የአቶ ግርማ አካሄድ በምዕራቡ ዓለም በሚካሄድ የፍርድቤት ችሎት አንዳንድ ጊዜ ጠበቆች መናገር የማይገባቸውን ነገር እያወቁ የሚናገሩትን ሁኔታ ይመስላል፡፡ እማኝ ዳኞችን (ጁሪ) እንዲሰሙት የሚያስፈልግ ነገርግን በፍርድቤቱ ውስጥ ለመናገር የማይፈቀድ ሃሳብ/መረጃ ጠበቆች ሆን ብለው ይለቃሉ፡፡ ይህ ልክ እንደተሰማም ተከላካይ ጠበቃ የተቃውሞ ድምጽ ያሰማል፤ ዳኛውም ንግግሩ እንዲሰረዝ ያዛሉ ሆኖም ከሰሚዎቹ እማኝ ዳኞች ጭንቅላት ውስጥ መሠረዝ ማንም አይችልም፡፡ ለአቶ ግርማ መሠረታዊ ጥያቄዎች አቶ ሃይለማርያም እጅግ መስመር የለቀቀ ምላሽ በመስጠት ጥያቄዎቹን ለመሰረዝ ቢሞክሩም የአቶ ግርማን ጥያቄዎች ከህዝብ ጆሮ መልሰው መውሰድ አይችሉም፤ ከህዝብ ልብ ውስጥ ማጽዳት አይችሉም፤ ከአየሩ ውስጥ መምጠጥ አይችሉም፡፡
ቤተሰቦቻቸው ኦነግ ተብለው የታሰሩባቸው፣ በፖለቲካ እምነታቸው በጨለማ ቤት የሚማቅቁ፣ በፈጠራ ክስ የተወነጀሉ፣ የተደፈሩ፣ ሃብታቸውን የተቀሙ፣ ስለመኖራቸው ባደባባይ እየታወቀና በየቀኑ ቶርቸር (torture) ሲደረጉ ሲቃቸው የሚሰማ ዜጎች ቁጥር በሺህ እንደሚቆጠር ይታወቃል። የፈረንጅ እማኝ እንኳን ካስፈለገ ሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች የቅርብ ጊዜ ምስክር ናቸው። ሁለቱ ስዊድናዊያን ጋዜጠኞች የማንም ብሄርና የፖለቲካ ድርጅት አባል ባለመሆናቸው “መረጃና ማስረጃ” ስለሚባለው የክስ ድራማ የተናገሩት ከሚታመነው በላይ ነው። እንግዲህ አቶ ሃይለማርያም ይህንን ሁሉ እያወቁ ነው “ድኜበታለሁ” በሚሉት አምላክ ፊት እንዲህ ያለ ጥያቄ ማንሳት “በእሳት የመጫወት ያህል ነው” ያሉት። አናትመውን ካልነው አስተያየት ውስጥ “… ልጆቻቸውና ባለቤቶቻቸው ሳይቀሩ ይታዘቡዋቸዋል” የሚል ይገኝበታል።
ብቸኛው ተቃዋሚ “አንከራከርበትም ህዝብ ይፍረደው”
በኢትዮጵያ አንድም የፖለቲካ እስረኛ አለመኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በድፍረት ተናገሩ። የመንግስታቸውን ፍርድ ቤቶችና የፍርድ ሂደት እንደማስረጃ ጠቅሰዋል። በተወካዮች ምክር ቤት ብቸኛው የመድረክ ተወካይ ለጥያቄያቸው የሚሰጣቸውን መልስ አስቀድመው በመገመት “አንከራከርበትም ህዝብ ይፍረደው” ብለዋል። ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ንግግሩን “ፍጹም ቅጥፈት የተሞላበት” በማለት ሲኮንኑት በእስር የሚማቅቁት ከቁጥር በላይ “ስም፣ ቤተሰብ፣ ልጅ … ያላቸው የምናውቃቸው ሰዎች ናቸው” በማለት ተናግረዋል፡፡
ታህሳስ 23 ቀን 2005 ዓ ም በተካሄደው የ10ኛው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የተገኙት ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከመድረኩ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ የቀረበላቸው ጥያቄ ከወትሮው በተለየ ህሊናንና ውስጣዊ ማንነትን በሚፈታተን መልኩ ነበር።
የፖለቲካ እስረኞችን አስመልክቶ “መቼም የታሰረ ዘመድ የለዎትም” በማለት ነገሩን “በኔ ላይ ቢደርስ” ብለው እንዲያስቡ በመማጸን አቶ ግርማ አንድ ሰው ከማያውቀው ቦታና ድርጅት በግል ሞባይሉ መልዕክት ቢላክለት እንዴት አልቃይዳ ሊባል እንደሚችል፣ ከማያውቀው ድርጅት ወይም ከማያውቀው የአልቃይዳ አባል መልዕክት ቢላክለትና መልስ ሳይለዋወጥ የተገኘ ሰው እንዴት ወንጀለኛ እንደሚባልና እንደሚፈረድበት በመግለጽ ጥያቄ ሰነዘሩ።
ከኦነግ ጋር ግንኙንት አለሽ ተብላ ከ3 ለጆችዋ ተነጥላ 10 ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደባት ሌሊሴ ወዳጆ
“አልቃይዳ ሞባይላቸውን እንዴት እንደሚያገኘው ባይገባኝም” በማለት ወገኖቻቸውን ባስፈገጉበት መልሳቸው ቀድመው የተናገሩት አቶ ሃይለማርያም፣ “አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለም” በማለት ነበር። የፍታብሔርና የወንጀል ጉዳዮችና፣ በዚሁ አግባብ የተፈረደባቸው ካልሆኑ በስተቀር የፖለቲካ እስረኛ የሚባል እንደሌለ አስረግጠው በመግለጽ የመንግስታቸውን የፍትህ አሠራር ደረታቸውን በመንፋት አሞካሽተዋል።
በፖለቲካ ሽፋን ወንጀል የሚሰሩ፣ የአሸባሪ መሳሪያ የሚሆኑ፣ የፖለቲካ መሪና አባል በማስረጃ መከሰሳቸውን የጠቆሙት አቶ ሃይለማርያም “መረጃ ቢኖረንም ማስረጃ ያላገኘንባቸውና ወደ ህግ ሳይቀርቡ የተቀመጡ አሉ” ሲሉ የ“ቢጫ” ካርድ ማስጠንቀቂያ በመሳብ የህሊናን ነገር ወደ ጎን በመተው በደረቁ በመሸምጠጥ አቶ መለስን በልጠው ታይተዋል። በድጋሚ ጥያቄ የመጠየቅና የመሟገት እድል አለመኖሩ ጠቀማቸው እንጂ “የሚፈለጉትን ሰዎች ስልክ ከቴሌ ወይም ከጓደኞቻቸው በመውሰድ በሶማሊያ አገር በተመዘገበ ስልክ ከሽብር ጋር የተያያዘ መልዕክት ኢህአዴግ እንደላከው እናውቃለን በማለት አቶ ግርማ ቢከራከሩ መልሳቸው ምን ሊሆን ይችል ነበር?” በማለት ስርጭቱን ሲከታተል የነበረ አስተያየት ሰንዝሯል።
ዕውቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ይህንን የአቶ ሃይለማርያም ምላሽ በተመለከ በተለይ ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በስካይፕ ለተጠየቁት ሲመልሱ “በእውነቱ ይህ ፍጹም ቅጥፈት የተሞላበትና አጸያፊ ነው” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ “እነዚህ እስረኞች እኮ በቁጥር የሚታወቁ ብቻ ሳይሆኑ ስም፣ ቤተሰብ፣ ልጅ፣ ዘመድ፣ ወዘተ አላቸው፡፡ እናውቃቸዋለን፤ ዓለም ያውቃቸዋል፤ እንግዲህ ጠ/ሚ/ሩ ለእነዚህ ልጆችና ቤተዘመዶች ነው አባታችሁ/እናታችሁ/ዘመዳችሁ ወንጀለኛ አሸባሪ ነው እንጂ የፖለቲካ እስረኛ አይደለም እያሉ ነው ያሉት፤ … ሥነምግባር የጎደለው ንግግር ነው” ብለዋል፡፡
አቶ ኦባንግ ሲቀጥሉም “የጋራ ንቅናቄያችን አቶ ሃይለማርያም ሥልጣን እንደያዙ ደብዳቤ ልከን ነበር፤ በደብዳቤውም ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን የሚገባው በዕርቅ ዙሪያ ላይ መሥራት ሲሆን ይህም የሚጀምረው የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት እንደሆነ ጠቅሰን አጽዕኖት ሰጥተን ጽፈን ነበር” በማለት ድርጅታቸው ከሦስት ወራት በፊት ለጠሚ/ሩ በስም የጻፈውን ደብዳቤ አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም እስካሁን ምንም ምላሽ ያላገኙ እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን በደብዳቤው ላይ አቶ ሃይለማርያም በአሁኑ ጊዜ የህወሃት/ኢህአዴግ ሥራአስፈጻሚ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ በመሆናቸው ለሚደግፏቸው ብቻ ሳይሆን ለሚጠሏቸውም ጭምር በቅንነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው መጥቀሳቸውን ተናግረዋል፡፡ “ይህ ዓይነቱ ማሳሰቢያና ጥያቄ ግን እንዲሁ ሲቀጥል አይኖርም፤ እኛም ሆነ ሕዝብ በቃኝ የሚልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፤ ለዘመናት አምባገነኖች ተመሳሳይ ጥሪ ሲቀርብላቸው ቆይተው ሁሉም ንቀው በመጨረሻ የውርደት ጽዋ እንደተጎነጩ ታሪክ ምስክር ነው፤ ህወሃት/ኢህአዴግ ከዚህ የታሪክ ክስተት ፍጹም የተለየ ሊሆን አይችልም” በማለት አቶ ኦባንግ የማስጠንቀቂያ ተግሳጽ ሰጥተዋል፡፡
ስኳሩን እየላሱ በሞቀ ቤታቸው ስለተቀመጡ “የመንግስት ሌቦች” ለተጠየቁት “ለጸረ ሙስና ኮሚሽን መረጃውን በማቅረብ ቢተባበሩን ራሴው ተከታትዬ ለማስፈጸም ቃል እገባለሁ” የሚል መልስ የወረወሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፣ መንግስታቸው ማስረጃ ባገኘባቸው ላይ ርምጃ እየወሰደ እንደሆነ አመላክተዋል።
አቶ ሃይለማርያም “ለህሊናቸው ይቀርባሉ” በሚል ይመስላል አቶ ግርማ በየቀበሌው ያሉ የኢህአዴግ ካድሬዎች “ኢህአዴግ ከሌለ አገሪቱ አትቀጥልም” በማለት ስለሚያስፈራሩ ህዝብ የፈለገውን የመምረጥ መብት እንዳለው በግልጽ ማረጋገጫና መመሪያ እንዲሰጡላቸው በተማጽኖ ጠይቀው ነበር።
የአቶ ግርማ ጥያቄ እንደተነሳ አቶ መለስ አማራ ክልል ቡግና ወረዳ በሚገኘው አባላቸው ላይ አቶ ልደቱ ላቀረቡት አቤቱታ የሰጡትን ዓይነት ምላሽ የጠበቁ ነበሩ፤ በ2002 ምርጫ አቶ ልደቱ አዲስ አበባን ለቀው በትውልድ ስፍራቸው ቡግና ለመወዳደር ሲቀሰቅሱ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የስም ማጥፋት ተካሂዶባቸው እንደነበር ጠቅሰው ይከሳሉ። አቶ መለስም “… እንዲህ ያለ ወራዳ፣ እንዲህ ያለ ቆሻሻ… እደግመዋለሁ እንዲህ ያለ ወራዳና ቆሻሻ የድርጅታችን አባል ሊሆን አይገባም…” በማለት የስድብ ናዳ አወረዱ። አራዳው ኢቲቪ አቶ ልደቱ ተደስተው ፈገግ ሲሉና አንጀታቸው መራሱን የሚያሳብቀውን ፊታቸውን አሳየ።
አቶ ሃይለማርያም አቶ ግርማ ላቀረቡት ተመሳሳይ ጥያቄ “አባሎቻችን ይህን አይፈጽሙም” በማለት ባጭሩ መልሰዋል። ህዝብ የሚመርጠውን ስለሚያውቅ እንዲህ አይነቱ ጥያቄ የህዝብን የምርጫ ልምድና ንቃተ ህሊና አሳንሶ የማየት ያህል እንደሚቆጠር በመናገር ቀጥተኛውን ጥያቄ የፖለቲካ እርሾ ለማድረግ ሞክረዋል።
በማተሚያ ቤት ችግር የፓርቲያቸው ጋዜጣ ከህትመት መውጣቱን በመጥቀስ አንድ ከፍተኛ ጉዳይ አንስተው ነበር። ፓርቲያቸው ከአባላቱ፣ ከደጋፊውና ከህዝብ ጋር የሚገናኝበትን ብቸኛ ሳምንታዊ ጋዜጣውን በግል ማተሚያ ቤቶች ለማሳተም ሲሞክር በስልክ በሚሰጥ ማስፈራሪያ አታሚዎቹ እየፈሩ እንደማይተባበሯቸው፣ የህትመት ጥያቄያቸውን ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበሉ በመግለጽ በስልክ ማስፈራሪያ ለሚደርሳቸው የግል አታሚዎች በግልጽ ህዝብ እየሰማ ሳይፈሩ ስራቸውን መስራት እንዲችሉ እንዲነግሩላቸው አሁንም የተማጸኑት አቶ ግርማ ያገኙት መልስ ለጠየቁት የሚመጥን አልነበረም።
አቶ ሃይለማርያም “ማተሚያ ቤቶቹ ስራቸውን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በስልክ ማስፈራሪያ ስራቸውን ያቆማሉ ብዬ አላስብም” በማለት ከደመደሙ በኋላ “ማተሚያ ቤቶቹ ስለመፍራታቸው መረጃ የለኝም። እንደጭራቅ ለምን ፈሩን የሚለውን ራሳችሁን ጠይቁ” የሚል ከጥያቄው ጋር ግንኙነት የሌለው ምላሽ ሲሰጡ ተደምጠዋል። አያይዘውም ችግሩ አጋጥሞም ከሆነ የአታሚዎች ማህበር አለ በዚያ በኩል ሊቀርብ እንደሚችል አመላክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህገወጥ ደላሎች ምክንያት ከአገር ስለሚወጡ ዜጎች ሲናገሩ፣ አንድ ሰው የሚከፍለው 50ሺህ ብር መሆኑን በማመልከት ይህን ገንዘብ በመያዝ አገር ውስጥ በመደራጀት ስራ መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል። ይህንን ገንዘብ ራሳቸውን ለማጥፋት ከሚያውሉት ራሳቸውን ወደሚጠቅም ስራ እንዲቀይሩት ሰፊ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል። ይህን ያህል ብር በመክፈል መሰደድን ስለሚመርጡበት የተለየ ነገር ግን የተናገሩት ነገር የለም። የጠየቀም ወገን አልታየም።
አስመራ በመሄድ ለመደራደር ፈቃደኛ እንደሆኑ ለአልጃዚራ ቴሌቪዥን ተናግረው የነበሩት አቶ ሃይለማርያም፣ ኤርትራን በተመለከተ አስመራ ለመሄድ ፈቃደኛ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በራሳቸው አባል ለቀረበላቸው ጥያቄ ቀደም ሲል የነበረው የኢትዮጵያ ፖሊሲ አልተቀየረም፣ ይህ ኢትዮጵያ የያዘችው የሰላም ፖሊሲ ወደፊትም የሚቀጥል ነው በማለት መልስ ሰጥተዋል። የኤርትራ መንግስት በተለይም የመሪዎቹ ባህሪ የሚታወቅና የአስመራ መንግስት ኢትዮጵያን የማተራመስ ስራውን እንዳላቆመ የተናገሩት አቶ ሃይለማርያም፣ የኤርትራ መንግስት ለሚፈፅማቸው እኩይ ተግባራት የኢትዮጵያ መንግስት የዓለም አቀፍ ህግጋትን መሰረት በማድረግ ተመጣጣኝ እርምጃ ለመውሰድ የተያዘው አቋም እንደማይቀየር አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ የአስመራው መንግስት ለድርድርና ለሰላም ራሱን የሚያስገዛ ከሆነ በሩ ክፍት መሆኑን ተናግረዋል። በሌላም በኩል የሰላምና ፍላጎት እንደሌለው ለዓለም ማስታወቃቸውን ለጠየቋቸው ገልጸዋል።
የምዕራብ አገሮች በስፋት ኢንቨስትመንት ላይ ያልተሰማሩት በመንግሥት ችግር ሳይሆን በራሳቸው የኢኮኖሚ ቀውስ መሆኑንን በማመልክት አስተያየት ሰጡት አቶ ሃይለማርያም፣ ቻይናና ህንድ በኢትዮጵያ ከፍተኛውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደተቆጣጠሩት፣ በአነስተኛ ደረጃም ቢሆን የቱርክ ባለሃብቶች እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል። ቻይናና ህንድ እያስመዘገቡ ያለው እድገት ከፍተኛ በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በስፋት ኢንቨስትመንት ላይ መሳተፋቸውን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት 11.4 በመቶ መሆኑንን የዓለም ባንክ ማመኑንና የተጀመሩት ከፍተኛ የልማት ስራዎች በተያዘላቸው የአምስቱ ዓመት እቅድ መሰረት በርብርብ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። በቤቶች ግንባታ “በአፍሪካ በዓመት 100ሺህ ቤቶች የሰራው ኢህአዴግና ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በቻ በመሆኑ ልንደነቅ ይገባል” ሲሉ በቤቶች ግንባታና ግንባታውን ለመቆጣጠር የተጀመረው አካሄድ በተጀመረው መልኩ ይቀጥላል ብለዋል። መንግሥታቸው ይህንን “ግንባታ” ሲያደርግ በየጊዜው ስለሚያፈርሰው የዜጎች ንብረትና ህይወት ከእርሳቸው የ“ልማትና ግንባታ” ንግግር ጋር የሚሄድ ባለመሆኑ ሳይጠቅሱት አልፈውታል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
No comments:
Post a Comment