የለንደኗ ማሪያም ቤ/ክን ወዴት እያመራች ነው?
ከታምሩ ገዳ (ነጻ እና የግል አሰተያየት)
በምድረ እንግሊዝ በለንደን ከተማ የምትገኘው የርእሰ አድባራት ደብር ጽዮን ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ፈታኝ የሆኑ ችግሮችን
በመጋፈጥ ላይ ትገኛለች፡፡
የቤተክርስቲያኒቱን ስም በግል ስማቸው ለማዛወር ጥረት አድርገዋል የተባሉ ሁለት ምእመናን ከአባልነት ታገዱ፡
የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ለመስጠት ወደ ቤተክርስቲያኔቱ ግቢ ያቀኑ ሁለት አገልጋዮች ተቃውሞ ገጠማቸው ፡
የጸጥታ ሃይሎች በቤተክርቲያኒቱ ጉዳይ ሰሞኑን ሁለት ጊዜ ተጠርተዋል፡፡
ከተመሰረተች ከሶስት አስርት አመታት በላይ ያስቆጠረችው የደብረ ጽዮን ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን በሺዎች ለሚቆጠሩ
በለንደን እና በአካባቢዋ ለሚገኙ የኢ/ኦ/ተ/ ቤ/ክን አማኞች አምባ እና መጠጊያ በመሆን ስታገለግል ቆይታለች ፡፡የድንግል ማሪያምን
አምላጅነት አምነው የተማጸኗት በርካታ ምእመናን አያሌ ተአምራት ሲሰራላቸው እንደቆዩ በተቃራኔው ድግሞ የማሪያምን ጥቅሟን
የነኩ ወገኖች አይወድቁ አወዳደቅ እንደገጠማቸው እነዚሁ ማእመናን የመሰክራሉ፡፡ ይህቺ ለአብዛኛው ስደተኛ ማህበረሰብ በሃዘን
ሆነ በደስታ ጊዜያት መሰባሰቢያ እና መጽናኛ የሆነች ቅድስት ቤ/ክን ከአራት አመት በፊት በ1,700, 000 የእንግሊዝ ፓውንድ
(47,600,000 ብር ) የራሷ የሆነ ህንጻ ቤ/ክን ግዢ ሲፈጸም ብዙዎች ህልማቸው እውን መሆኑን በማየታቸው የደስታ እምባቸውን
አምብተዋል፡፡ ሁኔታውንም በጊዜው በግንባር ተገኝቼ ለተለያዩ ድህረ ገጾች ዘግቤዋለሁ ::
ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ግን ቤክርስቲያኔቱ በምን መልኩ ትተዳደር?፡ የ ጊዜ ገደቡ ያለፈው የሰበካ ጉባኤው መቼ ነው ወርዶ አዲስ
አባላት የሚመረጡት? ፡ ቤክርስቲያኔቱ ከየትኛው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ትሁን ?(በአገር ቤት ካለው ሲኖዶስ ? ወይስ በውጪ ካለው
ሲኖዶስ? ወይስ አሁን ባለችበት በገለልተኛነት አቋሟ ትጽና?... ወዘተ) የሚሉ ሃሳቦች ዙሪያ የተካረሩ እሰጣ ገባዎች በሃሳቦቹ ደጋፊዎች
እና በተቃዋሚዎች መካከል በአውደ ምህረት ላይ: በኪራይ አዳራሾች እና በተለያዩ ደህረገጾች አማካኝነት ሲንሸራሸሩ ተስተውለዋል፡፡
ወደ ዋና የጽሁፊ መነሻ ወደሆነው ወቅታዊ የቤተክርስቲያኒቱ ችግሮች ሰመለስ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሰለተከሰቱ አንኳር
የቤተክርስቲያኒቱ ችግሮች መካከል በሁለቱ ጉዳዮች ዙሪያ ትንሽ የግሌን አሰተያየት ልሰንዝር ፡፡
ባለፈው ታህሳስ 13 ቀን 2005 አ/ም (22 ታህሳስ 2012 እኤአ )የቤተክርስቲያኒቱ አሰተዳደር ጉባኤ በ Ref DTM 568 Ext-Msl
00568/ 12 ያወጣው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው “አቶ ግርማ ተሊላ እና አቶ ጥላዬ የሻነው የተባሉ ምእመናን በመስከረም 2
2012 እ ኤ አ የቤተክርስቲያኒቱን ስም በመጠቀም ኩባንያ ካምፓኔ ቁጥር 8200045 የሚል በአቶ ግርማ ተሊላ የመኖሪያ ቤታቸው
አድራሻ በማውጣት ላለፉት ሶስት ወራት ያህል ጉዳዩን ደብቀው አንደቆዩ በመደረሱ ሁለቱ ግለሰቦች ከቤተክርስቲያኒቱ
አባልነታቸው ለጊዜው እነደታገዱ” ይፋ አድርጎ ወደፊትም በህግ እንደሚጠየቁ የቤ/ክኗ ማህተም እና ፊርማ ያዘለው መግለጫ
ያትታል፡፡ ይህ መግለጫ ባለፈው እሁድ እለት (ከሁለት ሳምንት በፊት ) ለምእመናኑ በአውደ ምህረት ላይ ይፋ በተደረገበት ወቅት
“የሁለቱ ግለሰቦች ሃሳባችው መደመጥ አለበት በሚሉ እና የለበትም” በሚሉ ወገኖች መካከል የተካረረ አስጣ ገባ እንደነበር ፡
ሁኔታውንም ለማርገብ የጸጥታ ሃይሎች ጣልቃ እንደገቡ በእለቱ የተገኙ ምእመናኖች ሁኔታውን በሃዘኔታ አጫውተውኛል ፡፡ጉዳዩም
በህግ የተያዘ በመሆኑ ለጊዜው ብዙ አስተያየት መስጠት ባይቻልም ሁለቱ “ተወቃሽ ግለሰቦች” በ 19 ታህሳስ 2012 እኤአ በ ኤ-ሜል
አማካኝነት አሰተላለፉት የተባለ እና ስማቸው የሰፈረበት ነገር ግን ፊርማቸውን ያላካተተ ጸሁፍ አንዳመለከተው ከሆነ
“ቤተክርስቲያኔቱን በቻሪተእብሌ ካምፓኒይ ሊሚትድ ባይ ጋራንቲ ለማቋቋም ወራት የፈጀው እና እስከአሁን ድረስ እልባት
ያላገኘው ድርድር ባለመቋጨቱ ለቤተክርስቲያኒቱ ተገቢው የሆነውን ሰው ሌላ ግለሰብ ወይም ድርጅት እንዳይወስድባት በማሰብ
የቤተክርስቲያኒቱን ስም ተጠቅመናል ፡፡ሁኔታዎች ሲረጋጉ ያስመዝገብነውን ድርጅት በነጻ ለቤተክርስቲያኒቱ በቻሪተብል ካምፓኒ
ሊሜትድ ባይ ጋራንቲ አትመዘገብም ከተባለ በስማችን ያስመዘገብነው ድርጅትን ወዲያውኑ እንደምንዘጋ ለሰበካ አሰተዳደር
ለማስተዋወቅ እንወዳለን::” ይላል፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች እስከ አሁን ድርስ ለምን ዝምታን መረጡ? እነርሱን ይህንን ታላቅ ሃላፊነት በግል
እንዲቀበሉ ማን መረጣቸው? ቤተክርስቲያኒቱ የውሳኔ መግለጫ ካወጣች በሁዋላ ለምን የማስተባበያ ደብዳቤ ማውጣት አሰፈለገ
?ለሚሉት እና መሰል ጥያቄዎች ተጠቃሾቹ ግለሰቦች ሆኑ በእነርሱ ስም የጻፉት ወገኖች ለጊዜው ያሉት ነገር የለም፡፡ የእነዚህን ሁለት
ግለሰቦች ተግባር “እንደግፋለን” የሚሉ ነገር ግን ሰማቸውን እና ማንነታቸውን በውል ያልገለጹ ወገኖች ያሰራጩት መልእክት በበኩሉ
አንደሚያትተው ከሆነ “ሁለቱ ግለሰቦች የከፈቱት ድርጅት ከለንደኗ ጽዮን ማሪያም ቤ/ክን ጋር አይገናኝም” የሚል መልእክት ያዘለ
ሲሆን ይሄው ጽሁፍ ወረደ ብሎ “ሁለቱ ግለሰቦች ( አቶ ግርማ እና አቶ ጥላዮ) ይህንን አርምጃ የወሰዱት ሌሎች ግለሰቦች
የቤተክርስቲያኒቱን ስም እንዳይጠቀሙ ወይም እንዳይወስዱ ለማድረግ አስበው ነው::” የሚል ድጋፍ አይነት መልክት
እስተላልፏል፡፡
ሌላኛው አራሳቸው የቤተክርስቲያኔቱ ካህናት እና ምእመናን በሚል ሰም በኤ-ሜል አማካኝነት ሰሞኑን የተሰራጨ የቅስቀሳ እና
ማስጠንቀቂያ መልእክት የተሰራጨ ሲሆን የዚህ ወቀሳ ሰለባዎች መካከል የደብሩ አሰተዳዳሪ የሆኑት ቆሞስ አባ ግርማ ከበደ አንዱ
ሲሆኑ ይሄው ጽሁፍ “የማሪያም ቤ/ክን ከስላሴ ቤ/ክን ጋር ያላትን የአቋም ልዩነት ወደ ጎን አደርገው ከስላሴ ቤ/ክን እና ከሌሎች
የሟቹ ፓትሪያርክ አባ ጳውሎስ ደጋፊዎች ጋር በመወገን የቤተክርስቲኗን ህልውና አሳልፎ የሚሰጥ ተግባር እየፈጸሙ ሲሆን ይህ
ድርጊታቸው በቤተክርስቲያኒቱ አባላት ፈጥኖ ካልተገታ ቤተክርስቲያናችንን ከእጃችን ወጥታ ልትቀር አንደምትችል በሚገባ መረዳት
ያሰፈለጋል… ወዘተ፡፡ “ ይላል፡፡ ይሄው የቅስቀሳ ኢ-ሜል ጽሁፍ አንገብጋቢ ችግር ነው ያለውን ጉዳይ ሲያብራራ “ በርእሰ አድባራት
ለንደን ጽዮን ማሪያም ቤ/ክን የሚደረገው ቅዳሴ: ቁርባን: ክርስትና ሁሉ የማይሰራ እና የተወገዘ ነው በማለት ቤተክርስቲያናችንን
የኮነነ እና ስሟን ያረከሰ ዲያቆን ብርሃኑ የተባለ ሰባኪን ከስላሴ ቤ/ክን በ16 ታህሳስ 2012 እኤአ በማምጣት ዲ\ን ብርሃኑ የአባ
ግርማ ከበደን አላማን ሊያሳካ የሚችል ስብከት እንዲያደርግ አባ ግርማ ጥረት በማደረግ ላይ ናቸው… ወዘተ፡፡ “የሚል ነው
በአጭሩ፡፡
እውን አባ ግርማ ከበደ 360 ዲግሪ ተቀየሩ?
የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ የሆኑት ቆሞስ አባ ግርማን እስከ ቅርብ ጊዜ እስከ ማቃቸው ድረስ በኢትዮጵያ ያላውን የሰብአዊ መበት እና
የሃማኖታዊ ጭቆናን በተመለከተ በርካታ ወገኖች ከአገዛዙ ጋር ያላቸው የጥቅም እና የቅርርቦሽ ትስስር እንዳይቋረጥቧቸው ዘምታን
በመረጡበት በአሁኑ ወቅት አባ ግርማ ግን ድርጊቱን በአደባባይ በማውገዝ በተለያዩ ሃዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች እና ስብሰባዎች ላይ
በመገኘት ለጸረ- የሰባዊ መብት ዘመቻው አጋርነታቸውን በገሃድ የገለጹ መነኩሴ ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን እንቅስቃሴ በተመለከተ
ደግሞ መረጃን እንኳን ለዜና ሰዎች ለመስጠት ሙሉ ነጻነት የሌላቸው አባት ለመሆናቸው ከአንዲም ሁለት ጊዜ ላነጋግራቸው ሞክሬ
“ጥያቄህ ማእከላዊነቱን መጠበቅ ስላለበት በጽሁፍ አቅርብ…ወዘተ” ያሉኝ የቅርብ ጊዜ ትዝታዪ ነው ፡፡ ታዲያ እኛ በቤተክረስቲያኒቱ
አስተዳደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንቅስቃሲያቸው ሆነ አነጋገራቸው በአመዛኙ ውሱን መሆኑ የሚታወቀው አባ ግርማን አንዳንድ ወግኖች
በቅርቡ “አቦይ ግርማ “አስከ ማለት ደረሰው ሲጠሯቸው ስሰማ እውን ቆሞስ አባ ግርማ መሰረታዊ የአቋም ለውጥ አሳዩ? ወይስ
በታላቁ መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ በየዋህነት የተመሰለው በጉ ካመረረ… የሚለውን ቃል ተግባራዊ አደረጉት? ስል ከእይምሮዩ ጋር ሙግት
ገጥሜ ስንብቻልሁ፡፡ በነገራችን ላይ አባ ግርማ ፍጹም ሰው ናቸው የሚል እምነት የለኝም ፡፡አርሳችውም ቢሆኑ “ፍጹም ነኝ “የሚሉ
አይመስለኝም፡፡ ታዲያ በአበዛኛው የለንደን ሰላማዊ እና ህዝባዊ ስብሰባዎች እና የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የማይጠፉት አባ ግርማ ምን
አይነት “የሚያማልል አለማዊ” ነገር አገኙ ተብሎ ነው “ቤተክርስቲያኒቱን እያመሷት ናቸው …ወዘተ” የሚሉ በረካታ ወቀሳዎች
ሰሞኑን የሚሰነዘሩባቸው?
ከላይ የቀረበውን የኤ-ሜል ጽሁፍ በመንተርሰስ በምስራቅ ለንደን ከተማ ለምተገኘው እና በአብዛኛው የካሪቢያን ተወላጆች እና
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ተከታዮች የሆኑ የ ጸራጼዮን ማሪያም ቤ/ክን በቅርቡ ለገዙት አዲስ ህንጻ ቤ/ክን የማስፋፊያ የገቢ ማሰባሰቢያ
ፕሮግራም ከአዲስ አበባ ለስበከት ወንጌል አገልግሎት ተጋብዘው ወደ ለንደን የመጡት ዲ/ን መምህር ብርሃኑ አድማስ እና ዘማሪ ዲ/ን
ምንዳዮ ብርሃኑ በአባ ግርማ ከበደ የግል ጥሪ ወይስ በራሳቸው መንገድ ወደ ማሪያም ቤ/ክን ሄዱ? የሚል ጥያቄ በአይምሮዬ ውስጥ
ተጭሮ ነበር ፡፡ ለጥያቄዬም ያገኘሁት ምላሽ ሁለቱ አገልጋዮች (ዲ/ን በርሃኑ እና ዲ/ን ዘማሪ ምንዳዮ ) በለንደን አና በአካባቢዋ የሚገኙ
የኢትዮጵያ ፡የካሪቤያን አና የኤርትራ ተወላጆች የሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክረሰቲያኖች በመዘዋዋር የስብከተ ወንጌል ትምህርት
እና አገልግሎት በመስጠት እና ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር በህብረት በማዜም መሰንበታቸውን የተረዱ በለንደን ደበረ ጽዮን ማሪያም
ቤተክርስቲን የሚገኙ ምእመናን ለቤተክርስቲያኒቱ የካህናት ጉባኤው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት አንደተጋበዙ እና የሁለቱንም አገልጋዮች
ወደ ማሪያም ቤ/ክን መምጣት በመቃወም ረገድ መሪ ጌታ አዲስ አዱኛ የተባሉ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋይ ብቻ ሲቃወሙ የመሪ
ጌታ አዲስ ተቃውሟቸው ተመዘግቦ የግብዣ ሃሳቡ በድምጽ ብልጫ ተቀባይነት ማግኘቱን ለማወቅ ችያለሁ፡፡
ሁለቱ አገለጋዮች (ዲ/ን በርሃኑ እና ዲ/ን ዘማሪ ምንዳዮ ) በግብዣው መሰረት ወደ ማሪያም ቤ/ክን ሲያመሩ የጠበቃቸው የዘንባባ
ዝንጣፊ ሳይሆን ሁለቱ አገልጋዮች “ ወደ ቤ/ክኗ ይገባሉ… !! አይገቡም…!! “የሚሉ የሁለት ወገኖች የከረረ አለመግባባት የታየበት እና
ሁኔታውን ለማርገብ እና ለምቃኘት የጸጥታ ሃይሎች ወደ ቤተክርስቲያኒቱ የጋበዘ ሁኔታ ተስተውሏል፡፡ ለሶስት ቀናት ይካሄዳል
የተባለው የስብከተ ወንጌል ፕሮግራሙ ሁለቱ ሰባኪያኑ ከነበራቸው የተጣበበ ፕሮግራም የተነሳ ለሁለት ቀናት ብቻ ተካሄዷል፡፡
ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ማናቸው ?
በዚህ ሰብከተ ወንጌል ላይ የተገኙት ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ “ሰለ ማሪያም ቤክርስቲያን መጥፎ ስብከት ሰጥተዋል” ተብሎ ወቀሳ
የተሰነዘረባቸው ሲሆን በመሰረቱ ዲ/ን ብርሃኑ በአገር ቤት ምን አይነት ስብከት እንደሚሰጡ ለመታዘብ አጋጣሚውን ባላገኝም በባህር
ማዶ ሰብከታቸው ግን ዘወትር በስብከተ ወንጌል ትምህርታች ላይ ጥቁሩን ጥቁር: ነጩን ነጭ : ጎባጣውን ጎባጣ :ቀጥ ያለውን
ሸንቃጣ ብለው በስሙ ከሚጠሩ ጥቂት የዘመናችን ወጣት ሰባኪያን መካከል አንዱ እንደሆኑ እና በተለያዩ ጉባኤዎች ላይ
አሰረገጠው ሲናገሩ ከሰማሁዋቸው መልክቶቻቸው መካከል “የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የራሷ የሆነ ሰርአት እና ደንብ ያላት : የማትከፋፈል
ሃይማኖታዊ ተቋም በመሆኗ ይህንን ሰርአቷን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚያፈርሱ ወይም የሚጻረር መንገድ ላይ የቆሙ
በየተኛውም ጎራ የተሰለፉ ፖለቲከኞች ሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ነን የሚሉ ወገኖች አካሄዳቸውን ሊመረምሩ ይገባል ፡
ቤተክርስቲያኒቱም የሰላም እና የፍቅር መድረክ እንጂ የጸብ እና የንትርክ ቦታ ልናደርጋት አይገባም ፡ በቤተክርስቲያናችን ህግ እና
ደምብ መሰረት ጳጳስ ካልባረከው በሰተቀር አንድ ቄስ ተነሰቶ አዲስ ቤ/ክን ሊከፍት ወይም የድቁና ማእረግ ለአገልጋዩች ሊሰጥ በፍጹም
አይችልም …ወዘተ “ በማለት አስረግጠው ሲሰብኩ አዳምጫለሁ፡፡ ይህ ሰብከታቸው ሁሉንም ምእምናን ሊያስድስት የችላል ማለት
ባይቻልም ከስርአተ ቤ/ክን አንዱ አካል በመሆኑ መቀበል አለመቀበለ በእያንዳንዱ ምእመን የሃይማኖታዊ ግንዛቤ ደረጃ ላይ ይወደቃል
፡፡ ዛሬ አውነታውን ፍርጥርጥ አደርግው ለምናገር የሞራል ብቃቱ ሆነ ብልሃቱ የጎደላቸው በረካታ መሪዎች ሆኑ ሰባኪያን
በተበራከቱበት አለም ውስጥ ስንገኝ ከወገንተኝነት የጸዳ ስብከት እና ስርአተ ቤ/ክን ትምህርት የሚሰጡ ወገኖችን እንዲያው በደፈናው
ማሳጣቱ ወይም ለወቀሳ መዳረጉ ልዪነቶችን ከማስፋቱ በተጨማሪ እንዴ ጎብዝ ምን አይነት ዘመን ላይ ደረሰን? ፡ወዴትስ እያመራን ነው?
የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም ፡፡ይህ ማለት ግን የአገር እና የሃይማኖት ጉዳይ የጥቂት አዋቂዎች ወይም መሪዎች ብቻ ስለሆነ ዝም
በሉ ወይም የሚሰጣችሁን መምሪያ ሆነ ውግዘት አሜን ብላችሁ ተቀበሉ ማለት ሳይሆን ለሁለት ሺህ አመታት ስርአቷን እና ትውፊቷን
ጠብቃ የቆየች ሃይማኖትን “የእነ አባ እገሌ ደጋፊዋች እና ተቃዋሚዋች ወይም ከዚያ ዝቅ ሲል የዚህ እለት እና የዚያኛው እለት
ጉባኤተኞች… ወዘተ” በሚሉ ልዩነቶች በመተብተብ ወደ ማያባራ ልዩነት ለመውስድ መሯሯጡ በየትኛውም መንገድ ሊደገፍ
የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ቢቻል ልዩነቶችን ለማጥበብ መሞከር ብልህነት እና የሚያጸድቅ ስራ ሲሆን ካልሆነ ደግሞ ጊዜ ፈቅዶ ወደ
አንድነት እስኪመጣ ድረስ እንኳን ላለመነቋቆር እናኳን በጨዋ ደንብ ተወያይቶ መለያየት ሲቻል ነጋ ጠባ በነገር ቁርቃሶ
መውነጫጨፉ ጉዳቱ ለተፋላሚ ወገኖቹ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖቱን ሃይማኖቴ ብሎ ከፈጣሪው ጋር ለመገናኘት ዘወትር ማልዶ ወደ
ቤተክርስቲያን የሚሄደውን ህዝበ ክርስቲያንን ማሳዝን እና ከሃይማኖቱ አንዲርቅ እንደሚያደርገው መዘንጋት የለብንም ፡፡
ፖለቲካኛ ገዢዎች በተፈራረቁ ቁጥር የጨፍልቀህ ወይም የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲያቸውን ለማሳካት ሲሉ ዛሬ ድርሰ እጃቸውን
ያላነሱባት ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከተደቀነባት የመከፋፈል እና የመለያየት አደጋ ለምታደግ የህዝበ ክርስቲያኑ የጋራ ጾም ፡ጸሎት እና
ስርአት ያለው የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት አግባባነት ያለው እና ሊደገፍ የሚገባው መንገድ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም ፡፡ ይህ ሳይሆን
ቀረቶ “አኛ ካልነው ሃሳብ ውጪ ምንም አይነት ሃሳብ አይበጀንም ፡ ከየትኛው ወገን ይሁን ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጡ ወገኖችን
ዘወትር በጥርጣሬ አይን ማየቱ … ወዘተ “ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበት ሃዋሪያዊ ተልእኮዎች መካከል አንዱ የሆነው ጠላትህን
እንደ ራስህ አድርገህ ውደደው የሚለውን ከባድ ትእዛዝን ለመተግበር ቀረቶ “የገዛ ወንድምህን እንደራስህ ለማየት ሞክር “ በሚል
እንኳን ብንተካው ከፊታችን በርካታ የቡድን እና የግል ፈተናዎች የተደቀኑብን ይመስለኛል ፡፡ ( tamgeda@gmail.com)