Pages

Nov 27, 2012

ብርሃንና ሰላም = ጽልመትና ሽብር


ብርሃንና ሰላም = ጽልመትና ሽብር

ከሰሎሞን ተሰማ ጂ.
emnaworeq.blogspot.com

“ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ ሳምንታዊውን የፍትሕ ጋዜጣ እንዳይሰራጭ አገደ፤” (www.fetehe.com እና በአዲስጉዳይ መጽሔት፣ ሐምሌ 2004 ዓ.ም)

“ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ ሳምንታዊው የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ እንዳይታተም ከለከለ፡፡” (www.fnotenetsanet.com እና amharic.voanews.com October 02, 2012/ መስከረም 22 ቀን 2005 ዓ.ም)

“ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ የሪፖርተር ጋዜጣን ገጽ ቁጥር ገደበ፡፡” (ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም)

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በሁሉም ዜናዎች በበጎ ጎኑ አልተነሳም፡፡“እንዳይሰራጭ አገደ!” “እንዳይታተም ከለከለ!” እና “ቁጥር ገደበ!” የሚሉት ሃረጎች የማተሚያ ቤቱን ስምና ክብር የሚያጎድፉ ናቸው፡፡ ይህ ማተሚያ ተቋም፣ የዛሬዎቹ ሹመኞችና ባለሥላጣናቱ አወቁትም – አላወቁትም ትልቅ ራዕይና አላማዎችን አንግቦ የተነሳ ነበር፡፡ እነዚህን ተልዕኮዎቹን ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል መስዋዕት ማድረግ ግን ከተጠያቂነትና ከታሪክ-ሕሊና ተወቃሽነት አያድንም፡፡

“ብርሃንና ሰላም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማተሚያ ቤት” በመስከረም 3 ቀን 1914 ዓ.ም በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ተቋቋመ፡፡ ይህ ማተሚያ ቤት በጥቃቅን ፔዳሎች ማለትም በእግር በመርገጥ በሚንቀሳቀሱ የማተሚያ መኪናዎች ሥራውን የጀመረው ስድስት ኪሎ በሚገኘው የዛሬው የቋንቋዎች አካዳሚ ሕንፃ ውስጥ ነበር፡፡ በዚያ ሁናቴ የተጀመረው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት  በ1958 ዓ.ም ሠላሳ ሺህ ጋዜጦችን በሰዓት ለማተም የሚችሉ ዘመናዊ የኦፍሴት ማተሚያ መኪናዎች ባለቤት ሆኗል (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ቅዳሜ ኅዳር 18 ቀን 1958 ዓ.ም፤ ገጽ 3 ይመልከቱ)፡፡

በወቅቱ፣ የማተሚያ ቤቱ የቴክኒክና ፕሮዳክሽን ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ አክሊሉ እንዳሉት፣ “ማተሚያ ቤቱ እየተሻሻለ በመሔዱ ባለፈው ዓመት እንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ መጽሐፍትን (1,500,000)፣ ከአስር ሚሊዮን በላይ ጋዜጦችን  (10,000,000)፣ ሠላሳ ሚሊዮን (30,000,000) ቴምብሮችና ሃያ ሁለት ሚሊዮን (22,000,000) ሌብሎችን፣ አንድ ሚሊዮን ተኩል (1,500,000) የአውቶቡስ ካርኔና ቁጥራቸው ያልተገለጠ እጅግ ብዙ የምስጢር እትሞች እና የሎተሪ ትኬቶችንም አትሟል፡፡”

አቶ አክሊሉ ጨምረውም፣ “ማተሚያ ቤቱ ከሁለት ዓመታት በፊት ገዝቶ ያስመጣው ትልቁ ኦፍሴት፣ 32 ገጾች ያሉትን መጽሐፍ 18ሺ እትም በሰዓት፣ አጥፎና ቆርጦ ሲቆልላል፣ እንዲሁም በቀን አንድ መቶ ሺ ጋዜጦችን ለመሥራት እንደሚችል፣” አስታውቀዋል፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህም አድገቱ አርባ በመቶ (40%) ያህል ያደገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው እንደገለጹት ከሆነ፣ በ1958 ዓ.ም እንኳን፣ ሮላንድ የተባለው ኦፍሴት መሳሪያ በልዩ ልዩ ሕብረ ቀለም አድርጎ ከሦስት ሺ እስከ አምስት ሺ ጋዜጦችን በአንድ ሰዓት ውስጥ ለማተም የሚችል ነበር፡፡ ትልቁ ኦፍሴት ደግሞ በሦስት ቀለማት አድርጎ በሰዓት ሠላሳ ሺ ጋዜጦችን ለማተም መቻሉን ገልጸዋል፡፡

“ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አምስት መቶ ስድሳ ሠራተኞች የሚሠሩ ሲሆን፣ አራቱ ብቻ የውጭ አገር ሰዎች ናቸው፡፡ ከጠቅላላው ሠራተኛ ውስጥ ስድሳ በመቶዎቹ (60%) ሴቶች ናቸው፡፡ ማተሚያ ቤቱ በሥራው ጥራትና በቀጠሮ አክባሪነቱ ብዙ ደንበኞችን ለመሳብ ይችላል፤” ይላሉ አቶ አክሊሉ፡፡

ዛሬ ደግሞ አቶ አክሊሉ ስለማተሚያ ቤቱ እንዲገልጹ ቢጠየቁ፣ እነዚህን ወርቃማ ቃላትና ሐሳቦች አፋቸውን ሞልተው እንደማይደግሙት እግጥ ነው፡፡ ዛሬ፣ ብርሃንና ሰላም በቀጠሮ አክባሪነቱና ደንበኞቹን በመሳብ በኩል ብዙ ርቀት ቁልቁለቱን ይዞ ተንሸራቷል፡፡ ይህ ቁልቁለት የተጀመረው ደግሞ የአራት ኪሎው ግርማ “ሽብር ነዝቶ” የማተሚያ ቤቱን ወዝአደሮች በ1970 ከፈጀና ካስፈጃቸው በኋላ እንደነበር ይታወሳል (ነበር፣ ቅጽ 1፣ ገጽ —)፡፡

ባለፈው ሰሞን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር በፓርላማ ስለብርሃንና ሰላም ሲጠየቁ የመለሱት ነገርም በማተሚያ ቤቱ ላይ ሕዝባዊ ትኩረትን ስቧል፡፡ “የወረቀት ችግር የለብንም፡፡ … ማተሚያ ቤቱ አስተዳደራዊ ርምጃ የመውሰድ” መብት አለው፤ አይነት ነበር ንግግራቸው፡፡ ንግግራቸውን ለማመን ግን ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም፣ ማተሚያ ቤቱ ነፃና ገለልተኛ የንግድ ተቋም አለመሆኑን ስለምናውቅ ነው፡፡ ማለትም፣ በኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የዕዝ ትዕዛዝ ሥር እንደሚሰራም ግልጽ ነውና፡፡ ሁለተኛውም ምክንያት፣ የውጭ ምንዛሪው እጥረት ምን ያህል መንግሥትንና ባንኮቹን እግር ተወርች አሳስሮ እንደሚኮረኩዳቸው አብጠርጥረን ስለምናውቅ ነው፡፡

*  *  *

በአገራችን የጽሕፈት መኪናዎች ከመምጣታቸው በፊት የነበረው ችግር ብዙ ህትመት እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲቋቋም ጀምሮ ለበርካታ አመታት ያህል በቁም ጸኃፊነት የሠሩት አቶ ተክለ ጊዮርጊስ ናቄ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ሪፖርተር ጠይቋቸው ሲመልሱ እንዳሉት ከሆነ፣ “በአገራችን የቁም ጽሐፊ የሚባለው መንፈሳዊ መጽሐፍትንና ቁም ነገርነት ያላቸውን ጽሑፎች የሚጽፍ ፀሐፊ ናቸው፡፡ ክታቡን፣ አስማቱን፣ ድግምቱንና ሌላውን ተራ ነገር የሚጽፍ ቁም ጸሐፊ አይባልም፡፡ ሐዲሳትን፣ ድጓውን፣ ስንክሳሩን፣ መልኩን ለመጻፍ የሚያገለግለውን የኢትዮጵያውያን አበውን ከዚህኛው ለመለየት ጽሑፉ “ቁም ጽሕፈት” ተባለ፤” ሲሉ ስለሙያቸው ያስረዳሉ፡፡

አያይዘውም፣ “ቁም ጽሕፈትና ድርሰት በአገራችን ቀድሞ ያለ ቢሆንም፣ በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በጣም ተስፋፍቶ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከዚህም ወዲህ በጎንደር ነገሥታት ዘመነ መንግሥት በተለይም በአፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት መጽሐፍትን የሚጽፉና የሚያዘጋጁት ሊቃውንት ተመድበው ይሠሩ ነበር፡፡ እንዲያውም መለክዓ ፊደሉ የተጠነቀቀው በአፄ አድያም ሰገድ እያሱ ዘመን ነበር፡፡” ሆኖም፣ የጋዜጣና የኅትመት ጉዳይ ለብዙ ዘመናት ፈቅም አለማለቱን አቶ ተክል ጊዮርጊስ ያስረዳሉ (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ኅዳር 18 ቀን 1958 ዓ.ም፤ ገጽ–)፡፡

ይኼው፣ በኅዳር 18 ቀን 1958 ዓ.ም የወጣው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ በፊት ለፊት ገጹ ላይ ደግሞ እንዲህ የሚል ዜና አስነብቧል፡፡ “ግርማዊ ጃንሆይ 3,886,812 ብር የፈጀውን የብርሃንና ሰላም ሕንፃ መረቁ!” ከጋዜጣው ሐተታ ውስጥ የሚከተለው ዘገባ ቀልብን ይገዛል፡፡ እንዲህ ይላል ዝርዝሩ፡፡ “አዲሱ ማተሚያ ቤት ሕንፃ የፈጀው 1,385,581 ብር ከ36 ሳንቲም ሲሆን፣ ለሌሎች የሲቪል መሐንዲስ ሥራዎች 116,352 ብር ከ33 ሳንቲም ወጪ ሆኗል፡፡ እንዲሁም፣ ከፈረሳይ፣ ከእንግሊዝ፣ ከጀርመ፣ ከሲዊድንና ከጃፓን ተገዝተው የመጡት ለማተሚያ ቤቱ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ዋጋ 2,364,879 ብር ከ17 ሳንቲም ነው፡፡ በጠቅላላው ለሕንፃውና ለመሣሪያው የፈጀው 3,886,812 ብር ከ86 ሳንቲም መሆኑ ታውቋል፡፡” (በወቅቱ የነበረው የብር ምንዛሪ ከዶላር አንፃር ሲታይም አንድ ዶላር በሁለት የኢትዮጵያ ብር ነበር የሚመነዘረው፡፡ ስለዚህም፣ በወቅቱ የምንዛሬ ታሪፍ መሠረት $1,943,406.43 የአሜሪካን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡)

በዕለቱ ተመርቆ ሥራውን የጀመረው ዌቭሴት የተባለው የማተሚያ መኪና፣ ባለ16 ገጽ የሆነውን A-2 size አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በሰዓት 30,000 ኮፒ በስምንት ቀለማት አትሞና አጥፎ የሚያወጣ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አዲሱ ሕንፃ፣ 200,000 የተማሪዎች መማሪያ ደብተሮችን በ24 ሰዓት ውስጥ የሚያዘጋጅ መሣሪያ ያለው ሲሆን፤ 60,000 ኢንቨሎፖችን በአንድ ቀን አትመውና አዘጋጅተው የሚያወጡ መሳሪያዎችም አሉት፡፡  የተቀናጀው የኢንቨሎፖች መሥሪያ ክፍልም የተሟላ በመሆኑ፣ በልዩ ልዩ መጠንና ዓይነት በየቀኑ እስከ ስድሳ አምስት ሺ እንቨሎፖችን እያቀናበረ ያቀርባል፡፡ ባመት ሲታሰብም ደግሞ ከሠላሳ ሚሊዮን የማያንስ ኤንቨሎፖችን እያዘጋጀ  ያትማል፤” ሲሉ ኃላፊው አቶ አክሊሉ ገልጸው ነበር፡፡ የጋዜጣው ሪፖርተር እንዳለው ከሆነ፣ “ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አሁን (በ1958 ዓ.ም) ባለው አቋሙ መሠረት መጽሐፍትንና ጋዜጦችን በብዛት በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ለማሰራጨት የሚችል ታላቅ ድርጅት ሆኗል” (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ኅዳር 18 ቀን 1958 ዓ.ም፤ ገጽ–)፡፡

ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ መውጣት አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ በዕለተ ዓርብ ኅዳር 17 ቀን 1958 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በበኩሉ፣ ጃንሆይ ማተሚያ ቤቱን ሲመርቁ ያደረጉትን ንግግር ሙሉ ቃል ይዞ ነበር፡፡ በዕለቱም ባደረጉት ንግግራቸው እንዳወሱት ከሆነ፣ በሁለት ቁም ነገሮች ላይ አተኩረው ነበር (በገጽ 1 እና 3 ላይ ይመልከቱ)፡፡ እንዲህ አሉ፤ “ማተሚያ ቤቱ ሥራውን የጀመረው፣ የመጀመሪያውን ማተሚያ መሣሪያ በግል ገንዘባችን ገዝተን በቤተ መንግሥታችን ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ አሁን ለዩኒቨርሲቲነት በሰጠነው የአባታችን ቦታ ላይ ነው፡፡ እንደምናስታውሰው ቁጥራቸው ከ15 በማይበልጡ ሠራተኞች ስናቋቁም በሁለት ዓይነተኛ ምክንያቶች በመመራት ነበር፡፡

“አንደኛ፣ የመጻሕፍተ ብሉያትና የመጻሕፍተ ሐዲሳት ንባባቸውና ትርጓሜያቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በየስፍራው እንዲገኙና ክርስቲያን የሆነ ሁሉ እየተመለከተ እንዲጠቀምባቸው ለማድረግ በእጅ ጽሑፍ ተጽፎ በየገዳማቱና በየአድባራቱ፣ እንደዚሁም በየአውራጃው ለኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን ለማደል የሚቻል መሆኑን በማሰብና፤ ሁለተኛም፣ የአገራችን ሕዝብ በጽሑፎች ፍላጎት ረክቶ ርምጃው የተፋጠነ እንዲሆንና በዕለት ወሬም ያገሩንና የውጭውን ሁናቴ ማወቅ እንዲችል በመመኘት ነበር፤” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጃንሆይ አክለውም፣ ሦስት አንኳር ጉዳዮች ላይ አጽንዖት ሰጥተው ነበር የተናገሩት፡፡ አንደኛ፣ “ማተሚያ ቤቱን በ1914 ዓ.ም ስናቋቁም በዚያን ጊዜ ከነበሩት ሰዎች መካከል አቶ ገብረ ክርስቶስ ተክለ ሃይማኖት ለስራው ሃሳባችንን ጥለንበት ስለነበር – የማቋቋም ሥራውን በእጅጉ ረድቷል፡፡ የመጀመሪያው ሥራ አስኪያጅም በመሆን ሠርቷል፡፡” ካሉ በኋላ፣ “ማተሚያ ቤቱ ሥራ እንዳይፈታም በማለት እንደብላቴን ጌታ ኅሩይ ያሉት ልዩ ልዩ ጽሑፎችን ለአገራችን በማበርከት ረገድ ረድተዋል፤” ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ሁለተኛም፣ “ይህ ማተሚያ በልዩ ልዩ አውራጃዎች (ከተሞች) ‘ከሣቴ ብርሃን የልዑል ራስ መኮንን ማተሚያ ቤት’ ተብለው ሦስት ቅርንጫፎች በሐረር፣ በአሥመራና በጎንደር እንዲኖረው ማድረጋችንንም እናስታውሳለን፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ በግፍ ወረራዋ ጅምራችንን እስከምታደናቅፈን ድረስ ብዙ ጥረናል፡፡” በመጨረሻም አሉ ግርማዊነታቸው፣ “ከዚህ ማተሚያ ቤት የሚገኘውን ገቢ ሁሉ፣ ለቤተ ሳይዳ ሆስፒታል (የዛሬው የካቲት 12 ሆስፒታል ነው፤) እንዲረዳ ስለወሰንን፣ የተወዳጁ ሕዝባችንን ጤንነት በመጠበቅ በኩል እንዲያግዝልን ሰጥተናል፡፡ የማተሚያ ቤቱ ገቢ ለአካል ጉዳተኞች መርጃ እንዲሆንም አዘናል፤” በማለት ነበር ንግግራቸውን የቋጩት፡፡

ማሳረጊያ፤

ስለብርሃንና ሰላም አንድትና ጥምረት የሚያስረዱ አንድ ሦስት ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንጥቀስ፡፡ ነቢዩ ኢሳያስ በትንቢቱ እንደተናገረው፣ “ንባብዋ ውስተ ልባ” (ለኢየሩሳሌም የልቦናዋን ተናገሩዋት) ሲል ስለሕዝቡም የተናገረው ቃል ነው (ምዕራፍ 40፣2)፡፡ ነቢዩ ሲራክም በ(ምዕራፍ 30፣13) ላይ በተመሳሳይ መልኩ፣ “ናዝዛ ለልብከ” (ልብህን አጥናናው) ሲል ምክሩን የሰጣል፡፡ ለሰብዓዊ ባሕሪያት በሞላ፣ የልቦናን መናገርና ልብንም ማጽናናት አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ሰው ብርሃንን ካገኘና ዕውቀትንም ከተመገበ፣ አእምሮውም እንደምኞቱ መጠን ይጎለብታል፡፡ አእምሮው የጎለበተም ሰው፣ ልቦናውን ስለሚያስደስት እዝነ-ልቡናው ዕረፍትንና መጽናናትን ያገኛል፡፡ ያን ጊዜም አእምሮው ሰላምን አገኘ ማለት ነው፡፡

በዮሐንስ ወንጌል (ምዕራፍ 4፣5) ላይ የተጠቀሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ኃይለ-ቃልም፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ!” ካለ በኋላ፣ ደቀመዛርቱን “እናንተም የዓለም ብርሃን ናችሁ!” ሲል ያውጃል፡፡ ይኼው የብርሃን አዋጅም ወደ ኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያው ምዕራፍ ይወስደናል፡፡ ያኔ፣ ፈጣሪ “ብርሃን ይሁን” (ለይኩን ብርሃን) ነበር ያለው፡፡ ከምዕራፉ እንደምንማረው ከሆነ፣ የብርሃን ጉድለት (ጽልመት) የነገሰበት ወይም የሰፈነበት ዓለም፣ እርሱ ዕውቀት አልባም ነው፡፡ ያለብርሃን የመኖርን ባዶነት የምንረዳው፣ በብርሃነ-አእምሮአችን እንጂ በጽለመታዊው እእምሮአችን አይደለም፡፡ ብርሃን ሲጠፋ፣ ያኔ አእምሮም ወደ ጽልመቱ ተመልሶ ይገባል፡፡

ብርሃን ለሰው ልጆች ተፈጥሮአዊ ፀጋ ነው፡፡ “ሕፃን ልጅ ልክ እንደተወለደ ዓይኖቹን ወደ ብርሃነ ቀላይ በአራቱም ማዕዘናት እያዟዟረ ያቁለጭልጫል” ይባላል፡፡ በብርሃን ውቅያኖስ ውስጥ እንደፈለገው ለመዋኘት ያለውን ሰብዓዊ ናፍቆት በሕፃኑ ውስጥ እናያለን፡፡ ጨቅላው በብርሃኑ አማካይነት የሚያየው ነገር ውሱን ነው፡፡ ወሰኑም በአድማሳት አጥር/ኬላ መጠን የተከለለ ነው፡፡

ስለዚህ ሰው በዐይኑ ብርሃን ከሚያየው የበለጠ ረቂቅ የሆነ ብርሃን በአእምሮው ዐይኖች ያያል፡፡ ማየት የተሳነው ሰው ቢሆን እንኳን፣ በአእምሮው ብርሃንን ያያል፡፡ የአድማስ ጥጋት ከማየት አይከለክሉትም፡፡ ብርሃኑ በተለይም በትምህርትና በዕውቀት ከጎለበተማ የባሕር መቀመቅ፣ የምድርም ጥልቅ ውስጥ ዘልቆ ይገባል፡፡ ረቂቅ አቅምን የሚጋርደው ግንብም ሆነ ድንበር ስለሌለ ነው፡፡

ከዚህ የአእምሮ ብርሃንም ሰላመ ይወለዳል፡፡ ስጋት፣ ፍርሃት፣ ጭንቀትና ሽብር እንዲሁም “ምን ይመጣብኝ ይሆን?” የሚል ስሜት ሁሉ በብርሃን ይወገዳል፡፡ የሽብር ምንጩ ጽልመት ነው፡፡ ምን ይመጣብኝ ይሆን ብሎ መስጋት ከጭለማ የሚወለድ ጋኔል ነው፡፡ ጽልመቱ በብርሃን ጮራዎች ከተወገደ በኋላ ግን፣ ልብ ሰላምን ያገኛል፡፡ ሰላምም፣ ሰላማዊ መንግሥት እንዲመሠረት ያደርጋል፡፡ ለሰው ልጅ ሰላምን ከመስጠት የበለጠ ምን በጎ ምግባር አለ?

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትም የያዘው ስያሜ ሞላው ዓለም የሚስማማበት ምኞት ነው፡፡ የብርሃንና የሰላም ምኞት ነው፡፡ ብርሃን ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ሰላምም ሰብዓዊ ነው፡፡  የመላው ዓለም ሕዝብ ለብርሃንና ለሰላም የጋለ መሻት፣ ጉጉትና ናፍቆት አለው፡፡ ዘላለማዊ መሻት ነው፡፡ ጊዜያዊ የፖለቲካ ሽቀላና ትርፍ አጋባሽነት ያንን ዘላለማዊ ናፍቆትና መሻት አያሰናክለውም፡፡ ከጽልመትና ከሽብር ይልቅ ብርሃንና ሰላም በመላው ዓለም እንዲነግስ፣ በተለይም በኢትዮጵያችን እንዲንሰራፋ ዘላለማዊ ጸሎታችንን እናድርስ!

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate