Pages

Jan 5, 2013

አዲሱ የሃይማኖት ህግና የሃገሪቱ ህገመንግስት


አዲሱ የሃይማኖት ህግና የሃገሪቱ ህገመንግስት

constitution and religionአዲሱ የሃይማኖት ህግና የሃገሪቱ ህገመንግስት (በሰለሞን)
መንግሥት ሕገ-መንግስቱን ሊያከበር ይገባል! (ከእምነት ቤቶች)
በጉዳዩ ላይ እንድንወያይ ስንጠየቅ ይህ  የሃገረቱን ህገመንግስት ይቃረናል እኛም እዚህ ተወክለን የመጣነው ለሌላ ጉዳይ እንጂ በህግ ላይ ህግ ለማውጣት አይደለም ብለን አጀንዳው እንዲመለስ አድርገናል ፡፡(ከተስብሳቢዎች አንዱ)
በስራ ላይ የዋለውን እንደ አዲስ ለማጸደቅ በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ ውይይት እንዲደረግ የእምነት ተቌማት የጋራ ጉባኤ ላይ ቀርቦ ነበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አይመለከተኝም ብላ ወጥታ ነበር ቀጥሎም የኢትዮጵያ እስልምና ጽህፈት ቤትም አይመለከተኝም ብሎ ነበር፡፡ በመጨረሻምወንጌላዊያን ይህ ህግ እነርሱ ላይ ተፈጻሚ ሆኖ የቆየ ቢሆንም በህግ መልክ እንደገና ሲቀርብ ግን ተገርመውበታል፡፡
“ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መርጠው በላኳቸው ተወካዮቻቸው አማካይነት ሕዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስትን በአዋጅ ቁጥር 1/1987 ያጸደቁት” ሕገ መንግሥትን መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት እየጣሰ መሆኑን የሀገሪቱ የተለያዩ ህብረተሰቦችና ተቋማት መናገር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡
በቅርቡ ደግሞ “በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተዘጋጀ የሃይማኖት ድርጅቶች እና ማኅበራትን” አስመልክቶ የወጣው “መመሪያ” የተጠቃሻቹ የሃይማኖት ድርጅቶች እና ማኅበራትን በበቂ ሁኔታ ሃሳባቸው ሳይሰማና በማያውቁት ሁኔታ ሥራ ላይ በማዋሉ ምክንያት የሃይማኖት ድርጅቶችና ተቋማትን  በተለይም ደግሞ የክርስትና እምነት ተከታዩ ኅብረተሰቡን በእጅጉ የማጉረምረሚያ ሃሳብ ከመሆን አልፎ መንግሥት መመሪያውን በድጋሚ እንዲያስብበት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያና ሃይማኖት የአምስት ሳንቲም ግልባጮችና ፈጽሞ ሊለያዩ የማይችሉ መሆኑን መንግሥት በ1997 ዓ.ም ያወጣው እስታስቲክስ 62.8 ከመቶ ክርስቲያን፣ 33.9 ከመቶ ሙስሊም ፣ 2.7 ከመቶ ባህላዊ እምነት ተከታይ ፣ 3.3 ከመቶ ሌሎች  እና ስለ እምነታቸው መልስ ያልሰጡ ደግሞ 0.6 ከመቶ መሆኑን ባሳየው እስታስቲካዊ መረጃ አረጋግጣአል፡፡ ይህ እስታስቲካዊ አሃዝ እንደሚያሳየው በሀገሪቱ ውስጥ ያለእምነት የሚኖር ከቁጥር የማይገባና መሆኑንና በአጠቃላይ በሃገሪቱ የሚኖሩ ዜጎች 100 ፐርሰንት ሃይማኖተኛ እንደሆኑ ያሳያል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን ማለት ሃይማኖተኛ የበዛባት ሃገር ማለት ሳትሆን ራሷ ሃይማኖት ማለት ናት ብንል የምንሳሳት አንሆንም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሃይማኖትን አስመልክቶ የሚያወጣቸው መመሪያዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ የታከለበትና ከሕገመንግሥቱ ሃሳብ ጋር የማይቃረን ማድረግና በሕገ መንግስቱ ውስጥ የተገለጡትን ሃይማኖታዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊኑን ካልተወጣ ሀገሪቱን ወዳልታሰበ ቀውስ ውስጥ ሊከታት ይችላል ብለው ያሳሰባቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 27 በግልጽ ለሕዝቡ ያረጋገጠለትን ተፈጥሯዊ የሃይማኖት ነጻነቱን ወንጀል እስካልፈጸሙ ድረስ ሊያከብርለትና ሊያስከብርለት ይገባል እንጂ ሊሸራርፍ የሚችል ሕግ ወይም መመሪያ ሊያወጣ በምንም መልኩ ሕገመንግስታዊ መሠረት የለውም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከረቂቂነት አልፎ የሃገሪቱ መመሪያ በመሆን ሥራ ላይ የዋለው የሃይማኖት ድርጅቶችንና ማኅበራትን አስመልክቶ የወጣው መመሪያ በሚኒስቴሩ መስራቤት የተዘጋጀ መሆኑንና መጠቀሻውም “የሃይማኖት ድርጅቶችን እና ማኅበራትን ለመመዝገብና ተዛማጅ አገልግሎቶችን ለመስጠት የወጣ መመሪያ ቁጥር 1/2005 ተብሎ ሊጠቀስ” እንደሚችል “ክፍል አንድ ጠቅላላ” ከሚለው አንቀጽ ሥር በንዕስ አንቀጽ ሁለት ላይ ይናገራል፡፡ ይሄው መመሪያ በዘጠኝ ክፍል ተከፋፍሎ 45 አንቀጾች ያሉት ሲሆን በእያንዳንዱ አንቀጽ ሥር ከ 2-15 ንዑስ አንቀጾችን ያቀፈ ነው፡፡
ወደዚህ መመሪያ ዝርዝር ይዘቱ ከመምጣታችን በፊት በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 11 “የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት” በሚለው አንቀጽ ሥር ንዑስ አንቀጽ 1-3 የተቀመጠውን ብንመለከት “መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡” በሚል በግልጽ መንግስትና ሃይማኖትን የማይገናኙ በሀገሬ አባባል “አራንባና ቆቦ” እንደሆኑ ይናገራል፡፡
እንደገናም ይሄው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 27 “የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነጻነት” በሚለው አንቀጽ ሥር ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የተቀመጠው ብንመለከት “ማንኛውም ሰው የማሰብ ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነጻነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ የመከተል የመተግበር የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡ በአንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ  2 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ(ስለአስኮላ ትምህርት ቤት የትምህርት ይዘታቸው በሚመለከት የሚናገር አንቀጽ ነው) የሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችላቸው የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋም ይችላሉ” ይላል፡፡(ጽሑፉን ያወፈርንና ያሰመርንበት ልብ ይሉት ዘንድ እኛው ነን)
እንደገናም አንቀጽ ዘጠኝ በ “ሕገ መንግስት የበላይነት” በሚለው አንቀጽ ሥር ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ “ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሃገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡” በሚል ተቀምጧል፡፡ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፋዊ ሕጎችና ቃልኪዳኖች እኤአ የ 1966 የሲቪልና የፓለቲካ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ቃልኪዳን ስምምነቶች ውስጥ ሃይማኖታዊ መብትን እውቅና ይሰጣል፡፡
ስለዚህ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 5 በግልጽ እንደተቀመጠው “መንግሥት ሃማኖትና እምነትን የመግለጽ መብትን ሊገድብ የሚችለው የሕዝብን ደህንነት፣ ሰላም፣ ጤናና ትምህርት፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ የሌሎችን ዜጎች መሠረታዊ መብቶች፣ ነጻነቶች እና መንግሥት ከሃይማኖት ነጻ መሆኑን ለማረጋገጥ” ካልሆነ በቀር በምንም መልኩ የሃይማኖትን የትምህርትና የአስተዳደር ተቋማዊ ቅርጾቻቸውን ሊወስንላቸው፣ ደንብ ሊቀርጽናቸውና እኔ በምፈልገው መልኩ ተደራጁ ሊላቸውና ሊወስንላቸው በመካከላቸውም ጣልቃ እየገባ እንደ ዳኛ ሊሆን አይችልም፡፡
ይሁን እንጂ መመሪያው እነዚህን ተፈጥሯዊና ሕገ መንግስታዊ የሃይማኖት መብት ክፉኛ የሚጥስ ብቻ ሳይሆን ዕውቀት ጎደል መሆኑ ጭምር ጥቂት ክፍሎችን ብቻ ለዋቢነት እየጠቀስን እንመልከት፡፡
በአንቀጽ 5 የሚንስቴሩ ስልጣንና ተግባር በሚለው ርእስ ሥር በንዑስ አንቀጽ 2 ላይ “በድርጅቶቹ ወይም በማኅበራቱ በሚቀርብ ደንብ ላይ የማሻሻል አስተያየት መስጠት፣ ማጽደቅና መመዝገብ” የሚንስቴሩ ሥልጣንና ተግባር እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህ ማለት ሃይማኖታዊ ድርጅቶችም ሆኑ ማኅበራት በሚኒስቴሩ ለመመዝገብ በሚቀርቡበት ወቅት እነርሱ ከሚከተሉት ሃይማኖታዊ  አስተምህሮ አንጻር የቀረጹትን ደንባቸውን ከመቀበልና ከመመዝገብ ይልቅ ሚኒስቴሩ ደንባቸውን እርሱ በሚፈልገው መሰረት እንዲያሻሽሉ ሃሳብ ያቀርብባቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህ “የማሻሻያ አስተያየት መስጠት” የሚለው ቃል ሚኒስቴሩ ለሃይማኖት ተቋማቱ የሚያቀርበው “የማሻሻያ አስተያየት” ምን አይነት አስተያየት እንደሆነ ግልጽ ያልሆነ፣ ገደብ የሌለው በራሱ ህሊናና በራሱ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረተ በመሆኑ ለራሱ የሚመች ሃሳብ አቅርቦ ደንባቸውን ቀርጸው እንዲያመጡ ሊያስገድዳቸው የማይችልበትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶችንና ማኅበራትን ወደፈለገው መስመር ለማስገባት የሚገድበው አይደለም፡፡
ይህም አንድ ሃይማኖት የሚከተል ተቋም ወይም “ሃይማኖታዊ ድርጅትና ማኅበራት” ባቀረቡት ደንብ ላይ ካስተካከለና ከጠመዘዘ አለዚያ ያቀረበላቸውን “አስተያየት” አንቀበልም ካሉ መመዝገብ እንደማይችል ከገለጸ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 እና 27 ንዑስ አንቀጽ 2 የተቀመጠውን በተለይም ደግሞ መንግሥት በሃይማኖት ትምህርትና በአስተዳደር ተቋማት ላይ አይገባም የሚለውን ይጥሳል ማለት ነው፡፡
ሃይማኖታዊ ድርጅትም ሆነ ማኅበር የሚወለደው የሃይማኖቱ ተከታዮች ከሚያምኑበት ሃይማኖታዊ እሳቤና ምንጭ አንጻር በመሆኑ እምነትና ማኅበር ወይም ሃይማኖትና ድርጅታዊ አወቃቀር የአንድ አካል  ክፍሎች በመሆኑ በመነጣጠል በተለይም ደግሞ እነርሱ የሚተዳደሩበት ደንብ ቀርጾ ማውጣትም ይሆን ባወጡት ላይ “የማሻሻያ አስተያት” እንዲቀበሉ ማድረግ መንግሥት ሃይማኖት ውስጥ አልገባሁም የሚልበት ምክንያት አይኖረውም፡፡ ስለዚህም “የማሻሻያ አስተያየት” ከሰጠበት ደቂቃ ጀምሮ ሕገ መንግስቱን ይጥሳል ማለት ነው፡፡
ሌላው በዚሁ በአንቀጽ 5 የሚንስቴሩ ስልጣንና ተግባር በሚለው ርእስ ሥር በንዑስ አንቀጽ 9 ላይ “ሞዴል መተዳደሪያ ደንቦች የማዘጋጀት” ስልጣንና ተግባር የሚኒስቴሩ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህ ደግሞ የሃይማኖት ድርጅቶችም ይሁኑ ማኅበራቱ ደንብ ይዘው ሲመጡ “የማሻሻያ አስተያየት” ከመስጠት አልፎ ደንብ የሚያዘጋጅላቸውም እራሱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ “ሞዴል መተዳደሪያ ደንብ” ማለት እርሱ በሚፈልገው መልኩ የተቀረጸ ይዘት ያለው ሆኖ የተዘጋጀ ማለት ነው፡፡
በመሆኑም ደንብ የየሃይማኖቱ ከሚከተሉት እምነት አንጻር ለራሳቸው የሚመች የሚያወጡትና የሚከተሉት እንጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሃይማኖት ተቃማትና መተዳደሪያ ደንብ ማውጣትና መቅረጽ አይችልም፡፡ የመንግሥት ሚና የፖለቲካ ወይም ሃይማኖቶች ራሳቸው በራሳቸው እንዲዋቀሩና እንዲመሩ መንገድ መክፈት እንጂ ደንብ የመቅረጽና በሚፈልገው መልኩ እንዲያምኑና እንዲዋቀሩ ማድረግ አይደለም፡፡
ሌላው በዚሁ በአንቀጽ 5 በንዑስ አንቀጽ 10 ላይ ሚኒስቴሩ ባወጣው በዚሁ መመሪያ መሰረት “ለሚሰጣቸው ለምዝገባና ተዛማጅ አገልግሎቶች ክፍያ እንደሚያስከፍል” ያናገራል፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 6 በንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ደግሞ “ህጋዊ የምዝገባ ፈቃድ ሳያገኝ በምስረታ ላይ እያለ ከመስራች አባላት በስተቀር ህዝብን በመጥራት ሃይማኖታዊ ስብሰባ ማካሄድ ማስተማር ወይም መስበክ እና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችን መፈጸም አግባብነት ባለው ሕግ የሚያስጠይቅ ይሆናል” ይላል፡፡ በመሆኑም መክፈል ሳይችሉ ቀርተው መመዝገብ ያልቻሉ ሃይማኖቶች በግልም ይሁን በቡዱን ሃይማኖታቸውን ማራመድ፣ መስበክ፣ መሰብሰብ፣ ማስተማር ወይም ሌላ ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ድርጊት መፈጸም እንደማይችሉ የሚናገር ብቻ ሳይሆን ይህን ያደረጉ ድሆች ሃይማነተኞች በሕግ የሚጠየቁ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ተፈጥራዊና ሕገ መንግስት የሰጣቸውን አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 በግልም ይሁን በቡድን በመሆን በይፋ የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብታቸውን በመንጠቅ ሕገ መንግሥቱን ይጥሳል ማለት ነው፡፡
በሌላ መልኩም ይህ አንቀጽ 6 በንዑስ አንቀጽ 5 የተቀመጠው  “ህጋዊ የምዝገባ ፈቃድ ሳያገኝ በምስረታ ላይ እያለ ከመስራች አባላት በስተቀር ሕዝብን በመጥራት ሃይማኖታዊ ስብሰባ ማካሄድ ማስተማር ወይም መስበክ እና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችን መፈጸም አግባብነት ባለው ሕግ የሚያስጠይቅ ይሆናል” የሚለውን ስንመለከት አንድ የግል እምነት ያለው ዜጋ የሚያምነውን እምነት ለሌሎች በመስበክ በማስተማርና ተከታይ በማፍራት ወደ ሃይማኖታዊ ማኅበርነት ስለማይቀየር ሃይማኖቱን በነጻ የመግለጽ ብሎም የማስፋፋት ተፈጥሯዊና ሕገ መንግስታዊ መብቱን ያፍናል ይገድባል፡፡ እርሱን ብቻ አይደለም በንዑስ አንቀጽ 6  ደግሞ ይሄ እንደማኅበር መመዝገብ ደረጃ ላይ ያልደረሰ ዜጋ እርሱ ለሚያደርገው የመስበክ የማስተማር ወይም ሌሎች ሃይማኖታዊ ድርጊት “የደገፈና መሰል ትብብሮችን ያደረገ ማንኛውም ሰው በተመሳሳይ አግባብነት ባለው ሕግ የሚጠየቅ” እንደሚሆንም መመሪያው ይገልጻል፡፡ ይህም ሕገ መንግሥቱን ሳይጥሱ ጤናማ ሃይማኖታዊ ሥራ ሲያካሂዱና ሲደግፉ የነበሩትን በወንጀል መጠየቅ ከሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች መንፈስ የሚጻረርና ወንጀል ባልተፈጸመበት ወንጀል እንደመፍጠር ነው፡፡
እንዲያውም ሃይማኖታዊ ድርጅቶችና ማህበራት ዓለማቀፋዊ ግንኙነት ለማድረግና ምቹ መንገድ እንዲኖራቸው ራሳቸው ከማሳብ አንጻር ሊመዘገቡ ወደ ሚኒስቴሩ ይሄዳሉ እንጂ ካልተመዘገባች ሃይማኖት አይደላችሁም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ እስካልጣሱ ድረስ ሊከለከሉ አይገባም፡፡
ሌላው ይሄው መመሪያ በአንቀጽ ሰባት “አደረጃጀት” በሚለው ሥር በንዑስ አንቀጽ 1 ላይ “ማንኛውም የሃይማኖት ድርጅት ወይም ማኅበር በመተዳደሪያ ደንብ መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ፤ የስራ አስፈጻሚ / አመራር ቦርድ ፣ ስራ አስኪያጅ / ፕሬዝዳንት ፣ ዳይሬክተር ፣ ኦዲተር ፣ ሂሳብ ሹምና ሌሎች እንደድርጅቱ ወይም ማኅበሩ አደረጃጀት አስፈላጊ የሆኑ የሥራ ክፍሎች ሊኖሩት ይገባል ይላል፡፡” ይህም የሃይማኖት ድርጅቶችና ማኅበራት ከሚከተሉት እምነትና ከመንፈሳዊ መርህ አንጻር አደረጃጀታቸውን ያወጣሉ እንጂ መንግሥት አደረጃጀታቸውንና የስልጣን ተዋረዳቸውን እንዲሁም የማዕረግ ስሞቻቸውን ሊያወጣላቸው አይችልም፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ብንወስድ ሃይማኖቷዊ ቀኖናዋና የራሷ ሕገ ቤተክርስቲያን እንደሚያዘው ቀድሞ በፓትሪያሪኩ የበላይ ጠባቂነትና አመራር ሰጪነት በኋላም ተሻሽሎ  በብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ምልአተ ጉባዔ እንድትመራ ከወሰነችበት እለት ጀምሮ አሁን በዚሁ እየሄደች ያለችን ቤተክርስቲያን ፣ ወደ ፊትም ቤተክርስቲያኗ እንደ ቀኖናዋ መሰረት እንዳመቻትና ለራሳ በምታምነው አደረጃጀትና አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርግታ ብትሄድ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እንደ ሃይማኖት ድርጅት ወይም ማኅበር ተዋቅረሽ ጠቅላላ ጉባኤ፤ የስራ አስፈጻሚ / አመራር ቦርድ ፣ ስራ አስኪያጅ / ፕሬዝዳንት ፣ ዳይሬክተር በሚል መዋቅር ውስጥሽን ካላደራጀሽ ሃይማኖት አይደለሽም ሊላት እንደሆነ ይሄው መመሪያ ያስረዳል ማለት ነው፡፡
ይህ መመሪያ የያዘው እነዚህ ስያሜዎች ማለትም ጠቅላላ ጉባኤ፤ የስራ አስፈጻሚ / አመራር ቦርድ ፣ ስራ አስኪያጅ / ፕሬዝዳንት ፣ ዳይሬክተር ፣ ኦዲተር ፣ ሂሳብ ሹምና ሌሎች ተብለው የተቀመጡት መዋቅራዊ ስያሜዎች  በራሳቸው “ዓለማውያን” ቋንቋዎችና ትርጓሜዎች ያሏቸው እንጂ ሐይማኖታዊ ቋንቋዎች ለመሆናቸው በራሱ አነጋጋሪ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ሌላም እንደምሳሌ የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናትን ይዘትና አወቃቀር ብንመለከት አንዱ ቤተክርስቲያን ከሌላው በመሰረታዊ ክርስትና አስተምህሮ አንድ ቢሆንም በአስተዳደራዊ አወቃቀሩ ግን የተለያየ ሲሆን አንዳንዱ በ “ሐዋርያዊ አመራር” የሚያምንና የተዋቀረ ሌላው  በ “ሽማግሌያዊ አስተዳደር” የሚያምንና የተዋቀረ ሌላው ደግሞ በ “ፓስተራል አስተዳደር” የሚያምንና የተዋቀረ ወዘተርፈ በመሆኑ እነዚህን በአንድ አስተምሯቸውን ተከትሎ ካዋቀሩት አስተዳደራዊ አደረጃቸት አውጥቶ እንደልማት ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ፤ የስራ አስፈጻሚ / አመራር ቦርድ ፣ ስራ አስኪያጅ / ፕሬዝዳንት ፣ ዳይሬክተር ብላችሁ ተደራጁ ብሎ በ “ማሻሻያ ሃሳቡ” ጠምዝዞ ካላዋቀራቸው አትመዘገቡም እንደሃይማኖትም መንቀሳቀስና ማስተማር መስበክ አትችሉም ሊል እንደሚችል በግልጽ ያሳያል፡፡  ይህም  “መንግስት በሃይማኖት አይገባም” የሚለውንና “የሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችላቸው የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋምይችላሉ” የሚለውን በአንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 2 የተቀመጠውን የራሳቸውን መብት በመንጠቅ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር መሠረታዊ ስህተት መሆኑን ያሳያል፡፡
ለነገሩ ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ይህ አዲሱ መመሪያ ከመውጣቱም በፊት በነበረው መመሪያ መሠረት እንደልማት ተቋማትና ድርጅት ይመዘገቡና ስራቸው ሃይማኖታዊ ይሁን ልማታዊ ሳይታወቅ የስራና የሂሳብ ሪፖርታቸውን እንዲሁም የቀጣይ የበጀት ዓመት የሥራ እቅዳቸውን ጭምር ካላቀረቡ በቀር የሥራ ፈቃድ ስለማያገኙ ይህን ለማቅረብ ይገገደዱ ነበር፡፡ መንግስትም የሃይማኖት የስራ ሪፖርትና እቅድ የበጀት አስተዳደራቸውንም ጭምር የማየትና የመቀበል በውጭ ኦዲትርም እንዲመረመሩ የማድግ ምንም ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን የሌለው ቢሆንም ለረጅም ዘመናት ሲያካሂድባቸው ኖሯል፡፡ ይህም መንግስት በሃይማኖቶች ውስጥ በትምህርታቸውም ሆነ በአስተዳደር ስልጣናቸውና አወቃቀራቸው ውስጥ ገብቶ እንደነበረ በሚንስትሩ የሃይማኖትና የእምነት ዳሬክቶሪት የተጨናነቁ መዝገብ ቤትን ማየት በቂ ምስክር ነው፡፡ በዚህም በመንግስት ጣልቃ ገብነትና የአወቃቀር ውሳኔ ምክንያትና የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት እርስ በርሳቸው በመዋቅሩ እንዳይስማሙ የመካሰስ የመለያየት እንዲሁም አላግባብ የቤተዘመድ አመራር እንዲፈጥሩ ወዘተ ጭምር ተገደው እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላው መነሳት ያለበት ነጥብ በዚሁ መመሪያ በአንቀጽ 3 “ትርጓሜ” በሚለው ሥር በንዑስ አንቀጽ 6 ላይ “መንፈሳዊ አገልጋይ ወይም ሰባኪ ወይማ ዳኢ ማለት በሃይማኖት ድርጅቶቹ ወይም ማኅበራት ውስጥ እውቅና ኖሯቸው በክፍያ ወይም ያለክፍያ የሃይማኖት ትምህርት የሚያስተምሩ ወይም የሚሰብኩ አገልጋዮችን ያጠቃልላል፤” ይላል፡፡ እዚህ ላይ መመሪያው በየሃይማኖታዊ ድርጅቶችና ማህበራት ውስጥ ያሉትን ልዩ ልዩ ስያሜዎችና የአገልግሎት ማዕረጋትን በአንድ መጠቅለሉና መጥራቱ መሠረታዊ ስህተት ነው፡፡ ይህ ጠቅልሎ የመጥራት ሥራና ኃላፊነት የየሃይማኖቱ ድርጅቶችና ማኅበራት ተግባርና ሥልጣን እንጂ እንዴትስ እንዲህ ብሎ መጠቅለልና መጥራት ይችላል? የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ በዚሁ መመሪያ አንቀጽ 13 “የውጭ ዜጎችን ማሰማራት”  በሚለው አርእስት ሥር ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ  ሃይማኖታዊ ድርጅቱ ወይም ማኅበሩ “ ያሰማራው የውጭ ዜጋ ከመጣበት ዓላማ ውጪ በመንቀሳቀስ ለሚፈጽመው ጥፋት በተናጠልና በጋራ በሀገሪቱ ህግ ተጠያቂ ይሆናል” የሚለው ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ፈረንጅ ከሃይማኖታዊ ተቃሙ ወይም ማህበሩ ጋር በመሆን መንፈሳዊ ሥራ ለመስራት ተስማምቶ በመግባት መንፈሳዊ ሥራው ጋር ባልተገናኘ ሁኔታ ባለው ትርፍ ጊዜም ሆነ በግሉ ሌላ ወንጀል ቢሠራ ለፈጸመው ወንጀል ተቋሙ ወይም ማኅበሩ በወንጀል መጠየቁ አግባብ አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ ድርጅቱ ወይም ማኅበሩ ላለው ሃይማኖታዊ ተግባር ተስማምቶ አሰማራው እንጂ ሌላ የግል ስህተቱን ሁሉ ተቋሙን ወይም ማኅበሩን አይመለከትም፡፡
በአንቀጽ 18 “የተከለከሉ ተግባራት” በሚለው ርእስ ሥር ንዑስ አንቀጽ 8 ደግሞ ብንመለከተው መመሪያው ሌላ አስገራሚ ነገርንም ይዟል፡፡ “ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳያገኙ ከአምልኮ ቦታ ውጪ ሰዎችን በማሰባሰብ ባልተፈቀደ ቦታ የሃይማኖት ትምህርት ማስተማር ወይም መስበክ” በንዑስ ቁጥር 12 ደግሞ ከሌሎች ጋር “አብሮ መስራት” ፣  በንዑስ አንቀጽ 13 ደግሞ “የሃይማኖት ተግባርን ከበጎአድራጎት ዓላማና ተግባር ጋር ቀላቅሎ መሥራት” ይከለክላል፡፡
ይህም ማለት እንደምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነትና አስተምህሮን  ብናይ ለረዥም ዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የህዝቡን የቤት ለቤት ጽዋ ማህበራት ያለፈቃድ ሰብስቦ እንደወትሮው ማስተማር መስበክና ሃይማኖታዊ ተግባራት መፈጸም ይከለክላል ማለት ነው፡፡ ቄሱም የነፍስ ልጆቻቸው ከአምልኮ ቦታ (ከቤተክርስቲያን ቅጥር ጊቢ) ውጭ ሰብስቦ ቢሰብክ ቢያስተምር በሕግ ያስጠይቀዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የአደባባይ ክብረ በዓላትንም ጭምር ያለ መንግስት ፈቃድ እንደወትሮ ቢያካሂዱ መሰብሰብ በዓላቱንም ማካሄድ አይችሉም ማለት ነው፡፡ ይህን ሃይማኖታዊ ነጻነታቸውን ከሚመለከተው የመንግስት ቢሮ ሄደው “ይሁንታ” ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ካላገኙም ቀረ ማለት ነው፡፡
ወደ ካቶሊኩም ወደ ወንጌላውያኑም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ይገጥመዋል፡፡ ከተፈቀደላቸው የአምልኮ ቤቶች  (ይህም ተከራይተው የሚያመልኩበትን ቤት ያካትት አያካት መመሪያው ግልጽ አያደርግም ) ውጭ የቤት ለቤት ጸሎት ፕሮግራሞች፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የጥናት ፕሮግራሞች በሀዘንና በደስታ ወቅትም በሚያደርጉት የቤትና የድንኳን አገልግሎቶች ሁሉ የተከለከሉ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
ሌላው ሃይማኖት የሚወልደው ለሌሎች በጎ የማድረግ የመደገፍ ተግባር ነጥሎ እናንተ እንደ ሐይማኖት መጸለይ ብቻ ይገባችኋል እንጂ ሃይማኖትን ከምግባር አታቀላቅሉ ብሎ የሚገልጸው መመሪያ ለክርስቲያኑ ህብረተሰብ “ተርቤ አብልታችሁኛል ፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛል፣ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋል ብሎ ጌታ በመጨረሻ  በማቴወስ ወንጌል 25፡34-46 እንደተገለጸው የሚጠይቀውን ቃልና “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” የሚለውን የያዕቆብ መልእክት ምዕራፍ 2፡18-26ን የእምነት መሠረት የሚጥስ አሊያም ነጣጥሎ በዚህ መልኩ ሥጡ ብሎ ያለ እምነት መሰረታቸው አካሄድ መግለጹ ሲሆን ለእስልምና እምነት ተከታይም ከአምስቱ የእስልምና ማእዘናት ውስጥ በሦስተኛ ደረጃነት “ዘካት” መስጠትን የሚከለክል ወይም ይህንን እንዴት መፈጸም እንደሚገባቸው ከሐይማኖታዊ አስተምህሯቸው ውጪ መንግስት መመሪያ እየሰጠ በመሆኑ መንግሥት ሕገ መንግስቱን ጥሶ በሐይማኖት ጣልቃ መግባቱን ያሳያል ፡፡
እንግዲህ ሕዝቡ ይህ ሃይማኖትን በነጻነት የመቀበል፣ በግልና በጋራ የማራመድ የማስፋፋትና የማደራጀት ሕገ መንግስታዊ መብቱን የገፈፈው መመሪያ ለውይይት ለመጀመሪያ ጊዜ መንግስት የሃይማኖት ተቋማትን በጠራና ሃሳቡን በገለጸ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን “አይመለከተኝም” ብላ ስብሰባውን ረግጣና ጥላ እንደወጣች ካቶሊክም “እኔ አለም አቀፋዊ አወቃቀር እንጂ ብሔራዊ ብቻ ስላልሆንኩ አለም አቀፋን ቤተክርስቲያኗን ጠይቁ” ብላ ጥላ እንደወጣች፣ እስልምናም በተመሳሳይ “አይመለከተኝም” ብለው ሲወጡ ጥቂት ፕሮቴስታንት አካላት ብቻ ቆይተው የመንግሥትን ይህን ሃሳብ እንዳዳመጡ የውስጥ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የእምነት  ተቋማት ባይቀበሉትም ቅሉ መመሪያው ጸድቆ እንደመመሪያ እየተተገበረ ሲሆን ብዙዎችን ግራ እያጋባ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ሕገመንግስቱ ሐይማኖቶችን “ሃይማኖት” ይላቸዋል እንጂ እንደዚህ መመሪያ ድርጅቶችና ማኅበራት ብሎ የማይጠራቸው ከመሆኑ ጀምሮ ማንኛውም ሃይማኖት እምነቱን ለመግለጽና ዓለማቀፋዊ ግንኙነት ለመፍጠር እንጂ የእምነት ነጻነቱን ለማስፈቀድ ወደየትም መሄድ አያስፈልገውም፡፡ እምነት ዲሞክራሲ ያጎናጸፈው ስጦታ ሳይሆን የዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ሳይፈጠር ከሰው ማንነት ጋር የተገጠመ ተፈጥሯዊ በመሆኑ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ መግባቱን አቁሞ ሕገ መንግስቱን ሊያከብር ይገባዋል፡፡ በሃይማኖት ሽፋን ለሚደረጉ ወንጀሎች ካሉ ራሳቸው የሃይማኖት ተቋማቱ እንደዜጋ እንዲከላከሉ ሕገ መንግስቱን ማሳወቅና እንጂ በውስጣቸው ገብቶ አስተዳደራቸውን የመቆጣጠር የመምራት ወዘተ ተግባር አቁሞ ሕገ መንግስቱን ሊያከብር ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate