Pages

Apr 13, 2013

ትዝታ ዘ አራዳ! (እንደወረደ)


ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ

ከአዲስ አበባ ስታድየም ድምቀቶች አንዱ (አረ ዋናው ነው መሰለኝ…!) ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲጫወቱ የሚታየው ድምቀት ነው፡፡
የዛሬ ሁለት አመት ከመሃመድ ሰልማን ጋር ፒያሳ መሃሙድ ጋር  ከተገናኘን በኋላ፤ ተያይዘን የፒያሳ ልጅ መጽሀፍን ያበረከተልን፤ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የጋሽ ይድነቃቸው ጓደኛ እና ታላቁ ኢትዮጵያዊ፤ (መሃመድ ሰልማን እንደነገረን ደግሞ ከፈለገ ዛሬ ሄዶ ከማንዴላ ጋር ማኪያቶ የሚጠጣው!) ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ ያረፈበት ሂልተን ሆቴል ሄደን ነበር፡፡
በጋሽ ፍቅሩ ጋባዥነት ምሳችንን ድብን አድርገን በላን፡፡ እንዴት ያለ መታደል ነበር መሰላችሁ…! የሁለት ዘመን የፒያሳ አራዶች መሃከል ቁጭ ብሎ ምሳ መብላት ራሱን የቻለ አመት በዓል የማክበር ያኸል አይደለምን…!?
የጋሽ ፍቅሩን ግብዣ ኮምኩመን፤ ፊርማውንም ተቀበልነው፡፡ መሃመድ ሰልማን ፊርማዋን ከሲቪዬ ጋር አያይዛታለሁ… ብሎ ነበር፡፡ እኔም ለብዙ ጓደኞቼ እያሳየሁ፤ “ጋሽ ፍቅሩ እኮ ነው!” ብዬ ጎርሬባት ሞገስን አግኝቼባታለሁ…!
በመቀጠል ከመሃመድ ሰልማን ጋር ተያይዘን ወደ አዲስ አበባ ስታድየም ሄድን፡፡
ስታድየም ስንደርስ ጨዋታው እያለቀ ቢሆንም፤ የአዲስ አበባ ስታድየም ድምቀት ግን ገና መጀመሩ ይመስላል፡፡ ትኬት መሸጫ በሮች በሙሉ ተዘግተው ፖሊሶች በበራፉ ላይ ተኮልኩለዋል፡፡
ደፈር ብለን ወደ አንዱ በር ሄድን…  ፌደራል ፖሊሱ ኮስተር ብሎ “ወደዛ ተንቀሳቀሱ…” አለን፡፡ “… አረ እኛ…” ብለን ለመለማመን ስንጀምር አንድ የአዲስ አበባ  ፖሊስ አሳዝነው ነው መሰለኝ፤ “… እነዚህማ መምህራኖች ናቸው ይግቡ እንጂ…” አለን፡፡
ለካስ ፌደራል ፖሊሶች ለመምህራን ትልቅ አክብሮት አላቸው፡፡ … አረ እግዜር ያክብራቸው፡፡ እንደዚሁ ወደፊት ደግሞ፤ ተማሪዎችንም ነዋሪዎችንም የሚያከብሩ እንደሚሆኑ ተስፋ አለኝ፡፡
ያቺ ቀን አዲስ አበባ ስታድየም፤ የመጨረሻዋ ቀኔ እንደሆነች አልታወቀኝም ነበር፡፡  ግን ነበረች፡፡ ከዛ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም በሀሳብ እንጂ በአካል መግባት አልተቻለኝም፡፡
ስታድየሙ ቢጫ በቀይ የጎርጊስ ደጋፊዎች ቡኒ እና ቢጫ ደግሞ የቡና ደጋፊዎች ለብሰው ማዶ ለማዶ በዜማ ሲበሻሸቁ እና ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ማየት ከየትኛውም ኮንሰርት በላይ አስደሳች ነው፡፡
ዛሬ፤ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ እየተጫወቱ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር በዚህ ሳምንት ውስጥ ያለሁበት ከተማ  ማንችስተር ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ ካደረጉት ደርቢ ይልቅ የተቀማዋት ሸገር ላይ እየተደረገ ያለው ደርቢ ይበልጥ ቀልቤን ይስበዋል፡፡
እናንት መንታፊዎች ስንት ነገር እንደቀማችሁን ይገባችሁ ይሆን…!? በህግ አምላክ ሀገራችንን መልሱልን!
አሁን መሀመድ ሰልማን ስዊዲን ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ ፓሪስ ነው ያሉት፡፡ እኔ ደግሞ ማንችስተር እገኛለሁ፡፡ ሁለቱ የአራዳ ልጆች አዲሳባ ስታድየምም ሆነ መላው አራዳ ሲናፍቃቸው   ”ሻ…” ባላቸው ቀን ወደ ሸገር መሄድ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን መች እንደምሄድ አላውቅም፡፡ እንደምንም ለድፍረቴ ጠላ ጠጥቼም ቢሆን የሆነ ቀን መሄዴ ግን አይቀርም!
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
ሰዎቹን ሸኝተሸ አትጠሪንም ወይ
እስከመቼ ድረስ እንቁም በረንዳ
በገዛ ሀገራችን አደረግሽን ባዳ
አቦ ግቡ በይን ናፈቀን አራዳ
አደረች አራዳ አደረች አራዳ
የኔ ብርቱካኔ የኔ ፅጌሬዳ…
እናንተዬ እንዲህ እንዲህ እየተባለ እኮ ነው የዘንድሮ ዘፈን ግጥም የሚጀመረው… አረ አበረታቱን!

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate