Pages

Oct 7, 2013

ከቀይ ሽብር ተፅዕኖ ያልተላቀቀው ፖለቲካ



‹‹የምን ይቅርታ? ለሕዝብና ለአገር ዕድገት ነው የተነሳነው፡፡ በትግሉ ሒደት ስህተት ፈጽመናል፤ ስህተቱ የትግሉ አካል ነው፡፡ ዘውዳዊ ሥርዓቱን ጥለናል፤ የኢትዮጵያንም ሕዝብ ነፃ አውጥተናል፡፡
የደቡብና የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ይናገሩ፡፡ ከወላይታ የመጣውና ከአናሳ ሃይማኖት የመጣው ግለሰብ አገር የሚመራው በእኛ ትግል ምክንያት ነው፡፡ በማያውቀውና ባላነበበው ታሪክ የበሰበሰ ይለናል? የመጀመሪያ ዘመቻችን የዕውቀት ዘመቻ መሆን አለበት፡፡››
ከቀይ ሽብር ተፅዕኖ ያልተላቀቀው ፖለቲካይህን የተናገሩት የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ሲሆኑ መልስ እየሰጡ የነበረው ደግሞ ፓርቲያቸው ኢሕአፓንና የትግል አጋሮቻቸውን አስመልክቶ ትችት ላቀረበ አንድ ወጣት ነበር፡፡ ወጣቱ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ዘግናኝና ሰቅጣጭ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል፡፡ መድረክ ላይ ያላችሁት ሰዎች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በተለያየ መስመር ተሰማርታችሁ ባመናችሁበት አቋም የአገሪቱን የፖለቲካ እመርታ ለማስለወጥም ሆነ ለማሳደግ የራሳችሁን ሚና ተጫውታችኋል፡፡ የ60ዎቹና 70ዎቹ ትንታግ ትውልድ ዳፋ አሁንም ባለንበት የፖለቲካ ተግባራዊ ሁኔታ ላይ በእጅጉ ሲንፀባረቅ ነው የምናየው፡፡ መጠላላቱና ጥቅመኝነቱ እንዳለ ነው፡፡ እዚህ አዳራሽ ውስጥ በመኢሶን፣ በኢሕአፓና በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ የታገላችሁ ሰዎች አላችሁ፡፡ ያ የከሰረ፣ የበሰበሰ፣ የተቀበረና የሞተ የትግል ውጤት እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ግን አሁንም ሰንኮፉ አልለቀቀንም፡፡ በምትጽፏቸው መጽሐፎችና በምታቀርቧቸው ፕሮግራሞች ላይ አሁንም የቀይ ሽብር ትውስታዎች እንዳሉ እናያለን፡፡ መቼ ነው ኢሕአፓዎችና መኢሶኖች በአደባባይ ወጥታችሁ የሠራነው ስህተት፣ የፈጸምነው በደል ይኼ ነበር፤ ትውልድ ከእኛ ተምሮ እዚህ ላይ ትኩረት ያድርግ በማለት ይቅርታ የምትጠይቁት? አሁንም እየተታኮሳችሁ ነው፣ ዛሬም ኢትዮጵያን የምትተረጉሙት በተለያየ መንገድ ነው፤›› በማለት ነበር አስተያየት የሰጠው፡፡ 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ መሆኑን የገለጸው ወጣት አስተያየት ቁጣን የቀሰቀሰው በፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ላይ ብቻ አልነበረም፡፡ መድረኩ ላይ የጥናት ሥራዎቻቸውን ያቀረቡትን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ፣ ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ፣ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን ጨምሮ ከታዳሚዎቹ ውስጥ “Tower in the Sky” በተሰኘ መጽሐፏ በአጭር ጊዜ ዝነኛ የሆነችው የኢሕአፓ የቀድሞ ታጋይ ሕይወት ተፈራና ከኢሕአፓ መሥራቾች አንዱ የሆነው የብርሃነ መስቀል ረዳ ባለቤት አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤልን ጨምሮ፣ የ1960ዎቹ እና የ1970ዎቹ ትግል አካል የነበሩ በርካታ ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡ 
መስከረም 19 ቀን በደሳለኝ ሆቴል የተዘጋጀው ሕዝባዊ መድረክ በአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ መብት መታሰቢያ፣ በኢንተር አፍሪካ ግሩፕና በጀስቲስ አፍሪካ ትብብር ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማው ቀይ ሽብር በኢትዮጵያ ዳግም እንዳይከሰት ምን ማድረግ ይገባል? በሚለው ጥያቄ ላይ ውይይት ለማድረግ ቢሆንም፣ በመድረኩ ላይ የተንፀባረቁት የሐሳብ ልዩነቶች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዛሬም ከቀይ ሽብር ተፅዕኖ ያልተላቀቀ መሆኑን ያረጋገጠ ነበር፡፡ 
ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግን ጨምሮ በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ የፖለቲካ ትግል ተሳታፊ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት የዛሬዋ ኢትዮጵያን የመንግሥትና የተቃውሞ ፖለቲካ መዋቅርን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉ ወሳኝ ዘርፎችን በበላይነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዕድሜና በጤና ምክንያት ከመድረኩ ሲገለሉም ከማርክሲስታዊ ሌኒኒስታዊ ርዕዮተ ዓለም የተቀዳውን አካሄዳቸውን ለአዲሱ ትውልድ እያወረሱ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግም ዲሞክራሲን የሚሰብከውን ሕገ መንግሥት፣ ከሕገ መንግሥት ጀርባ ያለው ሌላው ሕገ መንግሥት በሚባለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንዲሸረሸር ያደረገው ከዚሁ ከማርክሲስታዊ ሌኒኒስታዊ ርዕዮተ ዓለም ጋር ካለው ጥብቅ ቁርኝት አንፃር እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡ የቡድኖቹ ቅርበትና ልዩነት ርዕዮተ ዓለምን መሠረት ያደረገና ከኋላ ታሪክ መቀዳቱ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ለውጥ እጅግ አዝጋሚ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ 
በመድረኩም የተስተዋለው ይኼው እውነታ ነው፡፡ የወጣቱ ትውልድ አባላት ጥያቄ በአላዋቂነት ነው የተዘጋው፡፡ አንድ የመኢሶን አባል የነበሩ ግለሰብ ጥያቄም በተቃውሞ ነው የተመለሰው፡፡ ለነገሩ ግለሰቡም ውስብስቡን ፖለቲካ እጅግ አቃለው ኢሕአፓ ለኤርትራ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ማሰቡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለውጭ ኃይል አሳልፎ ከመስጠት ጋር ነው ያያያዙት፡፡ ኤርትራ በወቅቱ የኢትዮጵያ አካል ነበረች፡፡ የኢሕአፓ አባል የነበሩ ምሁራን የፓርቲውን ስህተት ይደፋፍናሉ ለሚለው ጥያቄም ምላሽ አልነበረም፡፡ ለዘመኑ ወጣት አክብሮት አትሰጡም ተብለውም ሲተቹ አንድ ዕድሜያቸው ገፋ ያለ ግለሰብ፣ ‹‹የዘመኑ ወጣት እንደያኔው በቀላሉ አይነዳም›› ሲሉ፣ የአብዮቱ ተሳታፊዎች በጥቂት ወራት ባዕድ የሆነ የሌላ አገር ርዕዮተ ዓለምን ወደ ኢትዮጵያ አውድ ለመቀየር እንኳን ሳይሞክሩና በጥልቀት ሳይረዱት በመከተላቸው አገሪቱ መታመሷን ሲገልጹም ድጋፍ አላገኙም፡፡ 
ወጣቱ ትውልድ ከእናንተ ምን ይማር? በሚል ለቀረበው ጥያቄ ከመድረክ ጥናት አቅራቢዎቹና ከታዳሚዎቹ መካከል የተለያዩ ምላሾች ቀርበዋል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የዕውቀትን አስፈላጊነት መማር ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የሕዝቡን ሁኔታ በማርክስ ጽሑፎች መመለስ አይቻልም ነበር፡፡ መቻቻልና መደማመጥ መማር ይቻላል፡፡ ስህተትን መቀበል መማር ይቻላል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በበኩላቸው፣ ‹‹የኢትዮጵያን ታሪክ በብቸኝነት ልንይዝ እንደማይገባ ልንማር ይገባናል፡፡ ታሪካችን ከሌሎች አገሮች ጋር ተመሳሳይነት ነበረው፡፡ እያነፃፀርን ልንረዳው ይገባናል፤›› ብለዋል፡፡ 
በአብዮቱ ዕጣ ፈንታ ላይ የዳያስፖራው ሚና ምን ነበር? የመኢሶንና የኢሕአፓ ልዩነት ምን ያህል ሰፊ ነበር? መኢሶን ወይም ኢሕአፓ ከሕዋሓት ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? ከመኢሶን ወይም ከኢሕአፓ አንዳቸው በደርግ ቦታ ሥልጣን ቢይዙ ቀይ ሽብር እንደማይኖር ምን ማረጋገጫ አለ? በአሁኑ ወቅት የአደባባይ ምሁራን የጠፉት ከቀይ ሽብር ጋር በተያያዘ ነው ወይ? ቀይ ሽብር ለመንግሥትና ለሕዝብ አሉታዊ ግንኙነት እንዴት ነው አስተዋጽኦ ያደረገው? በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባሕል እንዴት መፍጠር ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎችም ከተሳታፊዎች የተሰነዘሩ ሲሆን የተወሰኑት ብቻ ምላሽ አግኝተዋል፡፡ 
ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ መኢሶንና ኢሕአፓ ‹እናሸንፋለን› እና ‹እናቸንፋለን› ከሚለው እጅግ የዘለለ ልዩነት እንደነበራቸው በመጥቀስ ልዩነታቸው ጥቃቅን እንዳልነበር ያመለከቱ ሲሆን፣ ሁለቱም ድርጅቶች በትክክል ማርክሲስታዊ ሌኒኒስታዊ ነበሩ ለማለት እንደማይቻልም አስረድተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ልዩነቱ የፖለቲካ ሥልጣን ጉዳይ እንደነበር አስገንዝበው፣ ደርግም ሆነ እሱን ለመፋለም የተሠለፉት ኃይሎች ጥፋተኞች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ መኢሶንና ኢሕአፓ በጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ ጉዳይ እስከ ጥር ወር 1967 ዓ.ም. ድረስ አንድ የነበሩ ቢሆንም፣ መኢሶን ‹ሒሳዊ ድጋፍ› በሚል ከደርግ ጋር ለመሥራት መወሰኑ በሥልጣን አያያዝ አካሄድ ላይ መሠረታዊ ልዩነት እንዲኖራቸው ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ 
የመኢሶንና የኢሕአፓን የአደባባይ ይቅርታ በተመለከተ ዶ/ር ካሳሁን በግለሰቦችና በመጻሕፍት ውስጥ ይቅርታቸው ቢታይም፣ በአሁኑ ወቅት ድርጅቶቹ ሕልውና ስለሌላቸው ያን ማድረግ አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ በስሜት መናገር እንደማይጠቅም የገለጹት ፕሮፌሰር ባህሩ፣ ድርጅቶቹ ይቅርታ የመጠየቅ ፍላጎት የሌላቸው መነሻቸው ለኢትዮጵያ በጎ ነገር ለመሥራት መሆኑን በመጥቀስ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ የያኔውን የዳያስፖራ ተፅዕኖ በተመለከተ አስተያየት ሲሰጡ የያኔው የዲያስፖራ ተፅዕኖ እንዳሁኑ ጠንካራ እንዳልነበር አስገንዝበዋል፡፡ 
አንድ አስተያየት ሰጪ የቀይ ሽብር ተጎጂዎችን ለመደገፍና በእነሱ ዙሪያ የተሟላ መረጃ የመስጠት ችግር እንዳለም ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤል በቀይ ሽብር ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር በውል ሊታወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ 
ቀይ ሽብር እንዳይደገም
የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሲመረቅ የአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ መብት መታሰቢያ ስብሰባ አዳራሹ ላይ የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡ የመታሰቢያው ጊዜያዊ የአመራር ቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ እ.ኤ.አ. ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. መሠረት ድንጋይ ሲጣል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቦታውን ልዩ አብነት አስመልክቶ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር በጥሞና ማውሳታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ቦታው የቀድሞው የከርቸሌ እሥር ቤት እንደነበርና ‹ዓለም በቃኝ› የተሰኘ በጣልያን ወረራ ጊዜና በኋላም በደርግ በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሰቃዩበትና የገደሉበት ቦታ እንደነበርም ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል፡፡ 
መታሰቢያው ቀይ ሽብርን ጨምሮ በሩዋንዳና በደቡብ አፍሪካ የተፈጸሙትን የዘር ማጥፋትና የአፓርታይድ ጭቆና፣ ባርነትና ቅኝ ግዛት የሚታወሱበት እንደሚሆንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በመታሰቢያው ብዙኃን ጉዳተኞችን ከማስታወስ አልፎ በአፍሪካውያን መሠረታዊ ለውጦች ላይ መሰል አደጋ መቼም በማንም ላይ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ያሉ ሕዝቦች አቋም የሚያንፀባርቁበት ነው፤›› በማለትም ዋነኛ ዓላማውን አመልክተዋል፡፡ 
የመጀመሪያው ዙር ስብሰባ በሩዋንዳ እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 10 እስከ 12 ቀን 2012 መካሄዱን የጠቆሙት ፕሮፌሰር አንድሪያስ፣ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ሰለባዎችን ለማስታወስ በየዓመቱ የ100 ቀን የሐዘን ጊዜ መኖሩን አስታውሰው፣ በኢትዮጵያም ለቀይ ሽብር ሰማዕታት የሐዘን ጊዜ መመደብ ያስፈልግ ይሆን ወይ? ብለው እንዲጠይቁ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የተደረገው የመታሰቢያው ስብሰባ ስለ ቀይ ሽብር የሚመለከታቸው አካላት ሐሳብ በመለዋወጥ የተሻለ መግባባት ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 
የቀይ ሽብር ፖለቲካዊ አንድምታዎች
የ1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አብዮት ሒደት የተጀመረውና አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖዎቹን እያሳደረ የተጓዘው የዳበረ ሰላማዊ ፖለቲካ ሽግግር ባሕልም ሆነ የነቃ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ባልተለመደበትና ባልዳበረበት አጠቃላይ ማዕቀፍ እንደነበር የገለጹት ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ፣ አብዮቱ ተስፋ እንደተደረገው ሰላማዊና ከደም መፋሰስ የፀዳ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡
ለቀይ ሽብር መከሰት ዋነኛው ምክንያት በለውጡ እንቅስቃሴ መፍትሔ በሚያስፈልጋቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ በቂ የሐሳብ ልውውጥ ተደርጎ ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ የአብዮቱ መቀጣጠል ድንገተኛነትና ግብታዊነት፣ እንዲሁም ብሔራዊ ፍላጎቶችን አቀናጅቶ ሒደቱን መምራት የሚችል ግንባር ቀደም ድርጅት ተዘጋጅቶ አለመቆየቱ እንደሆነ ዶ/ር ካሳሁን አስረድተዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተባለው ድርጅት በርካታ አባላትና ደጋፊዎችን አፍርቶ የጀመረው የከተማ ሽምቅ ውጊያ የበርካታ ሺሕ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈውንና በአጠቃላይ የኅብረተሰቡን ሕይወት ያናጋውን ቀይ ሽብር ተብሎ የሚታወቅ ክስተት ማስከተሉን የጠቆሙት ዶ/ር ካሳሁን፣ ይህ አሉታዊ ውጤት በአገሪቱና በዜጎቿ ላይ ያደረሰውን ፈርጀ ብዙ ጉዳት ተቋቁሞ በትክክለኛ መስመር ላይ የተመረኮዘ ግንባታና ተሃድሶ ለማካሄድ እስካሁንም ድረስ እጅግ ሰፊ ልፋትና ጥረት የሚጠይቅ ዓብይ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ 
ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ በቀይ ሽብር የተነሳ ሦስት መሠረታዊ የፖለቲካ አንድምታዎች መድረሳቸውን ያስረዳሉ፡፡ የመጀመሪያው ተፅዕኖ ከመንግሥትና ከሕዝብ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ በአብዛኛው የኅብረተሰቡ ክፍል ባሕልና እምነት መንግሥት ሕዝብን ከአደጋና ክፉ ነገሮች የሚጠብቅ፣ የሚከላከልና የሚታደግ አካል ተደርጐ ሲወሰድ የነበረበት ሁኔታ ቀይ ሽብር ባደረሳቸው ጥፋቶችና መናጋቶች የተነሳ ተቀይሮ የሕዝብ አስተዳዳሪ የሆነው መንግሥት በአጥፊነት፣ በግፈኝነትና በመከራ ምንጭነት በሚታይበት ሁኔታ የመተካት ዝንባሌ በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል፡፡ የኅብረተሰቡና የመንግሥት ግንኙነት የጥርጣሬ፣ የፍርኃትና ያለመተማመን ገጽታዎች እንዲላበስ አስገድዷል፤›› ብለዋል፡፡
ሁለተኛው ተፅዕኖ ከዜጎች የፍርኃት ስሜት ጋር የተያያዘ እንደሆነም ዶ/ር ካሳሁን ገልጸዋል፡፡ “ቀይ ሽብር በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ያሳደረው የፍርኃትና የጭንቀት ድባብ በርካታ ዜጎች በአገሪቱ የፖለቲካ ዋና ዋና ጉዳዮች በንቃት የመሳተፍና የየበኩላቸውን ገንቢ አስተዋጽኦ የማድረግ አስፈላጊነትን በርቀት እንዲሸሹና በገለልተኛነት እንዲያዩት የሚያደርግ አዝማሚያ አስፍኗል፤” በማለት አስረድተዋል፡፡
ሦስተኛው ተፅዕኖ ከዜጎች ባሕሪ መለወጥ ጋር የተያያዘ መሆኑን ዶ/ር ካሳሁን ጠቁመዋል፡፡ “በቀይ ሽብር ሳቢያ ብዙዎች የፖለቲካ አስመሳይነት፣ የአድርባይነትና የለዘብተኝነት ባህሪያትን ተላብሰው ነገሮችን ከአጭር ጊዜና ግላዊ ጥቅምና ፍላጎት ማሟያ አንፃር ብቻ የመመልከት አጉል ባሕሪ እንደ ዓላማ እንዲይዙ አድርጓል፡፡” 
ዶ/ር ካሳሁን ስለ ቀይ ሽብር በተደጋጋሚ ከማውሳትና የድርጊቱን ተዋናዮች ከማውገዝና ከመኮነን በዘለለ፣ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይደገሙ በተለያዩ ጎራዎች ተሰልፈው ደም የተቃቡና ቂም የተያያዙ ወገኖችን በማገናኘት ከቁርሾ ከመራራቅ ተቆጥበው የየግላቸውና የጋራ ስህተቶቻቸውን የሚገመግሙባቸውን መድረኮች በማመቻቸት፣ ለጋራ ጥቅምና አብሮነት በትብብር የሚሠሩበትን ሁኔታ ማገዝና ማበረታታት አስፈላጊ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ የተፈጸመውን ሳይረሱ ይቅር መባባል እንዳለባቸውም ዶ/ር ካሳሁን መክረዋል፡፡
የቀይ ሽብር ታሪካዊ ዳራዎች
ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ለቀይ ሽብር የዳረገው አብዮት በ1966 ዓ.ም. ሲከሰት አገሪቱ ለአብዮት ፈጽሞ ዝግጁ እንዳልነበረች አስረድተዋል፡፡ በዓለም ታሪክ እጅግ ጥቂት የሆኑት ማኅበራዊ አብዮቶች የኅብረተሰቡን የፖለቲካ ሥርዓትና ማኅበራዊ መዋቅር ሙሉ በሙሉ የሚቀይሩ፣ ኅብረተሰቡን የሚመራውን ገዥ ርዕዮተ ዓለም ቀይረው በሌላ የሚተኩና በኅብረተሰቡ በኩል ትልቅ ምስቅልቅል የሚያመጡ ክስተቶች በመሆናቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከእነዚህ ጥቂት ማኅበራዊ አብዮቶች መካከል አንዱን በ1966 ዓ.ም. ማስተናገዷንም ገልጸዋል፡፡
ከ1933 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. ባለው ጊዜ አገሪቱ በግንባታና በለውጥ ላይ የነበረች ብትሆንም፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የራሱ ለውጥ የፈጠራቸውን የለውጥ ኃይሎች ሊቆጣጠራቸውና ሊቀድማቸው እንዳልቻለ ፕሮፌሰር ሽፈራው አስታውሰዋል፡፡ ከአራት እስከ አምስት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት በ1950ዎቹ ሲመዘገብ በዓለም ባንክ ጭምር የተከበረ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እንደነበር የገለጹት ፕሮፌሰር ሽፈራው፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱ የሕዝብ ብዛት እንዲጨምር ገዳይ በሽታዎችን በመቆጣጠር አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ የሕዝቡ ብዛት ግን ቤት አልበኝነትንና ፍፁም ድህነትን በማምጣት የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ጥያቄ እንዲያነሳ መጋበዙን ያስረዳሉ፡፡ “መንግሥት መዋቅር ቢለውጥም ንጉሣዊ አገዛዙ ስላልተለወጠ በአዲሱ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው ኃይል ከንጉሣዊ አገዛዙ ጋር ሊሄድ አልቻለም፡፡ የመንግሥት መዋቅሩ ለውጥ በጣም ፈጣን ሲሆን፣ ንጉሣዊ አገዛዙ የሚያደርገው ለውጥ እጅግ ዘገምተኛ ነበር፡፡ አዲሱ ኃይል በጣም ትዕግሥት ያጣ፣ መሄድ መወርወር አለብን የሚል ነበር፡፡ አባቶቹ የነበሩትን ጊዜ ጨርሶ አያመዛዝንም ነበር፤›› ብለዋል፡፡
አዲስ የፖለቲካ ባሕል
የተማሪዎች ንቅናቄ ብዙ በጎ ጎኖች ቢኖሩትም በርካታ አሉታዊ አሻራዎች እንዳሉት ያስታወሱት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ አብዮቱ በውስጡ ቀይ ሽብርን የፈጠሩ መሠረታዊ ምክንያቶች እንደነበሩትም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የመጀመሪያው ምክንያት ቀኖናዊ የሆነ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም አስተሳሰብ ማስረፅ ነው፡፡ ሁለተኛው የአመፅ ባሕል ፈጥሯል፡፡ ሦስተኛው የተፈጠረው ነገር ተፈጥሮአዊ ክፍፍል ነው፤›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ሌላው የቀይ ሽብር ምንጭ የአመፅ ባሕል እንደሆነ ፕሮፌሰር ባህሩ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የአመፅ ባሕል የተለያዩ ዘርፎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የሃይማኖት ዘርፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ወታደራዊ ዘርፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው ጦርነት የተደረገው እርስ በርስ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ገለን መሸለል ባሕላችን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሦስተኛው የቀይ ሽብር ምንጭ የ1953 ዓ.ም. የእነ ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ሁለት አንድምታዎች አሉት፡፡ ሙከራው በመክሸፉ ከመንግሥት ይልቅ የተማሩት ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ ወታደሮቹ በተለይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፍ ማለት ሞት መሆኑን ተምረውበታል፡፡ ሌላው ሙከራው ከከሸፈ በኋላ ተሳትፎ አድርገዋል በተባሉት ሰዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ ከቀይ ሽብር ጋር የተገናኘ ነበር፤›› በማለት አነፃፅረዋል፡፡
የቀይ ሽብር ውጤት ብሩህ አዕምሮ ያላቸውን ወጣቶች በመፍጀት፣ አምባገነናዊ ሥርዓት በመፍጠርና ኅብረ ብሔራዊ ተቃውሞን በማክሰም እንደሚገለጽ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ባህሩ፣ ቀይ ሽብር እንዳይደገም ከዝክር ባሻገር አዲስ ፖለቲካዊ ባሕል መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ጃፓንና ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፅልመት መጥተው ብሩህ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ገንብተዋል፡፡ ያ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በጀርመን በየጊዜው የሒትለር ሥራ በኤግዚቢሽን ይታያል፡፡ አዲሱ ትውልድ ያን እያየ ወላጆቹን ‹ይኼ ሁሉ ሲሆን ምን ታደርጉ ነበር?› ብሎ ይጠይቃል፡፡ በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ይህን ለማምጣት አዲሱ ትውልድ ከሥር ከሥርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ ቀይ ሽብርን እንዲያውቀው ማድረግና ዲሞክራሲን በተላበሰ መንገድ እንዲያድጉ መደረግ አለበት፤›› ብለዋል፡፡
በውይይቱ ጥናት አቅራቢዎቹም ሆኑ ተሳታፊዎቹ አገሪቱ ወደፊት ልትሄድበት የሚገባው ጎዳና ሙሉ በሙሉ ከቀይ ሽብር የፀዳ እንዲሆን የተስማሙ ቢሆንም፣ በቀይ ሽብር ተፅዕኖ ስሜታዊነት ተስተውሎባቸዋል፡፡ ቢያንስ ግን በአንድ መድረክ መነጋገርና ሐሳብ መለዋወጥ (በአብዛኛው ራስን በመከላከል መንፈስ ቢሆንም) አንድ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate