ልጃቸው በፖሊስ ኮማንደር የተገደለባቸው አባት ከሆስፒታል ወጥተው በወቅቱ ስለተፈጠረው ድረጊት ተናገሩ
ጥር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ታህሳስ ፳፮(ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ልጃቸው በፖሊስ ኮማንደር የተገደለባቸው አባት ከሆስፒታል ወጥተው በወቅቱ ስለተፈጠረው ድረጊት ተናገሩ
በጌዲዮ ዞን በዲላ ከተማ ኮማንደር ግርማ በየነ የተባለ የዞኑ የፖሊስ የሰው ሀብት ማደራጃ መምሪያ ሃላፊ ከ10 ቀናት በፊት አንድ የ14 አመት ታዳጊን ወጣት በሽጉጥ ገድሎ አባቱን ደግሞ ማቁሰሉን መዘገባችን ይታወሳል።
የማቹ አባት አንገታቸው አካባቢ በመመታታቸው ወደ አዋሳ ሪቨራል ሆስፒታል ተወስደው የነበረ ሲሆን፣ ምንም እንኳ ጥይቱ ባይወጣላቸውም መጠነኛ መሻሻል አድርገው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።
አቶ ሚፍታህ ሙሀመድ ለኢሳት እንደገለጹት ኮማንደሩ ልጃቸውን የገደለባቸው ያለምንም ምክንያት ሲሆን፣ ልጃቸው መሞቱን እንዳዩ ኮማንደሩን “ልጄን ገድለህ አትሄድም ” በማለታቸው እሳቸውንም እንደመታቸው፣ እንዳጋጣሚ ሆኖ ጥይቱ አንገታቸውን ሸርፎ በመሄዱ መትረፋቸውን ተናግረዋል፡፡ ደማቸው እየፈሰሰ ከኮማንደሩ ጋር ግብግብ ተያይዘው አብረው መውደቃቸውን፣ ጩሀት በማሰማታቸው አንድ የፖሊስ አዛዥ መድረሱንና ግለሰቡ መያዙን እርሳቸውም ብዙ ደም ፈሷቸው ስለነበር መዘረራቸውን ተናግረዋል::
ከባለስልጣኑ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልነበራቸው የተናገሩት አቶ ሚፍታህ ባለስልጣኑ በማን አለብኝነት ተነሳስቶ ያደረገው ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ጉዳዩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን የተናገሩት አቶ ሚፍታህ ፣ መጨረሻውን ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው ብለዋል።
የዲላ ነዋሪዎች ወታቱ በተገደለ ማግስት ከፍተኛ ተቃውሞ በመሰማት ገዳዩ ለፍርድ እንዲቀርብ ጠይቀው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። አንዳንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ሰዎች እንደሚሉት በአካባቢው ተወላጅ በሆኑትና ባልሆኑት ላይ ከፍተኛ አድልዎ ይታያል።
No comments:
Post a Comment