Pages

Apr 14, 2013

በደል እንዴት ይረሳል!!


አማኑኤል ኦጋላ የህይወትን  ለዛም ይሁን መዘዝ ገና በዉል ለይቶ ያላወቀ የ14 አመት ልጅ ነዉ። እህቱ ማጂን እሷም ብትሆን ወንድሟን አመት ከመንፈቅ ትብለጠዉ እንጂ ገና ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ዉብ የአኝዋክ ኮረዳ ናት። ማጂን አጎጠጎጤ ጡቶቿና  ፈገግ ባለች ቁጥር ምሽቱን ወደ ንጋት የመለወጥ ችሎታ ያላቸዉ ነጫጭ ጥርሶቿ በአጭር ሊቀጫት ታጥቆ የመጣን የአግአዚ አዉሬ  ቀርቶ መሽቶበት እቤታቸዉ ያደረ ቤተዘመድንም ያባብላሉ። ማጂን መልኳ ብቻ ሳይሆን በትምህርቷም የላቀ ዉጤት የምታመጣ ጎበዝ ተማሪ ናት። ታናሽ ወንድሟ አማኑኤል ደግሞ ትምህርት ለሱ ብቻ እሱም ለትምህርት የተፈጠረ የሚመስል ጓደኞቹ “ቀለሙ” ብለዉ የሚጠሩት እጅግ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነዉ። በከፊል እርሻና በከብት ርቢ የሚተዳደሩት ወላጆቻቸዉ አቶ ኦጋላ ኦሞትና እናታቸዉ ወይዘሮ አቻላ የትምህርትን እሴት ጠልቀዉ የተረዱ ሰዎች ስለሆኑ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የተረፋቸዉን ጥሪት እንዳለ የሚያፈስሱት በሁለቱ ልጆቻቸዉ ትምህርት ላይ ነዉ። አማኑኤልና ማጂን ተወልደዉ ያደጉባት ፖቻላ እነዚህን ወንድምና እህት የምታዉቃቸዉ በትምህርት ጉብዝናቸዉ፤በታዛዥነታቸዉና በቤ/ክርስቲያን አገልግሎታቸዉ ነዉ . . . . . በእርግጥም አማኑኤልና ማጂን የፖቻላ ቤተል ወንጌላዊት ቤ/ክርስቲያን ወጣት መዝምራን ናቸዉ።

ግን አማኑኤልና  ማጅን ወጣትነታቸዉ፤ጉብዝናቸዉ፤ዝማሬያቸዉ፤ የወደፊት ተስፋነታቸዉና ሁሉም ነገራቸዉ እንዳለ በነበር ቀርቷል። እነዚህን ድፍን ፖቻላና አካባቢዉ ዬት ይደርሳሉ ብሎ በተስፋ ይጠብቃቸዉ የነበረ ወንድምና እህት ዛሬ ማንም የሚያስታዉሳቸዉ ሰዉ የለም። ወላጆቻቸዉም በነበር ቀርተዋልና አማኑኤልንና ማጂን አባትና እናታቸዉም አያስተዉሷቸዉም። የአኝዋክ ህዘብ በባህሉ ልጆቹን አይረሳም፤ በአኝዋክ ባህል ደግሞ ልጅ የሚባለዉ መንደርተኛዉ ሁሉ ነዉ። ሆኖም የወያኔ ዘረኞች አኝዋክን የቀሙት መሬቱን ብቻ ሳይሆን ባህሉን፤ ወጉንና የንግግር መብቱን ጭምር ስለሆነ አኝዋክ ወያኔ የጨፈጨፋቸዉን ልጆቹን ባሰበና በዘከረ ቁጥር የእሱም ዕጣ ፋንታ መጨፍጨፍ ስለሆነ ለግዜዉም ቢሆን ሙታን ልጆቹን መዘከር አቁሟል።
ታህሳስ አራት 1996 ዓም ዕለቱ ቅዳሜ ነበር። ቅዳሜ ቅዳሜ አማኑኤል፤ እህቱ፤ አባቱና እናቱ ቤታቸዉ ዉስጥ የሚሰራ ካለ የየድራሻቸዉን እየሰሩ፤ እያወጉ፤ እየበሉና እየጠጡ አንድ ላይ የሚሆኑበት ግዜ ነዉ። የነአማኑኤል ቤተሰብ ዕለተ ቅዳሜ ታህሳስ አራትን ያሳለፈዉ ይህንኑ የተለመደዉን የቤተሰቡን ልማድ ተከትሎ ነበር። የምሳ ሰአት ሲደርስ ቤተሰቡ ምሳ አንድ ላይ በላና አማኑኤልና ማጂን የመዝሙር ልምምድ ስላለባቸዉ ወደ ቤ/ክርሲቲያን ሄዱ። ወላጆቻቸዉ ደግሞ  አንዱ ቤት ሲያጸዳ ሌላዉ የተሰበረ እየጠገነ ሁለቱም በየግል ስራቸዉ ላይ አተኮሩ።
ቀኑ እያጠረና እየመሸ በሄደ ቁጥር . . . .  ዛሬ ልጆቹ ምን ነካቸዉ እያሉ ከመስጋርት በቀር የአማኑኤልና የማጂን ወላጆች ልጆቻችንን እንደገና አናይም የሚል ጥርጣሬ አጠገባቸዉም አልነበርም። ሁለቱ ልጆቻቸዉም ቢሆኑ የመዝሙር ልምምዳችንን ጨርሰን መቼ አባዬና እማዬጋ እንሄዳለን የሚል ጉጉት እንጂ ወላጆቻቸዉንና ያቺን ያደጉባትን ጎጆ እንደገና አናይም ብለዉ አስበዉም አያዉቁም ። አማኑኤልና ማጂንም ሆኑ ወደዚህ አለም ያመጧቸዉ ወላጆቻቸዉ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት አረጋገጥኩ ብሎ የማለላቸዉ የወያኔ አገዛዝ አኝዋክ ስለሆኑ ብቻ ተወልደዉ እንዳደጉበት እንደ ጋምቤላ ጫካ ጨፍጭፎ ያጠፋናል ብለዉ በፍጹም አልጠረጠሩም።
የፖቻላ ቤቴል አማኑኤል ቤ/ክርስቲያን ፓስተር ሁሌም እንደሚያደርጉት ቅዳሜ ታህሳስ አራት 1996 ዓም ቢሯቸዉ ገብተዉ ስራቸዉን እየሰሩ ነዉ። ትኩረታቸዉ በነገታዉ እሁድ ስለሚያሰተምሩት ሰንበት ትምህርት ቢሆንም ከተዘጋዉ በር ጀርባ የሚመጣዉ የመዝሙር ቃና ቀልባቸዉን የሳበዉ ይመስላል። ፓስተር ኡጁሉ የተቀመጡበት ወንበር ላይ አንደገና ተደላድለዉ ተቀመጡና . . . . .  መዝሙሩን ነገ መስማቴ አይቀርም ምነዉ ስራዬን ብጨርስ ብለዉ አይናቸዉንም ሃሳባቸዉንም መ/ቅዱሳቸዉ ላይ አደረጉ። የቤ/ክርስቲያኑ አዳራሽ ዉስጥ አማኑኤል፤ ማጂና ጓደኞቻቸዉ የመዝሙር ልምምዳቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ። ፓስተር ኡጁሉም መዝሙሩን ነገ እሰማለሁ ባሉት ዉሳኔያቸዉ ፀንተዉ የሰንበት ትምህርት ዝግጅታቸዉን ተያይዘዉታል። “ሁሉን ነገር በተስፋ ጠብቁ” የሚለዉን የፈጣሪ ቃል አምነዉ ነገን በተስፋ የሚጠባበቁት ፓሰተር ኡጁሉ የእሳቸዉ ነገ ከዛሬ እንደማያልፍ የሚያመልኩት ፈጣሪ አልነገራቸዉም እሳቸዉም ያወቁ አይመስልም።
ፓስተር ኡጁሉ የሰንበት ትምህርት ዝግጅታቸዉን እንደጨረሱ ወደ በቤታቸዉ ከመሄዳቸዉ በፊት ሁሌ እንደሚያደርጉት መንገዳቸዉን ለእግዚአብሔር አምላካቸዉ አደራ ለመስጠት ተንበረከኩ። ከፓስትር ኡጁሉ አፍ የመጀመሪያዉ የፀሎት ቃል ሲወጣና የቤ/ክርስቲያኑ የፊት ለፊት በር ተበርግዶ የወያኔ ታጣቂዎች እግዚአብሔር በሚመለክበት ቦታ ላይ መሳሪያቸዉን ሲያቀባብሉ የወጣዉ ድምጽ አንድ ላይ ተሰማ። ክላሺንኮቭ ጠመንጃቸዉን የደገኑ አራት ወታደሮች እጃቸዉ ላይ መ/ቅዱስ ብቻ የያዙትን ፓስተር ለፀሎት ከተንበረከኩበት አስነስተዉ ማዋከብ ጀመሩ . . . . . እኔኮ የእግዚአብሄር አገልጋይ ፓስተር ነኝ . . . .  አሉ ወያኔ የሚፈልጋቸዉ ፓስተር በመሆናቸዉ ሳይሆን አኝዋክ በመሆናቸዉ መሆኑን ያልጠረጠሩት ፓስተር ኡጁሉ። ክላሺንኮቭ በታቀፉ የወያኔ ነፍሰ ገዳዮች የተከበቡት የፓስተር ኡጁሉ  ፊት አሁንም ፈገግታ አልተለየዉም፤  ከፊታችዉ የሚነበበዉ ትህትናና እግዚአብሄር ያስተማራቸዉ ፍቅር እንጂ ጥላቻና ፍርሃት እንዳልሆነ በግልጽ ይታያል። . . . . . .  ቅደም አንተን ነዉ የምንፈልገዉ አለ . . . .  የአማርኛ ቃላት አደራደሩ የትግራይ ተወላጅ መሆኑን የሚያሳብቅበት የነፍሰ ገዳይ ቡድኑ መሪ። ፓስትር ኡጁሉ ከተንበረከኩበት ሳይነሱ . . .  እሺ ምንም ችግር የለም ሂድ ወዳላቸሁኝ ቦታ ሁሉ እሄዳለሁ ግን እባካችሁ ፀሎቴን ልጨርስ ግዜ ስጡኝ ብለዉ የቡድኑን መሪ ለመኑት። የሚሰማህ ካለ ጸልይ አላቸዉና ጓኞቹን ይዞ ወደ ዉጭ ወጣ።
ፓስተር ኡጁሉ ቀና ብለዉ ሲመለከቱ የቤ/ክርስቲያኑ ግማሽ ተቃጥሎ እሳቱ እሳቸዉ ወዳሉበት እየመጣ ነዉ። ክፋትና ጭካኔ መታወቂያ ካርዳቸዉ የሆነዉ የአግአዚ ነፍሰገዳዮች ቤ/ክርስቲያኑ ላይ ቦምብ ከወረወሩ በኋላ የፓስተሩን መጨረሻ ለማየት በርቀት ተደርድረዉ ቆመዋል። የእሳቸዉ ህይወት ሳይሆን የወጣት መዘምራኑ ህይወት ያሳሰባቸዉ ፓስተር በእሳቱ መሀል ሮጠዉ መዘምራኑ የነበሩበት ክፍል ሲደርሱ የክፍሉን ዉስጥና ዉጭ መለየት አቃታቸዉ። ያ ለአመታት የእግዚአብሄርን ቃል ያስተማሩበት ቤ/ክርስቲያን ተቃጥሎ የቀረዉ ነገር ቢኖር እሳቱ ለብልቦ ያለፈዉ አልፎ አልፎ የቆመዉ ማገር ብቻ ነበር። ከሚቃጠለዉ እሳት ዉስጥ እንደሚመዘዝ ሀረግ እየተንቦገቦገ የሚወጣዉ ወላፋን ለብልቦ የፈጃቸዉ  ፓስተር ኡጁሉ እራሳቸዉን ለማዳን እየሮጡ የቤታቸዉን አቅጣጫ መፈለግ ጀመሩ። ሆኖም ብዙም ሳይጓዙ አድፍጦ ይጠባበቃቸዉ የነበረዉ የወያኔ ገዳይ ቡድን የ41 አመቱን ፓስተር በሳንጃ ከታተፏቸዉ። ከአንድ ሳምንት በኋላ የሟቾች አስክሬን ከየቦታዉ ሲሰበሰብ የፓስተር ኡጁሉ አስከሬን የተለየዉ አጠገባቸዉ በነበረዉ ወርቃማ መስቀልና በጋብቻ ቀለበታቸዉ ነዉ እንጂ ወያኔማ እንኳን በአይን በዘመናዊ መሳሪያም ማንነታቸዉ እንዳይተወቅ እንደ ክትፎ ነበር የከተፋቸዉ።
ከወያኔ አልሞ ተኳሾች ጠመንጃ አፈሙዝ የሚወጠዉ ባሩድና ጭስ ከተፈጥሮ መዐዛ ዉጭ ሌላ ምንም ሽታ የማያዉቀዉን የፖቻላን አየር በክሎት አፋንጫ ማሽተት አይን ማየት ተስኖታል። አማኑኤልና መዘምራን ጓደኞቹ ሽሸት ከያዙ ግማሽ ሰዐት ያለፈ ሲሆን የአማኑኤል እህት ማጂና ሌሎቹ መዘምራን አንድ ላይ ሲሆኑ አማኑኤል ግን ከእነሱ ጋር አልነበረም። ከምሽቱ አስራሁለት ሰዐት ተኩል ሲሆን አካባቢዉን ሲያስስ የነበረዉ የወያኔ ገዳይ  ቡድን መዘምራኑ የተሸሽጉበትን ቦታ ከበበ። ወዲያዉ ከመዝሙር ዉጭ መፈክር እንኳን ከአንደበታቸዉ ወጥቶ የማያዉቀዉን ወጣቶች ጨካኞቹ የወያኔ ወታደሮች በሰደፍና በቆመጥ መደብደብ ጀመሩ። የአማኑኤል እህት ማጂን ዱላ ሰዉነቷ ላይ አላረፈም፤ ሆኖም ማጂን የወያኔን ባለጌ ወታደሮች ፀባይ ሰምታለችና ሴት እሷ ብቻ በመሆኗ ሰዉነቷ በፍርሀት መንቀጥቀጥ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ማጂን የፈራችዉ ደረሰ። አንድ የወያኔ ወታደር እጇን ይዞ እየጎተተ ወደ ሰዋራ ቦታ ይዟት ሄደ::  ወንድ የማታዉቀዉ ማጂን አንድ፤ ሀለትና ሦስት እያለ ተራ በተራ የሚመጠዉን የወያኔ አዉሬ ማስተናገዱ ታያትና እግሯም ልቧም አንድ ላይ ከዷት። መራመድም መተንፈስም አቃታት። እንደእናቷ ተድራ ወግ ማዕረጓን ለማየት ትጓጓ የነበረችዉ የማጂን  የሴትነት ክብርና ንጽህና ህግና ስርዐት በማያዉቁ ህግ አስከባሪዎች ረከሰ።
መዝሙር ልምምድ ብላ ከቤቷ የወጣቸዉ የአስራ አምስት አመቷ ማጂን እራሷን ስታ እራቁቷን መሬት ላይ ተጋድማለች።  የወያኔ ወንጀለኞች አንዱ ሱሪዉን እየታጠቀ ሲመለስ ሌላዉ ሱሪዉን እየፈታ ይመጣል፤ ያልጠገበዉ ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር ይመላለሳል። ገና ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰችዉ የ15 አመቷ ኮረዳ ማጂን እንደ ዘጠና አመት አሮጊት ሰዉነቷ እራሱን መሸከም አቅቶት ተልፈሰፈሰች፤ አነባች፤ አማጠች። መታጠቢያ ቤት ዉስጥ የቆመ ሰዉ እስከትመስል ድረስ ሰዉነቷ ላብ በላብ ሆነ። ግማሽ ሰዉነቷ በላብ ግማሹ በደም የተለወሰዉ ማጂን እራሷን ስታ በድን መሰለች።
ከአንድ ሰአት በላይ ሾክ ባለ ቁጥር ጉድባ ለጉድባ እየተደበቀ ሲሸሽ የቆየዉ አማኑኤል በድንገት ሳያዉቀዉ ከቀኑ 11 ሰአት ጀምሮ ሲሸሽና ሲደበቅ ከነበረዉ የወያኔ ነፍሰ ገዳይ ቡድን ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጠ። አማኑኤል  በጠመንጃዉ ጋጋታና የገዳይ ቡድኑ አባላት በሬድዮ በሚያደርጉት ንግግር ቢደናግጥም እራሱን እንደገዛ የአግአዚ መንጋ ጦር መሀል ጸጥ ብሎ ቆመ።  ያ ፓስተር ኡጁሉን “የሚሰማህ ካለ ጸልይ” ብሎ ያማተበዉ የገዳዮቹ ቡድን መሪ . . . . . .  ሂድና ከጓደኞችህ ጋር ተቀላቀል ብሎ እንደመብረቅ ጮኸበት። አማኑኤል ወደ ኋላዉ ዞሮ ሲመለከት መዘምራን ጓደኞቹ መሬት ላይ አንገታቸዉን ደፍተዉ ተኮልኩለዋል፤ እህቱ ማጂን ግን ከእነሱ ጋር አልነበረችም። አማኑኤል ሁለት እጆቹን እራሱ ላይ አድርጎ ……ማጂንስ? ብሎ ሲጮህና የመጨረሻዉን የወያኔ ባለጌ ማስተናገድ የተሳናት እህቱ ማጂን ጣረሞቷን ስትጮህ ድምጹና ድምጿ ገጠመ። . . . .  ቁጭ በል አንተ ከልቢ……. ብሎ የአግአዚዉ አለቃ ክላሺንኮቩን አቀባበለ። አማኑኤል ግን የእህቱን የማጂንን የጣረሞት ድምጽ እንጂ የአግአዚን ትዕዛዝ ከቁብም አልቆጠረዉምና እየሮጠ የታላቅ እህቱን ድምጽ ወደሰማበት አቅጣጫ ሄደ።  ማጂን  በባለጌ ጓደኞቹ ስትደፈር እንደ ኢቲቪ ድራማ ቁጭ ብሎ ሲመለከት የነበረዉ የአግአዚ ወታደር ከተቀመጠበት ተነሳና አማኑኤል ላይ የጥይት እሩምታ አዘነበበት። ታላቅ እህቱን አድናለሁ ብሎ ሩጫ የጀመረዉ አማኑኤል እህቱ እግር ስር የመጨረሻዉን አየር ተነፈሰ። በጅግንነት የተጀመረዉ የወጣት አማኑኤል አጭር ታሪክ በጀግንነት ተደመደመ፤ . . . . . . ንታ ጓል ወዲእያ . . . . .  ብሎ የገዳይ ቡድኑ መሪ ንግግሩን ሳይጨርስ አማኑኤልን የገደለዉ ወታደር ክላሺንኮቩ ላይ የተሰካዉን ሳንጃ ነቅሎ የማጂንን ጭንቅላትና ሰዉነት ለያየዉ። ምነዉ በገደሉኝ ብላ ስትጮህ የነበረችዉ ማጂን የወንድሟ የአማኑኤል ነፍስ የሰማይን በር ሳያንኳኳ ልድረስበት ብላ ተከተለችዉ።በአንድ አመት ተኩል ተለያይተዉ ወደዚህ አለም የመጡት አማኑኤልና ማጂን በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት እቺን አለም ለቅቀዉ ሄዱ። ፖቻላን ለቅቀዉ ወደሚቀጥለዉ መንደር ለመሄድ በዝግጅት ላይ የነበሩት የወያኔ ወታደሮች የጥይት ድምጽ በአካባቢዉ እንዲሰማ ስላልፈለጉ የተቀሩትን የመዘምራን ቡድን አባላት ተራ በተራ ለድግስ አንደሚታረድ በሬ በቢለዋ አረዷቸዉ። ለሁለት አመት የፖቻላ ቤተል ቤ/ክርሲቲያንን በመዝሙር ያገለገሉት ወጣቶች አንዱ የሌላዉን ስቃይ እየተመከተ አንድ በአንድ የወያኔ ሳንጃ እራት ሆኑ።
የሁለት ልጆቻቸዉ አለወትሮዉ መዘግየት ያሳሰባቸዉ የአማኑኤልና የማጂን ወላጆች አቶ ኦጋላና አና ወይዘሮ አቻላ ጎጇቸዉ ዉስጥ ቁጭ እንዳሉ አንዱ ሌላዉን በዝምታ ይመለከታል። አይኖቻቸዉ በተቁለጨለጩ ቁጥር አፋቸዉ ትንፍሽ ባይልም አይናቸዉ ግን አንዱ ሌላዉን . . . . .. እንዴ ሂድና ልጆቹን ፈልግ እንጂ የሚል ይመስላል። በቤተሰብ ፍቅር የሞቀችዉ የነአማኑኤል ጎጆ በድንገት በተፈጠረዉ ፍርሀትና ጥርጣሬ ቀዘቀዘች። አማኑኤልና ማጂን የሄዱት ለመዝሙር ልምምድ ወደ ቤ/ክርስቲያን ስለሆነና ደግሞም ሁለቱን ጨዋ ልጆቻቸዉን የመንደሩ ሰዉ ሁሉ እንደራሱ ልጅ ስለሚሳሳላቸዉ ወላጆቻቸዉ ለግዜዉ ቢሰጉም ዬት ገቡ ብለዉ ነዉ እንጂ ፖቻላን በመሰለ ሰዉም ከብቱም የመሸበት በሚያድርበት ሠላማዊ መንደር ዉስጥ አማኑኤልንና ማጂንን የሚጎዳ ፍጡር ይኖራል ብለዉ በፍጹም አልጠረጠሩም፤ . . . . . . ግን . . . . ምሽቱ ወደ ሌሊት በተለወጠ ቁጥር ስጋታቸዉና ጥርጣሬያቸዉ እየጨመረ መጣ፤ ደግሞም ወላጅ ናቸዉና የሁለቱም ልብና አይን ልጆቻቸዉን ለማየት ተርገበገበ። ሲከፋቸዉ እምባቸዉ የሚቀድመዉ ሆደ ቡቡዉ  አቶ ኦጋላ ባለቤታቸዉን ላለማስደንገጥ ለሰአታት አምቀዉ የያዙት እምባ ከቁጥጥራቸዉ ዉጭ ሆነና ፊታቸዉን ሸፈነዉ። ወ/ሮ አቻላ ከተቀመጡበት ተነስተዉ ባለቤታቸዉን ለማጽናናት ሲሞክሩ አቶ ኦጋላ ቀድመዉ ተነሱና . . . . . አንቺ ቁጭ በይ እኔ ይዣቸዉ እመጣለሁ ብለዉ ከሰአታት በፊት ወደ ሰማይ ቤት ሩጫ የጀመሩትን ልጆቻቸዉን ፍለጋ በሩን ከፍተዉ ወጡ -
 …. እንዴ! አንቺማ እቤት ቁጭ በይ እንጂ ……ከመሸ ቤት ባዶ አይተዉምኮ አሉ የአማኑኤል አባት ባለቤታቸዉ ቤቱን ዘግተዉ ሲከተሏቸዉ አይተዉ – ተወኝ እባክህ ለምን ቤት ሁኚ ትለኛለህ?  . . . .  አብረን እንዳመጣናቸዉ አብረን እንፈልጋቸዋለን … ቤቱኮ ቆየ ባዶ ከሆነ ብለዉ ባለቤታቸዉን ተከትለዉ ወጡ።
አቶ ኦጋላና ወ/ሮ አቻላ ብዙም ሳይሄዱ ሁለት ልጆቻቸዉን አኝኮ ከዋጠ የጨለማ ሀይል ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጡ። አኝዋክን  ከገዛ መሬቱና ከገዛ ቤቱ እየጎተተ ሲገድል ያመሸዉ የወያኔ ገዳይ ቡድን እንደገና የሚገድለዉ ሲያገኝ በድን እንዳገኘ ጥምብ አንሳ ተደሰተ።    . . . . . . . . .ከመሸ ዬት ነዉ የምትሄዱት አላቸዉ አለ ያ አፉም ጠመንጃዉም መቅደም የሚቀናዉ የወያኔ ገዳይ ቡድን መሪ፤ . . . . . ልጆቻችንን ፍለጋ ነዉ የምንሄደዉ . . . .ለመዝሙር ልምምድ እንደሄዱ አልተመለሱም አሉ ወ/ሮ አቻላ ረጋ ባለና በሰከነ ድምጽ።   ወ/ሮ አቻላ መሳሪያ የታጠቀ የወገን ሀይል አገርን ከጠላት ሲያድን ነዉ እንጂ የገዛ ወገኑን ሲገድል አይተዉም ሰምተዉም ስለማያዉቁ ፊት ለፊታቸዉ የቆመዉና የሁለት ልጆቻቸዉን ህይወት የቀማዉ ነፍሰ ገዳይ ቡድን እነሱንም እንደማይምር አልገባቸዉም። ቢያዉቁማ ኖሮ እሳቸዉም እንደልጃቸዉ እንደ አማኑኤል  ወግድ ብለዉት ቢገድላቸዉም በጅግንነት ይሞቱ ነበር።
ለወያኔ መሪዎችና ለአግአዚ ነብሰ ገዳዮች እዉነት፤ርህራሄና ፍቅር ነዉ እንደ ክምር ድንጋይ የከበዳቸዉ እንጂ ሰዉን ማሰቃየትና መግደልማ የተካኑበት ስራቸዉ ስለሆነ ምንም አይሰማቸዉም። የወያኔዎች ሰዉ ካልገደሉ አገር የመሩ አይመስላቸዉም፤ የአግአዚ ገዳዮች ደግሞ ሂዱና ግደሉ ሲባሉ “ስንት እንግደል” ነዉ እንጂ ለምን እንግደል ብሎ የሚጠይቅ አዕምሮ የአብሯቸዉ ስላልተፈጠረ መግደልን አንደ ሙያ የያዙ የጫካ ዉስጥ አዉሬዎች ናቸዉ። እንግዲህ ከዚያ ፍቅር ካሞቀዉ ጎጆ ልጆቻቸዉን ፍለጋ የወጡት አባትና እናት ከእንደነዚህ አይነቱ መንታ የጥፋት ሀይል ነዉ  ጋር ነዉ በዉድቅት ሌሊት ፊት ለፊት የተፋጠጡት። አዎ! የዋሆቹ አቶ ኦጋላና ወ/ሮ አቻላ ሁለት ልጆቻቸዉን በጭካኔ የገደለዉን አረመኔ የወያኔ ሀይል ነበር ልጆቻችንን አፋልጉን ብለዉ የሚደራደሩት።
“ኑ” ተከተሉኝ . . . . . ልጆቻችሁ ወዳሉበት ቦታ ልዉሰዳችሁ አለ  .  . . . ያ ልክ እንደ ፖሊስ ዉሻ የሱን ቋንቋ የማይናገርና እሱን የማይመስል ሁሉ ጠላት የሚመስለዉ የአግአዚ ወታደር። አቶ ኦጋላና ወይዘሮ አቻላ እዉነትም ልጆቻቸዉን የሚያዩ መሰላቸዉና ያ” ቀኑን ሙሉ እንደ ከሰል ከስሎ የዋለዉ ፊታቸዉ በፈገግታ ተሞላ። የአኝዋክ ህዝብ ቃሉን አክባሪ እንግዳ አሳዳሪ ህዝብ ነዉ። በአኝዋክ ባህል ከአፍ የወጣ ቃል መከፈል ያለበት ዕዳ ነዉ። አኝዋኮች ቀልድና ጨዋታ ይወዳሉ ግን ቀልድን ከቁም ነገር አይደባልቁም። በአኝዋክ ወግና ደንብ አንድ ሰዉ አዋቂ ነዉ ተብሎ የሚከበረዉ እዉነትና ዉሸት መደባለቅ ሲተዉ ብቻ ነዉ። ለዚህ ነዉ የዋሆቹ ወ/ሮ አቻላና አቶ ኦጋላ “ልጆቻችሁን ላሳያችሁ” የሚላቸዉ የወያኔ ባንዳ ሰዉ መስሏቸዉ ኑ ልጆቻችሁ ጋ እንሂድ ሲላቸዉ ደስ ብሏቸዉ የተከተሉት። የሚቀጥለዉን የግማሽ ሰአት ያክል “የመስቀል ጉዞ” ባልና ሚስት ዬት ነዉ ቦታዉ ወይም መቼ ነዉ የምንደርሰዉ ብለዉ ሳይጠይቁ የአግአዚ ገዳዮችም አንዲት ቃል ሳይተነፍሱ አግአዚ ጠመንጃዉን ባልና ሚስት ነጠላቸዉን እንደያዙ በዝምታ መንገዱን ተያያዙት።
ሀምራዊ ቀለም እንደተቀባ ድፎ ዳቦ ሰማዩን የሞለችዉ ሙሉ ጨረቃ ምሽቱን ቀን አስመስላዋለች፤ አልፎ አልፎ የሚነፍስ አየር ድምጽ ቢሰማም ጫካዉና ቁጥቋጦዉ እንደ ሰዉ የተኙ ይመስል ፖቻላ ዉስጥ ሁሉም ነገር ዘጭ . . .  እረጭ ብሏል። አልፎ አልፎ የሚሰማ ድምጽ ቢኖር ከጀበርናዉ ጋር የእየተጋጨ የሚያቃጭለዉ የወያኔ ገዳዮች ጠመንጃ ድምጽና እንደ ገና በግ ወደ መታረጃ ቦታቸዉ የሚሄዱት ባልና ሚስት ዱካ ብቻ ነዉ።
ወ/ሮ አቻላ እግራቸዉን መሰንዘር እስኪሳናቸዉ ድረስ ሰዉነታቸዉ ዝሏል፡ ሆኖም ከአሁን አሁን ልጆቼን አያለሁ የሚል ተስፋ ጉልበት ሆኗቸዉ ባለቤታቸዉን በግማሽ እርምጃ ቀድመዉ የማያዉቁትን የማታ ጉዞ ታያይዘዉታል። እኩለ ሌሊት ሊሆን ትንሽ ሲቀረዉ መንታ መንገድ ላይ ደረሱ። በቀኛቸዉ ወንዝ በግራ በኩል ደግሞ ተከርክሞ የተሰራ የሚመስል ኮረብታ ጉብ ጉብ ብሏል። ከወንዙ ባሻገር በሩቁ አነስተኛ መንደር ይታያል። ባልና ሚስትን ለመግል አመቺ ቦታ ሲፈልጉ ያመሹት የወያኔ ነፍሰ ገዳዮች ይጠብቁት የነበረዉ ግዜ ደረሰ። ወንዙን ለመሻገር ሁለት እርምጃ ሲቀራቸዉ አቶ ኦጋላ በፍጥነት የሚጓዝ መኪና እንደገጨዉ ሰዉ ከባለቤታቸዉ ኋላ መሬቱ ላይ በፊት ለፊታቸዉ ወድቀዉ ተከሰከሱ . . . . . . . .  እኔን ይድፋኝ ብለዉ ወ/ሮ አቻላ ባለቤታቸዉን ለማንሳት ጎንበስ ሲሉ ያ የሴት ልጃቸዉን የማጂንን ሰዉነት ሁለት ቦታ የከፈለዉ የአግአዚ ሳንጃ የሳቸዉንም አናት ለሁለት ከፈለዉ።“እኔን ይድፋኝ” በዚህ ምድር ላይ የወ/ሮ አቻላ የመጨረሻዉ ድምጽ ነበር። የቤቴል ቤ/ክርስቲያን መዘምራን ቡድንን፤ፓስተር ኡጁሉን፤ ማጂንን፤ አማኑኤልንና እናቱን በአንድ ምሽት የጨፈጨፈዉ የወያኔ ነፍሰ ገዳይ ቡድን አቶ ኦጋላን የወደቁበት ቦታ ከጨረሳቸዉ በኋላ ሌላ የሚገደል አኝዋክ ፍለጋ ከወንዙ ማዶ ወዳለቸዉ መንደር አቀና። እንደ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ባህል በአኝዋክም ባህል ልጅ አባቱን እንጂ ወላጅ ልጆቹን አይቀብርም ይባላል። እድሜ ለወያኔ ዘረኞች . . . እነ አማኑኤል ግን እነሱ ወላጆቻቸዉን ወላጆቻቸዉም እነሱን መቅበር አልቻሉም ።
አንግዲህ . . . . የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ እንዴት ይረሳል እንዲህ አይነት በደል . . . . .በላ ንገረኝ እንዴት ይለመዳል የዘር ማጥፋት ወንጀል ። . . . .  እባክህ ንገረኝ በደል እንዴት ይለመዳል የሰዉ ስጋ እንደ ክትፎ ሲከተፍ  በደል እንዴት ይረሳል አኝዋክ በተኛበት በወያኔ እባብ ሲነደፍ። በደል አንዴት ይረሳል የእርሻ መሬት በሰዉ ገላ ሲደለደል  . . . . በደል እንዴት ይለመዳል አኝዋክ በቁሙ ሲገደል መሬቱን ተቀምቶ ስጋዉ በአሩር ሲነደል።  
እስኪ አስበዉ ወገኔ በደል እንዴት ይረሳል ቤተሰብ ለእልቂት ሲሰለፍ፤ እንዴት ይለመዳል በደል ባል ሚስቱ ፊት ታስሮ ሲገረፍ አባት እናትና ልጅ ለመታረድ ሲሰለፍ። እባክህ ንገረኝ በደል እንዴት ይረሳል አኝዋክ እንደበሬ ሲጠለፍ አጅና እግሩን ታስሮ ሲገረፍ . . . . . እንዴት ይለመዳል በደል ክቡር የሰዉ ገላ እንደቅጠል ሲረግፍ።
አረ ምነዉ . . . .ምነዉ አልደፈፍር አለ ልባችን አልቆርጥ አለ ሀሞታችን . . . . . እኮ ምነዉ አልሰነዝር አለ እጃችን፤ ወያኔ ዘር ለይቶ ሲፈጀን ሽብርተኛ እያለ ሲፈርጀን ተራ በተራ እየለቀመ ሊፈጀን። ምነዉ . . .  አረ ምነዉ  . . . . .  ምንድነን እኛ በሬ ነን ወይስ ጌኛ ሲረግጡን ሲገድሉን ዝም ብለን የምንተኛ። ማነሽ አንቺ . . . ማነህ አንተ አበሻ ነህ ወይስ ፈላሻ  ቱለማ ነህ ሜጫ ገፍተዉ ሲጥሉህ የማትንጫጫ እምትወቀጥ እንደሙቀጫ። እስኪ ንገረኛ ማነህ አንተ?   አደሬ ነህ ተጉለቴ ጎጃሜ ነህ ይፋቴ እባክህ ነገረኝ በሞቴ። በልኮ ንገረኝ ጉራጌ ነህ ሲዳማ፤ ሃዲያ ነህ ሱማሌ  ምንድነህ ንገረኝ ኦሮሞ ነህ ወይስ አማራ እንዳባቶችህ የማታቅራራ ።
ምንም ሁን ምን ሁሉም መልካም ነዉ . . .  ማንነትህ ግን አንድ ነዉ . . . .  ኢትዮጵያዊነት ነዉ ….አዎ! ማንነት ኢትዮጵያዊነት ነዉ
ኢትዮጵአዊነት ደግሞ  ድፍረት ነዉ
አትንኩኝ ባይነት ጀግንነት ነዉ
ኢትዮጵያዊነት  . . .   .አኝዋክ ሲገደል አላስገድል ማለት ነዉ . . . አማራ ሲፈናቀል ፈንቃዩን መፈንቀል ነዉ
አዎ! ኢትዮጵያዊነት እንደ እስክንድር ጽናት ነዉ . . .  እንደ አንዱ አለም እምቢ ማለት ነዉ
ኢትዮጵያዊነት እንደ መይሳዉ ለአገር መሞት ነዉ …. እንደ ዬኔሰዉ መስዋዕት መሆን ነዉ . .
 እንደ ዬኔሰዉ . . . . .  . እንደ ዬኔሰዉ  . . . . .  እንደ ዬኔሰዉ   መስዋዕት መሆን ነዉ!

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate