Jan 3, 2013
ኢህአዴግ የአ.አ. መራጮችን A, B, C በሚል መክፈሉ አንድነት ፓርቲን አስቆጣ
በዘሪሁን ሙሉጌታ
በመጪው ሚያዚያ ወር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ የአካባቢ ምርጫ መካሄዱን ተከትሎ ኢህአዴግ የአዲስ አበባ መራጮችን በሦስት
መክፈሉ የአንድነት ፓርቲን አስቆጣ።
ኢህአዴግ በበኩሉ ከ2002ቱ የተለየ አዲስ የምርጫ ስትራቴጂ ግብ እንደሌለው አስታውቋል። ምርጫው በሕዝቡ ዘንድ ተአማኒነቱን ጠብቆ እንዲሄድ አባላቱን
በተለያየ መንገድ እያነቃነቀ መሆኑን ግን አልካደም።
ቀደም ሲል ለ2002ቱ ምርጫ ኢህአዴግ የገነባው የምርጫ ሰራዊት (አንድ ለአምስት) አደረጃጀት እንዳለ ቢሆንም ግንባሩ በተለይ የአዲስ አበባ መራጮች በሦስት
ደረጃ በመክፈል ለአባላቱ አዲስ ቅፅ አሳትሞ ማሰራጨቱ ታውቋል። በየቀበሌው የተበተነው ቅፅ መራጮቹን ‘‘ኤ’’፣ ‘‘ቢ’’ እና ‘‘ሲ’’ በሚል በመክፈል የምርጫ
ቅስቀሳው በዚሁ ቅደም ተከተል የሚፈፀም መሆኑን የሚያመለክት ነው።
‘‘ቅፁ በእጃችን ገብቷል’’ ያሉት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ አስራት ጣሴ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ቅፁ የኢህአዴግ አርማ
ያለበት ሆኖ የቀበሌውን ስም፣ መዝጋቢውን፣ የመራጩን ስምና የሚኖርበትን ቀበሌ፣ የቤት ቁጥር የተመዘገበበት ቀን የመሳሰሉትን መጠይቆች የያዘ መሆኑን
ገልፀዋል። ቅፁን በመያዝ የኢህአዴግ አባላት ሕዝቡን መመዝገብ መጀመራቸውን ገልፀዋል።
በቅርቡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የማኀበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት አቶ ሙክታር ከድር በስራቸው የሚገኙ 22 የመንግስት ሚኒስቴር
መስሪያ ቤቶችንና ኤጀንሲዎች ላይ ግምገማ ካካሄዱ በኋላ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች አንድ ለአምስት መደራጀት እንዳለባቸውና አደረጃጀቱም በሦስት
ዘርፎች እንደሚሆን መግለፃቸው፣ እነዚህም ሶስት ዘርፎች የኢህአዴግ ዘርፍ፣ የመንግስት ዘርፍ እንዲሁም ሶስተኛው አንድ ለአምስት ከሚያደራጀው መስሪያቤት
ወይም ከኤጀንሲው ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው የህብረተሰብ ክፍል እንዲሆን መወሰኑ አቶ አስራት አስታውሰዋል።
ለምሳሌ የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በአንድ ለአምስት አደረጃጀት በኢህአዴግ ዘርፍ፣ በመንግስት ሰራተኛ ዘርፍ ከተደራጁ በኋላ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር
ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ተማሪዎችና ወላጆች መሆናቸው በመጥቀስ ኢህአዴግ የአደረጃጀት አካሄድ ሀገሪቱን የአንድ ፓርቲ ስርዓት ከማድረግ ባለፈ በመንግስትና
በኢህአዴግ መዋቅር መካከል ያለው ልዩነት ተደምስሷል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።
ኢህአዴግ በሚያዚያ ወር በሚካሄደውም ምርጫ መሰረት በማድረግ መራጮችን በሶስት መክፈሉ ምርጫውን ይበልጥ ያወሳስበዋል ያሉት አቶ አስራት ‘‘ኤ’’፣ ‘‘ቢ’’
እና ‘‘ሲ’’ የሚለው መዋቅራዊ አካሄድም የመራጩን ስነ-ልቦና የሚነካ እንደሆነም ነው የገለፁት።
በስትራቴጂው መሰረት በ‘‘ኤ’’ ስር የሚመደቡ መራጮች በአስተማማኝ ኢህአዴግን የሚመርጡ በመሆኑ ከእነዚህ መራጮች ላይ ብዙ መስራት አያስፈልግም፣
በ‘‘ቢ’’ ስር የተፈረጁ ደግሞ በኢህአዴግ እና በተቃዋሚ መካከል የሚዋልሉና መጠነኛ ቅስቀሳ የሚካሄድባቸው ሲሆን በ‘‘ሲ’’ ስር የተፈረጁ መራጮች ደግሞ ሙሉ
በሙሉ ተቃዋሚ የሚመርጡ በመሆኑ የበለጠ መስራት የሚል እንደሆነ ተጠቁሟል።
የኢህአዴግ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተመስገን ጥላሁን ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ግንባሩ ለአዲሰ አበባ አስተዳደር እና በመላው ሀገሪቱ ለሚካሄደው የአካባቢው
ምርጫ የተለየ የምርጫ ስትራቴጂ እንደሌለው ተናግረዋል። ምርጫው በሕዝቡ ዘንድ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና በሕዝቡ ዘንድ ተአማኒ እንዲሆን ግንባሩ እየሰራ
እንደሆነም አረጋግጠዋል። ግንባሩ በምርጫው ስኬታማ ለማድረግ ነባር መዋቅሩን መሰረት በማድረግ አባላቱን እያነቃነቀ መሆኑን በመግለፅ ስብሰባ እየመሩ
በመሆኑ በቀጣይ ጊዜ ወስደው በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚሰጡበት ገልፀዋል።
ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment