Pages

Nov 23, 2012

የትግራይ ህዝብን ማታለል ይብቃ! በቃ!


በትግራዩ ህዝባችን ስም የሚደረገው ንግድ አሁንም ከ21 የግፍና የከፋፍለህ ግዛ አመታት በኋላ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። ዘረኛው የወያኔ ቡድን ህወአት “እውነት እውነት እላችኋለሁ መለስ ከመሞቱ በፊት ለትግራይ ህዝብ ያስቀመጠው ጣፋጭ ከረሚላ አለ እና ዝም በሉ” ሲሉ ይደመጣሉ። የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የስርአቱ የስቃይ፣ የሰቆቃ፣ የስደት፣ የግድያና የእስራት ገፈት ቀማሽ ነው። ከጥቂት የሕወአት ጎጅሌዎች በስተቀር! ታዲያ ይህንን እውነት በጠራራ ጸሃይ ላይ በህወአት/ወያኔ የጨለማ ዘመን የሚኖረውን ምስኪኑን የትግራይ ህዝብ ለመካድ እና እንደ ህጻን ልጅ የሚጣፍጥ ከረሚላ አዘጋጅተንልሃል እና ስለዲሞክራሲ ስለነጻነት አትናገር አትጠይቅ ዝም በል አታልቅስ በሚል የማታለል ስራቸውን አሁንም በማደስና ተግባራዊ ለማድረግ በአምባገነኑ የሟቹ ባለቤት አዜብ መስፍን አማካኝነት የትግራይ ህዝብን ለመስበክ ያስባሉ።
የትግራይ ህዝብ እንደሌሎቹ የሀገሪቱ ህዝቦች በችግር የሚገኝ ህዝብ እንጅ እንደ ህወአት ባለስልጣኖች ደልቶት የሚኖር ህዝብ አይደለም። ይሁን እንጅ ወያኔ የትግራዩን ህዝባችንን ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለማጋጨት ብዙ ሙከራዎችን ላለፉት 21 አመታት ሲያደርጉ ቆይተዋል። መለስ ትግራይን የኢንደስትሪ ማእከል ለማድረግ ያዘጋጀው ፕላን እጄ ላይ ይገኛል የሚሉት አዜብ “ለህዝብ የሚጠቅም ፕላን ከነበረ ምነው በሚስጥር መለስ እስኪሞት ተጠበቀ?” ቢባሉ የሚሉት ምንም ነገር አይኖራቸውም፤ ይልቁንም ይህ የሚያሳየው በአሁኑ ሰአት በትግራይና አካባቢዋ በየግዜው የሚነሳውን ተቃውሞና በአካባቢው ብረት አንስተው እንታገላችኋለን የሚሉትን የትግራይ ተወላጆችን የነጻነት ጩኸት ላንቃን ለመዝጋት የታሰበ ነው። ለዚህም ኤፈርት በሚሊዮን የሚቆጠር ሰራተኞችን ቀጥሮ ማስራት እየቻለ ጥቂት የህወአት ጋሻ ጃግሬዎችን ብቻ በማሰራት ትርፍ በማካበት ነገርግን ይህን የሚመለከተውን ሰፊውን የትግራይ ህዝብ ሜዳ ላይ በመጣል የቅርጫው ተካፋይና ተጠቃሚ በማስመሰል ስለ ኢንደስትሪ ማእከል ይለፉፉልናል::
የአዜብ መስፍንና የህወአት ወያኔ ጉጅሌዎች በአካባቢው የሚነሳ ጩኸት እንዳይኖርና ጩኸቱ እና እምቢታው እንዳይበላቸው እንዲሁም የበላይነታቸውን አስጠብቀው ለመሄድ የሚያደርጉት መፍጨርጨር ከግዜው እውነታ ጋር ያልተገናዘበ ነው። ዛሬ ትውልድ እንደ ጥዋት ጸሃይ በአዲስ ምእራፍ የአሮጌ አስተሳሰብ ስርአቶችን እየጣለ በአንድነት፣ በመከባበር እና እምቢ አልገዛም በሚልበት ጉዞ ላይ ህወአት/ወያኔ አሁንም በትግራይና በትግራያን መካከልና በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የከፋፍለህ ግዛ ያረጀ ያፈጀ ፓሊስ እከተላለሁ ብሎ ማሰቡ ሞኝነት ነው። በዚህ የትግራይ ህዝብን ማታለል ከቶ አይቻልም ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ በኤፈርት ማን ተጠቃሚ እንደሆነ ነጋሪ ወይም አስረጅ ጎሻሚ አያስፈልገውም።
በኢትዮጵያ የሚደረጉ ማናቸውም የልማት እንቅስቃሴዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ማእከል ያደረገ መሆን እየተገባው፤ ህወአት/ወያኔ ግን ለቱባ ባለስልጣናቶቹ እና ለስርአቱ አደርባዮች ብቻ ጥቅምን በማመቻቸትና በመዝረፍ፤ በእጥፍ የኢኮኖሚ እድገት በትግራይ እያገኘን ነው ማለታቸው የተለመደ ቅጥፈታቸው ነው። በአንጻሩ የተቀረው የትግራይ ህዝብ በሀገሩ እንደ ባእዳ እየታዪ የወያኔ ሃብታሞች በደጁ ውስኪ እየተራጩ ሲያልፉ እያዪ ይህ ህዝብ ከቶ እንዴት ሊያታልሉት የሚችል የመስላቸዋል? ይህን ታሪክና ትውልድ የሚፋረጀው ሆኖ እያለ የአንድን ብሄረሰብ ተጠቃሚ በማስመሰል በትግራይ የሚነሳባቸውን የውስጥ ተቃውሞ ለማፈን የታለመ ነው።
የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስለ አንድነት፣ ስለዲሞክራሲ፣ ስለሰበአዊ መብትና መልካም አስተዳደር ጠንቅቆ የሚያውቅና ለነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች እስከ ህይዎት መሰዋእትነት የሚታገል ህዝብ ነው እንጅ፤ እነ አዜብ እንደሚያዎሩት ዳቦ እንወረውርልሃለን ዝም በል የሚባል ህዝብ እንዳልሆነ ሊረዱት እና ሊያጤኑት ይገባል። በተመሳሳይ ህዝቡም በአንድ ድምጽ በስማችን የሚነገደው ንግድ በአስቸኳይ ይቁም በማለት የአምባገነኖችን የከፋፍሎ መግዛት ባህሪ ያለፈበት ያረጀ አስተሳሰብ ከመለስ ጋር የተቀበረ ሃሳብ ነው በሚል እስከመጨረሻው ለአንድነቱ ሊታገል ይገባል።
ልማት በአንድ ክልል ብሄረሰብ ብቻ ከሆነ ጤናማ ያልሆነና አንድነትን የሚለያይ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ለህወአት ጉጅሌዎች ያስፈልጋቸዋል።
ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ትግራይን ጨምሮ በህወአት/ወያኔ አማካኝነት በአንድነታችን የተደቀነብንን የጥላቻና የመከፋፈል አጥር በማፍረስ የኢትዮጵያዊነታችን አንድነት መገለጫችን የሆነውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራን በማውለብለብ የ21 አመት የከፋፍለህ ግዛ ስርአቱን በአንድ ላይ ልንቀብረው ይገባል!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!   

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate