እዩልኝ ሲያቅመኝ፤ ”አቤ ወደ ሙርሲ የላካቸው ጀቶች ግጭት”
አንድ አማርኛ መመህር ነበሩን ጺማቸው የጎፈረ ጸጉራቸው የተንጨበረረ ነበር፤ በአንዱ ቀን ታድያ ፊት ለፊታችሁ በምታዩት ነገር ግጥም ጻፉ አሉና አዘዙን፡፡ ሁላችንም አንገታችንን ደፍተን ስንንደፋደፍ አንዱ ሳተና ጨርሻለሁ… ሲል እጁ
ን አወጣ… በል እስቲ አጋራን… አሉና መድረኩን ሰጡት፡፡ እርሱም ጀመረ፤
ያጎፈረው ጢምዎ…
ዝንጀሮ አስመስልዎ…
አቤት የፀጉርዎ…. ብሎ ገና ከመጀመሩ ተማሪው ሳቁን መቆጣጠር አቅቶት ከት…ት ብሎ መሳቅ ጀመረ፡፡ ይሄን ጊዜ መምህሩ ተቆጡ…
ተዉ እንጂ ተማሪዎች… ገና እኮ ነው በደንብ ያቅመኝ እንጂ… አሉን፡፡ ሌላ ሳቅ…
አንድ ወዳጄ ባለፈው ግብጽን አስመልክቶ ያወጋሁትን በእንዲህ መልኩ ይዋጋዋል… ደህና አድርጎ አቅሞኛል፡፡ ለነገሩ እኔም የምለቀው አይመስለኝም… ስለ ባዕድ ሀገር የማውራት ሞራሌ እስኪሰባሰብ ግን እስቲ እርሱ ያቃመኝን ላልደረሰው ላዳርሰው ብዬ በድረ ገፃችን ላይ ለጥፌዋለሁ፡፡
አንዳንዴ ሁለት ተዋጊ ጀቶች ከአንድ የጦር ሰፈራቸው ቦምብና ሮኬት ወይም ሚሳይል አንግበው ይነሱና በጠላት ወረዳ ደርሰው ከማጥቃታቸው በፊት በሚፈጠር ስህተት እርስ በርሳቸው ተላትመው ቦምቡም፣ ሚሳይሉም፣ ሮኬቱም ለጠላት መሆኑ ቀርቶ ለራሳቸውና ለአብራሪዎቻቸው ይተርፋል። አቤ “ደግሞ በግብፅ እንጣላ እንዴ” በሚል አርእስት የላካቸው ጀቶች (ፌስቡክ ላይ ያሰፈራቸው መልእክቶች) ይህ ዕጣ ገጥሟቸዋል እያልኩ ይህን ከበላይ አካል ፈቃድና እውቅና ያገኘ ፅሑፍ ልጋብዝ።
ግጭቱ እንዲህ ነው፤ አቤ በአንድ በኩል ‘ሙርሲ ዋጋውን አገኘ’ ይልና በሌላ በኩል ‘የተመረጠን የገለበጡትን መቃዎም ተገቢ ነው’ ይለናል። እዚህ ላይ አቤን እንደ ፌስቡከኛ ብቻ በማየት ባለማለፍ በጉዳዩ ላይ መነጋገር አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ለምን አቤ ኢሳት ላይም የሰራልና ነገሮችና የነገሮች ሂደት የሚገዙበት ደንብ መጣረስ የለበትምና። መጣረስ ደግሞ አንዱ የኢሳት ችግር ነው፤ ለምሳሌ ኢሳት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ውስጥ መከራና ችግር በዛ፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተጣሱ፣ አምባገነንነቱ ገደብ አጣ፣ የኢትዮጵያ ጉዞ ወደ ጥፋትና ወደ በመበታተን እየሆነ ነው ወዘተ የሚሉ መልዕክቶችን ያስተጋባል። በሌላ በኩል ደግሞ “ምንም የለም በሉ ከደስታ በቀር … ምንም ችግር የለም… አዲስ ነው ዘመኑ … ኧረ አዲስ ነው! ክፉው ዘመን አልፏል…” የሚለውን ዘፈን ደጋግሞ ይጋብዘን ነበር። የአሁኑን እንጃ በናይል ሳት ላይ በነበረበትና እንደ ልብ እንከታተለው በነበረበት ጊዜ ግን ይህ ነገር በተደጋጋሚ ነበር የሚሰማው። ለመሆኑ ዘፈን የምንጋበዘው ስለ መልዕክቱ ነው ወይስ ስለዘፋኙ ወይስ ስለዘፋኙ ቲፎዞዎች ሲባል? አንድ ጊዜ ‘ኢሳቶች ገና ከመጀመራችን ለትችት ተሽቀዳደሙ’ ሲል ሰምቻቸው ነው እንጅ ይህን መሰል ነገር ቀደም ብሎ ማድረግ ጥሩ ነበር። ‘እናቴ ሆይ በእንቁላሉ … ’ አለ ነው የተባለው በሬ ሰርቆ ለስቅላት የቀረበው ሰውዬ?!
በኢሳት የተላለፉ ተመሳሳይ መጣረሶችንና በደንብ ያልታሰበባቸው የሚመስሉ ዝግጅቶችን ከተለያዩ ፕሮግራሞቹ በመሞነታተፍ ማቅረብ ይቻላል። አንድ ቀን ይህን ማድረግ ተገቢ ነው።
ወደ አቤ እንመለስና በመጀመሪያ ሁለቱን ጀቶቹን እንያቸው።
ጀት ቁጥር አንድ
“እንደኔ እምነት የግብፅ ወታደር ኩዴታ ፈፅሟል የሚያስብል ነገር አላየሁም፡፡ በርካታ ህዝብ አደባባይ ወጣ ተቃውሞውንም አሰማ … ሙርሲ ይሂዱልን ከዚ… አሉት ..። ስለዚህ በእኔ በምስኪኑ እምነት የእነዚህ ብዙሃን አቤቱታ መሰማት አለበት፡፡ ለዚህም ወታደሩ ያደረገው መፈንቅለ መንግስት ሳይሆን አፍቅሮተ ህዝብ ነው ባይ ነኝ፡፡ ለብዙሃኑ ጆሮ ሰጥቷልና!” ጥቅስ አቤ ቶኪቻው።
ጀት ቁጥር ሁለት
“ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ተቃዋሚዎች (የሙርሲ ደጋፊዎች) እየጠየቁ ያለው ጥያቄ ትክክል ነው፡፡ ድምጻችን የት ነው…! የመረጥነውን ሰውዬ የት አደረሳችሁት…! እያሉ ይገኛሉ፡፡ ይሄ እጅግ በጣም ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡… እኔ ይቺን እየተየብኩ ባለበት ሰዓት የወታደሩን ጣልቃ ገብነት በመቃወም በተቀሰቀሰው አዲሱ ተቃውሞ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ሃያ ሊደርስ እየተንደረደረ ነበር፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ተቃዋሚዎች እየጠየቁ ያለው ጥያቄ ትክክል ነው፡፡ ድምጻችን የት ነው…! የመረጥነውን ሰውዬ የት አደረሳችሁት…! እያሉ ይገኛሉ፡፡ ይሄ እጅግ በጣም ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡” አሁንም ጥቅስ ከአቤ ቶኪቻው ነው።
የሁለቱ ጀቶች ፍፃሜ
የአሜ ጥቅስ ሲቀጥል የሚከተለውም ይገኝበታል “መጨረሻ ላይ እንደኔ አስቴየት ያኛውም ትክክል ይሄኛውም ትክክል ሆነ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ዲሞክራሲ አጣብቂኝ ውስጥ የምትገባው ይሄኔ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የሚል ሌላ አስተያየት ልጨምራ!”
አቤ ይቀጥላል፤ “አሁን ከሙርሲ እና ሌሎች ባለስልጣናት ወደ ማረፊያ ቤት መውረድ በኋላ ተቃዋሚዎቹ (የሙርሲ ተቃዋሚዎች) የልባቸው ደርሶ ወደ ጎጇቸው ሲመለሱ የሙርሲ ደጋፊዎች ደግሞ ይቺን ይወዳል የሙርሲ ልጅ ብለው እየቀወጡት ይገኛሉ፡፡ ይህ ሊመጣ እንደሚችል ተንታኞቹ ድሮውንም ገምተዋል፡፡ ማለቂያው ምን ሊሆን እንደሚችል ግን የሚያውቀው የላይኛው ብቻ ነው፡፡”
የአቤን ጀቶች ይዘት እንመርምራቸው!!
አቤ ጀት ቁጥር አንድን “ብዙሃን” እና “ህዝብ” የሚል ታርጋ በመለጠፍ ጥሩና ትልቅ ጀት አድርጎ ሲያሳየን፤ ቁጥር ሁለት ጀትን ግን “ተቃዋሚዎች” እና “ሰዎች’ የሚል ታርጋ በመስጠት አሳንሰን እንድናያት በዘዴ እየሰራ ነው።
አቤ የሙርሲን ተቃዋሚዎች በወታደራዊ ሃይል መደገፋቸውን እሰየው የሚያስብል፣ በሰዎች ሊደረግ የሚገባው እርምጃ አድርጎ ወሰደውና የመርሲ ደጋፊዎች ወዮታን ግን ከፈለገ የላይኛው ይርዳቸው በሚል ለበጣ አልፎታል።
አቤ እንዳሻኝ እፅፋለሁ ለማለት ‘መቼም ለሙርሲ ሞራል ተጠንቀቅ [አትሉኝም]…’ ሲል ፅፏል። በቀልድ መልክ አስተምራለሁ ብሎ መጣጥፍ የሚያቀርብ ሰው ግን በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ መመራት የለበትም እላለሁ። ይህ ፅሑፍ የአበበን አመለካከት ብቻ ሳይሆን አቤ ነገሮችን የሚፈርድበትን ሚዛንም ነው የሚያሳየን። አቤ ስለ ምንም ነገር ሲፅፍ የሱን ፅሑፍ ለሚከታተሉ ሰዎች ስለሚለግሰው እውቀት፣ በልባቸው ሊያኖረው ስለሚችለው ተስፋና ሞራል፣ ዝንባሌና አመለካከት መጠንቀቅ እንደሚጋባው ማሰብ የለበትም ይሆን?
አቤ በድፍረት “እንደኔ እምነት የግብፅ ወታደር ኩዴታ ፈፅሟል የሚያስብል ነገር አላየሁም” ብሏልና ይህ ነገር ብዙ ብዙ ይናገራል።
“በሕዝብ የተመረጠ መሪ አጉራ ዘለል ሆኖ ተገኘ ከተባለ በመጣበት መንገድ ለመሸኘት ድጋሚ ምርጫ ማድረግ ነው የሚገባው ወይስ የአደባባይ ግርግርን መሰረት አድርጎ መዘርጠጥ?” ይህ ለአቤ የማቀርበው ጥያቄ ነው። አቤን የምጠይቀው ሌላም ጥያቄ አለኝ “ይህን ያህል ሃይል ያለው የግብፅ ጦር ለምን ሕዝብ ድምፁን በስነ ስርዓት የሚያሰማበትን ወይም በሕጋዊና ‘ዓለም ዓቀፍ ተቀባይነት’ ባለው የድምፅ አሰጣጥ ስነ ስርዓት የሚካሄድበትን መንገድ አላመቻቸም?”
ስለ ሰልፍ ካነሳን አይቀር የሙርሲ ደጋፊዎችም ገና ከመጀመሪያው አንስቶ አደባባዮች ላይ ነበሩ። በቢቢሲ መስኮት ያልታየ ሕዝብ “ሕዝብ” አይባል ይሆን? ብየም ልጠይቅ።
ሚዲያንና ድምፅን የማሰማትን ነገር ከወሳን አይቀር ከሐምሌ 5-7/ 2013 ባለው ጊዜ ብዙዎቹ የአውሮፓ ሚዲያዎች ለመጥቀስ ያህልም ቢቢሲ፣ ዩሮ ኒውስ፣ ፍራንስ-24 ወዘተ ገና ከማህፀን ያልወጣው ከእንግሊዛዊ ልዑል ባለቤቷ ኬቲ የፀነሰችውን ልጅ ‘መጣ፣ ደረሰ፣ ቀረበ’ ሲሉና ስለ ህፃን አልጋ፣ ስለ ህፃን ልብስ፣ ስለ አራስ ልብስ ወዘተ ሃተታ ብቻ ሳይሆን የዜናቸው ዋና ክፍልም አድርገውት አይተናል። እንግሊዝ ውስጥ ሌሎች የተወለዱ፣ የሚታዩና እዚህና እዚያ የሚኖሩ ድምፃቸው ሊሰማ የሚገባ ሰዎች የሉምና ነው ለአንድ ‘እጭ’ ይህ ሁሉ ጫጫታ?! Mail On Line የተባለው የእንግሊዝ ድረ ገፅ Royal birth the world is waiting for ሲል ነው ነገሩን የዘገበው። ምን ያህል ሕዝብ ቢጓጓ ነው ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው መወለድ ያለው? ሚሊዮን ወይስ ቢሊዮን? ሚዲያ እንዲህ ነው። ለራስ ሲቆርሱ…
ሚዲያዎች የተቋቋሙበት ዓላማ አላቸው። ነገራቸው ሁሉ በዚህ የተቃኘ ነው። የግብፅ ጦር ከሄሊኮፕተር አበባና በመልዕክት የተሞላ ወረቀት እየበተነ ያበረታታው ሰልፈኛ (ሕዝብ) የመኖሩን ያህል በተመሳሳይ ዕለት በታጠቀ ሃይል ከበባ ውስጥ አስገብቶ መንቀሳቀሻና መላዎሻ ያሳጣው ሕዝብም ነበር። አቤ ‘ቢቢሲ ሁለቱን ሰልፎች ጎን ለጎን እያሳየ ነው’ ያለን የሙርሲ ቁርጥ ከታወቀ በኋላ ነው፤ ቢቢሲ ለቀናት የሙርሲን ደጋፊዎች ችላ ብሎቿ ነው የነበረው። የአሜሪካ ባለስልጣናትና የአውሮፓ ጋዜጠኞች የስልጣንና የስራ ጊዜያቸው ካለፈ በኋላ ችላ ያሉትን ሃቅ ወደ ኋላ ተመልሰው በማስተጋባት ይታወቃሉ። ይህን የሚያደርጉት የህሊና ወቀሳ አላስተኛ ብሏቸው ወይም በዚያ ሚስጢር ቀዳሚ (ብቸኛ) ተጠቃሚ በመሆን ታዋቂነት ወይም ‘ታላቅነት’ ወይም ገንዘብ ለማግበስበስም ሊሆን ይችላል። ቢቢሲም ይህን ባህል በመጠቀም ይታወቃል። ስለ ቦብ ጌልዶፍና እሱ ያሰባሰበው የዕርዳ ገንዘብ የት ገባ በሚል ፕሮግራም የተሰራው ነገሩ ከተፈፀመ ከ25 ዓመታት በኋላ ነው። መጀመሪያ ላይ ይህ ፕሮግራም ለሕዝብ ቀርቧል። ከዚያም ይህ ታሪክ ብዙ ውዝግብ ፈጥሮ ከቢቢሲ ከድረ ገፅ እስከመሰረዝ ደርሷል። ይህ ለአቤ ቅርብ የሆነው ታሪክ ነውና አቤ የሚዲያዎችን አካሄድ በዚህ ሊመዝነው ይችላል። ቦብ ጌልዶፍ በእንግሊዝ ንግስታዊ መንግስት “ሰር” ተብሎ የተሾመ ነውና ቢቢሲን አናውጦታል። ከማናወጥም አልፎ ቢቢሲን አፉን ይይዝ ዘንድ አስገድዶታል። ሌላም ታሪክ እናስታውስ፤ በአጠያያቂ ሁኔታ ሕይወታቸው ስላለፈው ስለ እንግሊዛዊው ዶክተር ኬሊ እና በግድያው (በሞታቸው) ዙሪያ ጉዱን ለማጋለጥ ያስችላል የተባለን አንድ ፕሮግራም ቢቢሲ ለሕዝብ በማቅረቡ አታካራ መፈጠሩንና አታካራው አንድሬ ግሊጋንን (የቢቢሲ ዳይሬክተር የነበረ) ከሓላፊነቱ ስለ ማስነሳቱ ታሪክ ፈተሽ ፈተሽ እናድርግ!!
ሰውን ማመን ቀብሮ አለች ቀበሮ። ወንድሜ ሚዲያን ማመን ብዙ መርምሮ ነው። ሰሞኑን ኦባማ አፍሪካን ሲጎበኙ “ኦባማ አምባገነን ናቸው ያሏቸውን አገራት አይጎበኙም” እያልን የበኩላችንን ደረት የመንፋትና ክብረ ቢስ ‘ጌቶቻችንን’ የማሸማቀቅ መከራዎችን እያደረግን ነው የሰነበትነው። ለነገሩ ይህን እያልን ሰዎችን እንጎሻሽም እንጅ ኦባማ የአምባገነን አገር አይጎበኝም የሚለው እውነት ሆኖ አይደለም። ኦባማም ይሁን እየተነሳ ያለፈ የአሜሪካ ፕሬዘደንት ሁሉ ከአምባገነን ጋር ሳይላላስ የቀረበት ጊዜ የለም። አዲስ የአሜሪካ ፕሬዘደንት በተመረጠ ቁጥር ወደ ሳውዲ ዓረቢያ ለገብኝት ይጠራል፣ ይሄዳል፣ የውሻ ሰንሰለት የሚያክል የወርቅ ሃብል ከነ ሜዳሊያ ከሳውዲ ነገስታት እጅ በአንገቱ ተጠልቆለት ይመለሳል። በኔ አመለካከት ሳውዲ ውስጥ የለየለት ኋላቀር፣ የለየለት የምዕራባውያን (በተለይ የአሜሪካ) አሻንጉሊት ወይም ገረድ፣ ሰው አራጅ (ስለ ‘Chop Chop Square’ ማንበብ ጥሩ ነው )፣ ሴቶችን እንደ እቃና እንድ እንስሳ የሚቆጥር ወዘተ ወዘተ መንግስት ነው ያለው። ዕድሜ ሚዲያን በገንዘብ ሃይል ሰለመቆጣጠር በሰሜን ኮርያ ስልጣን የቤተሰብ ‘ቮሊቦል’ ሲሆን የተከፉት ‘ዲሞክራቶችና’ ‘ጋዜጠኞች’ በሳውዲ ስልጣን ብቻ ሳይሆን አገር ‘ቮሊቦል’ ሲሆን ጭጭ ነው።
አቤ አንተ እነዚህን ሚዲያዎች ሰምቶ ነው የግብፅ ሕዝብ ሰልፍ ሲባል እነማንን ማሰብ እንደሚገባ የፈረደው። የነፃነትና የዲሞክራሲ ሰባኪ የሆነችው እንግሊዝ ያቋቋመችው የመገናኛ ቢሮ (Office of Communication- OFCOM) ያገዳቸው ወይም አፈና ያካሄደባቸውና በምድረ እንግሊዝ እንዳይሰራጩ የከለከላቸው እነ ፕረስ-ቲቪን ብታይ ደግሞ የተሰለፈው ሕዝብ የሚለው አመለካከትህ ሰፋ ይላል ወይም ይቀየራል ብዬ እገምታለሁ። በእርግጥ እኔ የማምነው ከቢቢሲ፣ ከቪኦኤ፣ ከስካይ ኒውስ፣ ከፎክስ ኒውስ የምሰማውን ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ግን ወደ ትክክለኛና ሚዛናዊ ፍርድ አያመራም።
አቤ “በርካታ ህዝብ አደባባይ ወጣ ተቃውሞውንም አሰማ… ሀቂቃውን ለመናገር ግን በግብጽ ተቃውሞ የወጡት ብዙሃን አንደነበሩ እድሜ ለቴክኖሎጂ በወቅቱ በቦታው ተገኝተው ሲዘግቡ የነበሩቱ ቀጥታ ሲያነፃጽሩልን ነበርና፤ ሙርሲ ይሂዱልን ከዚ… ያሉት ብዙ እንደነበሩ ድንጋይ ነክሰን ብንምልም አንፈራም” ብሎናል። ይህ አቤ ከምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች የወረደን ነገር እንዳለ የመቀበልና አማራጭ ሚዲያዎችስ ምን ይላሉ ብሎ ቅራና ቀኝ ለማየት እንደማይፈልግ ወይም ለዚህ ጊዜ እንደሌለው ወይም ከቢቢሲ ወዲያ ለአሳር ብሎ የማለ መሆኑን ያሳየናል ለማለት ልድፈር ይሆን? አቤ ለጠቅ አደረገና ሚዛኑን ሲያሳየን በድጋሜ “ወታደሩ ያደረገው መፈንቅለ መንግስት ሳይሆን አፍቅሮተ ህዝብ ነው ባይ ነኝ፡፡ ለብዙሃኑ ጆሮ ሰጥቷልና!” ብሎናል። ለአቤ መረጃ አቀባይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማለት ቢቢሲ እና መሰሎቹ ብቻ ይሆኑን? ብዙ ድረ ገፆችና ነፃ ሚዲያዎች እንደ ልብ በሞሉበት በዚህ ዘመን… ምነው… ምነው… ?
አቤ በዜማ (በግጥም) ይህን ብሏል “ተመረጥኩኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር… ከልተመቸው “ንኪው” ይልሻል ባላገር…” የሚል ዘፈን አለ አይደል…። የዚህን ዘፈን ዜማ ባልሰማውም ከ1997 ምርጫ በኋላ የአና ጎሜዝን ሪፖርት ተከትሎ አንድ ጋዜጠኛ ለአንድ የአውሮፓ ፓርላማ አባል ‘ምርጫ ተጭበርብሯል እየተባለ የአውሮፓ መንግስታትም ሆኑ የአውሮፓ ህብረት ለምን ጠንካራ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጠቡ?’ ሲል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። ለዚህ መልስ ነው ብለው የፓርላማ አባሉ ብዙ ነገር ነው የተናገሩት። ዋና ዋና ነጥቦች ለመጥቀስ ያህል “… የአካባቢው (የአፍሪካ ቀንድ) ወታደራዊ ሚዛን ሊዛባና ክልሉ ሊበጣበጥ ብሎም የሽብር መነሃሪያ ሊሆን ይችላል… የመለስ ተቃዋሚዎች ከአዲስ አበባ ውጭ ጠንካራ መሰረት የላቸውምና… ሂትለር ወደ ስልጣን የመጣው በምርጫ ነበር፤ የሰው ልጅ ነገሮችን አስቀድሞ የሚያይ ቢሆንና ያንን የምርጫ ውጤት ቢቀለብሰው ኖሮ ለዓለማችን ትልቅ በረከት በሆነ ነበር። ያ የምርጫ ውጤት ቢገለበጥ ለዓለማችን ትልቅ ጠቀሜታ ነበረው ነገር ግን ይህ ነገር ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ምርጫ ተጭበረበረ እያልን እንተቸው ነበር እንጅ ምርጫው መገልበጡ ያስቀረውን ችግርና መከራ ስለማናውቀው እናመሰግነውም ነበር…” እኝህ ሰው በግልፅ ይናገሩት እንጅ ምዕራባውያን ለጥቅማቸው ሲሉ ከዚህ የከፋ ምክንያትም ሊዘረዝሩ ይችላሉ። የ1997ተን ምርጫ ከታዘበ በኋላ ጂሚ ካርተር ቦሌ ላይ ምን ብሎ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሰጠ ሰምተኸዋል የሚል ግምት አለኝ። ካርተር ሃሳቡን የቀየረው የአና ጎሜዝን መግለጫና ጥንካሬ ካየ በኋላ አልነበረምን?
አቤ! ወደራዊ ጣልቃ ገብነት በለው መፈንቅለ መንግስት ይህ ነገር በቱርክ ቢፈፀ ምን ትለን ነበር? የቱርክ ወታደር አደባባይ የወጡ ቱርካውያንን በመደገፍ ተመሳሳዩን እርምጃ ቢወስድ እነ ኦባማ እነ ሜርክል ምን ይሉ ይመስልሃል? ሚዲያዎችስ?
የሙርሲንና የጓደኞቹን መታሰርም ልትቀልድበት ሞክረሃል። ማንም ሰው በምንም ላይ ቢቀልድ ‘መብቱ’ ሊሆን ይችላል ወይም በማን አለብኝነት መብቴ ነው ብሎ ሊያደርገው ይችላል። ነገር ግን ሁልጊዜም አሳሪ ትክክለኛ ታሳሪ ወንጀለኛ አድርገን ከወሰድን ምርጡ ኢትዮጵያዊ ወንድማችንንና ምርጧን ኢትዮጵያዊት እህታችንን (እስክንድርና ርዕዮት) ከነ ምርጥ የሙያና የአላማ ጓደኞቻቸው እስር ቤት ናቸው። ጊዜ የሰጣቸው ደግሞ ‘አሸባሪዎቹ’ እያሉ ነው የሚያብጠጥሏቸው። ሰው የፈለገው አቋም ሊኖረው ይችላል በሚዲያ ላይ የሚቀርብ ሲሆን ግን ቢያንስ የህሊና ተጠያቂነትን ግምት ውስጥ ያስገባ ስራ ቢሰራና አስተሳሰቡንም በዚሁ ቢቃኝ ጥሩ ነው። ምዕራባውያን ድሮ ለቅኝ ግዛት ሲመጡ እንስረቅ፣ እንግደል ብለው አልመጡም። ክርስትና እናስፋፋ፣ ጣዖት አምልኮና አረመኔነትን እናስወግድ፣ የባሪያ ንግድን እናጥፋ ወዘተ ነበር ያሉት። እዚህ ላይ ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወርር የሰጠውን ምክንያት ለማወቅ ‘The Lion of Judah’ የሚለውን ጥናታዊ ፊልም ልጋብዝ።
ለነገሩ አቤ ባለስልጣናትን አስመልክቶ ለበጣ ይፅፋል ይናገራል፤ ይህን ስለ እንግሊዟ ንግስት ማድረግ የሚቻል ይመስላችኋል? አቤ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለእነሱ በሚገባ ጥሩ እንግሊዝኛ የዚህ ዓይነት ነገር መፃፍ ቢጀምር ከሁለትና ከሶስት መጣጥፍ አያልፍም። ቀልድ አይደለም ወቅቶችን ጠብቀው ንግስቲቱንና የቤተመንግስቱን ቡድን የሚቃዎሙ እንግሊዛውያንን ሰልፍ እየተከታተለ በጥሩ እንግሊዝኛ ቀጥተኛ ዘገባ ቢሰራበት መዘዝ ያለው መሆኑን መርሳት አይገባም። እኛ ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስ እንደምንለው በእንግሊዝም “What happens in the Palace Remains in The Palace” የሚል መመሪያ አለ። በደም የጨቀየ ታሪክ ያለው ቤተመንግስት ነው ባኪንግሃም ፓላስ። ስለ ዲያና አሟሟት የተሰራውን ፊልም እንውሰድ። ይህ ፊልም እንግሊዝ ውስጥ ለመታየት ከ80 በላይ ክፍሎች ተቆርጠው መውጣት አለባቸው ተብሎ ታግዷል። ልክ ነው ‘ዘ-ዲክታተር’ የተባለው ልብ-ወለድና በተራ ጭብጥ ላይ ተመርኩዞ የተሰራ ፊልም በአፍሪካና በዓረቡ ዓለም ሲከለከል ብዙ የተጮኸውን ያህል በዲያና ታሪክና በአሟሟቷ ላይ ብዙ መረጃዎችን አጭቆ የተሰራው እውነተኛ ፊልም በምድር እንግሊዝ እንዳይታይ ሲከለከል ሚዲያዎች ብዙ አልደሰኮሩም። ከዚህ ሌላ በቅርቡ ሰሞኑን ብዙ የተወራለት የኬቲ ፅንስ ምርመራ እየተካሄደለት በነበረበት ጊዜ ወደ ሆስፒታሉ ስልክ ተደውሎ ነበር፣ ይህን ተከትሎ ስልኩን ተቀብላ ነበር የተባለችና በዚያ የምትሰራ አንዲት ነርስ ሞታ ወይም ተገድላ መጠነኛ ውዝግብ ተከትሎ ነበር። ነገር ግን ብዙም ሳቀጥል ጭጭ ተብሎ ታልፏል- What happens in the Palace Remains in The Palace። ይህ ደግሞ ገና በፅንስነቱ ማስገደል ጀመረ ያሉ ግን አሉ።
አበበ ሆይ ይህን መሰል (የግብፅንና የመርሲን) ነገር ለሕዝብ የምታቀርብ ከሆነ ግራና ቀኝ ማየት አለብህ ብዬ አልመክርህም። ምክንያቱም ይህን አንተ አታጣውምና። በተጨማሪም የታላላቅ ሚዲያዎችን አሰራር ታውቀዋለህና። አበበ ገላው በዋሽንግተኑ የሬገን አዳራሽ የቃውሞውን ባወረደበት ወቅት በዚያ ወኪሉን (ሪፖርተሩን) ያልላከ የሚዲያ ድርጅት አልነበረም። የአበበ ጩኸት ለሁሉ ተሰምቶ ይሆን የሚል ጥርጣሬ የሚያጭርም አልነበረም። በዚያች ደቂቃ በዚያ አዳራሽ ሁሉም ነገር ሰአቶች ሳይቀሩ የቆሙ የሚያስመስል ተአምር ስለተፈጠረ በዚያ የተገኘ ሁሉ የአበበን ስራ ተግቶታል። “አቶ መለስ ሆይ ንግግርዎ አይሰማም፣ ድምፅ ይጨምሩ” ያለ መስሎን ነው እንዳይሉ ደግሞ በጠራ እንግሊዝኛ ነው መልዕክቱን ያስተጋባው። በዚያ ቦታ በዚያች ዕለት እንግሊዝኛ ቋንቋ የማይሰማ ጋዜጠኛ ወይም ሪፖርተር የላካል ብሎ መገመት ጅልነት ነው የሚሆነው። ነገር ግን ይህ ነገር ዜና ላይ አልተሰማም። ቪኦኤን ጨምሮ በዝምታ ነው ያለፉት። ቪኦኤ ነገሩን የዘገበው ከአድማጮች ብዙ ኡኡታና ተቃውሞ ከገጠመው በኋላ ነው። በተቃራኒው የኢራኑን መሪ በአንድ የአሜሪካ ዩንቨርስቲ ውስጥ አንድ ተማሪ ኢራን የግብረ ሰዶማውያንን መብት አታከበርም ብሎ ዘለፋ ሲሰነዝርባቸው ግን ሚዲያዎች እንዴት እየተቀባበሉ እንዳስተጋቡት እናስታውሰዋለን!!
የግብፅን ነገር ወይም የሙርሲን መውደቅ ብዙ ሰዎች ነገሩን የክርስቲያን-ሙስሊም ቁርቁስ አድርገው ያዩትና ሙርሲ እንኳን ሄደ ሲሉ ይሰማሉ። በሌላ ወገን ደግሞ ሙርሲና ደጋፊዎቹ ‘እስማለዊ’ ስለሚባሉ በጭፍን እስልምና ተጠቃ የሚሉ ወገኖች ይታያሉ። እኔ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ?
የአሜሪካና የአውሮፓ ሚዲያዎች ለምንድን ነው የሙርሲን ደጋፊዎች ‘ኢስላሚስቶች’ የሚሏቸው?
ይህ ብቻ አይደለም አልሸባብ፣ ቦኮሃራም፣ የማሊ ተዋጊዎች ወዘተ ሲጠቀሱ ይህ ‘እስላማዊው’ የሚለው ቅጥያ ተዘውትሮ ጥቅም ላይ ይውላል። ቪኦኤ የአማርኛና የትግርኛ ክፍለ ጊዜ ‘እስላማዊው’ ሲሉ ቪኦኤ ኦሮምኛ ደግሞ ‘ኢስላሙማ’ ሲል ይሰማል። የቸችኒያ፣ የሶርያ፣ እየኮሰመኑ የመጡት የኢራን መጂሃዲኖችና የመሳሰሉት የአሜሪካ ጠላት የሆኑ መንግስታትን ያጠቃሉ የሚባሉ ተዋጊዎች ሙስሊሞችና የእስልምናን መመሪያ አንግበው የሚዋጉ ቢሆንም ‘እስላማዊ’ ሲባሉ አይሰሙም። በአውሮፓና በአሜሪካ ለእስልምና ጥላቻን ማራመድ እየተስፋፋ ነው፤ ታዲያ ይህ ‘እስላማዊው’ ማለት ‘የምትጠሉት’ ወይም ‘መጠላት ያለበት’ እንደማለት ሆኖ እያገለገለ ነውን? በኡጋንዳ የጌታን ትዕዛዛት ለማስከበርና ይህን መሰረት ያደረገ መንግስት ለመመስረት እዋጋለሁ የሚለው ‘የጌታ ተፋላሚ ጦር (Lord’s Resistance Army- LRA) መኖሩ ይታወቃል። ለምን ይህንን ቡድን ‘ክርስቲያናዊው’ እያሉ ሲጠሩት አልተሰሙም?
እኔ ሙስሊም አይደሁም። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ለዘመናት አብረን የኖርን ወንድማማቾች ነንና አንዱ የውስጥ ወይም የውጭ አካል ለራሱ ይመቸው ዘንድ እኛን ሊያጫርስ የሚጭራትን ትንሽ እሳት ገና በእንጭጯ ለማጥፋት ንቁ መሆን እንዳለብን ይሰማኛል።
በመጨረሻም የሙርሲን አባባል ያጋነንከውና ልዩ ትርጉም የሰጠኸው ይመስለኛል። ይህን ያደረግከው ለአገርህ ብለህ ነው ወይስ ሙግትህን ለማጠናከር። አቶ ሙርሲ “ኢትዮጵያውንን እርስ በርስ እናበጣብጣታቸው ብለው ሲዶልቱ” ያልከው የኢትዮጵያን ተቀዋዋሚዎች በመርዳት የኢትዮጵያን መንግስት እናዳክመው ያሉትን ነው? እዚህ ላይ ምን እንደምልህ እንጃ! አንድ ታሪክ ግን ልንገርህ። ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን ወረረ፣ ከሸፈበት። ዚያድ ባሬ ያልተቋጨ የግዛት ጥያቄ አለውና ኢትዮጵያን እያዳከመ መቆየትና ሌላ ጦርነት ማካሄድ እንዳለበት ተሰማው። ሻዕቢያንና ወያኔን ማገዝ ጀመረ፣ አስታጠቀ፣ ፓስፖርት ሰጥቶ በፈለጉበት እየተንቀሳቀሱ የውጭ ሃይሎችን ድጋፍ እንዲያገኙና ደጋፊዎዎቻቸውን ማደራጀት ይችሉ ዘንድ ሀኔታዎችን አመቻቸ። በዚህ ግዙፍ እገዛ ዚያድ ባሬና ሶማሊያ ባይጠቀሙም ዚያድ ባሬ የረዳቸው በጣም እንደተጠቀሙ፣ ኢትዮጵያችን በእጅጉ እንደተጎዳች እያየን ነው። ይህ ጉዳት ይሽር ይሆን? “የጠላቴ ጠላት…” ሲባል ምን ማለት ነው?
የቪኦኤዋነ አዳነች ፍስሃዬ የሙርሲን ንግግር በዚህ መልኩ ደጋግማ አስተጋብታዋልች። ሙርሲ ሲወድቁም ለውድቀታቸው ድጋፍ የመሰለ ፕሮግራም ሰርታለች። ለኢትዮጵያ አስባ ነው ወይስ በአሜሪካ ሲገደፍ የነበረው የሙባረክ መውደቅ አሳስቧት ወይስ የአሜሪካ አሻንጉሊቶች የሆኑ አምባገነኖችን መገልበጥ አደጋ አለው የሚል ትምህርት ልትሰጠን ፈልጋ?
ቻው!!