ጀርመን፣ ፍራንክፈርት አውሮፕላን ማረፊያ፣ መነገር ያለበት (ቁጥር አራት)
ከበልጅግ ዓሊ
Beljig.ali@gmail.com
ጉዳዩ – እሁድ ጃንዋሪ 13 ጠዋት ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በምገኝበት ወቅት ነው የተከሰተው። የዜጎቻችንን ቁጥር ስለበዛ (አበሻ የሚለውን ቃል መጠቀም ስለሚደብረኝ) ምን ይሆን ምክንያቱ ብዬ አካባቢውን እየቃኘሁ ፓስፖርቴን አሳይቼ ወደ ውስጥ ገባሁ። ሰሌዳው ላይ የጀርመን አየር መንገድ የሆነው ሉፍታንዛ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እንዳለውና መግቢያውም በበር ቁጥር 22 እንደሆነ ይገልፃል። በተጠቀሰው በር በኩል ሳልፍ በርከት ያሉ ተሳፋሪዎች ተመለከትኩ። አንድ አውሮፕላን ይህን ሁሉ ሰው ይዞ ይጓዛል? ራሴን በራሴ ጠየቅሁ። መልሱ ብዙም ሰላላስጨነቀኝ ወደ ፊት ቀጠልኩ። እዚህ አካባቢ የተመለከትኩት የዜጎቻችን ኮተት ማብዛት ፈገግ እያስደረገኝ ወደ ፊት ገሰገስኩ። የፍራንክፈርት አውሮፕላን ማረፊያ ለንደንን አያክል እንጂ ትልቅ ነው። በተለይ ኮተት ለተሸከመ ሰው አድካሚ የውስጥ ለውስጥ ጉዞ ይጠብቀዋል።
ለንደን የሚጓዘው አውሮፕላን መግቢያው በር ቁጥር 47 ላይ ስለነበረ ጉዞዬን ቀጠልኩ። በመንገድ ላይ ተጨማሪ ዜጎቻችን ነበሩ። አንዳንዶቹ የያዙትን ኮተት መጎተት አቅቷቸው እረፍት ለመውሰድ ኮተታቸውን ከራሳቸው ላይ አራግፈው ቆመዋል። ከተጓዦቹ ማህል አንዷ እንዲውም በጣም ገርማኛለች። ከፍ ያለ ታኮ ጫማ ተጫምታለች። ቦርሳ አንግታለች፣ ላፕ ቶፕ ተደግሟል፣ አነስ ያለ ቦርሳ ይጎተታል፣ ከውስጥ የተገዛ ውስኪ በከረጢት ተደርጎ ተይዟል። ልብ ብሎ ለተመለከታት ቤት የምትለቅ ትመስላለች። ይህ ዓይነት ሸክም በብዙው ተሳፋሪ ላይ የሚታይ ነው።
ሁሉንም መርዳት ሰለማይቻል ጉዞዬን ቀጠልኩ። በመንገድ አንደ ጠና ያሉ ሴት አገኘሁና መርዳት አለብኝ ብዬ ተጠጋሁ። በትግሪኛ አነጋገሩኝ። እንደማልችል ገልጽኩላቸው። አማራ ነህ አሉኝ። ዘር መቁጠር ሰለማይጥመኝ ዝም አልኩ። ዘር መቁጠር ብጀምርም ማንነቴን ለመግለጽ እስከ ሰባት ቤት ድረስ መዘዘር አለብኝ። ሸክሙ ሲቀላቸው አፋቸውን ቀለለው መሰለኝ ጥያቄውን ያዥጎደጉት ጀመር። እኔ ደግሞ ሸክሙ ስለበዛ ለመልሱ ቦታም አልሰጠሁት።
- አዲስ አበባ ነው እንዴ የምትሄደው ?
- አይደለም። እርስዎ አዲስ አበባ ነው የሚሄዱት?
- አዎ።
- ከሆነ ቦታ ተሳስተዋል። በር ቁጥር 22 ነው’ኮ መግቢያው።
- እሱ ሉፍታንዛ ነው። የእኛ አውሮፕላን 48 ቁጥር ላይ ነው።
- አሁን ግራ ገባኝ ወደ አስመራ የሚሄድ ሌላ አውሮፕላን ያለ መሰለኝ። <<የኛ>> ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም።
ወደ መሳፈሪያው በር ላይ ስደርስ ነገሩ ግልጽ እየሆነልኝ መጣ። አዲሱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 787(Boeing 787 Dreamliner) ፊቱን ወደ መስታወቱ አዙሮ ቆሟል። ከውጭ ሲያዩት ደስ ይላል። ወደ ሃገሬ ምድር የቀረብኩ መሰለኝ። እቃውን አስረክቤ ሴትየዋን በሉ በሰላም ይግቡ አልኩና ተለያየሁ።
በነገራችን ላይ ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀርመን ቅርንጫፍ ሳነሳ አንድ የማይረሳኝ ነገር አለ። የፍራንክፈርት ባቡር ጣቢያ የሚገኘው መሃል ከተማው አካባቢ ነው። ከባቡር ጣቢያው ፊት ለፊት የታወቀው ካይዘር (Kaiserstraße)በመባል የሚታወቀው ሴተኛ አዳሪዎች የሚገኙበት መንገድ ነው። ከዚህ መንገድ ጎን ደግሞ ሙንሽነር መንገድ የሚባል አለ። በሁለቱ መንገዶች መሃል አንድ ሕንጻ አለ። ድሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ የነበረው በዚህ ሕንፃ ላይ ነው። በሕንጻው ላይ በትልቁ Ethiopianየሚል ተጽፎ ነበር። እሱን ባየን ቁጥር ዜጎች የሃገራችን ስም በፍራንክፈርት እምብርት ላይ በመለጠፉ እንደሰት ነበር። አየር መንገዱ በደከመ ዘመን እንኳን ይህንን ቢሮ ይዞት ከርሟል። አሁን ግን በወያኔ ዘመን ይህ ጽሁፍ ከቦታው ወርዷል። የአየር መንገዱም ሥራ ለወያኔ ደጋፊዎች ተበታትኗል። ቢሮውን ተለቋል ። ያ እንደ ትልቅ የምንኮራበትም ጽሁፍ አሁን የለም። እዚያ ሕንጻ ላይ መለጠፉ ትልቅ አየር መንገዱን ማስታወቂያ ስለነበር ገርሞኛል። ( ፎቶው የተጠቀሰው ሕንጻ ነው)
ወደ ቦታዬ ለመሄድ እየተዘጋጀሁ ዞር ከማለቴ ፍራንክፈርት አውቀው የነበረ ሰው አሁን የአየር መንገዱ ቢሮ ከፈረሰ በኋላ ሥራውን ተረክቦ ይራወጣል። በእሱ እድገት እየተገረምኩ መንገደኛውን አንድ በአንድ መመለክት ጀመርኩ። ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ ሰው ከውጭ እንጂ ከውስጥ አጋጥሞኝ ስለማያውቅ ብዙ የሚያሰገርም አዳዲስ ክስተቶች በዜጎቻችን ላይ ተመልክቻለሁ።
ከሁሉ በፊት የተረዳሁት የሴት ዜጎቻችንን ፀጉር ረጅም መሆኑን ነበር። አንድም ቀምቀሞ ላገኝ አልቻልኩም። ሹርባም የለም። ኢትዮጵያውያን ሴቶች የጸጉር ቀለማቸው ምን ዓይነት ነው? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ሊከብድ ይቻላል። ብሎንድ፣ ቢጫ፣ ነጭ፣ ቀይ ፣ ጥቁር በየዓይነቱ ጸጉር ተሰክቶል። ግሩም ማማር!መሽቀርቀር እንዲህ ነው። የሚገርመው ሁሉም ሴቶች አንድ አይነት የአንገት ሰበቃ ይዘዋል። ፈረንጆች ጸጉራቸውን ንፋስ አምጥቶ ፊታቸው ላይ ሲጥልባቸው ጸጉሩን ለመመለስ እንደሚደርጉት ዓይነት። የኛዎቹ ግን ጸጉር ወደ ፊት ቢመጣም ባይመጣም አንገት መስበቅ እንደ ልምድ አድርገውታል። እንደ ሥልጣኔ! እንደ ፈረንጅነት!
ጸጉሩን ተወት አድርጌ ወደ ታች ስመለከት የአለባበሱን ጉዳይ መናገር ያቅታል። ጉዞ ጀምሮ፣ ታኮ ጫማ አድርጎ መደናቀፉ የሚገርም ነው። የዝነጣው ዓይነት ግማሾቹ ከአውሮፕላን ሲወርዱ ሙሽራ የሚሆኑ ይመስላሉ። ማጥናቴን ቀጥዬ የእጅ ጥፍር ላይ ስደርስ ግን ግራ የሚያጋባ ነው። ሁሉም አዲስ ጥፍር አስክተዋል። ረጅም ለምንም ሥራ የማይመች። ያ ጥፍር ደግሞ ዜጎች ለለመድነው ምግብ ተስማሚ አይደለም። እንጀራን በሹካ ካልሞከርነው በቀር። ችግር የለም ለካ ክትፎ በቀንድ ማንኪያ መሆኑን ረስቼው ነው። ጥፍሩን ከማስነቀል እንጀራም በፈሳሽ መልክ ቢዘጋጅ ምን ነበረበት። ለቅምጥል ሲያንስ ነው።
ወደ ወንዶቹ ስዞር ደግሞ ጥቁር የቆዳ ጃኬት የታደለ ይመስላል። <<የተከበሩ>> ኢንቨስተሮቻችን መዳፈር አይሁንብኝ እንጂ የእጃቸው ስልክ አስሬ ነው የሚጮኸው። ዶላር ስንት ሆነ? ኢሮስ? መኪናው ደረሰ ወይ? ጠዋት ነው የምደርሰው መኪና ይጠብቀኝ? መኪናውን ለምን ሸጣችሁት ? አሁን በምን ልጠቀም ነው? ኮንቴነሮችን እስቶር አስገቧቸው! እኔ ስመጣ ነው የሚከፈቱት! ሆቴል ያዝልኝ! ። ጨኸት በጩኸት! ንግግሩ ለኛ ይሁን ለሌላው አይገባኝም። ግን ሁሉም እየጨኸ በሞባይል ያወራል። እድሜ አዲስ ጀርመን ለገባው የስልክ ካርድ – ላይካ። ስልክ እንደሆነ ረክሷል። ብዙዎቹ መነጽራቸው ወደ ላይ ወደራሳቸው ገፋ ተደርጓል። እዚህ እንደሁ ክረምት ነው ፀሐይ የለም። ምን አልባት ለአዲስ አበባ ይሆን ? ይሁን መቼስ።
ከሁሉ የገረመኝ አብረው የሚሄዱት ፈረንጆች ናቸው። ቱታ ለብሰው፣ አሮጌ የቴንስ ጫማ ተጫምተው ዘና ብለው ለመንገድ ተዘጋጅተዋል። ጥፍርም አላስተከሉ፣ አዲስ ልብስ አልገዙ፣ በታኮ ጫማም አልተደናቀፉ። ዜጎቻችን የሰባቱን ሰዓት ጉዞ የለበሱት፣ የተቀቡት፣ እንዳይበላሽ ሲጨነቁ ፈረንጆቹ በሰላም ሊደርሱ ነው። እንዲውም አንዱ ከላይ የሃገራችን መስቀል የተጠለፈበት ሸሚዝ ነው ያደረገው። ወይ እንደ ፈረንጅ መሆን።
ከተጓዦቹ ማህል አንዳንዶቹን በዓባይ ግድብ ቦንድ ሽያጭ ወቅት ፍራንክፈርት (Nordweststadt saalbau) በተደረገ ወቅት እየተንደረደሩ ሲገቡ በውጭ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ነበርንና ሰልፈኛው ሆዳም ሆዳም ብሎ ሲሰድባቸው አይቻቻዋለሁ። እነርሱም ሰላዩኝ ይህንን ካነበቡ ማንን ማለቴ እንደሆን ይገባቸዋል።
ወደ አውሮፕላኑ ሲገቡ የተለያየ ሁኔታ መገንዘብ ቻልኩ። አንዱ የባለቤትነት፣ ሌላው ደግሞ የእንግድነት። ቀደም ፣ ቀደም ብለው በድፍረት የሚሄዱ አሉበት፣ እንደ እንግዳ እየተሽኮረመሙ የሚገቡ አሉበት፣ እንደ እውነተኛ ነጋዴ የሚዝናኑ አሉበት፣ አስመሳይ ኢንቬስተሮችም አሉበት፣ ለመዘነጥ የሚሄዱ አሉበት፣ እውነተኛ የሃገር የቤተሰብ ፍቅር አንገብግቦት የሚሄድ አለበት፣። ሁሉም ድብልቅልቅ ያለ ነው። ስንቱ ይሆን ሱሱን ለማርካት የሚሄደው? ዋናው ጥያቄዬ እሱ ነበር።
ባለፈው ሳምንት በድረ ገፆች እየተዘዋወርኩ ሳነብ <<አዲስ አበባበ ህገወጥ ልማዶችና የወሲብ ድርጊቶች እየተናጠች ነው !!! >> በሚል እርዕስ ያነበብኩት ትዝ አለኝ። እንዲህ ይላል፡ -
ግብረሰዶም ከሚገመተው በላይ በከፍተኛ መጠን እየተስፋፋ ነውአብዛኞቹ የከተማዋ ማሳጅ ቤቶች የወሲብ ንግድ እንደሚያጧጡፉ ታውቋል። ከ3600 በላይ ህገወጥ ልማዶችና የወሲብ ድርጊቶች የሚፈፀምባቸው ቤቶች አሉ። ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ፖሊሶችና ነጋዴዎች የአነቃቂ እፆች ተጠቃሚ ናቸው።በእርቃን ጭፈራ ቤቶች ደጃፍ ከሚቆሙ መኪኖች አብዛኛዎቹ የመንግስትና የንግድ ታርጋ የለጠፉ ናቸው። በአዲስ አበባ ህገወጥ ተግባራት የሚከናወኑባቸው ቤቶች በከፍተኛ መጠን እየጨመሩ ምጣታቸውንና ከተማዋ አደጋ ላይ እንደሆነች ሰሞኑን ይፋ የተደረገ ጥናት አረጋገጠ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትናንትናው ዕለት ይፋ የተደረገው ጥናት “መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለይም በወጣቶችና ሴቶች ላይ እያስከተሉት ያለው አሉታዊ ተጽእኖ” በሚል ርዕስ የተካሄደ ሲሆን ከ3600 በላይ ህገወጥ የወሲብ ድርጊት የሚፈፀምባቸው ቤቶች እንዳሉ ጠቁሟል፡፡
ይህ ሁሉ አስከፊ ድርጊት ወደ ሃገሪቱ እንዴት እንደተዛመተ መገመት ይቻላል። ጥናቱም <<መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች>> በሚል አስቀምጧቸዋል። አንዳንድ ዜጎቻችንን ከውጭ እየያዙ የሚገቡትን አንዳንድ መጥፎ ተግባራት በአላቸው ገንዘብ በመጠቀም በእርካሽ አገር ውስጥ ስሜታቸውን አርክተው ግን ወጣቱን ትውልድ ወደ ውጭ እናወጣኻለን በሚል አበላሹት። ፈረንጆቹም ቢሆኑ ከእንደዚህ ዓይነት ተግባር የጸዱ አይደሉም። ወያኔ ደግሞ እንዲዚህ ዓይነት ብኩን ዜጎች መብዛታቸው ያስደስተዋል እንጂ አያስከፋውም። ሊያምጽ የሚችለውን ወጣት በሱስ ማደነዝ ቀዳሚ ተግባሩ ነውና።
እነዚህ ሁሉ ሲመለሱ ደግሞ የሃገሪቷን ሁኔታ በተለያ መነጽር መመለከታቸው አይቀርም። ለመዘነጥ የሄደው ፣ስለዘናጩ ብዛት ይነግረናል፣ ነጋዴው ስለነጋዴው የተሳካ ኑሮ፣ ኢንቨስተሩም እንዲዚሁ። የዛችን ሃገር ፣ የዛን ሕዝቡ ሰቆቃ ለማየት ያልፈለገ አያየውምና ተንጋግተው እንደሄዱ፣ ተንጋግተው ይመለሳሉ። ይህ መንጋ እውነቱን እንዳያይ፣ አዲሱ ጸጉሩ ፣ አዲሱ ጥፍሩ ፣ አዲሱ እሱነቱ የጥንቱን ማንነቱ ይሸፍንበታል። ችግር ከሃገሪቱ ጠፍቷል ብሎ ይቀደዳል። የተቃዋሚዎችን ስህተት እያጎላ ይሰብካል። ይህ በወያኔ የተሰጠው ሃገርን የማጥፋት ፍቃድ እንዳይቀርበት በሚያምበት ሁሉ ይሳላል።
ይህ ዝርክርክ፣ ግትልትል ዜጋ ትንሽ አፍ እላፊ ከተናገረና የወያኔን ማንነት ካጋለጠ ይህ ኑ እንታያይ የዝንጣ ኑሮ ሊቀርበት ሰለሆነ እንደ ዘመኑ ቋንቋ ጎመን በጤና! እያለ እየዘፈነ ይኖራል። ከዛም አልፎ የግድብ ቦንድ ገዥ፣ ለመለስ ሞት በየኤምባሲው ደረት መቺ ቢሆን አይደንቅም። ወያኔም ይህ ሽቅቅርቅር የዲያስፖራ ቡድን የተቃዋሚውን ትግል ለማዳከም መርዙን ለመርጨት ይጠቀምበታል።
ወገን እስከመቼ ነው እንደዚህ የምንኖረው?
እነርሱ ከገቡ በኋላ የእኔም ተራ ደረሰና ወደ አውሮፕላናችን ገብተን የለንደን ጉዞ ። እና የስደት ኑሮ ቀጠለ ! አውሮፕላኑ ውስጥ በእውቀቱ ስዩምን አስታወስኩ። ቆዳ ጃኬትና መነጽር አጥቶ ይሆን? የሃገር ልብስ ለብሶ ለንደን ውስጥ ለኦለምፒክ የተጋበዘ ጊዜ በየስብሰባው የሚሄደው። በሚቀጥለው ሳገኘው እስቲ እጠይቀዋለሁ።
ሰለዛች ሃገር የሚያስብ ሁሉ በሰላም ይክረም!
ፍራንክፈርት
ጃንዋሪ 13/2013
No comments:
Post a Comment