ሙስሊም ወገኖቻችን፤ ቁስላችሁን አስራችሁ ከወያኔ ጋር በምናደርገው ፍልሚያ ተቀላቀሉን!!!!
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ መግለጫ
ነሐሴ 3 2005 ዓ.ም.
በእስልምና እምነት እጅግ በደማቅ ሁኔታ ከሚከበሩት በዓላት አንዱ የሆነው ኢድ አልፈጥር ለ1434ኛ ጊዜ ነሐሴ 2 ቀን 2005 ዓ. ም. በመላው ዓለም በደስታ ሲከበር ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ግን ለዚህ አልታደሉም። በእለቱ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የኢድ ሰላታቸውን ሰግደው ወደ የመኖሪያ ቤቶቻቸው ሲመለሱ ለድብደባ በሠለጠኑ የወያኔ ወታደሮች አሰቃቂ ሰቆቃ ተፈጽሞባቸዋል። በዚህ እለት በአዲስ አበባና እና ሌሎች ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች በርካታ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ አሁን ሕፃናት የወያኔ የጥይት ሰለባ ሆነዋል፤ ከዚያ እጅግ አሰቃቂ ግድያና ወከባ ያመለጡት ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአስር ሺዎች የሚገመቱ ሙስሊሞች በዓሉን ያሳለፉት በወያኔ ማጎሪያዎች ውስጥ በሕመምና በረሀብ እየተሰቃዩ ነው።ይህ ለምን ሆነ?
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ጥንቃቄ የተሞላበት ተቃውሞ ሲያካሄዱ አንድ ዓመት አልፏቸዋል። እጅግ ጨዋ በሆነ መንገድ ላቀረቡት የመብት ጥያቄ በታላቁ በዓል ቀን ወያኔ የእንቢታ ምላሹን ወራዳ በሆነ መንገድ ሰጥቷል። ወያኔ ለሰላማዊ ተቃዉሞ ያለውን ንቀት እናቶችን፣ ሕፃናትንና አረጋዊያንን ጭምር በመደብደብ አሳይቶናል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሕይወታቸው ላለፈ ወገኖቻችን ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል፤ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችን ሕመም ይጋራል። በባለጌ የወያኔ ወታደሮች የተገደለየ፣ የተረገጡ፣ በቆመጥ የተደበደቡ፣ የተሰደቡ፣ የተተፋባቸው ወገኖቻችን ሁሉ ሕመማቸውን ችለው፤ እልሃቸውን ውጠው ለመረረ ትግል እንዲዘጋጁ ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ የደረሰው በደል በሁላችን ላይ የደረሰ ጥቃት፣ በደል ነው። የሙስሊም ወገኖቻችን የመብት ጥያቄ የኢትዮጵያዊያን ተበዳዮች ሁሉ ጥያቄ ነው። እነዚህ ጥያቄዎች በወያኔ አገዛዝ ሥር ምላሽ አያገኙም። ስለሆነም ተባብረን ኢትዮጵያችንን ከወያኔ ፋሽስታዊ አገዛዝ ነፃ አውጥተን ሁላችንም የነፃነት አየር የምንተነፍስባት አገር እናድርጋት ዘንድ ዛሬውኑ የጋራ የትግል ጉዞ እንጀምር።
“ሙስሊም ወገኖቻችን ሆይ! እልሃችሁን ውጣችሁ፤ ቁስላችሁን አስራችሁ ከወያኔ ጋር ለሚደረግ ፍልሚያ ተቀላቀሉን!!!” በማለት ግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ
No comments:
Post a Comment