Pages

Apr 8, 2013

በቤንች ማጂ አማርኛ ተናጋሪዎችን ማፈናቀል ዳግም ተጀመረ

በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን በሚገኘው ሜኒት ወልድያ ወረዳ በተለይም ዘንባብና አርፋጅ ቀበሌ ነዋሪዎች በካከል ከ350 በላይ የአማርኛ ተናጋሪ ዜጎች ተፈናቅለው በወረዳው አካባቢ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
ማን እንዳደራጃቸው በማይታወቁ ግለሰቦች ከመኖሪያ አካባቢያቸው 61 ከብቶችና ግምቱ ያልታወቀ እህል ተዘርፈው አካባቢያቸውን ጥለው ለመውጣት የተገደዱት አማርኛ ተናጋሪ ተፈናቃዮቹ ተሸሽገው ባሉበት ጫካ ለከፍተኛ ርሃብና ውሃ ጥም መዳረጋቸውን ለፍኖተ ነፃነት ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ከተፈናቃዮች መካከልም 4 በግፍ መገደላቸውንና የወረዳው አስተዳደር አካላት “እናጣራለን” ከማለት ውጭ ምንም መልስ ባለመስጠታቸው ጉዳዩ እየባሰ በመሄዱ ንብረቶቻቸው ተዘርፈው በአሁን ወቅት ለዓመታት የኖሩበትን አካባቢ ጥለው በጫካ መጠለልን መምረጣቸውን ተፈናቃዮቹ በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡
እንደተፈናቃዮቹ ገለፃ ከሆነ በአሁን ወቅት ከወረዳው ፖሊሶች ውጭ የአስተዳደሩ አካላት በግፍ መፈናቀላችንን በተመለከተ ያላቸውን ውሳኔ እንዲያሣውቁን ብንጠይቅም ምላሽ የሰጠን ባለመኖሩ አሁንም ለከፍተኛ ችግር በመጋለጣችን የሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሽ እንዲሰጠን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
በተለይ ጉዳዩ ላይ የደቡብ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ ሁሴን በበኩላቸው “በአሁን ወቅት በክልሉ ምንም ዓይነት የአማርኛ ተናጋሪ ዜጎችን ማፈናቀል ስራ አልተካሄደም፤ የተላለፈ መመሪያም የለም፤ እንደውም በተለያየ ምክንያት ከተለያየ ቦታ ወደ ክልሉ የመጡትን እንኳ እየተንከባከብን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከተፈናቃዮቹ ጋር በተያያዘ የአማራ ክልላዊ መንግስት ያለውን አቋም ለማረጋገጥ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ወደ ሆኑት አቶ ንጉሴ ጋር ደውለን ጉዳዩን ስናነሳላቸው ስልካቸውን የጋዜጠኛው ጆሮ ላይ በመዝጋታቸው የክልሉን መንግስት አቋም ልናረጋግጥ አልቻልንም፡፡
በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል ዜጎችን የማፈናቀሉ ጉዳይ እየቀጠለ በመሆኑና ዜጎች በሀገራቸው የመኖር ነፃነታቸውን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት ምን ያህል እየተተገበረ ነው የሚለውንና የዜጎችን ከነበሩበት ቦታ ቋንቋን መሰረት በማድረግ ብቻ ማፈናቀል መንግስት የሚከተለው ፖሊሲ ትግበራ መሆኑን ለማረጋገጥ የፌደራሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ምክትል ሚኒስትር አቶ ሽመልስ ከማልን ጠይቀናቸው “አሁን ከሰው ጋር ነኝ ትንሽ ቆይተህ ደውል(ሰዓት ቀጥረው) ቢሉም ባሉት ሰዓት ሲደወልላቸው ስልካቸውን ሊያነሱ አልቻለም፡፡
ከዚህ በፊት በዚሁ ቤንች ማጂ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎች በክልሉ መንግስት ፕሬዘዳንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ልዩ ትዕዛዝ ፤ በቅርቡ ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሶ ወረዳ ያሉ አማርኛ ተናጋሪ ዜጎች ያፈሩትን ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው እንዲፈናቀሉ መደረጉ ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate