Pages

Aug 5, 2013

በግብረሰዶም ተጠርጣሪዎች ላይ የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ባለሙያ የምስክርነት ቃል ሰጡ


child-sex-abuse


ሁለት የ10 እና የ11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የአራተኛና የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የግብረሰዶም ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት የካራክተር ሆልማርክ አካዳሚ ስድስት መምህራን ክስ ላይ፣ ከዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በተጨማሪ አንዲት የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ባለሙያ ሐምሌ 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የሙያ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጡ፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የመሠረተውን የወንጀል ክስ በማየት ላይ ያለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሰባተኛ የወንጀል ችሎት፣ ስማቸው በሚዲያ እንዳይገለጽ የከለከለላቸው የሳይኮሎጂስትና የሳይካትሪ ባለሙያዋ፣ በተጠርጣሪ መምህራን የግብረሰዶም ጥቃት ደርሶባቸዋል የተባሉትን ሁለት ወንድ ሕፃናት፣ ለሦስት ጊዜያት አግኝተው እንዳነጋገሯቸው ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹንም ሆኑ የጥቃቱ ሰለባ ናቸው የተባሉት ሕፃናትን እንደማያውቋቸው የገለጹት ባለሙያዋ፣ ሕፃናቱን ከአራት ወራት በፊት ቃለ መጠይቅ እንዲያደርጉ ታዘው ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለሙያዋ ከሕፃናቱ ጋር ቃለ መጠይቁን ያደረጉት፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤትና በፖሊስ ጣቢያ መሆኑን ጠቁመው፣ መጀመሪያ ከእናቶቻቸው ጋር ቀጥለው ደግሞ ሕፃናቱን ለብቻቸው ማነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡
ሕፃናቱን መጀመሪያ ከወላጆቻቸው ጋር ያነጋገሯቸው ስለማያውቋቸው ለመለማመድ መሆኑንና ቀጥለው ለብቻቸው ቤተሰቦቻቸውን ሳይፈሩ እንዲያነጋግሯቸው ማድረጋቸውን የገለጹት ባለሙያዋ፣ በምክር ወይም ድርጊቱን በማስጠናት የተሳሳተ ማስረጃ እንዳይሰጧቸው፣ ቃለ መጠይቁን ያደረጉላቸው እያጫወቱና ዘና እንዲሉ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠዋት ቁርሳቸውን ከበሉበት እስከ ማታ ከትምህርት ቤት ተመልሰው ወደ ቤታቸው እስከሚገቡበት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ያደረጉትን አንድ በአንድ እንዲያስረዷቸው በመጠየቅ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ባለሙያዋ የሚፈልጉትን በጨዋታ ዓይነት ተጎጂ የተባሉት ሕፃናት ምንም ሳይፈሩ የጠየቋቸውን ሁሉ በአግባቡ እንደመለሱላቸው አክለዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያትም ያንኑ ጥያቄ ሲጠይቋቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ማስረዳታቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ሕፃናቱ እንዴት ቀናቱን ሊያስታውሱ እንደሚችሉ ተጠይቀው ባለሙያዋ ሲመልሱ፣ ሕፃናቱ ቀኑን በትክክል ባያስታውሱም ድርጊቱ ተፈጸመ በተባለበት ጊዜ በዓል ካለ ወይም በዚያን ጊዜ የማይረሳ ነገር ካለ እሱን በማስታወስ እንዲያስታውሱት ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ከተጠቂዎቹ አንዱ ቀኑን በደንብ አስታውሶ እንደነገራቸው የገለጹት ባለሙያዋ፣ ድርጊቱን ፈጽመዋል ያሏቸውን ሰዎች ስምና ድርጊት እንዳስረዷቸው ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ሕፃናት ከድርጊቱ በኋላ የሚያሳዩት ባህሪ ካለና የጉዳዩ ባለቤት በሆኑት ሕፃናት ላይ ያዩት የባህሪ ለውጥ ወይም ምልክት ካለ እንዲያስረዱ ተጠይቀው፣ ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ሕፃናት አራት ባህሪያትን ያሳያሉ፡፡ ፈሪ፣ ኃይለኛ (ተደባዳቢ)፣ ብቸኛ መሆንን መፈለግና ከፍተኛ የሆነ የወሲብ ፍላጎት የማሳየት ባህሪያት እንደሚያመጡ አስረድተዋል፡፡ ሌላው በትምህርት ላይ የሚያሳዩት ሁኔታ ሲሆን፣ በአንድ ትምህርት ላይ ብቻ ጎበዝ የመሆንና ሌላውን የመጥላት ወይም ፍላጎት ያለማሳየትና ደብተራቸውን ጥሎ የመምጣት ባህሪም እንደሚያመጡ ባለሙያዋ ገልጸዋል፡፡
ተጠቂ ከተባሉት ሁለቱ ሕፃናት አንደኛው የወሲብ ፍላጎት እንዳለውና እሱም እንዳረጋገጠላቸው የገለጹት ባለሙያዋ፣ ይኼ ስሜት ሲመጣበት ከማን ጋር ለማድረግ እንደሚፈልግ ጠይቀውት፣ ከወጣት ወንዶችና እንደ አስተማሪዎች ካሉ ወንዶች ጋር ማድረግ እንደሚፈልግ፣ ወንድ ሕፃናትና ትልቅ ሰው እንደማይፈልግ እንዳስረዳቸው ገልጸዋል፡፡ ይኼንንም ጥያቄ ያቀረቡለት በጥናት ሕፃናት የሚጠቁት በአብዛኛው በሚያውቁትና በቤተሰብ፣ ወይም ዘመድ መሆኑን ስለተረጋገጠ በቤታቸው ውስጥ ወንድሞችና አባት ስለሚኖሩ ከነሱ ጋር ያለውን ሁኔታ ለማወቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሕፃናት ድርጊቱ እንደተፈጸመባቸው ወዲያውኑ የቤተሰብ እንክብካቤ፣ አማካሪ ዘንድ በመውሰድ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ፣ ድርጊቱ እንዳልተፈጸመ ሆኖ እንዲሰማቸው ወይም ጥፋቱ የእነሱ እንዳልሆነ እንዲያስቡ ስለሚያደርጋቸው በቀጣይ ከሚደርስባቸው ተፅዕኖ ማዳን እንደሚቻልም ባለሙያዋ አብራርተዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እያደጉ ሲሄዱ እነሱም ወደ ተመሳሳይ ተግባር እንደሚያመሩ፣ ኃይለኞች እንደሚሆኑ፣ ከቤት ወጥተው ተስፋ በመቁረጥ ወደማይሆን ነገር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉም አክለዋል፡፡
መምህራኑ የተጠረጠሩባቸው ሁለቱም ሕፃናት ‹‹ትምህርት አስጠልቶኛል፤ ባልሄድ ደስ ይለኛል፤›› እንዳሏቸው ባለሙያዋ ጠቁመው፣ በጥናትም የተረጋገጠው ሕፃናት ድርጊቱ ከተፈጸመባቸው በኋላ ብቸኝነትን እንደሚመርጡ፣ ፈሪና ኃይለኛ እንደሚሆኑ መረጋገጡንና በእነሱም ላይ ምልክቱ ተግባራዊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አንደኛው ተጠቂ ብዙ ትምህርት ቤቶችን እንደቀያየረና በሄደባቸው ትምህርት ቤቶች ጥቃቱ እንደደረሰበት በመጥቀስ፣ የድርጊቱን ፈጻሚዎች እንዴት ሊያውቁት እንደሚችሉ ጠይቀውት ከሆነ ባለሙያዋ እንዲያስረዱ ሲጠይቋቸው፣ በተለይ አንደኛው ተጠቂ ከፍተኛ የወሲብ ስሜት ስላለው፣ ተጠግቶ ስለግብረሰዶም እንደሚያወራቸው ነግሯቸዋል፡፡ ስሜታቸው ከፍተኛ ስለሚሆን ተጠቂዎች አንገት ሥር የመሳም፣ የመነካካት፣ በብልት አካባቢ መመልከትና መቀመጥ እንደሚያዘወትሩ ባለሙያዋ አክለው፣ በአንደኛው ሕፃን ላይም ይህንን ምልክት ማየታቸውን አስረድተዋል፡፡
ድርጊቱ በቤተሰብ ቢፈጸም በሌላ ሰው የማሳበብ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበትን አጋጣሚ በሚመለከት ለባለሙያዋ ጥያቄ ቀርቦ፣ ‹‹እውነት ነው፣ አድራጊውን በመፍራት በሌላ ሰው ላይ ያሳብባሉ፤›› ካሉ በኋላ፣ በሁለቱ ሕፃናት ቤተሰብ ዙሪያ ስላለው ሁኔታ ሲጠየቁ፣ ድርጊቱ የተፈጸመው በትምህርት ቤት ውስጥ መሆኑን ብቻ መናገራቸውን አውስተዋል፡፡
ስድስት መምህራን በአንድ ሕፃን ላይ ተፈራርቀው ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ ልጁ ያለምንም ጉዳት ወደ ጨዋታ የሚሄድበት ሁኔታ ካለ እንዲያስረዱ ባለሙያዋ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ አንዳንድ ጊዜ ሊገጥም እንደሚችል፣ ግን የልጁ ሁኔታ እንደሚወስን ካስረዱ በኋላ፣ ይኼ የአካል ጉዳትን የሚመለከት በመሆኑና እሳቸውም በዚህ ዙሪያ ማብራራት እንደማይችሉ ተናግረው፣ የሕክምና ባለሙያ ማብራሪያ ሊሰጥበት እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሕፃናት ተፅዕኖው አብሯቸው አድጎ ትዳር በሚመሠርቱበት ጊዜ ከፍተኛ ችግር እንደሚያስከትልባቸው ገጠመኛቸውን በማስረዳት አደገኛነቱን ተናግረዋል፡፡
ሕፃናቱ የግብረሰዶም ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው በኋላ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ምርመራ በማድረጋቸው፣ ፍርድ ቤቱ የምርመራ ውጤቱን ተከትሎ በሰጡት ማስረጃ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሆስፒታሎቹ መታዘዛቸው ይታወሳል፡፡ በትዕዛዙ መሠረት ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ‹‹ባለሙያ የለኝም›› ብሎ ምላሽ ሲሰጥ፣ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግን ባለሙያ ሳይልክ በመቅረቱ፣ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲልክ ፍርድ ቤቱ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል የሪፖርተር ጋዜጣ ዘጋቢ ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. የአካዳሚው መምህራን የተጠረጠሩበትን የግብረሰዶም ጥቃት ወንጀል አስመልክቶ ለመዘገብ በፍርድ ቤቱ የተገኘ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ የሚታየው በዝግ ችሎት መሆኑን ገልጾ እንዲወጣ በማዘዙ ችሎቱን ሊከታተል አልቻለም፡፡
ዘጋቢው በፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ በመዋል መረጃውን ከችሎቱ ታዳሚዎች በማግኘት ውሎውን በተመለከተ ‹‹ጋዜጠኞች ችሎት እንዳይገቡ ተከለከሉ›› በማለት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ችሎቱ ዝግ የሆነው በሌሎች መዝገቦች እንጂ በግብረሰዶም ጥቃት ወንጀል የተጠረጠሩትን እንደማያካትት አስታውቆ፣ ችሎቱ በግልጽ መካሄዱን በመግለጽ ማስተካከያ እንዲያደርግ አዟል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ሐምሌ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ችሎቱ ዝግ እንዲሆን የተደረገው በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ እንደሚገኘው አንዳንድ ክሶች (ጉዳዮች) በዝግ ችሎት መታየት ስላለባቸው፣ የሪፖርተር ዘጋቢ ከችሎት እንዲወጣ የተደረገው በዝግ ችሎት መታየት ለሚገባቸው ጉዳዮች እንጂ፣ በግብረሰዶም ወንጀል ተጠርጥረው ለተከሰሱት ባለመሆኑ፣ ዘገባው ስህተት እንዳለበትና ይኼው እንዲገለጽ በድጋሚ አዟል፡፡
የሪፖርተር ዘጋቢ በዕለቱ ለብይን ተቀጥሮ የነበረውን የግብረሰዶም ጥቃት ወንጀል ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ለመከታተል በሰዓቱ ችሎቱን ታድሟል፡፡ ችሎቱ በዝግ እንደሚታይ በመግለጽ ታዳሚዎች እንዲወጡ ዳኛዋ ሲያዙ ዘጋቢው ወደኋላ በመቅረት ለፍርድ ቤቱ ጋዜጠኛ መሆኑን በመግለጽ መታደም እንዲችል ሲጠይቅ አልተፈቀደለትም፡፡ ውጭ ቆይቶ በተደጋጋሚ ለመግባት ሲሞክር የችሎት ፖሊሶች ‹‹ዝግ ነው›› በማለት ሊያስገቡት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ችሎቱ እስከሚያበቃ እዚያው ቆይቶ ከችሎቱ ታዳሚዎች ባገኘው መረጃ መሠረት ሲዘግብ፣ ችሎቱ ጉዳዩን በዝግ ማየቱን በዘገባው አካቷል፡፡ ዘጋቢው የዕለቱን ችሎት በአግባቡ እንደዘገበ ቢታወቅም፣ ፍርድ ቤቱ መስተካከል እንዳለበት በማዘዙ በድጋሚ ለመዘገብ ተገደናል፡፡
ሌላው ፍርድ ቤቱ እንዲታረም ያዘዘውና ሪፖርተርም ስህተት መሆኑን አምኖ ተስተካክሎ እንዲነበብ አንባቢዎቹን የሚጠይቀው፣ የግብረሰዶም ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል በተባሉት ሁለት ወንድ ሕፃናት ዙሪያ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡ የታዘዙትን የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ባለሙያን በሚመለከት ስለተሠራው ዘገባ ነው፡፡
በወቅቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ሠራተኛ ሆኖ ሳለ፣ የሪፖርተር ዘጋቢ ግን ቀደም ብሎ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በምስክርነት ቆጥሯቸው የነበሩትን የሥነ ልቡና ባለሙያን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በተፈጠረው ስህተትም ፍርድ ቤቱንና አንባብያንን ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate