ከአንተነህ መርዕድ እምሩ
በድሮ አጠራሩ ሻንቅላ በአሁኑ የጉሙዝ ብሄረሰብ የተማርሁት ትልቅ ነገር አለ። "በትልቆች ጉዳይ ምን ጥልቅ አደረገህ" እየተባልሁ በሚያሸማቅቅ ባህል አድጌ በጉሙዝ ህብረተሰብ ህፃናት ታላላቆቹ ጋር ያለምንም ተፅዕኖ ሲወያዩ መመልከት አስደንግጦኝ ነበር። በጨዋታ መሃል "ግሰም እንግሻ ባኒያ" (እኔንም በተራዬ አድምጡኝ) ካለ አንድ ሰው ልጅንም ቢሆን ፀጥ ብሎ ማዳመጥና ማስጨረስ የተለመደ ክቡር ባህላቸው ነው።
የኔ ሃሳብ ብቻ ይደመጥ፣ አንተን እዚህ ምን አገባህ የሚለው ኢዴሞክራሲያዊ ባህሪ የአምባገነን ገዥዎቻችን ብቻ ሳይሆን የብዙዎቻችን እየሆነ የመጣ ይመስለኛል። አምባገነኖችስ ፀጥ ረጭ አድርጎ ለመግዛት ስለሚያመቻቸው፣ ህብረተሰቡ እውነትን በተረዳ ቁጥር የነሱም አገዛዝ እንዲያከትም ስለሚያደርግ ነው። ለዴሞክራሲ እታገላለሁ የሚለው ወገን የሌሎች ሃሳብ እንዳይደመጥ ጥረት ሲያደርግ ስናይ ግን ዓላማው ከገዥዎቻችን ጨርሶ ያልተለየ መሆኑን ከማረጋገጥ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
በቶሮንቶና ባካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለፈው እሁድ ኦክቶበር 13 ቀን 2013 ዓ ም ለሶስተኛ ጊዜ በደማቅ ሁኔታ በመሰባሰብ ኢሳትን የሚያጠናክር የገንዘብና ልዩ ልዩ ድጋፍ አድርገዋል። ወያኔ ከአገር አልፎ ውጭም የፈጠረውን ጊዜያዊ ፍርሃት ሰብሮ፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሚደረገውን ትግል ሁሉ ከወያኔ ባልተናነሰ በማደናቀፉ እርኩስ ተግባር የተካኑ የጨለማ ውስጥ ወገኖችም የፈጠሩትን አሉባልታ ከምንም ሳይቆጥር የመጣው ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ነፃነት ማንኛውንም መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ያረጋገጠበት ነበር።
ቀኑ የጨለመባቸው የወያኔ ደጋፊዎች የተለመደ የማደናቀፍ አንቅስቃሴ ቢያደርጉም ማንነታቸውና አላማቸው ለሁሉም ግልጽ ስለነበር የተሳካላቸው አልሆነም። ከነሱ በባሰ በኋላ በር የተንቀሳቀሱት ግን የህዝብ ወገን መስለው የቆሙ የጨለማ ላይ ፍጡራን ናቸው። የጨለማ ላይ ፍጡራን ያልሁበት ምክንያት አለኝ። እነዚህ ወገኖች እንደሌላው ኢትዮጵያዊ የዴሞክራሲ ታጋይ ወይንም በተፃራሪው እንደቆመው ወያኔ የራሳቸው ህልውና የላቸውም። በጨለማ ውስጥ ብስባሽ እየተመገበ እንደሚያድግ ሸጋታ (በሳይንሱ ፈንገስ) ብርሃን ሳያያቸው ከጨለማ ውስጥ ሆነው ሌሎችን በማደናቀፍና በመጣል የተካኑና የወፈሩ ናቸው።
አደባባይ ወጥተው እውንትን የመጋፈጥ ችሎታው የላቸውም። እነሱ ያልባረኩት፣ እነሱ ያልመሩት እንቅስቃሴ ሁሉ ከንቱ መሆኑን ውስጥ ለውስጥ ከመናገር ውጭ ተጨባጭ ነገር አቅርበው ወይም መርተው ዳር ያደረሱት ነገር የለም። የሰሞኑ እንቅስቃሴያቸው ኢሳትን የተለያየ ስም ለመስጠት ከመዳዳት በተጨማሪ የዕለቱ እንግዳ በሆኑ ሰዎች ስብዕና ዙርያ እየተሽከረከሩ ጥላሸት መቀባት፣ ካልሆነም ወያኔ የፈጠረውን ፍርሃት አጉልቶ በማቅረቡ ተሰማርተው ነበር። ነገር ግን ህዝቡ የብዙ ጊዜ ተመክሮው
ማንነታቸውን አጥርቶ ስላሳየው አልሰማቸውም።ከወትሮው በተለየ ሁኔታም ግልብጥ ብሎ በመምጣት አሳፈራቸው።
ሌላው በጎውና እንግዳው ነገር ኢትዮጵያዊው ዘወትር የሚታማበትን የመዘግየት ባህል ሰብሮ ታዳሚው በሰዓቱ አዳራሹን መሙላቱ ነው። ፕሮግራሙን በስነስርዓትና በብስለት መከታተሉም ከእለቱ እንግዶችና ከፕሮግራሙ ቁምነገር ቀስሞ ለመሄድ ያለውን ጉጉት አመልክቷል። ከቶሮንቶ በተጨማሪ ከኦተዋ፣ ከኪችነር፣ ከዋተርሉ፣ከሚስሳዋጋ፣ ከብራምፕተን እንዲሁም ከአሜሪካ በፋሎ ድረስ የመጡት ኢትዮጵያውያን ሙሉውን ፕሮግራም እስከለሊቱ 2 ኤም ተከታትለዋል።
ኢሳት በየቀኑ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም ዙርያ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲረዳ በማድረግ ብዥታን በመግፈፉ የህዝቡ ጥንካሬና የኢትዮጵያ ጠላቶች ማንነት ከምን ጊዜውም በላይ ጥርት ብሎ ወጥቷል። በህዝቡ ገንዘብና ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ኢሳት የሚገመገመው በየቀኑ አየር ላይ በሚያውላቸው እውነቶች ሲሆን በስራ ላይ ስህተቶች ቢፈጠሩ እንኳ በደጋፊው ህዝብ ምክርና ተግሳጽ ሊያርማቸው ይችላል። ሶስት ዓመት ብዙ አይደለም። የህዝቡ ጠላቶችም ደካማ አይደሉም። ያንን ሁሉ ተቋቁሞ በሶስት ዓመት ውስጥ ያደረገው አስተዋጾ ሲመዘን ግን ለህዝቡ ከሚሰጠው ተስፋ በተጨማሪ ጠላቶቹን እያራደ መሆኑን እያየን ነው።
የዕለቱ የክብር እንግዳ ከሆኑት አንዱ አበበ ገላው ነው። ይህንን ወጣት ጋዜጠኛና አክቲቢስት ለማየት ሆነ ካንደበቱ ለመስማት የሚጓጉ ኢትዮጵያውያን ብዙ ናቸው። አበበ የፖለቲካ ሰው አይደለም። አገሪቱ በዚህ ብትመራ ይሻላታል የሚል ፕሮግራምና ዓላማ ይዘው ከሚንቀስቀሱ የፖለቲካ ሰዎች እሱን የሚለየው እውነቱን ህዝቡ እንዲያውቅ የሚታገል ጋዜጠኛና ፍትህና ርትዕ እንዲኖር የሚታገሉትን ሁሉ
በግንባር ቀደምነት ለመደገፍ የሚንቀሳቀስ አክቲቢስት መሆኑ ነው። የሁሉም ድምፅ ያለምንም ገደብና ተፅዕኖ እንዲሰማ መስዋዕት ለመክፈል የተዘጋጀ ወጣት ነው።
አበበ ከተሰማራበት ሙያው በተጨማሪ ባጋጠመው ተገቢ ቦታና ተገቢ ሰዓት ላይ ተገኝቶ ከሰላሳ ዓመታት በላይ ራሱን በሃሰት ክቦ ማንም አይደፍረኝም ያለውን የመለስን ስብዕና ሰላሳ ሰከንድ በማይሞላ እውነት የሰባበረ ጀግና በመሆኑ ለብዙ ኢትዮጵያውያን አኩሪ ገድል ፈጽሟል። ኢሳትና አበበ ያደረጉት ትልቅ ነገር፤ ታፍኖ የተቀመጠን እውነት ማስተጋባት ነው። የአበበ ሰላሳ ሰከንድ ጩኸትና የኢሳት የሶስት ዓመት እውነት ላይ የተመረኮዘ ዘገባ በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ቀይረውታል። የአምባገነኖችን ስብዕና ብቻ ሳይሆን እነሱ የፈጠሩትን ፍርሃትም ሰብሯል። ስለሆነም በኢሳት ሆነ በአበበ ላይ የሚያነጣጥሩ ወገኖች ካሉ ህዝቡን በጨለማ ለመግዛት የሚፈልጉ ብቻ ናቸው።
ሁለተኛው የክብር እንግዳ ብርሃኑ ነጋ ነው። ብርሃኑ ነጋን ወያኔ ቢያብጠለጥለው ወይም ሊያጠፋው ቢሞክር አይደንቀኝም። ወያኔ ልቡ ላይ ተወግቶ እንደተያዘ ከጩኸቱ የማይረዳ የለም። በዚያ ዙርያ ግልጽ ስለሆነ ብዙ ማለት ያለብኝ አይመስለኝም።
የገቢ ማሰባሰቡን እንቅስቃሴ ስንጀምር የተለመዱ መሰናክሎች መኖራቸውን አውቀን የተዘጋጀን ቢሆንም በክብር እንግድነት የዶክተር ብርሃኑ ነጋ ስም መታከል ከወያኔ ባሻገር በሌሎች ዘንድ አቧራ ማስጨሱን ስናይ ገረመን። እነዚህ ወገኖች አደባባይ አያውጡት እንጂ የምር ጠላታቸው ወያኔ ሳይሆን ብርሃኑ ነጋና ሌሎች ቅን ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ስራቸው ይመሰክር ጀምሯል። ምክንያቱም
ጉልበታቸውና ጥረታቸው ሲባክን የሚታየው ወያኔን ለመታገል ሳይሆን ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ጠልፎ በመጣል ላይ ነው።
ብርሃኑ ነጋ የሚከተለውን የፖለቲካ አቋም መቶ በመቶ የምቀበለው ባይሆንም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ በጎ ተጽዕኖ በማሳደር ህይወታቸውን ሁሉ ለትግል አሳልፈው ከሰጡት ጥቂት ኢትዮጵያውያን አንዱ በመሆኑ እኮራበታለሁ። ብዙ ከሱ የምንማረው አለና። ገና በወጣትነት በከተማና በገጠር ትግል የጀመረው ብርሃኑ በመጀመርያ ስደቱ ወቅት ስላለፈ ገድል እያወራ ጊዜውን በከንቱ አላሳለፈም። የተሳካለት የአካዳሚ ሰው ሆኖ ወጣ እንጂ። እውቀቱንም እንዳንዳንዶች በዩኒቨርስቲዎች ምኩራብ ገድቦ አልተቀመጠም። አገሩም ተመልሶ ከማስተማር ባሻገር የኢትዮጵያ ኤኮኖሚስቶች ማህበር መስርቶ ኢትዮጵያ ልትከተለው የሚያስፈልጋትን የዕድገት ጎዳና የሚጠቁሙ በርካታ ጠቃሚ የምርምር ውጤቶችን ከባልደረቦቹ ጋር አበርክቷል።
እንደሌሎቹ በደርግ ጊዜ በደረሰው ውድቀት የተፈጠረው የፍርሃት ቆፈን ሳይይዘው እንደገና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ለማስፈን ትግሉን ተቀላቅሎ በቅንጅት የተጫወተውን ሚና እዚህ መዘርዘር ያለብኝ አይመስለኝም። በወያኔ እብሪት ለሁለት ዓመትታት በታሰረበት ወቅትም ቁስሉን እየላሰ እንደሚያስታምም ውሻ በተዘጋበት ክፍል ውስጥ ሆኖ በውድቀቱ እያዘነ ኩርምት ብሎ አላሳለፈም። ከስድት መቶ በላይ ገጽ ያለው "የነፃነት ጎህ ሲቀድ" የሚል መጽሃፍ አበረከተን። በዚህ መጽሃፍ ቅንጅትን፣ ወያኔን፣ ከርቸሌን፣ የኢትዩጵያን ህዝብ እንዲሁም የሚጠብቀንን ፈተናና የወደፊት ተስፋችንን ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል።
በሁለተኛ ስደቱም ቢሆን የ1997 ምርጫ በተከተለው ውድቀት ተሸማቆ አልተቀመጠም። በሙያውም፣ በፖለቲካ ትግሉም የበለጠ ገብቶበታል። አሁን ደግሞ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል እንዳለባት "ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ" በሚል የመወያያ ሃሳብ ያካተተ መጽሃፍ እንካችሁ ብሎናል። አቋሙንና ሃሳቡን ባደባባይ ለመናገር የማይፈራ ጀግና በመሆኑ የተሻለ ሃሳብ አለን የሚሉ ወገኖች የተሳሳተ መሆኑን ባደባባይ ወጥቶ ማቅረብ እንጂ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ጭቃ መወርወር የነዚያን ሰዎች ማንነትና ከንቱ አቋም ከማሳወቅ ውጭ የሚፈይደው የለም።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ብርሃኑ ነጋ ኢትዮጵያውያንን ሊያነጋግር ወደቶሮንቶ ብቅ ብሎ ነበር። እንደሌላው ወገኔ እኔም የሚለውን ላዳምጥና ላየውም ወደ አዳራሹ ስደርስ፣ ካዳራሹ ማዶ ጥቂት ሰዎችን መፈክር አስይዞ ብርሃኑ ነጋን የሚያወግዝ ሰው አየሁ። በሁኔታው ባዝንም ከሌሎች ከተደበቁት የዚያ ሰው ድፍረት የተሻለ ሆኖ አገኘሁት። የሚመረጠው ግን ባዳራሹ ተገኝቶ ብርሃኑን በጥያቄ ማፋጠጥና ከሱ የተሻለም ሃሳብ ካለው ለአድማጩ ማቅረብን ነበር። ያ አልሆነም። እነዚህን ዓይነት ሰዎች ክፋት እንጂ የተሻለ ሃሳብ በውስጣቸው ያለ አይመስልም።
ብርሃኑ ካወቅሁት ጀምሮ ራሱን ላደባባይ ያቀረበ ስው ነው። የሚያስበውንና የሚያደርገውን በግልጽ የሚናገር ሰው። ስህተት ካለው ፊት ለፊት ቀርቦ ሃሳቡን በሃሳብ መፋለም እንጂ ከኋላ ሆኖ የፈሪ አሉባልታ፣ የመጠጥ ቤት ቀረርቶ፣ ከፓልቶክ ጀርባ ማንቧረቅ አይጠቅምም። ዴሞክራሲ ባለበት ሃገር ሃያ ሰው ሰብስበው ሃሳባቸውን ማጋራት የተሳናቸው ሰዎች ሌላው ኢትዮጵያዊ የተለያዩ ሃሳቦችን ሊሰማ ሲፈልግ አትሂዱ ማለት ከወያኔ የባሰ የህዝብ ጠላት ያደርጋቸዋል። አንድ ለዴሞክራሲ ቆሜያለሁ የሚል ሰው አይደለም ወገኑ፣ ጠላቱም ሃሳቡን በነጻነት እንዲገልጽ ሊታገልለት ይገባል። ኢሳቶች ስብሃት ነጋን፣ በረከት ስሞንን የመሳሰሉ አፋኝ የወያኔ ባለስልጣናት እንኳ ስልክ እየደወሉ እንዲናገሩ የሚያፋጥጧቸው
እውነት ነው የሚሉትን የራሳቸውን ሃሳብ ከሌላው ጋር በንጽጽር እንዲያቀቡ ነው። እውነቱ ስለሚያጋልጣቸው ብዙ ጊዜ ፈቃደኛ አይሆኑም እንጂ። በግላቸው በያዙት መድረክ የራሳቸውን ሃሳብ ብቻ ህዝቡ እንዲያዳምጣቸው ከማስገደድ የዘለለ ድፍረት የላቸውም። ለራሱ የመናገር ነጻነት ተጎናጽፎ የሌሎችን ነፃነት ለመገደብ ከተንቀሳቀሰ ያ ሰው በውስጡ፣ በሰብዕናው አምባገነንነት አለበት። የበላይነቱን ማረጋገጥ የሚፈልገው በሃሳብና በውቀት የበላይ ሆኖ ሳይሆን የራሱን እምነት በብቸኝነት የሚያስተናግድበት መድረክና አዳማጭ ወገን በመፈለግ ነው።ገና ስልጣን ሳይይዙ የሌሎች ሃሳብ እንዳይደመጥ የተከላከሉ ወገኖች ነገ የስልጣን ባለቤት ሲሆኑ(አያድርገውና) ከወያኔ በባሰ ላለማፈናቸው እርግጠኛ አይደለንም።
በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን እንታገላለን የሚሉ ተቃዋሚዎች ሁሉ የብርሃኑ ነጋ ግንቦት 7 ጭምር ከኔ ወድያ ላሳር ነው ከሚል ነባር ተአብዮ(ትዕቢት) ነጻ ሁነው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድምጽ እንዲሰማ እንደጉምዞች ባህል "እኔንም አድምጡኝ" ለሚል ክብርና ዋጋ መስጠትን ባህል ማድረግ አለባቸው። ለድርጅቶች ሆነ ለግለሰቦች ማንነት መስካሪው የሚያቀርቡት እውነትና ተግባራቸው በህዝብ መመዘንና መዳኘ ሲገባው ራሳቸው ዳኛ፣ ራሳቸው እውነት ለህዝብ መራጭ ሆነው ሊቀርቡ አይገባም።
በቶሮንቶ የኢሳት የድጋፉ ዓላማ ተሳክቶ ጥረቱን በማደናቀፍ በተንቀሳቀሱት ወግኖች ላይ የበለጠ ጽሁፌን ትኩረት ማድረጌ ያለምክንያት አይደለም። እነዚህ ወገኖች የኢትዮጵያውያን ተስፋ ባበበበት ሁሉ እየተገኙ ዋግ እንዲመታው ከህዝቡ ግልጽ ጠላቶች ይበልጥ ስለሚተጉ ነው። ስራቸውን ባደባባይ እያወጡ ለፀሃይ ማብቃት ተገቢ ይመስለኛል። የመለስን በውሸት የተገነባ ስብዕና የሰበረው የሰላሳ ሰከንድ እውነት የነዚህንም ተንኮል ይሰባብረዋል ብዬ አምናለሁ። እውነት ኃያል ነው።
የኢሳት ዋና ዓላማ ለህዝቡ እውነትን ማሳወቅ ነው። እውነተኛ መረጃ የሚያገኝ ህዝብ ሃይል ይኖረዋል። ፈረንጆች እንደሚሉት (ኢምፓወር) ወይም የጉዳዩ ባለቤት ያደርገዋል። አምባገነኖች መረጃን ለማፈን የሚራወጡትም ይህንን በራሱ ጉዳይ ባለቤት መሆኑን ለመንጠቅ ነው።
የሞስሊሞች እንቅስቃሴ፣ የጉራ ፈርዳና የቤንሻንጉል ተፈናቃዮች፣ የኦጋዴኖች አበሳ፣ የኦሮሞዎች እንግልት፣ የታሰሩ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚዎች ስቃይ፣ የጋምቤላ መፈናቀልና እልቂት፣ የተለያዩ ምሁራን ሃሳብ፣ የብዙ ኢትዮጵያውያን ብሶት፣ የወያኔ ደጋፊዎችም ሃሳብ ሳይቀር በሚገባ በኢሳት ተስተናግዷል። ኢሳት በሚችለው ሃቅም የሁሉንም አስተሳሰብ መድረክ በመስጠት ኢትዮጵያዊ ሁሉ በተጨባጭ ያለውን እውነታ እንዲያውቅ በማድረጉ ህዝቡን የመረጃ ኃይል ሰጥቶታል። ይህንን ሃይል ለመንጠቅ ነው ወያኔም ሆነ ሌሎች የሚፍጨረጨሩት። ያሁኑ መፍጨርጨር ከንቱ ይመስላል። የኢትዮጵያውያን ትኩረት ኢሳትንና ሌሎችንም የሚድያ ተቋማት የሚጎለብቱበትን መንገድ ወደማጠናከሩ ነው የሚሆነው።
የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያ በነፃነት ትኑር!
ለተጨማሪ ሃሳብ ጸሃፊውን በamerid2000@gmail .com ማግኘት ይችላሉ።
No comments:
Post a Comment