ይድረስ ለእስልምናና ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች
ይሄይስ አእምሮ(yiheyisaemro@gmail.com)
ከሁሉ በፊት የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ2005 የአረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤
ኢሣት ኢትዮጵያ ውስጥ በመዘጋቱ ምክንያት ስንት ነገር አምልጦኛል ለካንስ እባካችሁ? ይህችነን ማስታወሻ ለመጻፍ አስቤ ብዕሬን ከወረቀት ላዋድድ ስል ከዜናና ከዜና ትንታኔው በኋላ ትቼው የተለየሁትን ይህን የኢትዮጵያ የወቅቱ ብቸኛ መተንፈሻ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተመልሼ እንድከታተል ባለቤቴ ስትጠራኝ “ተይኝ ባክሽ ሌላ ሥራ አለብኝ” ብላት ስሜቴን ስለምታውቅ “ታማኝ መጣልህ!” አለችኝና የመከታተል ወይ ያለመከታተል ምርጫውን ለኔው ትታ ወደሥራዋ ገባች፡፡ በዚህ ረገድ በደንብ ታውቀኛለችና እንድመለስ ሌላ ቃል አልጨመረችም፡፡ በዚህች አባባል ሌሎች በመንፈስ እንጂ በሥጋ እንዳትቀኑ አደራችሁን – “ወላድ በድባብ ትሂድ! የታማኝ እናት ደጋግመሽ ውለጂ! ቢስ አይይብን፡፡ የልጅ ዐዋቂ ነህና ከዐይን ይጠብቅህ፡፡” አሜን በል ወንድማለም፡፡ ከአሜን ይቀራል አሉ፡፡
ታማኝ – ወይ ጉድ ስም ይቀድሞ ለነገር አሉ – በኦነግና በግንቦት ሰባት ጥምረት በተደረገ ስብሰባ ተገኝቶ ያደረገውን ንግግርና ስብከተ ሀገር ነበር ኢሣቶች እያቀረቡ የነበረው – የቆዬ ዝግጅት ነው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ የምንኖር ዘጎች ከተናጋሪ እንስሳነት እምብዝም የማንለይ – ኧረ እንዲያውም እነሱ ከእኛ የሚሻሉበት ብዙ ነገር አላቸው – በመሆናችን ሁሉም የዜና ማዕከላት ተጠርቅመው የወያኔን ቅርሻት ብቻ እንድንሰማና እንድናይ ስለተፈረደብን በወቅቱ አላየሁትም፡፡ አሁን ግን ዕድሜ ለዲያስፖራው የኢትዮጵያ ሕዝብ – በኢሣት ጥረት የተደበቁ ዜናዎችንና መረጃዎችን መከታተል ጀምረናል፡፡ ይህ የዜና ተቋም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁለንተናዊ አቅም ያላችሁ ዜጎች እባካችሁን አንድነታችሁንና ኃይላችሁን አስተባብራችሁ ታገሉ፤ ሁሉም ያልፋል፡፡ የማያልፈው ግን አጥርን ዘልሎ የሚሻገር የመልካም ወይም የክፉ ሥራ ውጤት ነው፡፡ የዚህ የተገፋ ሕዝብ የየጨለመ የመኖር ተስፋ ብታለመልሙ ፈጣሪ ወሮታውን ይከፍላችኋል፡፡ የአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ጉዞ የሚጀመረው በአንድ ሜትር ነውና አንዳንድ ጨለምተኞች “ወሬ ምን ዋጋ አለው! በወሬ ሆድ አይሞላም…” ቢሉም ብዙም ጆሮ አንስጣቸው፡፡ መጽሐፉ “እስመበተስፋሁ ሀደረት ሥጋየ” ይላልና የነጻነታችን ፋናወጊ የመረጃ ምንጭ የሆነውን ኢሣትን በየአቅማችን እንርዳ – እርግጥ ነው ድረ ገፆቻችንንም ሳንዘነጋ፡፡ ምርጫም የለንም፡፡ ምርጫ ከተባለም ያለን ሌላውና ብቸኛው ምርጫ በቦሌም በባሌም ብለን ባከማቸነው ገንዘብ የተንደላቀቀ ኑሮ እየመራን እንደከብት እያመነዠክን እንደዓሣም ያገኘነውን መጠጥ እየማግን መኖር ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንስሳነት ነው፡፡ ይህ ከጤናማ ሰውነት የወረደ ወያኔያዊ ባሕርይ ለታሪክ ፍርድ አመቻችቶ ይተወናል፤ ለኋላ ፀፀትም ይዳርገናል – ‹ኋላ› ለሚባል ነገር ለምንደርስ፡፡ አንዳንዴ ‹ፊተኛ›ን ብቻ ለሚያውቅ ግብዝ ፍጡር ‹ኋለኛ› የሚባል ነገር ስለመኖሩም አይገባውም፤ ሁለቱንም ኑባሬያት በነቢባዊና ተግባራዊ አንድምታቸው የሚያውቅ ሰው የተረጋጋና ለየትኛውም መቼት የሚያበቃ ሕይወትን መርቶ በፊተኛውም በኋለኛውም የመኖርና ያለመኖር የሕይወት ቅምብቦች ውስጥ ዘወትር እየተወደሰና በሠናይ ምግባሩ እንደ አብነት እየተወሳ ዘመድ አዝማድንና ሀገርን አኩርቶ እስመለዓለመ ዓለም ይኖራል፡፡ (ታማኝ በርቺ – ጀምረሻል – እንዳትንሸራተች የኢትዮጵያን አምላክ ጠበቅ አድርገሽ ያዢ!! በተንሸራታች ፋብሪካ ሀገር ጥንቃቄና ምርመራ ውስጠት ዘወትር ካልታከለ ችግር ማስከተሉ አይቀርምና ራስን በየወቅቱ መፈተሽ፣ ራስን ብቻ ሳይሆን ግራ ቀኝን – ባላንጣን ጭምር ማዳመጥ ይገባል፤ ትምክህትን በፈጣሪና በምስኪን ሕዝብ ያደረገ ወድቆ አይወድቅም፡፡ ብዙዎች የአሁን ኢትዮጵያውን ደግሞ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ፍጡራን መሆናችንን ለማወቅ ይህች ጦማር በአንዱ ድረገጽ እስክትለጠፍ መጠበቅ አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ መንጌ ምን አለ? ‹ሀገሬን ለሰው አልሰጥም አለ› ብለህ እንዳትቀልድብኝ፤ ከርሱ ቀጥሎ ያለው ቁም ነገር አለ … ወርቅ ቢያነጥፉለት … ችግሩ እነሱ እንደሚሉን እየሆንላቸው የተግባራቸው ብቻም ሳይሆን ለትንቢቶቻቸውና ለዕብሪት ንግግሮቻቸው እውናዊነትና ተፈጻሚነት አጋር መሆናችን ነው፡፡ ለሁሉም ግን ተስፋ መቁረጥን ራሱን ተስፋ እናስቆርጠውና ለእውነት ልዕልና ቆርጠን እንነሳ … የቀረበው የነጻነት ቀን ልደት በምንም መንገድ አይጨነግፍም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ… ግን ጽንሱ ከታሪክ ማኅጸን በቅጡ እንዲወጣ ልምድና ዕውቀት ያላቸውን አዋላጆች ከዬአህጉሩ እየፈለግን በማሰባሰብ እንደስካሁኑ መደዴና ስድ አደግ ሁሉ እጁን ሳይታጠብና በቂ ችሎታ ሳይኖረው ማዋለጃ ክፍል ውስጥ እየገባ ችግር ከመፍጠሩ በፊት እውነተኞቹ ባለሙያዎች ዕድል እንዲያገኙ እናድርግ፡፡…)
ትናንት ማታ የዶክተር ብርሃኑንና የፋሲል የኔዓለምን ውይይት ተመለከትኩ – ግሩም ነበር፡፡ ግን ፋሲል ግማሹን ቃለ መጠይቅ በአንተ፣ ቀሪውን ደግሞ በአንቱ በማካሄዱ እንደመዝናኛም ቆጥሬ ፈገግ ብያለሁ፡፡ ወጥነት እንዲኖር ለማሳሰብ ፈልጌ ነበር ግን ቀላል ጉዳይ ስለሆነ ተውኩት፡፡ ለነገሩ ቀረቤታንና አክብሮትን በአንድ መድረክ በማሳየቱ በጨዋታነት ደረጃ ደስ ይላል፡፡ ይህችን ነቁጥ ነገር ለትችትም የሚያበቃት ሰው አይጠፋ ይሆናል እኮ፡፡ አደራ እኔ ለቀልድ ነው እያነሳሁ ያለሁት!
በነገራችን ላይ የ24 ሰዓት የዜናና የሀተታ አገልግሎት ዝግጅት በጣም ከባድ ነው፤ የሰው ኃይል አለ፤ የማቴርያልና የበጀት ጉዳይ አለ፤ ብዙ ተያያዥ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ኢሣት በቢሊዮን ዶላሮችና በሺዎች ሠራተኞች እንደሚንቀሳቀሱት የአልጀዚራና ቢቢሲ ጣቢያዎች እንዲሆን መጠበቅ አይገባንም፡፡ በአቅም ውስጥ ግን የሚቻለውን ያህል መንቀሳቀስ ይቻላል፡፡ እናም በበኩሌና በዚህ አጋጣሚ ይህ ጣቢያ ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ ሕጻናትን፣ አረጋውያንን… በጥቅሉ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል እንዲይዝ በብልሃት ቢመራ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ለምሳሌ በቀደምለት ‹ፈረቃ› በሚል ርዕስ የነዶኪሌን ቀልድ ስመለከት በጣም ደስ ብሎኛል – ደስ የማይለው ደግሞ ሊኖር ይችላል፡፡ ግን ለኔ ሲል ይታገሳል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስፖርት ለኔ ብዙም አይጥመኝም – ስሜቴ በአብዛኛው በሀገሬ ላይ ስላረፈ ከመዝናኛ ቀልዶችና ጭውውቶች ወጣ የሚሉ ሌሎች ዝግጅቶች እምብዝም አይስቡኝም፡፡ ለሌሎች ስል ግን እታገሳለሁ – እከታተላለሁም፤ የፖለቲካ ትንተና ሲጀመር ግን አፌን ከፍቼ ላነጋ እችላለሁ፡፡ በመሠረቱ ሁሉን ማስደሰት ከባድ ነው – በተለይ ሰውን፤ በተለዬ በተለይ ደግሞ የዘመኑ ኢትዮጵያውንን – እንዴ፣ ለይቶልን የጥንቶቹን ባቢሎንያውያንን ሆነናል እኮ፡፡ … ይሁንና በአስተያየት መስጫ መድረኮች የሚሰሙ ጥቆማና አስተያየቶችን በጥሞና ማዳመጥ ሲቻልም ለመቀበል መሞከር መልካም ነው፡፡ በኢንስትሩመንታል ሙዚቃ ብዙ ጊዜ ባይባክን፣ ከየብሔረሰቡ ማራኪ ዘፈኖችና ውዝዋዜዎች በፕሮግራም ማሸጋገሪያነት ቢገቡ፣ የነልመንህና አለባቸው፣ የነደረጀና ሀብቴ፣ የሌሎች ሀገሮች አርቲስቶች ቀልድና ጭውውቶችም ቢዘወተሩ… ጥሩ ነው፡፡ በተነሱበት ያልተነሱበትን መናገር በኔ አልተጀመረም፡፡
መነሻየን የሚከተል ሌላ ጉዳይ ላክልና ወደ ዋናው ጉዳይ ልንደርደር፡፡
እንደውነቱ ከሆነ ብዙ ጊዜ ልጻፍ እልና በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚው ሰው ቁጥር ተስፋ አስቆራጭ በመሆኑ ማን ያነበኛል በሚል እተወዋለሁ፡፡ የሀገራችን ወጣትና ጎልማሣ አንዳች ጠበል ካልተረጨ ወይም በወያኔ የተራገፈብን አፍዝ አደንግዝ ካልተነሳልን የሀገር ውስጡ ነገር አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ አብዛኛው ዜጋ በሚያሳፍር ሁኔታ ለሆዱና በሆዱ ምክንያት ታስሮ ቢኮረኩት እንኳን ለመሳቅ ጊዜ የሌለው ሆኗል፡፡ ኢንተርኔት ካፌዎች ብትገቡ ሰው ከአፍ እስከገደፋቸው ጢም ብሎ ሞልቶ ታገኛላችሁ – በተለይ ወጣቱ፡፡ ግና የሀገራችን ወጣት ምን ነካው ብለን እስክንገረም ድረስ ከሞላ ጎደል ሁሉም የሚፎሰቡከው ፆታዊ ግንኙነትን ማዕከል ያደረገ ትርኪ ምርኪ ነገር ላይ ነው፡፡ ሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳይ ይቅርና የረባ ቁም ነገር የሚፎሰቡክ ለማየት አንገትህ እስኪቀነጠስ ዙሪያ ገባህን ብዙ ብታማትር ማግኘት ይሳንሃል፤ ተረግመናል፡፡ እኔ ብዙ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ዳሰሳ ጥናት ለማድረግ ሞክሬያለሁ – በጨረፍታና በስለላ መልክ፡፡ ይሁንና ከዘመድ አዝማድና ጓደኛ ተራ የኢሜል ግንኙነትና ከወሲባዊ የፍቅር ጨዋታ እንዲሁም ከዚሁ ያልወጡ ግትርና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ምልከታ በስተቀር በፕሮክሲዎች ገብቶ የተቃውሞ ድረገጾችን ለመፈተሽ የሚደረግ ሙከራ አልታዘብኩም፤ እርግጥ ነው ፍርሀትና የግንዛቤ ዕጥረት በመንስኤነት ሊጠቀሱ ይችሉ ይሆናል፡፡ የግብጾችንና ሌሎች የአረቡ ዓለም ወጣቶችን ስታስብ ደግሞ ተስፋህ እንደጉም ሊበንብህ ይችላል – ስለዚህ መፍትሔው እነዚያን ሀገሮች አታስብ ብዬ ነው የምመክርህ፡፡ ወያኔና ተቃዋሚዎች እግዜር ይይላቸው – በተለይ ወጣቱን ስሜትየለሽ አደረጉት፤ ግዴለሽ ዜጋ በዛ፡፡ ሆዱ ከሞላ ለሌላ የማያስብና ለሀገር ቀርቶ ለራሱም የማይጨነቅ ነሁላላ ዜጋ እየተበራከተ መጣ፡፡ በጁ ቆንጨራና ጩቤ አታይም እንጂ ሰው በተለይ የንግዱ ማኅበረሰብ ድሆች ዜጎችን በጠራራ ጠሐይ እየከተፈ ይበላው ይዟል፤ በይውና ጠጪው አሥረሽ ምቺው ላይ ነው – ‹ነገ ዓለም ታልፋለች› የተባለ ይመስል፡፡ የቢሮ ሠራተኛው ሁላ በእጅህ ካልሆነ በእግርህ ሄደህ ጉዳይህን አይፈጽምልህም፡፡ የሚኖሩት በሚሞቱት ላይ እየጨፈሩ ሲታይ ሀገርና ሕዝብ ያሉ ይመስላሉ እንጂ ሁሉ ነገር አብቅቶልናል፡፡ እንደሕዝብም እንደሀገርም ትናጋችን ተዘግቶ ኅልውናችን ቀጥ ሊል የቀሩት ሐሙሶች ከሁለትና ከሦስት የሚበልጡ አይመስልም፡፡ ‹ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል› እንዲሉ ሆኖ እንጂ በቁማችን ሞተናል ብንል አልዋሸንም፡፡ እንደዘመነ ሶዶምና ገሞራ ልንሆን ነው መሰለኝ፡፡ አንዱ አንዱን እየበላ ገንዘብ ከማካበትና ሌትና ቀን በየዝጉብኚው ዳንኪራና ጮቤ ከመርገጥ በስተቀር አቅልን ገዝቶ ስለሀገር ቆም ብሎ የሚያስብ ሰው እየጠፋ ነው – በሀገር ቤት ውስጥ በተለይ፡፡ ምሁር ተብዬውም በዬወረቀቱ ተሸጉጦ ለዕለታዊ ጉርስና ለዓመታዊ ልብስ የምትሆነውን ሶልዲ የሚያገኝበት “የጥናትና ምርምር” ሥራዎችን በከተፋ – በኮፒ ፔስት የዘመን አመጣሽ ‹ምሁራዊ› ልክፍት ተጠምዶ – ከማምረት በስተቀር ይህ ነው የሚባል የረባ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ሥራ ሲሠራ አይታይም፡፡ ሀገሪቱ በርግጥም የወላድ መካን የሆነች ትመስላለች – ዛሬ! ስለነገው በአቤቶኪቻዊ አባባል በአዲስ መስመር እንገናኝ፡፡
የነገው ግን በርግጠኝነት ሌላ ነው፤ ከአሁኑ እንቅልፍና ስንፍና ብዙ የተማረ አዲስ ትውልድ ሲፈጠር ወይም የአሁኑ ከተኛበት ሲነቃ ኢትዮጵያ ልዩ ሀገር ትሆናለች፡፡ የቀኝ ኋላው ዙር ዐዋጅ ሲታወጅ በርግጠኝነት የመከራችን ደመናና ጭጋግ ይገፈፋል፤ ወያኔ የጀመረውን ጉዞ በቅርቡ ሲያጠናቅቅ ሁላችን ከየተሸጎጥንበት የጥፋት ጭምብልና ከየመሸግንበት የፍርሀት ዋሻ ስንወጣ – ማንና የት እንደምንገኝ ስንገነዘብ – ያኔ ያለንን ሁሉ አቀናጅተን በምንፈጥራት አዲሲቷ ኢትዮጵያ አዲስና የተከበረ ስብዕና ይኖረናል፤ በወያኔው የተዋረደው አሮጌው ስብዕናችን ከነዘረኝነቱና ከነሃይማኖታዊ የቁርቋሶ ቱማታው እንክትክቱ ወጥቶ ወደመጣበት ወደ ሀገረ ሳጥናኤል ሲመለስ ያኔ ዐይናችን ይበራል፤ ድንቁርናችን በዕውቀትና በማስተዋል ይተካል፤ የግላዊ ብልጽግና የተናጠል ሩጫችን እንደአሁኑ በዘርና በጎሣ በተቀነበበ ይሉኝታቢስነት አንዲትን ሀገር የብቻ ቁጥጥርና ዐይን ያወጣ ዝርፊያ ላይ ሳይሆን የንግድም ሆነ አጠቃላዩ የኢኮኖሚ ግንኙነት ለሁሉም ምቹ ሁኔታን በሚፈጥር የተስተካከለ የውድድር ሜዳ ላይ በሚከናወን የግልና የወል ሕጋዊና ሚዛናዊ ጥረት ላይ የሚመሠረት ይሆናል፡፡ የወደፊቷ ኢትዮጵያ በእኩልነትና በነጻነት የምንኖርባት የሁላችንንም የልብ ትርታ በሚያዳምጥና አንዳችም አድልዖ በማይኖረው ሀገራዊ የጋራ ሕግ ታስተዳድረናለች፡፡
አሁን በአዲስና ተለዋጭ ርዕስ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ከእውነት ገባሁ፡፡
የፋሲካው በግ በገናው በግ ይስቃል
ሰሞኑን በሙስሊሙ ማኅበረሰብና በመለስ ዜናዊ የሙት መንፈስ በሚታዘዘው የወያኔው ሥውር(abstract) መንግሥት መካከል የጦፈ ግጭት እንዳለ ይወራል፡፡ ይህም የሚደመጠው ድረገጾቻችንን ጨምሮ ኢሣትን ከመሳሰሉ የውጭ የዜና ማዕከላት እንጂ የሀገር ቤቱ የወያኔ የውሸት ወፍጮማ ሁሉም ሰላም እንደሆነ ነው ሰርክ እየተደሰኮረ ያለው፡፡ ይህ ሃይማኖትን ተመርኩዞ የተቀሰቀሰ ግጭት ወዴት ሊያመራ እንደሚችል መጨረሻው ወደፊት የሚታይ ሆኖ በተለይ ስለእስልምናና ክርስትና ሃይማኖቶች (በኢትዮጵያ) ትንሽ ነገር መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ግጭቱ የሃይማኖት ሳይሆን የመብት ረገጣ የወለደው የአትንኩኝ ባይነት ትግል መሆኑን አምናለሁ፡፡ ወያኔ ዜጎችንና ጦርነትን በቆረጣ መግጠሙ ዛሬ የጀመረው አይደለም፡፡ ጠላቶቹ ተቆጥረው አያልቁም፤ የሚገጥምበት ሥልት ግን በተራና በቆረጣ ነው፡፡ ይህን የተበላ ዕቁብ ሕዝበ ክርስቲያንና ሕዝበ ሙስሊም ካልነቃበት ራሱ ያልቅበታል፡፡ ወያኔ ተንኮለኛ ነው፡፡ ሃይማኖት የለውም፡፡ ሃይማኖት አለን የሚሉ ወገኖችን ግን እርስ በርስ ሊያባላቸው የአንዱ ዕንባ አባሽ መስሎ አንዱን ከሌላው ሊያጋጭ ይሞክራል፡፡ ሞኝ ካገኘ ይሳካለታል፡፡ ከተነቃበት ግን ራሱ ያልቅለታል፡፡ ይህን ነው ሁሉም ሕዝብ መረዳት ያለበት፡፡ በየተራ ማለቅ ነው የሚጠቅመው ዌንስ ተባብሮ የጋራ ጠላትን ልኩን እንዲያውቅና መብትን መርገጥን እንዲያቆም ማድረግ? ምርጫው የምዕመናን ነው፡፡
እንደደራሲ ሰርቫንቴስ የምናብ ፍጡር እንደዶን ኪሾት የሚመሰለው ወያኔ ይህን የሙስሊሞችን ጥያቄ በቀላሉ ሊመልሰው ሲችል ተፈጥሮው ከሁሉም ነገሮች ጋር(ሕይወት ካለውም ከሌለውም ጋር) የመጋጨት እንጂ ሰላምን የመፍጠር ባለመሆኑ ይሄውና የራሱን መቃብር እየቆፈረ ይገኛል፡፡ ወያኔ ሰዓት ስንት እንደሆነ እንኳ ቢጠየቅ – እንደተቋም – “ሰዓት መጠየቅ እንደአካሄድ ትክክል ሞሆን አለሞሆኑ አነጋጋሪነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ማን ነው ሰዓት ጠያቂው? የግንቦት ሰባት አባል ነው ወይንስ የመድረክ? ለምን ዓላማ? ሰዓት ጠያቂው ሰዓት መጠየቅ ከሽብርተኝነት ጋር ቁርኝት ሊኖረው እንደሚችል ያልተገነዘበበት ምኽኒያቱ ምንድነው? ሰዓት የተጠየቀው ለሽብር የሚጠመድን የ‹ሠ› ሰዓት ፈንጂ ለማስተካከል አለሞሆኑ እስኪረጋገጥ ሰዓት ጠያቂውና ዘመድ ወዳጆቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ከተጣራ በኋላ ሰዓቱ ሊነገረውም ላይነገረውም ይችላል…” ሊል ይችላል፡፡ ስለዚህ ወያኔን ምንም ነገር መጠየቅ በሽብርተኝነት ሊያስጠረጥር፣ ሊያስከስስና በታዛዥ ዳኞች – በሰው መሰል የወያኔ ሮቦት ዳኞች – ዕድሜ ይፍታህ ወይም የስቅላት ሞት ሊያስበይን የሚችል አደገኛ ወንጀል ነው፤ ‹ራበኝ አጉርሱኝ፣ ጠማኝ አጠጡኝ፣ ታረዝኩ አልብሱኝ፣ መንገድ አሳዩኝ …› በወያኔ በአሸባሪነት ሊያስጠረጥሩ የሚችሉ ‹ወንጀሎች› ናቸው፤ ይህ ዓይነት ዕንቆቅልሽ ፍጡር ለግማሽ ምዕተ ዓመት በሕይወት መኖሩ በርግጥም ያስደንቃል – በድንቃድንቅ ታሪኮች መዝገብም ሊሠፍር ይገባዋል፡፡ ወያኔ እኮ በማሰብህም የሚከስህ የመጀመሪያው የዓለማችን ጉድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራቸው ደግሞ በነጻነት መናገር እንደቅንጦት የሚቆጠር ሆኖ እንዲሁ ማሰብም መብላት መጠጣትም የማይቻልባት የመጀመሪያዋ ሀገር ናት – ለኢ-ወያኔያዉያን ነው ታዲያ፡፡ ኢ-ወያኔነት ደግሞ በእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት የሚያገኙት የሚከብድ ሸክም እንጂ በዘርና በሃይማኖት ተፈጥሯዊና የግል ጉዳዮች የሚወሰንና ለተመረጡ ብቻ የሚሰጥ ምንዳ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ሙስሊሙም፣ ክርስቲያኑም፣ አማራውም፣ ኦሮሞውም፣ አደብ ካልገዛና የወቅቱን በረከተ መርገም ከአሌታዊው(ዘረኛ) ሥርዓት ተለጥፌ ከርሴን አልሞላም ብሎ ከቆረጠ ትግሬውም ጭምር ከዚህ ወያኔያዊ የጭካኔ በትር አያመልጡም – አብዮት ልጆቿን የመብላቷ መዝሙር በደርግ ዘመን ብቻ ተዜሞ አልቀረም፡፡ ወያኔን ያልመሰለና ያልሆነ አሣር ይደርስበታል፡፡ በምንም ሁኔታ ተከፋፍሎ መገኘት ለወያኔው ዱላ ይበልጥ ምቹ መሆን ነው፡፡ አለመተባበር መሰባበርን እንደሚያስከትል ዶክተር መራራ አስቀድመው አስታውቀዋል- ለሚገባው፡፡ ግን ግን አፍዝ አንግዟን ማን ወንድ ይፍታት! ለነገሩ ከላይ የመጣው ከላይ ካሉት ፍትሃቱን ጀምሯልና ዋናው መታገስ ነው – ‹እናያለን ገና› ብሏል አቀንቃኙ፡፡ በጊዜ የተመለሰ ብቻ ይድናል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ ነው እንግዲህ ሙስሊሞች መብታችን ይከበር ሲሉ ክርስቲያኑ ፀጥ ረጭ ብሎ የሚታየው፡፡ ሁለቱም መታረዳቸው የማይቀር በጎች ናቸው – የገናና የፋሲካ በጎች፡፡ ነገር ግን የፋሲካው አንድ ሦስት ወሮች ያህል ዕድሜ ስላሉት እየታረደ ባለው የገናው በግ ይስቃል ይባላል – በምሳሌያዊ አነጋገሩ፡፡ ለነገሩ በግ ባኣኣ ይላል እንጂ አይስቅም፡፡ እኛም ክርስቲያን ነን የምንል ወገኖች እየሳቅን ሳይሆን ባኣኣ ባንልም ዕርዱ እንደማይቀርልን ተገንዝበን በማጉረምረም ላይ የምንገኝ የወያኔ ጭዳዎች ነን፡፡ ዝምታን ድጋፍን ሳይሆን በአብዛኛው ተቃውሞን እንደሚተቁም መገንዘብ ተገቢ ነውና የቁርጡ ሲመጣ ሙስሊሞች አጋዥ የለንም ብለው እንዳይሰጉ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ይልቁናም ሁለቱም ሃይማኖቶች መጠንቀቅ የሚገባቸው በውስጣቸው የሚገኙ የሁለት ጫፍ አክራሪዎችን ነው – ትልቁ መጥፎ ነገር ዘመድ መስሎ የሚቀርብ ጠላት ነው፡፡ የአክራሪነት ምንጭ ደግሞ የተወሳሰበ ነው – ያንተ ‹አክራሪ›ና የኔ ‹አክራሪ› የኛ አለመሆናቸውን ምናልባትም ከጋራ ጠላታችን የተላኩና በውስጣችን የሠረጉ ምንደኞች መሆናቸውን የምናውቅበት መንገድ ለሰላምና ለብዙኃን ድምጽ አንገዛም ያሉ እንደሆነ ነው፤ ‹አጭበርባሪ አይተኛኝም› ያለችዋን የሴተኛ አዳሪዋን ምሳሌ መቀበል ከብዙ ጉዳት ይሠውራልና ጠንቀቅ እንበል ጎበዝ፡፡ አክራሪነት በየትኛውም ሁኔታ ጎጂና አፍራሽ ነው፡፡ አክራሪ ክርስቲያን ይጠንቀቅ፤ አክራሪ እስላምም ይጠንቀቅ፡፡ አለበለዚያ ያከረሩት ነገር ሲበጠስ ከነአክራሪው ነው ገደል የሚከተው፡፡ አክርሮ ዘወር የማይባልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ሁልጊዜ ጌትነት የለም፡፡ … ወያኔን ስለምናውቅ በሌሎች መጨፍጨፍ የምንደሰት ጤናማ ዜጎች በመካከላችን አንኖርም፡፡ ግን የወያኔ ፕሮፓጋንዳና ለዘመናት የተረጨብን ፍርሀትን የሚያነግሥ ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም ከደርግ ጀምሮ የወረደብን የልጆቻችንን ሬሣ ሳይቀር ከመንግሥት የመግዛት አረመኔያዊ ድርጊት ሰንገው ይዘውን አንዳችን የአንዳችንን መከፋት ተከትሎ ብቻም ሳይሆን እኛ ራሳችን እየተገረፍንም ቢሆን ላለመጮህና ተቃውሞኣችንን ላለማሰማት የማልን እንመስላለን፡፡ እንጂ ይህ ወቅት ሁላችን ሃይማኖትና ብሔር ሳንል ሁላችን በህብረት ‹ሆ› ብለን በመውጣት ይህን አናቱ ተቆርጦ የተጣለ የቀትር እባብ ወያኔ ቆራርጠን የምንጥልበት ዘመን ነበር፡፡ መቆራረጥ ሲባል ሥጋዊ ትርጉም ሳይሆን መንፈሳዊ ፍቺን እንዲይዝልኝ እወዳለሁ፡፡ መቆራረጥ ክፉ ሃሳብን ነው – አካልን አይደለም፡፡ አካል ቢቆረጥ አካልን ይተካል፡፡ ክፉ አስተሳሰብ ከተቆረጠና ከተወገደ ግን የወደፊቱ ትውልድ ከመሰል ዕኩይ ፍልስፍናና ጠማማ አስተሳሰብ ይድናል፡፡ መቆራረጥ የሚለያየንንና የሚከፋፍለንን የወያኔን የዘውገኛነት ልክፍት ነው፤ መቆራረጥ ሀገርንና ሕዝብን ለከፋ ችግር የሚዳርግ የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን የሆድ አምላኪነት የአስተሳሰብ ደዌ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እስልምናና ክርስትና በሰላም ኖረዋል፡፡ የሃይማኖቶች በሰላምና በፍቅር የመኖር አርአያ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በአንዳንድ ወቅቶች በዚህ ወያ በዚያ ሃይማኖት ተከታይ ምክንያት አንዱ በሌላው ላይ የሚያደርስውን ጉዳት ከታሪክ ማኅደር ማስታወስ ይቻላል ፤ ግን የግጭትን ታሪክ እያስታወሱ የሻረ ቁስልን ከማንቆርና ቂም በቀልን ከማጫር ይልቅ ያሳለፍናቸውን የፍቅርና የደስታ፣ የመተሳሰብና የመተዛዘን ገጽታዎችን እያወሱ ተንኮለኞች ከቀደዱልን የጥፋት ቦይ መውጣት ነው የሚበጀን፡፡
አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ፡፡ የአንድን ሰው ወይም የአንድን ማኅበረሰብ ሃይማኖታዊና ዘውጋዊ ማንነት በተመለከተ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ንጹሕ ዘርና ንጹሕ ሃይማኖት የሚባል ነገር በጭራሽ የለም፡፡ በዘመናት የአብሮነት ሕይወት ምክንያት ሁሉም ተባዝቆ ተባዝቆ ተቀላቅሏል፤ አንዱን ከሌላው ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ ተዋህዷል – የኔን ብነግራችሁ ትገረማላችሁ፡፡ አንድ ወቅት የአፋሩ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ አባት አሊሚራህ እንዲህ አደረጉ አሉ፡- ሁሉም ሰው በዬሽብራሩ ወተት እንዲያመጣ አደረጉ፡፡ ሁሉም ያመጣውን ወተት ወደ አንድ ትልቅ ማጋቢያ እንዲገለብጥ አዘዙ፡፡ በኋላም ሁሉም ሰው ከዚያ የወተት ጋን ውስጥ የራሱን ወተት እየለዬ ባመጣበት ሽብራር መልሶ እንዲወስድ አስታወቁ፡፡ ሰው ሁሉ በአግራሞት ተጨንቆ “እንዴ! እንዴት ይታወቃል? ተደበላለቆ የለም እንዴ አባታችን?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ያም ብልሁ የሀገር አባት “የኢትዮጵያ ሕዝብም እንደዚህ ነው! ሁላችንም ስለተዋሃድን አንዳችንን ከአንዳችን ለመነጠል አይቻልም” በማለት ሕዝባቸውን በጉልበትና በዐዋጅ ከጋጋታ ሳይሆን በጥበብ አስተማሩ፡፡ የኢትዮጵያን ባንዴራ እንኳን አፋሮች ግመሎቻቸው እንደሚያውቋት የመሰከሩትም ያን ጊዜ ነው፡፡
ዶክተር ብርሀኑ በትናንቱ ቃለ መጠይቅ (እንዴት ያለ ግሩም ቃለ መጠይቅ ነበር!) እንዳሉት ከሞላ ጎደል በሁላችንም ቤት እስልምናና ክርስትና አሉ – እንዲያውም ከነዚህም በላይ፡፡ የሃይማኖት ውርርሱ በጋብቻ ወይም በትውልድ ሐረግ ከአባት እናት የተወረሰ ወይም በማወቅና በይሁንታ ከአንዱ ወደ ሌላኛው በመዛወር የተገኘ ሊሆን ይችላል፡፡ በየትም ይምጣ ዋናው ነገር ግን የሃይማኖት ጉዳይ የግል እንጂ የሀገር አይደለም፡፡ ሁሌ እንደሚባለው ሀገር የጋራ ናት፡፡ ሃይማኖት ግን የግል ነው፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ አምስትም አስርም ሃይማኖት ሊኖር ይችላል፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ ግን አምስትም አስርም ሀገር ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ የማይቀላቀልን ነገር ማቀላቀል ለብንም፡፡ ቅድሚያ መስጠት ላለብን ቅድሚያውን እንስጥ፡፡
ዋናው ነገር ሃይማኖትም ሆነ የራሳችን ኅልውና ሊኖረን የሚችለው በቅድሚያ ሀገር ስትኖረን ነው፡፡ ሀገር ሊኖረን የሚችለው ደግሞ የግልና የቡድን ነጻነታችንን የሚያከብር ቢቻል በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ራሳችን የምንመርጠው ባይቻል እንኳን የልብ ትርታችንን የሚያዳምጥ ከእኛው የወጣ እኛኑ የመሰለ ሀገርና ዜጋ የማይሸጥ እንደመለስ ያለ ወፍዘራሽ የርግማን ውጤት ሳይሆን ሀገር በቀል የሆነ መሪ ሲኖረን ነው – እንደኃይለማርያምም የራሱን ማንነት ለመናኛ ጥቅም ያልለወጠ – እንደኤሳውም በምሥር ብኩርናውን ያልሸጠ፡፡ ዴሞክራሲ እዬዬም ሲዳላ ነው እንዲሉ ነው፡፡ ቀድሞ የመቀመጫዬን ብላለች ዝንጀሮ፡፡ አሁን እኮ ብዙዎቻችን ጨካኙን መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ሳይቀር እየናፈቅን ነው – አትታዘቡኝ እኔ መንግሥቱን መናፈቅ ከጀመርኩ ቢያንስ ሰባት ዓመት አልፎኛል፡፡ መንግሥቱ እኮ ሥልጣኑን አትይበት እንጂ ከመሬት ተነስቶ የ‹ዐይንህን ቀለም› እያየ ሞትና እሥራት ርሀብና ሥቃይ አያዝብህም ነበር – እንዴ፣ መንጌ እኮ በጭካኔው ካባ ሥር የነበረው የሀገር ፍቅርና የሕዝብ ወገናዊነት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፤ ሰውን መጥላትም ሆነ ማፍቀር በፈርጅ በፈርጁ እንጂ ሕጻኑን ከነታጠበበት ቆሻሻ ውኃ መድፋት ተገቢ አይመስለኝም(አንድ የኦሮምኛ አባባል ትዝ አለኝ፡- ‹አህያ እረዱ ቢሉን አህያ አረድን፣ አይጠቅማችሁም ቢሉን ጠራርገን ጣልን፣ እንዴ – ይጠቅማችሁ ነበር እኮ ቢሉንና ሄደን ብንፈልገው አጣነው› ይላል ይህ ቆንጆ ብሂል፡፡ አሁን መንጌን የት እናግኘው?(አቤት – ብዙ ሰው ሲንጫጫብኝ ታየኝ!)፡፡ ሰው የሚመሰገነው አንድም ሲሞት አንድም ሲለይ የሚባለው አውነት ነው፡፡ የራሳችንን ጨካኝ እንደዋዛ ሸኝተን አሁን የሰው ዘመሚትና ተምች አንበጣና የዓሣማ ግሪሣ በላያችን ላይ አነገሥን፡፡ ሰበቡ እኛ አይደለንም፤ ደግሞም እኛው ነን፡፡ የዘመን ዕንቆቅልሽ፡፡
እስላምና ክርስቲያን አንድ ነን አንድ አይደለንም ቅብጥርሶ የሚለው ክርክር ለተመቸው ነው፡፡ እኛ እሾህ ላይ ቆመን፣ የሲዖል እሳት ላይ ተቀምጠን የምንገኝ ዜጎች በመሆናችን ቢያንስ በአንድ የሥቃይ ቋት ውስጥ ገብቶ እንደሚወቀጥ የጋራ ዕጣ ተቋዳሽ ራሳችንን በመቁጠር በተናጠል ላለማለቅ በጋራ የጋራ ጠላታችን ላይ እንነሳ እላለሁ፡፡ ወያኔ የዘራብንን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ከቁብ አንጣፈው፡፡ መጀመሪያ ሀገር ትኑረን፤ ሀገር እንዲኖረን በማድረጉ ሂደት ጎን ለጎን የዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምሥረታ በሚመለከታቸው የሀገሪቱ ልሂቃን ይሠራ፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ ቀጣፊና አጭበርባሪ ወደሥልጣን የማይመጣበት አስተማማኝ የሕግ መደላድል በሀገራችን እንዲፈጠር ሁሉም ወገን ከዘርና ከሃይማኖት ግላዊ ጉዳዮች ተቆጥቦ በጋራ የኅልውና ማስጠበቂያ አውታሮች ላይ ይረባረብ፡፡
ታማኝ በየነን ጆሮ እንስጠው፡፡ ዛሬ ጧት ያዳመጥኩት የዛሬ ዓመቱ ንግግሩ አንጀቴን ነው የበላው፡፡ ለመቃወም ሲባል የተፈጠረ ሰው ካልሆነ በስተቀር ያን ንግግሩን መቼም የሚቃወም ሰው የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ድል ማለት አንዱት ትቶ ሌላውን አንስቶ ነውና ግላዊ ጉዳዮችን ወደጎን እየተውን አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ብቻ እንሰባሰብ፡፡ ያን ባናደርግ ተጎጂዎቹ እኛ ስንሆን ተጠቃሚዎቹ የጋራ ጠላቶቻችን ወያኔና መሰል የሀገር ውስጥና የሀገር ውጪ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ ጨው የሚጣፍጠው በጨውነቱ እስከቆዬ ድረስ ነው፡፡ ጨው ድንጋይ ነበር፤ ድንጋይም ጨው ነበር፡፡ ምርጫው የጨውና የድንጋይ ነው፡፡ ይህን ነባራዊ እውነት ዕንወቅ – ወቅቱን ጠብቆ ጨውም ጨው ድንጋይም ድንጋይ ይሆናሉ፡፡ የጭንቅላት ሥጋ መብሰሉ ለማይቀረው እሳት ፈጃል ይባላል፤ የኢትዮጵያ ጠላቶችም መቸ(ሸ)ነፋቸው ለማይቀረው ብዙ ‹ትግስት›ን እየጨረሱብንና ውድመትን እስያከተሉብን ተቸገርነ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሀገራችንን ይባርክ!
አላሁዋክበር! (እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን)