በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ብዙ ተማሪዎች መደብደባቸውና መታሰራቸው ታውቀ
ኢሳት ዜና:-ታህሳስ 29 ቀን 2005 ዓም በእራት ሰአት ላይ በድሬዳዊ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተን ረብሻ ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ አባላት ቁጥራቸው የበዛ ተማሪዎችን ደብድበዋል፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተማሪዎችን ደግሞ ይዘው አስረዋል።ታህሳስ ፴(ሰላሳ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
እስከ ምሽት የዘለቀውን ይህንኑ የፖሊሶች ድብደባ መቋቋም ያቃታቸው ተማሪዎች በምሽት ግቢያቸውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ያመለከተው ዘጋቢያችን፤ የሚያድሩበት ቦታ በማጣታቸው በቤተክርስቲያኖች እና ሙስሊም ተማሪዎች ደግሞ ወደ መስጊድ ሄደው መጠለላቸው ታውቋል።
ፖሊሶቹ በምሽት ክፍላቸው ዉስጥ ተደብቀው የቀሩ ተማሪዎች ይኖራሉ በማለት ዶርም ለዶርም አሰሳ ሲያደርጉ ማምሸታቸውን የጠቀሰው ወኪላችን፤በ አሰሳው ዶርም ውስጥ ተሸሽገው የተገኙ ተማሪዎች ሲደበደቡ ማምሸታቸውን አጋልጧል።
አብዛኞቹ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ የተደረገው እራታቸውን ሳይበሉና ልብሳቸዉን ሳይወስዱ ባዶ እጃቸዉን እንደሆነ ከወኪላችን ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።
የችግሩ መንስኤ ለተማሪዎች ከሚቀርበው ምግብ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል። ተማሪዎቹ የተሻለ ምግብ ይዘጋጅልን በሚል ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ የፌደራል ፖሊሶች ወዲያውኑ ዩኒቨርስቲውን በመውረር በተማሪዎች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል።
ዩኒቨርስቲው ዛሬ መጠነኛ መረጋጋት የታየበት ቢሆንም፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት አሁንም አካባቢውን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ለማውቅ ተችሎአል።
ሰሞኑን በ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል የተከሰተን የብሔር ግጭት ተከትሎ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ በርካታ ተማሪዎች እንደተጎዱና ከመቶ የሚበልጡ እንደታሰሩ መዘገቡ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment