ህዳር ፲፭ (አስራ አምት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ድርጊቱ የተፈጸመው ትናንት ህዳር 13 2012 ዓም ነው። በተለምዶ ጀጎል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ለረጅም ጊዜ በቀበሌ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት የጥበቃ ሰራተኛው ባሻ ስዩም ተፈራ ባለፈው ዓመት ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ የቀበሌው ሹማምንት ይጠየቁዋቸዋል። ባሻ ስዩምም ዘመኔን በሙሉ የኖርኩበትን ቤት ትቼ መውደቂያ ሳይኖረኝ አልወጣም በማለት መልስ ሰጥተዋል። የክልሉ ባለስልጣናትም በቅርቡ ቤታቸውን ብቻ ትተው በቤቱ ቅጥር ግቢ የሚገኘውን ቦታቸውን በመውሰድ በባሻ ላይ የመጀመሪያ ምታቸውን ሰንዝረዋል።
ህዳር 12 ተከብሮ በዋለው የሀረር ሚካኤል የንግስ በአል ላይ በሰላም ታቦት አንግሰው ወደ ማረፊያ ቤታቸው የተመለሱት አዛውንቱ ባሻ ስዩም ወደ ቤታቸው ሲቀርቡ ግን የተመለከቱት ነገር ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነበር። የቀበሌው ባለስልጣናት ቤታቸው ሰብረው በመግባት፣ እቃቸውን ሜዳ ላይ በትነውታል። ቤታቸውንም አሽገው ሄደዋል። ባሻም ገብተው የሚያርፉበት ቤት ያጣሉ፣ ድርጊቱ አበሳጫቸው፣ ለዘመናት የኖሩበትን ቤት ያለምንም ምትክ ቤት በባለስልጣናት ተቀሙ። አዛውንቱ ባሻ ስዩም ሙሉ በሙሉ ተስፋ በመቁረጥ ህዳር 13 ራሳቸውን ሰቅለው ከዚህ አለም ጣጣ ተሰናበቱ።
በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የባጃጅ ሹፌር በትራፊክ ፖሊሶች ተገድሏል። ሾፌሩ የተገደለው ከሰአት ውጭ እየሰራህ ነው በሚል ምክንያት ነው። ሾፌሮች ለኢሳት እንደገለጹት ሹፌሩ የተገደለው ባህር እድሪስ በተባለ ፖሊስ ትእዛዝ ነው። ግለሰቡም በቁጥጥር ስር መዋሉን ሾፌሮች ተናግረዋል።
በሀርረና በጅጅጋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግፉ በዛብን በማለት በተደጋጋሚ በኢሳት ላይ ሲናገሩ መደመጣቸው ይታወሳል።
በሌላ ዜና ደግሞ በአምቦ ከመሰረታዊ አግልግሎት እጥረት ጋር በተያያዘ በምሽት ወንጀሎች እየተሰሩ ነው ተባለ።
የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች መብራት የሌላቸው በመሆኑ ሰዎች በሌሊት ይገደላሉ። ባለፈው ሳምንት በአንድ መንደር ውስጥ የተለያዩ ሰዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገድለዋል።
No comments:
Post a Comment