Pages

Jan 3, 2013

ኢሳያስ አፈወርቂ በጦር ወንጀለኝነት ሊጠየቁ ይገባል ተባለ


ር ያ ዕቆብ ኃይለማርያም ኢሳያስ አፈወርቂ “በጦር ወንጀለኝነት ሊጠየቁ ይገባል” አሉ። የፖለቲካ ኢኮኖሚ
ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው “የኢትዮጵያ መንግስት ኢሳያስን እና የጦር ጀኔራሎቹን በጦር
ወንጀለኝነት ሊከሰው የሚችልበት ዕድል አለ” ይላሉ።

በፋኑኤል ክንፉ
የኤርትራው ፕሬዝደነት ኢሳያስ አፈ ወርቂ ያቀረቡት የሰላም ድርድር ጥያቄ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ያለቅድመ ሁኔታ እደራደራለሁ ማለቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
በተለይ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጋር በተያያዘ በሃይደር ት/ቤት ላይ የተፈፀመው የቦንብ ድብደባ እና በምርኮ በተያዙት በኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ላይ የተፈፀመው ሰብዓዊነት የጎደለው አያያዝ በጀኔቫ የጦር ወንጀል ስምምነት መሠረት ኢሳያስ አፈወርቂና የጦር ጀኔራሎቻቸው በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ መሆኑ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች እየጠየቁ ነው፡፡
በዓለም አቀፉ ሕግ ከፍተኛ ባለሙያና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለጽት፤ “የጦር ወንጀለኝነትን በተመለከተ በጄኔቫ ኮንቬንሽን የሠፈሩ ሁለት ፕሮቶኮሎች አሉ፡፡ በእነዚህ ፕሮቶኮሎች ትንታኔ ውስጥ የጦር ወንጀል፣ የሚያስከትለው ክስ በፍትሐብሄርና በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ፣ ከጦርነት ቀጠና ውጪ ስለሆኑ ሰዎች እንዲሁም የጦር ምርኮኞችን በተመለከተ በዝርዝር ሰፍሯል፡፡ ከፕሮቶኮሎቹ ስንነሳ በሃይደር ት/ቤት በአስመራ መንግስት የተፈፀመው የቦምብ ድብደባ በግልፅ ከጦርነት ቀጠና ውጪ የተፈፀመ የጦር ወንጀል መሆኑ ግልፅ ሆኖ እናገኛዋለን፡፡”
አያይዘውም “የኰሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ የጦር ምርኮኛ ሆነው ከተያዙ በኋላ የተፈፀመባቸው ሰብአዊነት የጐደለው አያያዝ የጄኔቫ የጦር ምርኮኞች ፕሮቶኮል መሠረት በጦር ወንጀል የሚያስከስስ ነው፡፡ ፕሮቶኮሎቹ ወንጀልና ካሳን ለይተው ነው የሚያስቀምጡት፡፡ ካሳን በተመለከተ የአልጀርሱ የድንበር ኮሚሽን ስምምነት እና የሄግ ፍርድ ቤት ውሣኔ ሰጥተውበታል፡፡ ለኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ዶላር ሲቆረጥላት፣ ኤርትራ 100 ሚሊዮን ዶላር ተወስኖላታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ለሃይደር
ት/ቤት ተብሎ የተሰጠ የካሳ ክፍያ አለ፡፡ ይህ ግን በፍትሐብሔር የተፈፀመ የካሳ ክፍያ እንጂ በተማሪዎቹ ላይ ስለተፈፀመው የጦር ወንጀል የተሰጠ ብይን አይደለም፡፡ የፍርድ ውሣኔ ግን በፍትሐብሔር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሃይደር ት/ቤትን በተመለከተ የተከፈለ የገንዘብ ክፍያ መኖሩን የፍርድ ውሣኔ ሰነድ ቢያሳይም፤ የወንጀል ድርጊቱን በተመለከተ ያለው አንዳች ነገር የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወንጀል በቅጣት እንጂ በካሳ አይታለፍም፡፡ በእስር ያስቀጣል፡፡ ስለዚህም ኢሳያስና የእሱ የጦር ጀነራሎች የፈጸሙት የጦር ወንጀል በመኖሩ ሊጠየቁ ይገባል” ብለዋል፡፡ “ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል ሀገር አይደለችም፡፡ ይህን መሰል ክስ የት ልትመሰርት ትችላለች ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤
“ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል ባትሆንም የተፈፀመውን የጦር ወንጀል የሚያሳይ መረጃ ለፀጥታው ም/ቤት በማቅረብ በኢሳያስ ላይ የጦር ወንጀል ክስ ምርመራ ማዘዣ ማስወጣት ትችላለች፡፡ ምክንያቱም የፀጥታው ም/ቤት የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤትን የማዘዝ ስልጣን አለው፡፡ ቁም ነገሩ ግን፤ ይህን የጦር ወንጀል ድርጊት በባለቤትነት የያዘውም የጠየቀውም በኢትዮጵያ በኩል አለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አሁንም በጦር ወንጀል ኢሳያስን ለመክሰስ የሚቻልበት እድል ተዘግቷል ማለት አይደለም፡፡ አሁንም ኢሳያስ አፈወርቂ በጦር ወንጀል ሊጠየቁ ይገባል” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግራዋል፡፡”
የፖለቲካ ኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው፤ “የኢትዮጵያ መንግስት ኢሳያስን እና የጦር ጀኔራሎቹን በጦር ወንጀለኝነት ሊከሰው የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ከዓለም አቀፉ ረጅም ቢሮክራሲ አንፃር ምን ያህል ያስኬዳል የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁን ያለው ነገር በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት  ወደ ሁሉን አቀፍ የሠላም ድርድር ውስጥ ለመግባት የታሰበው መስለኝ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የምትቀበለውም የምትሰጠውም ነገር ይኖራል፡፡ ችግሩ ሁለቱም ሀገሮች
የአልጀርሱን ስምምነት አለመቀበላቸው ነው፡፡ ቁምነገሩ ድርድሩ ቢጀመር በምንድነው የሚጀመረው? የድንበር ኮሚሽኑ ውሣኔ ትክክል ነው? የኢትዮጵያ መንግስት ባድመን ለኤርትራ አሳልፎ ቢሰጥ በቀጣይ ምን ዓይነት የፖለቲካ ሁኔታ ሊገጥመው ይችላል? ከ70 ሺ በላይ የሰው ህይወት የቀጠፈው ጦርነት ለምን ተጀመረ?  ለሚሉት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ሊሰጥባቸው” ይገባል ብለዋል፡፡
ዶክተሩ አያይዘውም ፤ “የጦርነቱ መጀመር የባድመ ጉዳይ አይደለም፡፡ ናቅፋ የኤርትራ ገንዘብ ሆኖ መቅረቡ ነበር፡፡ በኤርትራ ውስጥ ሶስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ነበር፡፡ ይህን ገንዘብ የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት በዶላር እንዲከፈል ጥያቄ ቢያቀርብም ውድቅ ተደረገበት፡፡ ሌላው፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ኤርትራን ለማቋቋም የሰጠው ሶስት ቢሊዮን ብር እና ለኤርትራ ንግድ ባንክ ማቋቋሚያ ተብሎ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በብድር ሰጥቶ የነበረበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡ በወቅቱ ኤርትራ ትጠቀምበት የበረውን የኢትዮጵያን ብር ወደ ናቅፋ ስትቀይረው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ነባሩን ብር በአዲስ ብር ተክቶ ስራ ላይ አዋለ፡፡ ስለዚህም ኤርትራ ውሰጥ የነበረው የኢትዮጵያ ብር ከአገልግሎት ውጩ ሆነ፡፡ ይህ በመሆኑ የኤርትራ መንግስት ንዴት ውስጥ ወደቀ፡፡ የነበራቸው ግምት  በነበረው ግንኙነት በመጠቀም ወይም በጉልበት ፍላጐታቸውን ማሳካት የሚቻል መስሏቸው ነበር፡፡ የሆነው ግን ከጠበቁት ውጪ ነው፡፡ ጠብ የተጀመረው ከዚህ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራን የሚያክል መሬት ከሰጠ በኋላ 20 ኪሎ ሜትር ለማይሞላ በባድመ መሬት ጦርነት ውስጥ ሊገባ
አይችልም፡፡ አሁንም ሊደረግ የታሰበው ድርድር ባድመን ማዕከል ያደረገ ነው ተብሎ መውሰድም ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ ኤርትራዊያን ባድመን ቢወሰዱትም የቻይና ግንብ አይሰሩበትም፡፡ ባድሜ ያለውም ሕዝብ ኤርትራዊ ነኝ ብሎ የሚያምን ቢሆን ኖሮ፤ እስካሁን የድንበር ውዝግቡ መቋጫ ያገኝ ነበር፡፡ መሬቱን ኤርትራ ትጠይቃለች፤ ሕዝቡ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ ይላል፡፡ እዚህ ላይ ነው ጨዋታው ያለው፡፡›› ብለዋል፡፡ የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ቁርሾ በእርቅ ለመጨረስ በደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫኪር በኩል በይፋ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ የኢትዮጵያ
መንግስት አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱ የተለያዩ ምንጮች መዘገባቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate