Pages

Jan 5, 2013

የክርስትና እምነት ተከታይ ለሆናችሁ የኢህአዴግ አባላት ወገኖቻችን!




By Nasrudin Ousman 
ላለፉት 12 ወራት ስናካሂድ የቆየነውን ሰላማዊ የመብት ጥያቄ እጅግ በቅርበት እንደተከታተላችሁት እናውቃለን፡፡ የህዝበ
ሙስሊሙን ጥያቄዎች ምንነት እና ህገ መንግሥታዊ መብታችንን ለማስከበር እስካሁን የተጓዝንበትን ፍፁም ሰላማዊ


አካሄድም ከእናንተ በላይ የሚያውቅ የለም፡፡ በወርኃ መስከረም “ለመጅሊስ ምርጫ ተመዝገቡ” ልትሉን በራፋችንን
ባንኳኳችሁበት ጊዜ “እስኪ አረፍ በሉ” ብለን በሰከነ መንፈስ ያዋራናችሁ የኢህአዴግ አባላት ይህንን ሐቅ አሳምራችሁ
እንደምታውቁ በአንደበታችሁ ነግራችሁናል፡፡
በጥሩ መንፈስ ስላነጋገራችሁን በምርጫው የማንሳተፍበትን ምክንያት በዝርዝር ካስረዳናችሁ በኋላ፣ ያኔ የጠየቅናችሁን
አንድ  ጥያቄ ዛሬም እናስታውሳችሁ፡ እኛ ሙስሊሞች የእያንዳንዳችሁን በር ቀብቅበን ‘በሲኖዶስ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ
ተመዝገቡ’  ብንላችሁ፣ ምን ይሰማችኋል?”  ብለናችሁ ነበር፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑና ሙስሊሙ እጅተሰባጥ  
ተከባብሮ በሚኖርባት አገራችን፣ ይበልጡንም ይህ አብሮ መኖር ጎልቶ በሚታይባት ዋና ከተማችን፣ ለዘመናት የቆየው
የመከባበር ባህል ይህንን እንድናደርግ አይፈቅድልንምና እኛ አናደርገውም፡፡ አባል የሆናችሁበት ድርጅት ኢህአዴግ ግን
የክርስትና እምነት ተከታይ የሆናችሁትን እናንተን ይህንን እንድታደርጉ አዘዛችሁ፡፡ ይህንንም በማድረግ ድርጅታችሁ
ኢህአዴግ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መካከል በክፉም ሆነ በደግ ጊዜ ለፈተናዎች ሳይበገር ፀንቶ የቆየውን
በመከባበር አብሮ የመኖር ታላቅ ኢትዮጵያዊ እሴት ገሠሠው፡፡ አዎ፣ ድርጅታችሁ ኢህአዴግ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ኢትዮጵያ
የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ተሳስበውና ተከባብረው በሰላምና በፍቅር አብረው የሚኖሩባት አገር ስለመሆኗ
እየለፈፈ፣ መሬት ላይ ግን ይህንን የመከባበርና የመተሳሰብ ታላቅ እሴት በአደባባይ ረገጠው፤ ጨፈለቀውም፡፡
ድርጅታችሁ ነገ በታሪክ ፊት በአስነዋሪነት ለሚወሳው ለዚህ ዕኩይ ተግባር ሲያሰማራችሁ፣ እናንት ወገኖቻችን የዘመንን
አጥር ለተሻገረው  ተከባብሮና ተሳስቦ የመኖር ታላቅ ኢትዮጵያዊ እሴት ጥብቅና ከመቆም ይልቅ ጊዜውን ጠብቆ ማለፉ
ለማይቀረው ኢህአዴግ ታማኝ መሆናችሁ አሳዝኖናል፡፡ ምንም እንኳ የድርጅታችሁ ኢህአዴግ ርዕዮት እንደ ግለሰብ
የምታስቡትን፣ ኅሊናችሁ የሚነግራችሁንና የምታምኑበትን እንድትሠሩ ባይፈቅድላችሁም፣ መቼም ሰው ናችሁና አንዳንድ
ጊዜ “ምን እየሠራሁ ነው?” ብላችሁ ከኅሊናችሁ ጋር መነጋገር እንዳለባችሁ እኛ ልናስታውሳችሁ አይገባም፡፡ … ስለዚህ
ጉዳይ በስፋት እና በጥልቀት ብንወያይ ምንኛ በወደድን! … ነገር ግን ያንን ለማድረግ በቂ ጊዜ የለንም፡፡ ስለዚህ፣ ከፊት
ለፊታችን ስለተደቀነውና በእኛ እምነት ለአገራችን ሰላምና መረጋጋትም ሆነ ለህዝባችን ተሳስቦና ተከባብሮ የመኖር እሴት
አደጋ ስለሆነው የነገው ድርጅታዊ ተልዕኳችሁ ብንነጋገር ይሻላል፡፡
… ዘግይተን እንደሰማነው፣ ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በመጣ ትዕዛዝ በአዲስ አበባ የምትገኙ በርካታ የክፍለ ከተማና
የወረዳ ኢህአዴግ፣ እንዲሁም የ“ደኅንነት”  አባላት በነገው ዕለት የሚካሄደውን የህዝበ-ሙስሊሙ ሰላማዊ ተቃውሞ
በመስጊድ ውስጥና በዙርያው በሰጋጁ ህዝበ-ሙስሊም ውስጥ ሰርጋችሁ በመግባት እንድታስተጓጉሉ የቤት ስራ
ተሰጥቷችኋል፡፡ …
በዚህ ዙርያ አንዳንድ መሠረታዊ ሐቆችን ብንነግራችሁ መልካም መስሎ ታይቶናል፡፡ … በመጀመርያ እንደከዚህ ቀደሞቹ
ሁሉ ይህኛውም የቤት ስራችሁ እጅግ አስነዋሪና በታሪክ ፊት አንገትን በሚያስደፋ መልኩ እንድትታወሱ የሚያደርጋችሁ
ነው፡፡ ሁለተኛ፣ በከፍተኛ ቁጥር ወደ መስጂዶቻችን እንድትመጡ ኃላፊነት ከማይሰማቸው የመንግስት ባለሥልጣናት
የተሰጣችሁ ተልዕኮ ለአገራችን  ሰላምም ሆነ ለተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ተከባብሮ መኖር ምን ያህል አደጋ እንደሆነ ልብ

እንድትሉት እንፈልጋለን፡፡ ከእነዚህም በላይ ግን በዋነኝነት ይህን ትዕዛዝ ለመፈፀም የምትሰማሩ ወገኖቻችን በሙሉ
ከእምነታችን ጋር በጥብቅ የተቆራኘና በሀቅ ላይ የተመሠረተ ህጋዊ የነፃነት፣ የመብትና የፍትኅ ጥያቄ ያነሳነው
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለእንዲህ ዓይነት ዕኩይ ሤራዎች ፈጽሞ የማንንበረከክ መሆኑን እንድታውቁ እንፈልጋለን፡፡
...  እኛ ሁከትና ብጥብጥ ፈፅሞ አንፈልግም፡፡ ይህንን ባለፈው አንድ ዓመት በተግባር አሳይተናችኋል፡፡ በትንኮሳ
ወጥመዶች ውስጥ ላለመውደቅም እጅግ እንጠነቀቃለን፡፡ ነገር ግን ሁከት ይቀሰቀሳል በሚል ፍራቻ ስለመብታችን ከመጮህ
መቼም ቢሆን ወደኋላ ላንል ተማምለናል፡፡ ይህ ለእኛ የሃይማኖት፣ የእምነት ብሎም የሰብአዊ ክብራችን ጉዳይ ነው፡፡
ባለፈው
የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በድርጅታችሁ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ትዕዛዝ በሃይማኖታችንና በመስጂዶቻችን፣
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ በርካታ ነውሮችና ድፍረቶች ሲፈፀሙ እያየንና እየሰማን ለአገራችን ሰላም ስንል
ነገሮችን በከፍተኛ ትዕግስት አሳልፈናል፡፡ ይህንን ያደረግነው ግዴለም እኛ እየታሠርንም፣ እየተገደልንም፣ እኛ ግለሰቦቹ
እየተዋረድንም፣ እንደ ባዕድ እየተደበደብንም፣ እኛው በኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን አስፀያፊ ስድቦች እየተሰደብንም፣
የአገራችን ሰላም ሳይናጋ ለጋራ  ሃይማኖታዊ ጥያቄያችን በሰላማዊ መንገድ እንታገል ብለን ስለወሰንን ነው፡፡ ይህ የሰላም
ፈላጊነት አቋማችን በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ያለፈ ሲኾን፣ እነሆ ዛሬም አጥብቀን እንደያዝነው አለን፡፡
…  እያንዳንዳችን የምንጮኸው ከራሳችን በላይ ለሆነ ታላቅ ዓላማ ነው፡፡ በእርግጥም የሃይማኖታችን ክብር ከእኛ
ከግለሰቦቹ በላይ ነው፡፡ አባቶቻችንና አያቶቻችን ይህንን ሃይማኖት  በከፍተኛ መስዋዕትነት በክብር አቆይተውልናል፡፡
…  ታዲያ እኛ የሃይማኖት፣ የእምነትና የአስተሳሰብ ነፃነት በህገ መንግስት ተረጋግጧል በሚባልበት በዚህ ዘመን
የሃይማኖታችን፣  የእምነታችንና የመስጂዶቻችን ክብር ሲደፈር ዝም እንድንል ትጠብቃላችሁን?! … በፍፁም ይህንን ከእኛ
አትጠብቁ!
… የተከበራችህ የክርስትና እምነት ተከታይ የኢህአዴግ አባላት ወገኖቻችን ሆይ፣ ኃላፊነት በጎደለውና ከእብሪት በመነጨ
ስሜት ለነገ የተሰጣችሁን “መስጊዳቸው ውስጥ ዘልቃችሁ በመግባትና በመካከላቸው በመሰግሰግ የተቃውሞ
ትዕይንታቸውን አስተጓጉሉ”  የሚል ትዕዛዝም ሆነ፣ በሌላ ጊዜ የሚሰጧችሁን መሰል ትዕዛዛት ለመፈፀም ስትሰማሩ
ስለድርጅታዊ
ታማኝነት ብቻ ሳይሆን፣ ስለአገራችን ሰላምም፣ በየዘመናቱ አያሌ ፈተናዎችን አልፎ ዛሬ ላይ ስለደረሰው አብሮነታችንም፣
እንደኢህአዴግ ሳይሆን፣ እንደዜጋ አስቡ፡፡ እውነቱን ማወቅ ከፈለጋችሁ አንድ በግልጽ የሚታወቅ ሐቅ እንንገራችሁ፤ ከእኛ
መካከል ብዙዎች ትናንት የኢህአዴግ ደጋፊ ነበሩ፡፡ ብዙዎቻችን “ፍፁም ባይሆንም፣ ኢህአዴግ ጥሩ ድርጅት ነው” ብለን
እናምን ነበር፡፡ … የአህባሽ አጀንዳን ይፋ ባደረገበት በሐምሌ 2003  ግን “ኢህአዴግ ምን ነካው?!”  ብለን መጠየቅ
ጀመርን፡፡ የአህባሽ አጀንዳውን በመቃወማችን “ጥቂት አክራሪዎች” ሲለን ግን፣ … በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብቶ እያቦካ
በፕሮፖጋንዳ ህዝባችንን ለማሳሳት መወሰኑን ስናውቅ ግን፣ … “ጥቂት አክራሪዎች በኢትዮጵያ እስላማዊ መንግሥት
ለመመስረት ያልማሉ” በሚል ቅጥፈት ክርስቲያኑ ወገናችን እኛን በጥርጣሬ እንዲያየን አልሞ መንቀሳቀሱን በዉል ስንረዳ
ግን … በቃ የእውነትን መንገድ ይዘን ሐሰትን በሰላማዊ መንገድ ልንታገላት ተማማልን፡፡ …
…. ውድ የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ሆይ! እናንተስ ስለምን ከሐሰት ጎን ትሰለፋላችሁ?! መጽሐፍ ቅዱስ
“እውነትም አርነት ያወጣችኋል!”  ይል የለምን?! …  ከኢህአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዲስኩር ይልቅ፣ ይህ ታላቅ
እውነት አይደለምን?! … ለምን ነገሮችን  ሁሉ በኢህአዴግኛ ብቻ ታያላችሁ?! እናንተ ሰብአዊ ፍጡራን አይደላችሁምን?!
…  አንዳንድ የማይካዱ እውነቶችን እንደሰው፣ እንደ ጥሩ ክርስቲያን ብታስቡ መልካም አይደለምን?! … እባካችሁ፣
ኢህአዴግ ከመሆናችሁም ጋር …  ሰው ሁኑ፡፡ ለዘመናት በጉርብትና አብረን ስንኖር በቅርበት የምታውቁንን እኛን፣
ኢህአዴግ ‹‹ጥቂት አክራሪዎች››  የሚል ስያሜ የሰጣቸው ጭራቅ አድርጎ ስለሳለባችሁ ብቻ ያልሆንነውን ሁነን

አንታያችሁ፡፡ ይህ ለእናንተም፣ ለእኛም ለአገራችንም አይበጅም፡፡ … የሰማያትና የምድር፣ በመካከላቸው ያለውም ሁሉ
ፈጣሪ የሆነው ኃያል ጌታችን አላህ (ሱ.ወ.)  ቸር ያሳስበን፡፡ …  ኢትዮጵያንና መላ ህዝቧንም ኃያሉ    ፈጣሪያችን
ከተንኮለኞች ተንኮል ይጠብቃት፡፡
አሚን፡፡
ከነስረዲን ዑማን

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate