‹‹ከእስረኞች ሁሉ ህገ-መንግስታዊ መብቴ ተጥሶ ዘመድ አዝማድ እና ጓደኛ እንዳይጠይቀኝ የተደረኩት እኔ ብቻ ነኝ››ሲል የአንድነት ፓርቲ አመራሩ አንዷለም አራጌ ገለጸ
ታህሳስ ፴(ሰላሳ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አንዷለም ይህን ያለው፤የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ እንዲጠይቁት የተፈቀደላቸው የ አንድነት አመራሮች በቃሊቲ ተገኝተው በጎበኙት ጊዜ ነው።
ወጣቱ ፖለቲከኛ በዚሁ ጊዜ ቃሊቲ ለተገኙት የአንድነት አመራሮች ፦”በፍቅርና በመተሳሰብ የምንኖርባት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች”በማለት ህያው ራዕዩንና ውስጣዊ ምኞቱን ገልጾላቸዋል።
ከአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ አቶ ተመስጌን ዘውዴ፣ አቶ ዘካርያስ የማነብርሃን፣ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና አቶ ሙላት ጣሰው እና ከአስር በላይ የሚሆኑ አባላትም በመገኘት የአንዷለም የጤና ሁኔታና የእስር አያያዝ ምን እንደሚመስል ጠይቀዋል፡፡
አቶ አንዷለም በበኩሉ ከራሱ ይልቅ የገዥው ፓርቲ አፈናና ጭቆና እንዲሁም በዚህ ሁኔታ እየታገሉ ያሉ ባልደረቦቹ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ገልጦ፤ በእሱ በኩል እንደቀረበበት ክስ በማንም ላይ በክፋት ባለመነሳቱ የህሊና ሰላም እንደሚሰማው ተናግሯል፡፡
አሁንም ኢትዮጵያና ፖለቲከኞቿ ስለፍቅርና መተሳሰብ ሊገባቸው አለመቻሉና በፍቅር ተሳስቦ መኖር የሚባለውን መፍራታቸው ክፉኛ እንደሚያሳስበው ተናግሯል፡፡
በተያያዘም በቃሊቲ ከሚገኙ እስረኞች በተለየ ሁኔታ በጠባብ ክፍል የታሰረና እንደማንኛውም እስረኛ ዘመድ አዝማድና ጓደኛ እንዳይጠይቀው የተደረገ ብቸኛ ታሳሪ መሆኑን በማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ፊት ለፊት ተናግሯል፡፡
<<ለእኛ ቀርቶብን ለልጆቻችን እንኳን የተሻለ ማረሚያ ቤት ማስተላለፍ አለብን>> ያለው አንዷለም፤በተለየ መልኩ እሱ ላይ ብቻ ያነጣጠረው የመብት ገፈፋ ተገቢ እንዳልሆነ ፊት ለፊት ገልጧል፡፡
በዚህ ሃቅ የተበሳጩት ማረሚያ ቤቱ ኃላፊ፦ ‹‹ተነስ ግባ!› የሚል ዘለፋ የአንድነት አመራር አባላት በተገኙበት ፊት በብስጭት ተናግረዋል፡፡
የአንድነት አመራርና አባላትም የተጀመረው ትግል ግቡን እስኪመታና በፍቅርና መተሳሰብ የምንኖርባት ኢትዮጵያ እስከምትፈጠር ከትግሉ ሜዳ እንደማያፈገፍጉ ለአንዷለም አረጋግጠውለታል፡፡
No comments:
Post a Comment