ፌዴራል ፖሊስ አገሪቱን በስለላ ካሜራዎች ለማጥለቅለቅ አቅዷል
ኢሳት ዜና:- የፌዴራል ፖሊስ ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስአበባ ተክሎ ሥራ ላይ ያዋላቸው የስለላ ካሜራዎች (cctv ካሜራዎች)
ውጤታማ በመሆናቸው ወደክልሎች ለማስፋፋት ማቀዱን አስታወቀ፡፡
ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው በኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስአበባ
ዋናዋና መንገዶች ላይ ካሜራዎችን በመግጠም የመቆጣጠሪያ ክፍል በማቋቋም በመንገዶቹ ላይ የሚሰሩ ሕገወጥ
ድርጊቶችንና የትራፊክ አደጋዎችን በአነስተኛ የፖሊስ ኃይል ያለብዙ ወጪና ድካም ለመቆጣጠርና ጸጥታ ለማስከበር
መቻሉን ይጠቅሳል፡፡
ይህንኑ ቴክኖሎጂ በከተማውና በክልሎች ለማስፋፋትና ተጨማሪ ሥራ እንዲያከናውን ለማድረግ ተከታታይ ሥራዎች
እየተሰሩ መሆኑን መረጃው ጠቅሶ ፣ “ተጨማሪ ሥራዎች” ያላቸውን ስራዎች ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡
በሚሊየን ዶላር ወጪ በአዲስአበባ ከተማ የተተከሉት እነዚሁ ዘመናዊ ካሜራዎች ዋንኛ ጥቅማቸው ኢህአዴግ መራሹ
መንግስት ዜጎችን ለመሰለል ካለው ጥልቅ ፍላጎት ጋር የተያያዘ መሆኑን በመግለጽ መንግስት ለሕዝብ የሚያስብ ቢሆን
ኖሮ ገንዘቡን ድህነትንና የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ ባዋለው ነበር ሲሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውሞ
አሰምተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በተያያዘ ዜና ፌዴራል ፖሊስ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚፈጸሙ የሳይበር ወንጀሎችን ለመከታተልና
አጥፊዎችን ለመያዝ ቢሮ ከፍቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ(ICT) በመደገፍ የሚሰሩ ወንጀሎች(ሳይበር ክራይም) አሳሳቢ እየሆኑ በመምጣታቸው
ወንጀሎችን ለመከታተል፣ለመመርመርና ለማጣራት፣አጥፊዎችንም ለፍርድ ለማቅረብ በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ
ዘርፍ በፎረንሲክ ዳይሬክቶሬት ስር የሳይበር ላብራቶሪ ተቋቁሟል፡፡ላብራቶሪውም በሰለጠኑ ባለሙያዎች መደራጀቱን
የፖሊስ መረጃ ጠቁሟል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የፖሊስ መኮንን መንግስት በኢንተርኔት በሚደረጉት ትግሎች ተደናግጧል፣ በአገሪቱ የለውጥ ፍላጎት እያየለ መምጣቱ አስደንግጦታል። በዚህም የተነሳ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር ይፈልጋል ብለዋል።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment