንግስት ኮሙዩኒኬተር የሚል ስርተፊኬት ያለው የሒሳብና ፊዚክስ
ምሩቅ ጀማሪ ኮሙዩኒኬተር መነሻ ደመወዝ 3,348.00ብር ነው፡፡ ነገር ግን በቋንቋ፣ በጆርናሊዝምና
ኮሙዩኒኬሽን 3 ዓመት ሰልጥነን የመጀመሪያ ዲግሪ ያለን ነገር ግን ልዩ ሥልጠናውን ያልወሰድን የሕዝብ
ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች መነሻ ደመወዛችን 1,499.00ብር ነው፡፡ በተመሳሳይ መደብ ላይ
ተመሳሳይ ሥራ እየሠራን ይህን ያህል የደመወዝ ልዩነት ለምን? እውነታው እኮ ያማል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሞራል
ውድቀትም አስከትሎብናል፡፡ በምን መስፈርት ነው ተመሳሳይ ሥራ እየሠራን በ1,849.00ብር ወርሀዊ ደሞዝ
የሚበልጡን? አንዳንዶቻችን 8 እና 7 ዓመታት በሕዝብ ግንኙነት ሥራ ቆይተን ደመወዛችን ግን
ከሠለጠኑጀማሪ ኮሙዩኒኬተሮች እጅግ ያንሳል፡፡ ለምን? በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ሥልጠናውን ወስደውም
ግን በተለያየ ምክንያት ደሞዛቸው ያልተስተካከለላቸው ኮሙዩኒኬተሮች መኖራቸው ነው፡፡ ምክንያቱ ግልፅ
አይደለም፡፡ ብዙዎቹም ተስፋ በመቁረጥ ሥራ እየለቀቁ ነው፡፡ ለጽ/ቤትዎ ተፈራርመው ያስገቡት ማመልከቻም
መልስ አላገኘም፡፡
ሌላው ጉዳይ ደግሞ ጥቅማጥቅም ነው፡፡ በተለይ በእርስዎ ልዩ ትዕዛዝ ከየክልሉ ተሰባስበውና የ3 ወር ሥልጠና
ተሰጥቷቸው ኮሙዩኒኬተር የሆኑ (አብዛኞቹ በየክልሉ የተፈጥሮ ሳይንስ መምህራን የነበሩና በፖለቲካዊ
አቋማቸው የተመለመሉ) በርካታ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ቤት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለእነርሱ ለምን ተሰጣቸው
የሚል ተቃውሞ የለንም፡፡ ነገር ግን ለሌሎቻችን ቢያንስ ደመወዝ እንኳን ለምን አይስተካከልልንም? የእንጀራ
ልጅ ስለሆንን? በዚህ መልኩ እኮ እርስዎ የሚደክሙለት የኮሙዩኒኬሽን ሥራ ሊሻሻል አይችልም፡፡ ብዙ ጥሩ
ባለሙያዎችን በማሸማቀቅና ሞራላቸውን በመግደል የሚመጣ ለውጥ ያለ አይመስለንም፡፡ ለፌደራል መስሪያ
ቤቶች የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የተፈቀደው ደመወዝ እኛን የማይመለከት፣ ነገር ግን
ሥራው የሚመለከተን ከሆነ ትንሽ ይከብዳል፡፡
እናም ክቡር አቶ በረከት፡- እስከመቼ ነው እኛ የእርስዎ የእንጀራ ልጆች ሆነን የምንቀጥለው? እባክዎትን ደግ
አባት ይሁኑልን፡፡ አባት በልጆቹ መካከል ልዩነት መፍጠሩ ጥሩ አይደለም፡፡ እርስዎ የአባትነት ድርሻዎን
ካልተወጡና እኛን ካገለሉን እኛም ተጨቋኝ የእንጀራ ልጆች ሆነን የምንቀጥል አይመስለንም፡፡ ለቀጣይ ሌሎች
ችግሮችን ይዘን እንመጣለን፡፡ እባክዎትን ያስቡን፡፡”ከልጅ ልጅ ቢለዩ ዓመትም አይቆዩ” ሲባል አልሰሙ ይሆን?
ልዩ ማሳሰቢያ፡-
በአሁኑ ሰዓት የተበዳይ ኮሙዩኒኬተሮች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን በኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤትም ሆነ
በሌሎች መስሪያ ቤቶችና ባለስልጣናት ገመና ዙሪያ መረጃዎችን በማሰባሰብ ላይ እንገኛለን፡፡ ክቡር አቶ
በረከትም በተለመደ ንቀታቸውና ዝምታቸው የሚቀጥሉ ከሆነና እነደማነኛውም ኮሙዩኒኬተር የደመወዝና
ሌሎች ጥቅማጥቅሞች የማይስተካከሉልን ከሆነ ወይም በተለመደ የማታለል ስልታቸው (በሚቀጥለው ወር
ትሰለጥናላችሁ በሚል ፈሊጣቸው) የሚቀጥሉ ከሆነ በምስልና በድምጽ የተቀነባበሩ መረጃዎችን ለተለያዩ
የውጭና የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች በመስጠትና ለሕብረተሰቡ በማድረስ የምንቀጥል መሆኑን እናሳስባለን፡፡
እስከሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት መልስ የማይሰጠን ከሆን ወደ ቀጣዩ የከፋ እርምጃ ለሄድ እንገደዳለን፡፡ ሲሆን
ለዓመታት እየተበደልን ላገለገልንበት ካሳ እንዲከፈለን ባይሆን ግን በመመሪያው መሰረት እንዲከፈለን
ካልተደረገ በስተቀር በቀጣይ በተከታታይ የምንወስዳቸው እርምጃዎች እጅግ የከፉና እኛንም ሆነ መንግስትን
ውድ ዋጋ የሚያስከፍሉ ይሆናሉ፡፡ በእኛ በኩል እስከሞት ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅተናል፡፡ አንድ ቀን
ምንአልባትም በሳምንታት ውስጥ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ሥራ የማቆምና ከሥራ የመልቀቅ አድማ ለማድረግም
ተስማምተናል፡፡ ከዛም ስለቀጣይ ጉዟችን ከተለያዩ አካላት ጋር እየተመካከርን ሲሆን ጥገኝነት ለመጠየቅ
ኢምባሲዎችን እያነጋገርንና ባንዳንዶች ዘንድ በጎ ምላሽ እያገኘን ነው፡፡ ነገሮቹ ሁሉ ወደ ከፋ ደረጃ
ከመድረሳቸው በፊት ግን ቢታሰብበት መልካም ነው እንላለን፡፡ ለአገራችን ሁላችንም ያገባናል፡፡
መብታችንን ለማስከበር የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ እንከፍላለን!
በእርግጠኝነት እናደርገዋለን!
ምንም የሚያስፈራን ነገር የለም፤ ሞትም ቢሆን!
የተበዳይ ኮሙዩኒኬተሮች ሕብረት አንድነት ጉባኤ
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment