Pages

Jan 22, 2013

በምዕራብ አባያ ገበሬዎች ላይ ጥቃት ተፈጸመ


ፍኖተ ነፃነት
በደቡብ ክልል ጋሞ ጐፋ ዞን በሚገኘው ምዕራብ አባያ ወረዳ ልዩ ስሙ አልገሌ
ቀበሌ ሺለሸኮ አካባቢ ሰፊ የፍርፍሬ እርሻ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን መደረጉ
ተጠቆመ፡፡ በተለይ የአቶ መሐመድ መጠሎ እና የአቶ ተቀባ መጠሎ የሙዝ እርሻ
አላግባብ መመንጠሩ ተገልፆል፡፡
ድርጊቱ የተፈፀመው ሐሙስ ጥር 3 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ 4 ሰዓት አካባቢ የወረዳው መስተዳደር ተወካይ አቶ
ከፍያለው ቦጋለ እና የወረዳው ሲብልሰርቪስ ኃላፊ አቶ አርባ ጐጃ በተገኙበት በመሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ማድረጉን
ምንጮቻችን ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡ በዕለቱ የማሳው ባለቤቶች በሥፍራው የነበሩ ሲሆን የአካባቢው ሞሌ የተባለ
አጐራባች ቀበሌ ነዋሪዎች በድርጊቱ ላይ የተሳተፉም እንዳሉ ተገልፆል፡፡
የጉዳዩን አሳሳቢነት አስመልክተው ጉዳት የደረሰባቸው የአካባቢው ገበሬዎች ለዞኑ መስተዳደር አካል ለሆኑት ለአቶ
እሸቱ ቅሬታቸውን በአካል ሄደው ማምልከታቸው ታውቋል፡፡ የመስተዳደሩ አካልም የወረዳውን ዋና አስተዳዳሪ አቶ
አዲሱ አርባን ቅሬታ አቅራቢዎች በተገኙበት ስለጉዳዩ ሲጠይቋቸው “የፍራፍሬ ማሣው የተጨፈጨፈባቸው አላግባብ
ነው፤ ድርጊቱን የፈፀሙት ላይም እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ተጠቁሟል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው
ገበሬዎች ግን “እንኳን የፍራፍሬ ማሳችሁ ቀርቶ ገና ራሳችሁንም እናጠፋችኋለን የሚል ገና ማስፈራሪያ የወረዳው
አስተዳዳሪዎች ባሉበት ተሰጥቶናል፤ ስለዚህ አሁንም ጉዳዩ ግልፅ ስላልሆነ ስጋት አለን” ብለዋል፡፡
ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣም ስለጉዳዩ ለማጣራት የወረዳው ዋና አስተዳደር የሆኑትን አቶ አዲሱ አርባ ጋር ተደጋጋሚ ጥረት
ብናደርግም አልተሳካም፡፡

እንደ መከላከያ ሁሉ ኢትዮ ቴሌኮምም


ዘረኛው የወያኔ መንግስት ዘረኝነቱን በሚያጠናክርለት ና የራሱን ጀሌዎች ብቻ የስርአቱ ተጠቃሚ በማድረግ የአንድ ብሄር የበላይነቱን ይዞ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን የሚያሳይ ሌላ መረጃ ሰሙኑን የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የጥናት ክፍል ይፋ አድርጓል ። ቀደም ሲልም  በየካቲት 2002 በመከላከያ ሰራዊት በአዛዥነት ቦታዎች ያለውን የብሄር ተዋጽኦ ማጋለጣችን ይታወሳል።

ወያኔ በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ለረጅም ግዜ በየዘርፉ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች አባሮና አፈናቅሎ ታማኝ ያላቸውን የህወሃት ታጋዮችን “ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ያስመረታቸውን ምርቶች እና ከመቀሌ ኢንስቲዩት ቴክኖሎጅ ” በአብዛኛው ከአንድ ዘር በማምጣት መድቦ ኮርፕሬሽኑ የጀሮ መጥቢያ የስላላ ተቋምና የፓርቲው መሳሪያ በማድረግ የዜጎችን ሉዓላዊነት በመዳፈር ሀገራችንን በዚህ ዘመን የመረጃ ርሃብተኛ አድርጓታል።
በዚሁ ጥናት ሌላው አሳዛኙ ጉዳይ ከእያንዳንዱ 3.3 ሚሊዮን የኦሮሞ ተወላጅ ዉስጥ በኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ አመራር ቦታ የተሰጠዉ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ብቻ ሲሆን ትግራይን ስንመለከት ግን ከእያንዳንዱ 194 ሺ የትግራይ ተወላጅ ዉስጥ ቢያንስ አንድ ሰዉ በኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ አመራር ቦታ ላይ ተቀምጧል። ይህ የስራ አመዳደብ የትምህርት ችሎታንና ልምድን ተከትሎ የተሰራ ነዉ ቢባል እንኳን የላቀ የትምህርት ደረጃና የስራ ልምድ ያላቸዉ የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር ተመሳሳይ የትምህርት ደረጃና የስራ ልምድ ካላቸዉ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር በአስር እጥፍ መብለጡ ምንም ጥርጥር የለዉም።
ሌላው መራራ ሀቅ 66.2 በመቶ የሚሆነዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚያቅፉት ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል N1 በሚባለዉ ከፍተኛ የአመራር አርከን ዉስጥ በአመራር ቦታ የተቀመጡ ዜጎች ብዛት አራት ብቻ ነዉ (ሁለት ከኦሮሚያ ሁለት ከአማራ)። ከጠቅላላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዉስጥ 5.4 በመቶዉ ብቻ ከሚኖርበት ከትግራይ ክልል ግን ስምንት ሰዎች ኤን አንድ በሚባለዉ ከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ ተቀምጠዋል።
ሌላው ወያኔዎች ለወደፊቱ የአለም ቴክኖሎጂ ሲያድግ ህወሃቶች የተቀረውን የሀገራችንን ህዝብ አድልሆ በማድረግ አንድን ዘር በኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ የማሳደግ ስውር አጀንዳም ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጥናቶች በተደጋጋሚ እያሳዩን ነው። ስለዚህ ይህንን የማስቆምና ዜጎች በሀገራቸው እንደዜጋ የሁሉም መብቶች እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ አስፈላጊውን መሰዋእትነት በመክፈል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁላችንም እንገባ ዘንድ የግድ ነው።
ወያኔ/ህወሃት ለደረሰብኝ በደል ካሣ አሁን ተራዬን ሌሎችን የመበደል መብቴ ነው ብሎ የሚያደርገውን የአንድ ዘር የበላይነትንና ጨቋኝነቱን በድርጊቱ እንዲህ እየነገረን፤ በግልባጩ ግን ነጋ ጠባ የሚነገረን እኩል መሆናችንን ነው። ይህ ግን ሀሰት መሆኑን ጥናቱ አረጋግጦልናል። በቀድሞ ሥርዓት የተበደለ በአዲሱ ሥርዓት በዳይ ሆኖ ቢገኝ ጥፋቱን አቅልሎ ማየት፤ የሥርዓት ለውጥ የበዳይና ተበዳይ ቦታ መለዋወጥ አድርጎ ከመገንዘብ የሚመጣ እጅግ አደገኛ የሆነ አመለካከት ነው እና የሀገራችን ህዝብ ይህንን አረመኔ ዘረኛ ስርአት ብሄራዊ አደጋ ውስጥ ሳያስገባን ልንታገለው ጊዜው አሁን ነው።
ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ከእነዚህና ሌሎች እውነታዎች በመነሳት አሁን ግዜው የፍልሚያ ነው የሚለው፤ የቻለ በግንባር ያልቻለ በደጀንነት ይሰለፍ፣ ጠጠር ይወርውር ጠጠር ያቀብል! የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ሀገራችን ኢትዮጵያን ከሀገር በቀሉ ወራሪ ዘረኛ መንግስት የማዳን ጥሪ ጊዜው አሁን ነውና የምንችለውን ሁሉ በማድረግ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ! እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የረጅሙ ጉዞ ምእራፍ አሁን ነው እና የአንድ ዘር የበላይ ዘረኝነት ፓሊሲን እንዋጋ!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

ማፈራረስ ማተራመስ ማሸበር- የወያኔ ታላቁ ራዕይ

ከይኸነው አንተሁነኝ

ጥር 19 2013

“መካብ ሲያቅት ማፍረስ ሥራ ይሆናል” ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም

ወያኔ ላለፉት 21 ዓመታት የሀገራችንን ታሪክ ለማፈራረስና ለመቀየር የቻለውን ሁሉ ሞክሯል። የሕዝባችንን የአልደፈርም ባይነት ወኔ ለመስለብና ለማኮላሸት ያልቆፈረው ጉድጋድ አልነበረም። ሃይማኖታዊ ስርአታችንንና ወጋችንን ለመናድ ብዙ መንገድ በመጓዝ ደክሟል። አብሮ በመቻቻል የመኖር ወጥ ባህላችንን ለመጨፈላለቅና ለማጥፋት ሞክሯል። በኢኮኖሚ የወያኔ ጥገኛ እንድንሆንና የመብት ጥያቄ እንዳናነሳ ፀጥ ብለን እንድንገዛ ለማድረግ ሲጥር ከርሟል። ለወገናችን ጠብ ባላለው ልማት ስም ስንቶችን ከመኖሪያ ቤታቸው ከእርሻ ማሳቸው አፈናቅሏል። አሻፈረኝ ያሉትንም አስሯል ገድሏል። ራሱ የማያከብረውን የይስሙላ ህግም አስከብራለሁ እያለ የስንቶችን መብት ረግጧል። ወያኔ ከሳምንት እስከ ሳምንት ስገቴ ናቸው የሚላቸውንና ያላማሩትን ሁሉ አቅሙ እስከ ቻለ ተጉዞ በስደት ዓለምም ቢሆን ያፈናና የግድያ ሙከራ ከማድረግ ቦዝኖ አያውቅም። በዚህ የክፋት ድርጊቱም ጥቂት የማይባሉ ወገኖቻችን ላይመለሱ ክቡር ሂዎታቸውን ገብረዋል። ወያኔ ዛሬም ቢሆን በዓለም ዙሪያ እኩይ ስራውን አላቆመም።
በሀረር ከ30 ዓመታት በላይ በባለቤትነት ያስተዳደሯቸው ሱቆች ሊፈርሱ እንደሆነ የታወጀበትና በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤታቸውን በማፍረስ ሽዎችን ለልመናና ለጎዳና ተዳዳሪነት የዳረገው የወያኔ ራዕይ ሳያባራ አሁን ደግሞ ጉዳዩ ወደ ክልል ከተሞች ወርዶ የአላማጣ ነዋሪዎችን እያስለቀሰ ይገኛል። ህጻናት፣ አዛውንትና አቅመ ደካሞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤቶቻቸው እየፈረሱ በመሆናቸው መፍትሄ ለማያመጣ የተቃውሞ ሰልፍ ለመውጣት ተገደዋል።
ወያኔ በህግ ስም ህግን እየረገጠ እንደገና ራሱ ቀድሞ እየጮኸ፤ በልማት ስም ያሻውን እየገፋ የውድቀት ራዒዉን እያሰፋ የፈለገውን እያስፋፋ ሀገር እያጠፋ ቀጥሏል። መብታችን ይከበር ለሚለው ጥያቄ መብት እንደገፈፈ እንዳሰረና እንደገረፈ አለ። በማይመለከተው ይመለከተኛል በማያገባውም ያገባኛል እንዳለና ሕዝባችንን እንዳመሰ ባጅቷል። ለአንድ ዓመት ሳይቋረጥ ለቀጠለው የሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የመብት ጥያቄ አሉታዊ መልስ ሲሰጥ የከረመው ወያኔ በራሱ መንገድ መሪዎቻቸሁ እነዚህ ናቸው ብሎ አስቀምጧል። ለመብት የሚደረገው እንቅስቃሴ ባለመብረዱም በገርባ ቀበሌ የፈጸመውን ግድያና አረመኔያዊ ጭፍጨርፋ ገና ሳንረሳ አሁን ደግሞ በሀረር ገና ላቅመ አዳም ያልደረሰ ከ10 እስከ 12 ዓመት እድሜ የሚገመት ህጻን ባደባባይ በመግደልና ጥቂት የማይባሉትንም በማቁሰል ማንነቱንና ትክክለኛ ራዕዩን አሳይቶናል። በኦርቶዶክስ እምነት ላይም እየደረሰ ያለው አፈናና እኔ አውቃለሁ ባይነት ቀጥሎ ወያኔ የፈለገውን ፓትሪያርክ በአባ ጳውሎስ ቦታ ለማስቀመጥ የሚያደረገው ሩጫ የተበላ እቁብ ያህል እርግጠኛ ወደ መሆን ተቃርቧል።
ሰላሳ ሶስት የምርጫ ፓርቲዎችን ያካተተው ሰብስብ የወያኔ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ህጉ ይገዛ፣ ከምርጫ በፊት የመሮጫ ሜዳው ይስተካከል፣ ጥያቄዎች አሉንና እንወያይ በማለታቸው “በባለቤቱ የተማመነ…” እንደሚባለው የወያኔው ምርጫ ቦርድ ሁሉንም ፓርቲዎች ከወያኔ የወረዳና የአካባቢ ምርጫ ውጭ አድርጓል።
የመሰብሰብ፣ የመናገር፣ የመጻፍና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን አስከብሬያለሁ እያለ ለዓለም የሚለፈው ወያኔ አንቱ የተባሉ ጋዜጠኞችን በእስር ከማማቀቅ ቀሪዎችንም ከማሰደድ ከማስገረፍና ከማሰሩም በተጨማሪ እንደ ባለራዕይ ወጣቶች አይነት ደፋር ለሀገር አሳቢ ማህበር ድንገት ብቅ ሲል ደግሞ ምክንያት እየፈጠሩ ከሕዝባቸው ጋር እንዳይገናኙና ዓላማቸውን እንዳያሳውቁ ከማስፈራራትና ጉሸማ አንስቶ ለእንደ አዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም አይነቶች የተፈቀደውን የስብሰባ ቦታ ከመከልከሉም በላይ በራሳቸው ተሯሩጠው ካገኙት የስብሰባ አዳራሽ ድረስ ካድሬዎቹን አስርጎ በማስገባትና የመሰብሰብ መብታቸውን በመጋፋት ዓላማቸውን እንዳያሳውቁና ወደ ሕዝባቸው እንዳይደርሱ ለማድረግ ስራ በዝቶበት ከርሟል።
በጋምቤላና በአፋር በኢንቨስትመንት ስም የአካባቢውን ኗሪ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ለዘመናት ከኖረበትና እጅጉን ካለማው የእርሻ ማሳው በሃይል በማፈናቀል በሰፈራ ስም ወደ ቦዳ መሬቶች የማዛወሩ ስራ አርሶ አደር ወገኖቻችን ላይ የፈጠረው ቀውስ ሳይስተካከል ዛሬ ይኸው ተግባር በሱሪ በከፋ መልኩ ቀጥሏል። በሱሪ የቀጠለው አርሶ አደሮችን የማፈናቀሉ የወያኔ እኩይ ስራ እጅግ ተካሮ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሱሪዎች ያሰቃቂ ግድያ ምክንያት ሆኗል። ምስኪን ሱሪዎች የእርሻ መሬታቸውን ተነጥቀው በሀገራቸው የመኖር መብታቸውን ተገፈው ባንድ ጉድጓድ ሰላሳ ሰባው እንዲህ እንደሰሞኑ እጅግ ሲከፋም እስከ አንድ መቶ ሃምሳ እየተቀበሩ ይገኛሉ። የወያኔ ራዕይም በሀገራችን በዚህ መልኩ ሳይበረዝና ሳይከለስ ተስተካክሎ ቀጥሏል።
በሕዝባችን ላይ እያደረሰ ያለው የሀገር ውስጡ ግፍና መከራ ሳይበርድ በምስራቅ አፍሪካ እንደልቡ የሚወጣውና የሚገባው ወያኔ በቀጠናው ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በስደት ዓለም ሌላ ስደት ለመሆን መከራውን እያየ ይገኛል።
ኢትዮጵያዊያን በጅቡቲ ይታፈናሉ ተላልፈውም ለሀገር ውስጥ እስርና ከዚህም ሲከፋ ለግድያ ይዳረጋሉ። በኬንያ የሚኖሩ ወገኖቻችን ያፈና ስጋት አለብን ሲሉ እየጮሁ ነው። በሱዳን በተለይም በደቡብ ሱዳን በቀድሞው የወያኔ ወታደር ያሁኑ ነጋዴ የይስሙላው ጀነራል ፃድቃን አቀነባባሪነት ወገኖቻችን የመታፈንና ወደ ሀገር አስር ቤት የመመለስ፣ ባሉበት የመገደል ወይም ወደ ሌላ ሶስተኛ ሀገር እንደገና የመከራ ስደት ለመጀመር በጭንቅ ላይ መሆናቸው ይሰማል። በሶማሊያ የወገኖቻችን ኑሮ የጭንቅ ነው። ወያኔ በእርግጥ ሰላም የማሳጣት ስራ በዝቶበት ከርሟል። ባንድ ጊዜ ሁሉም ላይ ለመገኘትና ጥቃት ለመሰንዘር እየሞከረ ይገኛል። ሁሉም ላይ ባንድ ጊዜ ለመገኘት መሞከር ግን አንዱንም ለመከወን አለመቻልን ሊያስከትል እንደሚችል የተረዳ አይመስልም። ኢትዮጵያዊያንን ለማጥመድ እጅግ በጣም ርቆ የብስና ውቅያኖስን አቆራርጦ ሲክለፈለፍ ከአሜሪካ የደህንነት ወጥመድ እንደዶለው የሰሞኑ ውርደቱ፤ አንድ ቀን እጅግ የከፋው የወያኔ እኩይ እንቅስቃሴ ወያኔን ላይመለስ ወደ መቃብር እንደማይከተው ምን ማረጋገጫ አለ… ምንም።

ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ ተቃውሞአቸውን አሰሙ


ጥር ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻ /  
ኢሳት ዜና:- በኢትዮጵያ እና በዛምቢያ መካከል የተካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ተከትሎ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ መንግስት በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የሚወስደውን እርምጃ ተቃውመዋል።
ሙስሊሞቹ መሪዎቻችን ይፈቱ፣ በእምነታችን አንደራደርም፣ የሀይማኖት ነጻነት ይከበር፣ የሚሉ መፈክሮችን በእንግሊዝኛ በመጻፍ ለአለም የቴሌቪዥን ተመልካቾች አሳይተዋል።
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ብሄራዊ ቡድኑን በከፍተኛ ስሜት ከመደገፍ አልፈው በእረፍት ሰአቶቻቸው ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ ተስተውሎአል።

መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ከአገር ውስጥ ባንኮች ሊበደር ነው


ጥር ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻ /  
ኢሳት ዜና:- የአገሪቱን  ኢኮኖሚና የዜጎችን ኑሮ እየተፈታተነ የሚገኘውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር  ከ እንግዲህ ከአገር ውስጥ አንበደርም ሲል የነበረው የ ኢትዮጵያ መንግስት ዘንድሮ ያጋጠመውን የበጀት ጉድለት መሸፈን ባለመቻሉ  ከ አገር ውስጥ ባንኮች ሊበደር እንደሆነ ሪፖርተር ዘገበ።
ለኑሮ ውድነቱ ጣራ መንካት አንዱና ዋነኛው ምክንያት መንግስት ከ አገር ውስጥ መበደሩና ይህንንም ብድር ለማሟላት ብር እንዲታተም ማድረጉ ነው በማለት የቀረበባቸውን ትችት ከብዙ ማንገራገር በሁዋላ የተቀበሉት  ሟቹ ጠ/ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ፤ “ከ እንግዲህ ግን መንግስት ፈጽሞ ከ አገር ውስጥ ባንኮች አይበደርም” ማለታቸው ይታወሳል።
ይሁንና የዘንድሮን 26.8 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ለመሸፈን  መንግስት  ከአገር ውስጥ እንደሚበደር  አስታውቋል።
መንግስት ብድሩን ለማግኘት ሲል እንዲታተም የሚያደርገው ብር እንደማይኖር ቢናገርም፤ባንኮች የማበደር አቅሟቸው እጅግ የተዳከመ በመሆኑ ገንዘብ ወደ ማተሙ ማምራቱ አይቀሬ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
ጋዜጣው የጠቀሳቸው የ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ፦”የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀዛቀዙ እና ከአገር ውስጥ ምንጮች ብድር ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ፣ መንግሥት ብር ማተም ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲሉ “ ያስጠነቅቃሉ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የ2005 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት በጀት 137 ቢሊዮን ብር መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህንን በጀት ለመሸፈን ከታክስና የተለያዩ ገቢዎች 111 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፣ ቀሪው 26 ቢሊዮን ብር ግን በበጀት ጉድለትነት ተይዞ በተለያዩ አማራጮች ለመሸፈን መታቀዱን ያስረዳል፡፡
ከእነዚህም መካከል 7.9 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ከውጭ አገሮች ከሚገኝ የፕሮጀክት ብድር፣ 5 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን በዓለም ባንክ በኩል ለመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ ከሚገኝ ብድር፣ እንዲሁም 169 ሚሊዮን የሚሆነውን ብር በእዳ ስረዛ ከሚገኝ ለመሸፈን መታቀዱን ይተነትናል፡፡
በመሆኑም ከላይ የተዘረዘሩት አማራጮች ከአጠቃላይ የበጀት ጉድለቱ 13 ቢሊዮን ብር ያህሉን የሚሸፍኑ ሲሆን፣ ቀሪውን 13 ቢሊዮን ብር ግን ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መታቀዱን ያብራራል፡፡
መንግሥት ከአገር ውስጥ ምን ያህል ሊበደር እንደሚችል የተጠየቁት  የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር አቶ ሐጂ ኢብሳ ፣ “አሁን ላይ ሆነን መንግሥት ምን ያህል ሊበደር ይችላል የሚለውን መገመት አዳጋች ነው” ብለዋል፡፡
ነገር ግን ከብሔራዊ ባንክ የመበደር ዕቅድ በጭራሽ አለመኖሩን፣ ብድሩን በኢኮኖሚው ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኝ ገንዘብ ለመሸፈን መታቀዱንና እየተረጋጋ የመጣውን የዋጋ ንረት በማይጎዳ ሁኔታ እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡
በኢኮኖሚ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኝ ገንዘብ ማለት ከሌሎች የመንግሥት አበዳሪ ባንኮች እንደ ንግድ ባንክና ልማት ባንክ እንደሆነ  ጋዜጣው ያነጋገራቸው ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ተንታኞች የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከመቀዛቀዝ ባለፈ ችግር ውስጥ ስላለ የባንኮች የማበደር አቅም የሳሳ መሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ብር የማተም ግዳጅ ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲሉ ፍርኃታቸውን ይገልጻሉ፡፡

Jan 21, 2013

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አስደናቂ ውጤት አገኘ

ጥር ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ብሄራዊ ቡድኑ ዛሬ ከአምናው ሻምፒዮን ዛምቢያ ጋር ተጫውቶ አቻ ተለያይቷል። ዋልያዎች ጀግንነታቸውን አስመሰከሩ

በ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ቀትር ላይ ከዓምናው ሻምፒዮን ከዛምቢያ ቡድን ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ 10 ሰው ተጫውቶ 1ለ1 ተለያዬ።

በሺዎች በሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው የእልታ ዜማ ታጅበውና ከላይ እስከ ታች በቢጫ አሸብርቀው ወደሜዳ የገቡት ዋልያዎች ፤በባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዎና በዛምቢያ ላይ በግልፅ የበላይነታቸውን እያሳዩ የመጡት ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ነው።

ጨዋታው ከመጀመሩ ዋልያዎች በማራኪ አጨዋወት አንድ ሁለት በመቀባበል ጫና ፈጥረው ቆዩ።

ከዚያም 10ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰይድ ብቻውን ኳስ ሲገፋ ከነበረው የዛምቢያ ተከላካይ በፍጥነት ኳሷን በማስጣል ወደፊት ሊያመራ ሲል በተከላካዩ ተጠለፈ። ዳኛውም የመጀመሪያውን ቢጫ ለዛምቢያ ተከላካይ አሳዩ፡፡

ሳላዲን እንደገና በ16ኛው ደቂቃ ከአዳነ ግርማ የተሻገረችለትንና ሁለቱን የዛምቢያ ተከላካዩች አልፉ እየነጠረች እግሩ ሥር የገባችለትን ኳስ የበረኛውን መውጣት በማየት ከፍ አድርጐ በረኛውን በመስቀል በአናቱ ላይ ቢያሣልፋትም መሬት ላይ በመንጠር ለጥቂት የአግዳሚውን ብረት ታክካ ወደ ውጪ ወጥታለች። ብዙዎችን ቁጭ ብድግ ያደረገች የመጀመሪያዋ ሙከራ ነበረች፡፡

ብዙም ሳይቆይ ዋልያዎች አንዱ ሁለት እየተቀባበሉ ከሁዋላ እየገፉ ያመጧትን ኳስ አዳነ ግርማ በፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ላይ ራሱን ነፃ አድርጎ ለቆመው ሳልሀዲን ሰይድ አቀበለው። ሳልሀዲን ኳሷን የሚመታ በመምሰል አጠገቡ የነበረውን የዛምቢያ ተከላካይ አታሎ ወደ ጎል ሊያመራ ሲል በዘምቢያ ተከላካይ ጥፋት ስለተፈፀመበት ዋልያዎች የፍጹም ቅጣት ምት አገኙ፤ ሆኖም ሳልሀዲን ረጋ ብሎ የመታትን ኳስ የዛምቢያው በረኛ በቀላሉ አድኗታል

ከዕረፍት በፊት በተደጋጋሚ በግራ በኩል በተደጋጋሚ ሲያጠቁ የታዩት ዛምቢያዎች አልፎ አልፎ ወደ ጐል በመድረስ ጫና መፍጠራቸው አልቀረም፡፡

በዚህ ሁኔታ 26ኛው ደቂቃ ላይ የዛምቢያው አማካይ በመሀከል ሰንጥቆ ያሣለፋትን ኳስ ለማግኘት፤ የዛምቢያው አጥቂና የኢትዮጵያው ጐል ጠባቂ ጀማል ጣሰው ወደ ኳስ ሲሮጡ ፤ጀማል ከኳስ ውጪ በዛምቢያው አጥቂ ላይ አደገኛ ጨዋታ በመጫወቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

ከ26ኛው ደቂቃ ጀምሮ ሙሉ 90ደቂቃው በ10 ሰው ለመጫወት የተገደደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጀማልን መውጣት ተከትሎ የተፈጠረበት ጫና፤ የጨዋታ የበላይነቱን እንዳሳጣው በግልፅ ታይቷል፡፡

ጀማል መውጣቱን ተከትሎ ብዙም ሣይቆዩ ዛምቢያዎች ጐል አስቆጠሩ፡፡ የመጀመሪያው ግማሽ ጨዋታ በዛምቢያ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ፡፡

እጅግ አስገራሚው ነገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 1-0 እየተመራ ቢሆንም፣ 1 ተጫዎች በቀይ ካርድ ቢወጣበትም፤ ደቡብ አፍሪካ የተገኘው ደጋፊ ስሜቱና ድጋፉ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱ ነው፡፡

በ10 ሰው ለመጫወት የተገደደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዕረፈት በኋላ መጠነኛ የአሰላለፍ ለውጥ በማድረግ ባሳየው ብስለት የተሞላበት ጨዋታ (ከብዙዎች ግምት ውጪ)ኳስ በመቆጣጠርም ሆነ ጥሩ ጨዋታ በማሣየት ከዛምቢያዎች ልቆ ታይቷል፡፡

ዋልያዎች የተፈጠረባቸውን የአንድን ሰው ክፍተት ለመሸፈን ይመስላል አብሮ በመከላከልና አብሮ በማጥቃት የተመሠረተ የካውንተር አታክ አጨዋወት ስልት በመከተልና የተቆጣጠሯትን ኳስ በድንቅ ቅብብል አፍጥኖ በመጫዎት የአምናውን ሻምፒዎና አስጨንቀውት ውለዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ 64ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አዲስ ህንፃ በመሀል ሰንጥቆ ለሳልሀዲን ያደረሰለትን ኳስ ፤ሳልሀዲን በቀኝ በኩል ለገባለት ለአደነ ግርማ በጥሩ ሁኔታ አቀበለው፡፡ የጨዋታው ኮከብና እውነተኛ ግርማ ሆኖ ያመሸው አምበሉ አዳነ ግርማም ኳሷን የሚመታ መስሎ- ሊደረብ ተጠግቶ የቀረበውን የዛምቢያ ተከላካይ ካስተኛው በኋላ ፤በረኛው ባጠበበትና ባልጠበቀበት በግራ በኩል አክርሮ መሬት ለመሬት የመታት ኳስ የግራውን ቋሚ በረት በመምታት ከመረቡ ተወህዳለች። አዳነ ግርማ ከጓደኞቹ ጋር ደስታቸውን ሊገልፁ ወደ ደጋፊዎቻቸው ሲያመሩ፤ የወደቁት የዛምቢያ ተከላካይና በረኛው ከመሬት አልተነሱም ነበር፡፡

ስታዲየሙ ዳር እስከ ዳር በጭፈራ አስተጋባ። ውሃ ሰማያዊ ሱፍ ከነጭ ሸሚዝና ከቀይ ክራቫት ጋር የለበሱት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በደስታ በመስፈንጠር ሽቅብ ዘለሉ፡፡ የራሳችንን አርሰን ቬንገርና አሌክስ ፈርጉሰን በታላቅ ውድድር ላይ ሲዘሉ አየን። በዚሁ 1ለ1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቀቀ፡፡

ከሌሎች አገሮች ደጋፊዎች በተለየ መልኩ ቡድናቸውን ለመደገፈ በስታዲየም ዙሪያ የተገኙት ውቦቹ ኢትዮጵያውያን፤ ለቡድናቸው ካበረከቱት ታላቅ አስተዋፅኦ በተጨማሪ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን አድምቀውትና ውበት አለብሰውት ታይተዋል፡፡

የ«ሪፖርተር» አዘጋጅ አማረ አረጋዊ ማላገጥህን አቁም! – (ከኢየሩሳሌም አርአያ)

(ከኢየሩሳሌም አርአያ)

አማረ አረጋዊን የማውቀው ጋዜጣውን
ሲጀምር ነው፤ አብሬው ለሶስት አመት
ሰርቻለው። …አማረ የግል ጥቅሙ
እስካልተነካ ድረስ በአገርና ሕዝብ ላይ የፈለገ
ነገር ቢፈፀም ደንታ አይሰጠውም። <ፍትሕ>
እና <ፍኖተ ነፃነት> ጋዜጦች ከህትመት ውጭ
ሲደረጉ « የፕሬስ ነፃነት ይከበር» ብሎ አንድ
መስመር በርዕሰ አንቀፅ አልፃፈም፤ እንዲያውም
የ<ፍኖተ ነፃነት> አዘጋጆች ስለጉዳዩ አማረን
ሲያናግሩት በረከትና ሽመልስ ከሚሰጡት
መልስ ጋር የሚመሳሰል ምላሽ በማመናጨቅ
ጭምር ነበር የሰጠው። በአንፃሩ የእርሱ ጋዜጣ
ገፁ ሲቀነስ፥ ያዙኝ-ልቀቁኝ እያለ ስለ ፕሬስ ነፃነት ይደሰኩራል። የህሊና እስረኛ የሆነው እስክንድር ነጋን እስር ለፕሬስ
ነፃነት የሚከፈል ዋጋ መሆኑን አማረ ሊናገር አይፈቅድም። ለነገሩ አማረ – ለእስክንድር ያለውን አመለካከት በጣም
አውቃለሁ!! ነሃሴ 13 1997ዓ.ም ቦሌ ከአማረ ጋ ተገናኝተን ያለኝን (ስለ እስክንድርና ሲሳይ ያለውን ጥላቻ)
እራሱም የሚዘነጋው አይመስለኝም። ..አሁንማ ቴሌቪዥን ሊጀምር ስለሆነ ከእንግዲህ « በኢትዮጲያ ነፃነት
ተረጋገጠ…» እያለ አማረ እንደሚለፈልፍ አያጠራጥርም። …ሌላው « ፍትህ የለም፤ ሙስና ተንሰራፋ…» እያለ
በሚለቀልቅበት ብዕሩ መልሶ « እነ እከሌ በሽብርተኝነት ተከሰው..» በማለት የ4ኪሎው መንግስት በውሸት
የሚፈበርከውን «ክስ» ተብዬ «ትክክል» አድርጎ ለማቅረብና ለቀድሞ ጓዶቹ «መስዋዕት» ሲሆን በተደጋጋሚ
ይታያል። በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት፡እስርና ግድያ… አይቶ እንዳላየ በመሆን «ተቃዋሚን
ያየህ ወዲህ በለኝ» እያለ በነአንዱዋለም አራጌ፡ በቀለ ገርባና ሌሎች ላይ ለማላገጥ..እግረ መንገዱን ደግሞ ገዢው
ፓርቲ ብቻ አገሪቱን መምራት እንዳለበትና « መንገድም ህይወትም ሕወሓት ብቻ ነው » እያለ ሊሰብክ
ይፍጨረጨራል። በጣም የሚያሳፍረው « ሕዝብ…እንዲህ አለ..» እያለ የሚዘላብደው ነገር ነው። መቼና የት ቦታ ነው
« ሕዝብ ኢህአዴግ ይሻለኛል..» ያለው?.ለሚለው ምንም .አይጠቅስም፤ ..ሌላው ስለሙስሊሙ ሕገ መንግስታዊ
የመብት ጥያቄ ትክክለኛነት ሊዘግብ ቀርቶ..ከዚህ በተቃራኒ « በሽብርተኝነት የተጠረጠሩ…» ወዘተ.እያለ የአለቆቹን
የውሸት ድርሰት ተቀብሎ ሌሎችን ሊያደናግር ይቃጣዋል፤ በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ በየቀኑ ስለሚፈፀመው ስቃይና
የመብት ረገጣ ደንታ ስለማይሰጠው – ተፅፎ ስለሚሰጠው የሽብርተኝነት ድርሰት ያላዝናል። በዚህ ሳያበቃ «
በድሬዳዋ በተናሳ ግጭት አንድ ታዳጊ ከመሞቱ በቀር የከፋ ጉዳት አልደረሰም» ሲል ያለሃፍረት በህፃን ልጅ ደም
ያላግጣል። ስንት ሰው መሞት ነበረበት?..
አማረ፥ ወገናዊነትህንና አቋምህን ለጊዜው ልተውና አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅህ፤ ሁለት ልጆች እንዳሉህ አውቃለው፤
እስቲ አንዱ ልጅህን በድሬዳዋ በተገደለው ልጅ ቦታ አድርገህ ውሰደው፤ የተገደለው ያነተ ልጅ ቢሆንና እንዲህ ያለ
ዘገባ ቢቀርብ ምን ይሰማሃል?…ከሶስት አመት በፊት ልጅህን ከትምህርት ቤት ልትወስድ ቆመህ ተደበደብክ፤ አንተ
በደረሰብህ አደጋ ልጅህ የሚሰማው ስሜት ምን አንደሆነ ግልፅ ነው፤ ያንተ ልጅ የተሰማው ስሜት አይነት ፥ እስክንድር
ከት/ቤት ሲያመጣው በነበረው ልጁ ላይ የፈጠረው መሪር የሃዘን የተለየ አይደለም!! ነገር ግን የአንተ «ሕሊና» ይህንን

ማየት አይፈልግም! ማመዛዘን አልፈጠረበትም!!…ፖሊስ ከፎቅ ላይ ወርውሮ የገደለውን ወጣት « በመለስ ሞት አዝኖ
ራሱን አጠፋ» ብለህ የድራማው አካል ሆነህ ስትተውን፤ በአንፃሩ ስለ የኔሰው ገብሬ አንድ መስመር ትንፍሽ
አላልክም።..አማረ ያንተን ማንነት ዲሲ የሚገኘው ወንድምህ ( ድሙ) ጭምር በግልፅ የሚመሰክረው ነው። ዛሬ
ጀመርኩ እንጂ አልጨረስኩም። ብዙ ስላንተ የምላቸው አሉኝ። በቀጣይ እመለስባቸዋለሁ።..

የአገር ፍቅር ከአቃጠለው

                                                          የአገር ፍቅርስ ማለት

                                                       እግራቸን ባህር ማዶ ረግጦ
                                                       አካላቸን ሰው አገር ተቀምጦ
                                             የአገር ቤት ዜና ካላየን ዜና ያየን ለማይመስለን
                                            እማማ ጦቢያን ሲያስነጥሳት እኛን ለሚርበን
                                            ሄደን እንኳን ላንሄድ መመለሻም ለሌለን
                                            ናፍቆት እንደ ልጅ አዝለን ህረፍት ለማያሻን
                                            ለኛ ምስኪን ስደተኞች ኑሮና ዘመን ለገፋችን
                                                              አዎ አዎ አዎ
                                            የአገር ፍቅር ማለት ለኛ ብቻ ነው የሚገባን
                                                                Yared Elias nome telemark

የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን 70 በመቶው የአመራር ቦታ በህወሀት አባለት የተያዘ ነው ተባለ


ጥር ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ግንቦት7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለኢሳት በላከው ሁለተኛ ጥናቱ ላይ እንዳመለከተው በ11 መምሪያዎች የተዋቀረው በስሩ አስራ ሦስት ግዙፍ እንዱስትሪዎቸን የሚያስተዳደርው የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን አስራ አንድ ትላልቅ መምሪያዎችና አስራ ሦስት ግዙፍ እንዱሰትሪዎች በዋና ሀላፊነት፤ በዳይሬክተርነትና በምክትል ዳይረክትርነት የሚመሩ በ29 የከፍተኛ አመራር አባላት ነው።
ከእነዚህ 29 ከፍተኛ አመራር አባላት ዉስጥ 69 በመቶዉ ወይም ሃያዉ የህወሀት አባላት የሆኑ ወታደራዊ መኮንኖች ናቸዉ።በዚህ ከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ያላቸዉ ቦታ 31 በመቶ ወይም ከእያንዳንዳቸዉ በቅደም ተከተል ሦስትና ስድስት ሰዎች ብቻ ሲሆን ከተቀሩት አምስት ክልሎች በዚህ ከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ የተመደበ አንድም  ሰዉ የለም ፣ እንደጥናቱ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ እንዱስትሪ ለመገንባት በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ ከፍተኛዉን ሚና ይጫወታል የሚባለዉ የብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን በሲቪልና ወታራዊ መምሪያዎች ተከፋፍሎ የተዳራጀ ሲሆን በስሩ አስራ ሦስት ግዙፍ እንዱስትሪዎች እንደሚገኙ የጠቀሰው ግንቦት7፣ ከአስራ ሦስቱ እንዱስትሪዎች ዘጠኙን የሚያስተዳድሩት የህወሀት አባላት ናቸዉ። በኮርፖሬሺኑ ዉስጥ ከፍተኛ ስልጣን ከተሰጣቸዉ የህወሀት አባላት መካከል ብረጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘዉ  የብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፖሬሺን ዋና ዳይሬክተር ፤ ኮ/ል ተከስተ ኃ/ማሪያም  በምክትል ዋና ዳይረክተር ማዕረግ የኮርፖሬት ፕሮዳክሺን ግንባታ ሀላፊ ፤ ኮ/ል ፀጋሉ ኪሮስ በምክትል ዋና ዳይሬክተር ማዕረግ የኮርፖሬት ወታደራዊ ምርቶች ሀላፊ ፤ ኮ/ል ሙሉ ወ/ሰንበት በምክትል ዋና ዳይረክተር ማዕረግ የኮርፖሬት ፕሮጀክቶች አስተደዳደር ሀላፊ፤ሻምበል ካህሳይ ክሽን የምርመራና ልማት ዳይረክተርና  ሻምበል ገ/ስላሴ ገ/ጊዮርጊስ የአቅም ግንባታና ስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር ይገኙበታል።
ከትግራይ ዉጭ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔሰቦች በብረታ ብረት እንጂኔሪንግ ኮርፓሬሺን እንዱስትሪዎች ዉስጥ ከፍተኛ የሀላፊነት ደረጃ ባለዉ የአመራር ቦታ ላይ የመቀመጥ ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያዉያን ቁጥር አራት ብቻ ናቸው። ኬሚካልና ሴንተቲክ እንዱስትሪ ሃለፊ መ/አ ሰለሞን ዘውዴ፣ አዳማ ጋርመንት እንዱስትሪ ሃለፊ ኮ/ል ፍሰሀ ግደይ፣ ሜታልስ እንዱስትሪ ሃለፊ ሻለቃ መኮንን በላይ፣ ፓወር እንዱስትሪ ሃለፊ፣ ሻምበል አሰፋ የሀንስ፣ ሆሚቹ ኢሚዩኔሽን ኢንጂነሪንግ ሃለፊ ኮ/ል ሀድጉ በላይ፣ ህብረት ማሽን ቱል ኢንጂነሪንግ ሃለፊ፣ ሻምበል ተሰማ ግደይ፣ ቢሾፍቱ አቶሞቲቭ ሎኮሞቲቭ ሀላፊ፣ ኮ/ል ገብረመድህን ገ ስላሴ ፣ የደጀን አቪየሽን እንዱስትሪ ሀላፊ ሳለቃ ኢሉ ጸጋየ እንዲሁም የጋፋት አርማመንት እንዱስትሪ ሀላፊ ሻለቃ ግሩም ገብረመድህን የህወሀት አባላት ትጋረይ ተወላጆች መሆናቸው በጥናቱ ተመልክቷል። የኢትዮ ፕላስቲክ እንዱስትሪ ሃለፊ አቶ ጋሻው እምሩ፣ እርሻ መሳሪያዎች እንዱስትሪ ሃለፊ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ እና የሀይቴክ እንዱሰትሪ ሀላፊ ኮ/ል ጸጋየ አንሙት የአማራ ተወላጆች ሲሆኑ፣ ከኦሮሞ ደግሞ የፋብሪኬንና ስትራክቸራል እንዱስተሪ ሀላፊው ኮ/ል ብቂላ ብቻ ተጠቅሰዋል።
ይህ ጥናት የተጠናዉ ከ2004 እስከ 2005 ዓም ባለዉ የአንድ አመት ግዜ ዉስጥ መሆኑን ተጠቅሷል። ግንቦት7 በቅርቡ በኢትዮቴልኮም ውስጥ ያለውን የብሄር ተዋጽኦ ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሰዎቹ የሚሾሙት በዘራቸው ሳይሆን በችሎታቸው ነው በማለት ይከራከራል። መንግስት 7ኛውን የብሄር ብሄራሰቦች ቀን 200 ሚሊዮን ብር በማውጣት በባህርዳር ማክበሩ ይታወሳል።

በቦረና ዞን ህዝቡ ለሚሊሻ ማደራጃ ገንዘብ እንዲያወጣ እየተገደደ ነው


ጥር ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቦረና ዞን የኢሳት ወኪል እንደዘገበው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መንግስት የአካባቢ ሚሊሻ ለማቋቋም በሚል ምክንያት እያንዳንዱ ዞኑ ነዋሪ 70 ብር በነፍስ ወከፍ እንዲከፍል አዟል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ” እኛን መልሶ ለሚበድለን ሚሊሺያ እንዴት ገንዘብ እናዋጣለን” በሚል ተቃውሞውን በማሰማቱ እስካሁን ድረስ፣ በቂ መዋጮ ሊዋጣ እንዳልቻለ ታውቋል።
መንግስት በዞኑ እየተባባሰ የመጣውን ከብሄር ጋር በተያያዘ የሚነሳውን  ግጭት ለማስቆም ባለመቻሉ በሶማሊ ክልል እንደተደረገው የአካባቢ ሚሊሺያ ለማቋቋም ማቀዱ ታውቋል።
ነዋሪዎች ገንዘብ እንዲያዋጡ የተገደዱት ለሚሊሺያዎቹ ማሰልጠኛ  ነው።
በቦረና ዞን በሶማሊ እና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል በተደጋጋሚ የሚታየው ግጭት በእየአመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። በአካባቢው ለሚታየው ግጭት መክንያቱ የመንግስት የዘር ፖሊሲ ነው በማለት የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሮ ኢሳት አንድ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል።

መንግስት በአገሪቱ በቂ ምርት አለ ቢልም ህዝቡ ግን ሸቀጦች ከገበያ እየጠፉ ነው ይላል


ጥር ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ ውስጥ የመሰረታዊ እቃዎች እጥረት በተለያዩ አካባቢዎች መታየቱን ተከትሎ 13 በመቶ የደረሰው ዋጋ ግሽበት ተመልሶ ያሻቅባል የሚል ስጋት ሰፍኗል። በተለይም በአገሪቱ የስንዴ፣ የዘይት እና ስኳር  እጥረት በስፋት መታየቱ፣ ህዝቡን ስጋት ላይ እንዲወድቅ አድርገውታል።
ዳቦ ቤቶች በቂ የሆነ ስንዴ ለማግኘት ባለመቻላቸው በርካታ ዳቦ ቤቶች ዳቦ ማምረት ሊያቆሙ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል። መንግስት ከዚህ በፊት ባልታየ መንገድ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ መግለጫውን የተከታተለው ዘጋቢያችን እንዳለው፣ መንግስት በአገሪቱ በቂ የሆነ የስንዴ ክምችት መኖሩን በመግለጽ ወሬውን የሚያስወሩት አንዳንድ ዋጋ ለመጨመር የሚአስቡ ነጋዴዎች ናቸው። ይሁን እንጅ ነጋዴዎች በአገሪቱ የሚታየው የእቃዎች አቅርቦት እጥረት በጊዜ ሂደት ገሀድ ይወጣል በማለት እንደሚገልጹ ዘገባው ያመለክታል።
መንግስት በእህል ምርቶች በኩል የሚታየውን እጥረት ለመከላከል ከውጭ አገር ስንዴ ማስገባቱን፣ በቅርቡም ወደ አገር ቤት የሚገባ ስንዴ መኖሩን ገልጿል። ስኳርና ዘይትም እንዲሁ በበቂ ሁኔታ በአገር ውስጥ እንዳለ አስታውቋል።
መንግስት የነጋዴዎችን ሚና በመውሰድ  ስኳርና ዘይት በየቀበሌው እንደሚያከፋፍል ይታወቃል።
በህብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረው ስጋት የምግብ እና የምግብ ነክ አቅርቦቶችን ወድሞ ወደ ነበሩበት ቦታ ይመልሳቸዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል። ብሄራዊ ስታትስቲክ መስሪያ ቤታ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው ሪፖርት የምግብ ሸቀጦች ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ማሳየታቸውን ገልጾ ነበር። ይሁን እንጅ ምግብ ነክ ባልሆኑ ሌሎች ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።

መንግስት እግር ኳሱን ፖለቲካዊ መልክ ለማስያዝ ያሰበውን እቅድ እንዲያቆም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጠየቁ

 ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከ31 ዓመት በሁዋላ የተገኘውን የስፖርት ውጤት በ አገር ቤት ውስጥ ለፖለቲካ ሲጠቀምበት የነበረው ገዥው ፓርቲ ፤በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው 29ኛው የ አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ተመሣሳይ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ ለማድረግ ማቀዱ ኢትዮጵያኑን አስቆጥቷል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አስተባባሪዎች ፤እንደሚባለው መንግስት ፦<<ባለ ራዕዩ መሪ >>የሚል ጽሁፍ የተፃፈበትንና የአቶ መለስ ፎቶ ያለበትን ቲ-ሸርቲ ተጫዋቾቹም ሆነ ደጋፊዎቹ እንዲለብሱ ካደረገ፤ <<ባለ ራዕዩ>.የሚል ጽሁፍ ያለበትን የአበበ ገላው ፎቶ የታተመበትን ፎቶ እንደሚለብሱ ለ ኢሳት ገልጸዋል።

“ኳሱ ከፖለቲካ ውጪ በሰላም እንዲካሄድ እንፈልጋለን፤ ተጫዋቾቹም ምንም ዐይነት ጫና እንዳያድርባቸው እንሻለን።መንግስት ከጀመረው ፖለቲካዊ ጨዋታ ካልታቀበ ግን የአበበ ገላውን ቲ-ሸርት ለብሰን ባለ ራዕዩ ማን እንደሆነ በከፍተኛ ስሜት ለዓለም ህዝብ እናሳውቃለን>> ብለዋል- በደቡብ አፍሪካ ያሉት ኢትዮጵያውያን።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙትና ለአገራቸው ነፃነት ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን፤በስፍራው ካሉት የ ኢህአዴግ ደጋፊዎች በብዙ እጥፍ እንደሚበልጡ ያስታወሱ ወገኖች፤መንግስት ያሰበውን የፖለቲካ ጨዋታ በመተው ስፖርቱ በሰላም እንዲካሄድና ተጫዋቾቹም ከተጽዕኖ ነፃ ሆነው እንዲጫዎቱ ያደርግ ዘንድ መክረዋል።

በሌላ በኩል አርብ ከቀትር በሁዋላ ጆሀንስበርግ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኢትዮጵያውያኑ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጫዋታዋን የፊታችን ሰኞ ካለፈው ሻምፒዮና ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ታደርጋለች።

ፈረንሳዊው የዛምቢያ አሰልጣኝ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ለቡድናቸው ከባድ እንደሚሆን ፤ኢትዮጵያ ባቋም መለኪያ ጫዋታዎች ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች አብነት በመጥቀስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው የምንገባው ለማሸነፍ ነው፤ እናሸንፋለን ብለን እናምናለን።ባናሸንፍ እንኳ ከእኩል መውጣት አንወርድም>>ብለዋል- ቡድኑ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከማምራቱ በፊት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት መግለጫ።

Jan 20, 2013

Teddy Afro's Concert in South Africa - Sile Fikir (In Pictures)

የ“ዝም በል ዳያስጶራ” – አዋጅ፦ ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ እምነት – ከኤፍሬም እሸቴ

ኤፍሬም እሸቴ) ፦ በዚህ ሰሞን መቼም ከእግር ኳስ ውጪ ማውራት በሕማማት ስለ ቁርጥና ጥብስ እንደማውራት
ሳይቆጠር አይቀርም። እኔም ብሆን ስለ እግር ኳሱ ማውራቱን መች ጠልቼው። በርግጥ ይኼ ሁሉ ወፈ ሰማይ የስፖርት
ተንታኝ በየኤፍ.ኤሙ ሲተችበት በሚውለው የተጫዋቾቻችን ብቃት፣ ጥራት፣ የኳስ ጥበብ፣ የሽልማት ዓይነት፤
የተጋጣሚዎቻችን ሁኔታ፣ የተጫዋቾቻቸው ዝና፣ ማን ከየትና ከየትኛው ክለብ እንደመጣ፣ አሰላለፋቸው እና
ከኢትዮጵያ ጋር ሲገጥሙ ሊኖራቸው ስለሚችለው አያያዝ ለመተንተን ሙያውም መረጃውም የለኝም። (“ችሎታ
የለኝም” አለማለቴ ይሰመርበት። ማን ይሞታል። መቸም “አልችልም” ማለት ጎጂ ባህል ሆኗል።) ቢያንስ የእንጀራ
አገሮቻችን አሜሪካ እና ስዊዲን ስላፈሯቸው እና ለእናት አገራችን ኢትዮጵያ ስላበረከቷቸው ተጫዋቾቻችን መወያየት
ይቻላል።
ኢትዮጵያውያን እንደ ጨው በመላው ዓለም ተበትነዋል። በብዙ ቦታዎች አንድ ትውልድ አልፎ ሁለተኛ ትውልድ ላይ
ደርሷል። በቅርብ ከሚገኙት ኬንያና ሱዳን እስከ አረብ አገሮች፣ ከምዕራብ አውሮፓና ስካንዲኔቪያን አገሮች እስከ
አሜሪካና አውስትራሊያ ድረስ ብዙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። ከእነርሱ መካከል
የአሜሪካ ሜኔሶታው ፉአድ ኢብራሒም እና የስዊዲኑ ዩሱፍ ሳላህ ተገኝተዋል። ፉአድ ኢትዮጵያ ተወልዶ አሜሪካ
ያደገ፤ ዩሱፍ ደግሞ እዛው ስዊዲን ተወልዶ እዛው ያደገ እግር ኳስ ተጫዋች ነው። የብዙ ኢትዮጵያውያን የኋላ ማንነት
ማሳይ ሊሆኑ የሚችሉ ልጆች ናቸው። አድገውና ለቁም ነገር ደርሰው አገራቸውን ለመወከል መብቃታቸው ደስ ይላል።
“አለ ገና፣ ገና፣ አለ ገና” እንላለን።
ጣዕመ-ኢትዮጵያ፣ ባህለ-ኢትዮጵያ በቀዘቀዘባቸው ባህሎች መካከል አድገው በመጨረሻ አገራቸውን ለመወከል
መቻላቸው ትልቅ ነገር ነው። ስለ ፉአድ ያነበብኩት አንድ ጽሑፍ ይህ ወጣት ለአሜሪካ እግር ኳስ ቡድን (ከ17
ዓመት በታች እንዲሁም ከ21 ዓመት ላሉት) ቢጫወትም የማታ ማታ ግን አገሩን ለመወከልና የአገሩን ማሊያ
ለመልበስ መወሰኑን ያትታል። ስዊዲን እነ ኢብራሒሞቪችን (በአባቱ ቦስንያዊ) እና ታዋቂው ሔንሪክ ላርሰንን (አባቱ
ከኬፕቬርዴ ናቸው) የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በማሰለፏ እናውቃታለን። ዩሱፍም ተመሳሳይ በሆነ መልክ ተመሳሳይ
ዕድል ሊያገኝ እንደሚችል እገምታለኹ። ነገር ግን ያንን ትቶ የአገሩን መለያ ለብሷል።
ዳያስጶራው ለረዥም ዓመታት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወደ አገሩ በመላክ አገሩን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሲደግፍ
ቆይቷል። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዳያስጶራው የሚገኘው ገቢ አገሪቱ ከወጪ ንግድ ከምታገኘው በእጅጉ
እንደሚበልጥ የዓለም ባንክ ጥናቶች በተደጋጋሚ አሳይተውናል። ከዚህ የቀጥታ ገንዘብ ርዳታ ባሻገር ትውልደ-
ኢትዮጵያዊው በአገሪቱ አጠቃላይ ሕይወት ላይ በጎ ሱታፌ ማሳየቱ አገሩን ለሚወድ ወገን ሁሉ ትልቅ ተስፋ ነው።
ዩሱፍና ፉአድ ለዚህ መልካም አብነቶች ይሆናሉ።
ዩሱፍና ፉአድ ወደ አገራቸው ሲመለሱ በዚያው መጠን ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ዳያስጶራነት ጎራ እየተቀላቀሉ ነው።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በዋሺንግተን ዲሲ የተደረገ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን/ት ሐኪሞች ማኅበር
ስብሰባ ተገልጿል እንደተባለው በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ዶክተሮች ይልቅ በውጪ የሚገኙት ቁጥር
ይበልጣል። አዝማሚያውን ስንመለከተው ይኸው የዕውቀትና የአዕምሮ ስደት እንደሚቀጥል እርግጥ ነው። ለዚህ
ምክንያቱ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ዋስትና ማጣት እና ፖለቲካዊ ነጻነት አለመኖር ነው። ከኢኮኖሚው በበለጠ ፖለቲካዊ
ጫናው ለብዙው ወገናችን መሰደድ ምክንያት ነው የሚለው የብዙዎች እምነት ነው። በፖለቲካዊ ምክንያቶች
የተሰደዱት ደግሞ በየወጡበት አገር ባላቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን መንግሥት ዘወትር መክሰስ

ቀጥለዋል። በቅርቡም ይቆማል ተብሎ አይጠበቅም። ይህም ፉአድንና ዩሱፍን የመሳሰሉ ትልውደ ኢትዮጵያውያን
በየሙያቸው ትውልድ አገራቸውን እንዳያገለግሉ እንቅፋት ይሆናል። በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት ገፈፋ ሲሻሻል
ዳያስጶራውም ተጠቃሚ ይሆናል። ዳያስጶራውን በጥቅማጥቅም ማባበል መጠነኛ ደጋፊ ያስገኛል፤ የዜጎችን ሰብዓዊ
መብት መጠበቅና ሕገ መንግሥቱን ማክበር ግን ሙሉ ድጋፍ ያስገኛል።
ዳያስጶራው በየሚኖርበት አገር የሚተነፍሰው ፖለቲካዊ፣ ኅሊናዊ፣ አካላዊ እና ሰብዓዊ ነጻነት ይኸው ነጻነት በአገሩ
እንዲኖር በጎ ምኞት ይቀሰቅስበታል። ስለዚህ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በአገሩ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ
ይኮንናል፤ ተጽዕኖ ለመፍጠርም የማይወጣው ዳገት የማይወርደው ቁልቁለት የለም። ይህም የተለያየ አመለካከት
መፍጠሩ አይቀርም። ዳጳስጶራው “አክራሪ ነው” ከሚለው ጀምሮ “የአገሩን ነባራዊ ሁኔታ የማያውቅ” እንዲሁም “50
ዶላር ልኮ አገር ውስጥ ያለው ወጣት እንዲማገድ ይፈልጋል” ወዘተ ተብሎ ይቀርባል።
ሐሳቡ ቀደም ብሎ በመንግሥት ብቻ ተደጋግሞ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ተርታ ዜጎችም
በማኅበራዊ ድረ ገጾቻቸው ሲያስተጋቡት ይስተዋላል። በአጭር አባባል ለማቅረብ “ዳያስጶራ ዝም በል” ወይም “ዝም
እንዲል አድርጉት” የሚል አዋጅ የተነገረ ይመስላል።
በመጀመሪያ ደረጃ አንድን ዜጋ ከአገሩ ርቆ በመኖሩ ስለ አገሩ ያለ ሐሳብ፣ በመንግሥቱ ላይ የሚኖረውን ቅዋሜ እና ለችግሮች የሚኖረውን መፍትሔ ከማቅረብ ሊከለክለው የሚችል ሕግ የለም።ስለ
አገርህ ለመናገር በአገርህ መሬት መኖር አለብህ የሚል “የቀበሌ ትእዛዝ” የመሰለ ሐሳብ ውኃ አያነሣም። ነቢዩ ዳዊት
ስለ ኢየሩሳሌም ሲናገር “ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” እንዳለው “እመሰ ረሳዕኩኪ ኢትዮጵያ ለትርስዐኒ የማንየ፣ ኢትዮጵያ
ሆይ ብረሳኝ ቀኜ ትርሳኝ” የሚሉ ኢትዮጵያውያንን ‘እኮ ምን አግብቷችሁ’ ማለት ከስድብ ይልቅ ያማል።
ዛሬ ባንኖርባት ተወልደንባት አድገንባታል፤ ዘር ማንዘሮቻችን ኖረው አልፈውባታል። ክቡር አጥንታቸው ረግፎባታል።
በየወቅቱ በሚመጣና በሚሄድ ሥልጣን የአንድ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱ አይገመገምም። ኢትዮጵያዊነትን ማንም
ባለሥልጣን አልሰጠንም፣ ማንምም አይነፍገንም። ከደርቡሽና ቱርክ፣ ጣሊያንና ግብጽ፣ ከሌሎችም ድንበር ገፊዎች
ሲታገሉ በወደቁ ወገኖቻችን የቆመ ዜግነት እንጂ እንጀራ ፍለጋ፣ ነጻነት ፍለጋ እንደምንኖርባቸው አገሮች በወረቀት
ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም። ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከወረቀት እና ከፖለቲካ ወገንተኝነት እንዲሁም ከየብሔረሰባዊ
ማንነታችን በላይ ነው።
በሌላም በኩል ካየነው ስለ ሰብዓዊ መብት ለመናገር የግድ የዚያ አገር ዜጋ መሆን፣ በዚያ አገር መኖርም አይጠይቅም።
ሰብዓዊ መብቱ እንዲጠበቅለት የሚፈልግ ማንም ሰው የሌላው ሰው መብት ሲጣስ አይደሰትም። ሌላው ሁሉ ታሪካዊ
ሐተታ እንኳን ቢቀር በቅርቡ ዘመን የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ከኛ ሚሊሻ ጋር አብረው የተዋደቁልንን ኩባውያንን
መስዋዕትነት እንደምናከብረው፣ ዕድሜ ዘመናቸውን በሴቶች (ፊስቱላ) ሕክምና ረገድ አገራችንን የጠቀሙትን
ሐኪሞች እንደምናመሰግነው ሁሉ ለዜጎቻችን ሰብዓዊ መብት የሚከራከሩትንም በዚሁ መነጽር ልንመለከታቸው
ይገባል።
በተጨማሪም የመንግሥትን አሠራር ማሔስ አገርን መተቸት አይደለም። መንግሥት የአገር መሪ እንጂ አገር አይደለም።
ፓርቲና መንግሥትነት ከዘር ጋር በመቆራኘታቸው ፓርቲውን መተቸት የመጣበትን ዘር እንደመውቀስ ተደርጎ
መቆጠሩም ትልቅ ስሕተት ነው። ፓርቲዎች በዓላማቸውና በአሠራራቸው መነቀስና መተቸት ግዴታቸው ስለሆነና
በዘር ላይ የተመሠረተ የፓርቲ አወቃቀር እስካለ ድረስ ከፓርቲው ጀርባ ያለው ዘር ወቀሳው ለርሱ የተወረወረ

አለመሆኑን ለመረዳት ብዙ ጥበብ አያስፈልገውም።
እንኳን የኢትዮጵያ መንግሥት በዲሞክራሲያዊነታቸው ወደር የማይገኝላቸው አገሮች የየጊዜው መንግሥታት ሳይቀሩ
ከትችት አያመልጡም። ትችት መንግሥታቱን ከዓምባገነንነት የሚያተርፋቸው ፍቱን መድኃኒት ነው።
ተቃዋሚዎችን፣ ፕሬሶችን፣ ጥቃቅን ስብስቦችን ሁሉ በመዋጥና በዓይነ ቁራኛ በመመልከት፣ ትችትን ሳይሆን ተቺውን
በማፈን ጥሩ መንግሥት መሆን አይቻልም። “ልማት ላይ ነን አትንኩን” የሚል ፈሊጥ ወንዝ አያሻግርም። ጥያቄው
ግድቡና ሕንጻው ላይ አይደለም። የዜጎችን ሰብዓዊ ሕንጻ እያፈረሱ የድንጋይ ሕንጻ እንሠራለን ማለት አይቻልም።
ከግዑዝ ሕንጻ ሰብዓዊ ዜጋ ይቀድማል፤ከግድብ ግንባታም መብት ይቀድማል።
በውጪ የሚገኘው ዜጋ የአገሩን ሁኔታ በትኩረት ለመከታተል ቴክኖሎጂው ትልቅ ዕድል ይሰጠዋል። አራት ኪሎ
የተፈጠረው አቃቂ፣ አንዱ ክፍለ ሀገር የተሠራው ሌላው ሳይረዳው ሳይሰማ፤ እረኛና አዝማሪ እንኳን ለዘፈኑና
እንጉርጉሮው በራሱ ላይ ግላዊ-ሴንሰርሺፕ በጣለበት ዘመን፣ ከአንድ አፍ በሚወጣ ተመሳሳይ፣ ተደጋጋሚና ቁጥጥር
የተደረገበት ወሬ አገር በሚተዳደርበት ጊዜ፣ አለመስማትን እና አለማወቅን (መንግሥታዊ የመረጃ ግርዶሽን) መታገል
ሲገባ የሰማውንና ያወቀውን “እኮ ማን ስማ አለህ” ማለት አያዋጣም። ይህንን የሚለው አካል ነገሩ እንዳይሰማበት
የፈለገው እንጂ ተጎጂው አለመሆኑም በቅጡ ይታወቃል።
ዳያስጶራውን አምርሮ የመጥላት እና በጅምላ ክፉ ስም የመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራ ፍሬ ማፍራቱን ለማወቅ ተርታ
ግለሰቦች እና ቤተ እምነቶች ሳይቀር ማንጸባረቅ የጀመሩትን ተመሳሳይ አመለካከት መመልከት ይገባል። የግለሰቦቹን
እንኳን ለጊዜው ብናቆየው የአንዳንድ ቤተ እምነት አስተዳደሮችና መሪዎች ከውጪ የሚመጣላቸውን የአማኛቸውን
ሐሳብ፣ ልክ እንደ መንግሥት፣ “አፍራሽ፣ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጥያቄ” አድርገው ሲመለከቱት ማየት እየተለመደ
መጥቷል። ‘አጋጣሚ ነው ወይስ የተላለፈ አዋጅ አለ?’ የሚያሰኝ ነው። የቤተ እምነት መሪዎች ሰማያዊውን መንግሥት
መጠበቅ ትተው ምድራዊውን መንግሥት ለመጠበቅ ደፋ ቀና ሲሉ እነርሱን የሚከተላቸው ምእመን
እንደሚመለከታቸው እንኳን ይዘነጉታል። እነርሱም ከምድራዊው ባለ ጉልበት ጋር ተደርበው “ውጪ ያላችሁት ዝም
በሉልን፣ እንደፈቀድን እንሁን” ሲሉ አዋጃቸውንም በደህና ጊዜ የሚናገሩትንም ሰማያዊ ቃል የሚሰማቸው ጆሮ
ያጣሉ። በርግጠኝነት ግን ማንም ዝም አይልም።
መልካም ዕድል ለብሔራዊ ቡድናችን!!!!
ይቆየን – ያቆየን

The blue sharks of Cape Verde silenced 90,000 South AfricansThe blue sharks of Cape Verde silenced 90,000 South Africans!

The Horn Times News-Jan 19, 2013
by Getahune Bekele, Johannesburg –South Africa
Had Cape Verde star striker Platini, simply composed himself and slot the ball into the empty net on the 5th minute after a defense splitting pass by the 22 year old rising star Ryan Mendez, the island nation would have celebrated a fairy tale victory against the host nation South Africa.
After a spectacular music and dance opening ceremony inside half-empty national stadium, the goalless draw is the first in the history of the tournament as far as opening matches are concerned.
According to CAF media sources, the 29th edition of African cup of nation which kicked off today has become the biggest in history in terms of ticket sell as more than half million tickets were snatched in short space of time.
Back to the match itself, with slight drizzle before and during the game, Cape Verde defenders, the gigantic Neves Nandos and the mercurial Carlitos, cousin of Manchester United star Lewis Nani, were instrumental in the credible and somewhat inspiring draw.
A fuming South African national team, Bafana Bafana coach Gorden Igsund was lost for wards to explain how his water tight defense led by Tottenham Hotspur’s Bongani Kumalo was cut to shreds by the likes of Cape Verde’s J.Tavaires and the young Ryan Mendez.
Now there is fear that South Africa might exit the 29th edition of AFCON 2013 it is hosting, with the dangerous Atlas lions of Morocco and the unpredictable Angola waiting to capitalize on the woefully poor showing of Bafana.
However, for the fans of the black lions of Ethiopia who were at the stadium in large numbers, the performance of Cape Verde must have been encouraging.
Although their team has disadvantaged itself by arriving late, less than 72 hours before the crunch group C  match against defending champions Zambia, with the support of thousands of colorful Ethiopians, snatching a win or a draw is a possibility.
Zambia arrived in Nelspruit on 13 Jan while Nigeria touched down on 17 Jan. The first to show up in the beautiful city of Nelspruit was the stallions of Burkina Faso on 11 Jan 2013.
It remains to be seen how the Ethiopian national team players will overcome the jet lag and adapt to the weather pattern of the high veld before the Monday Afternoon clash.
infohorntimes@gmail.com

His Holiness Abune Merkorios 2013 Epiphany Message [Must See)

ለዘ-ሐበሻ
የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና ብዙዎች ሲጠይቁት የነበረው “ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ይናገሩ” በመጨረሻም ምላሽ አገኘ:: ፓትርያርኩ በወቅታዊ ጉዳዮች ሁሉ ዙሪያ ተናግረዋል:: በቪድዮ ለኢሳት ቲቪ ልከዋል::አሁን የሚጠበቀው ኢሳት የፓትርያርክ መርቆርዮስን ቪድዮ እስከሚለቀው ነው:: ዘ-ሐበሻ ቪድዮው እንደደረሳት ታስተናግዳለች።
                :::

Jan 19, 2013

በውጪ ያለው ሲኖዶስ በአገር ውስጥ የሚደረግን የፓትርያርክ ምርጫ አወገዘ


ኢሳት ዜና:-እርቀ-ሰላሙ ያልተሳካውም ሆነ የፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው የመመለስ ጉዳይ ተቀባይነት ያላገኘው ቤተ-ክርስቲያንን ለማጥፋት ቆርጦ በተነሳው ኢህአዴግ የተባለ ሀይል ምክንያት ነው ሲል በስደት የሚገኘው ሲኖዶስ አስታውቋል።ጥር ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

“ ለ እግዚአብሔር ተገዙ፤ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ”በሚል ርዕስ በስደት ያለው ሲኖዶስ ባወጣው ባለ 7 ገጽ መግለጫ ላይ፤ አራተኛው ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ በከፍተኛ ባለስልጣናትና ትዕዛዝ በወታደሮች ተገደው እንዴት ከቦታቸው እንዲነሱ እንደተደረጉ በስፋትና በጥልቀት አብራርቷል።
ሀቁ ይህ በሆነበት ሁኔታ የ አገር ቤቱ ሲኖዶስ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አራተኛው ፓትርያርክ፦”ስላመመኝ ስልጣኔን ተረከቡኝ ብለዋል>> ማለቱ ፈጽሞ ውሸት መሆኑን ያመለከተው በስደት ያለው ሲኖዶስ፤አንዲትም የድምጽ ፣ የወረቀትም ሆነ የምስል ማስረጃ ማቅረብ በማይቻልበት ሁኔታ ህዝብን በሀሰት ማደናገሩ አግባብ እንዳልሆነ መክሯል።
የ አዲስ አበባዎቹ አባቶች፦<< ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ እንደመሆኑ መጠን አራተኛው ፓትርያርክ በራሳቸው አንደበት ሥልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ያደረገበት ምክንያት የራሱ የሆነ ምስጢር ይኖረዋል>>ማለታቸውን ያወሳው በስደት ያለው ሲኖዶስ፤ ምስጢሩ ምንም እንኳን ለ እውነተኛዋ የቤተክርስቲያን ልጆች ግልጥ ቢሆንም እንደገና እንገልጠዋለን>> በማለት  ፓትርያርኩ በ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በ አቶ ታምራት ላይኔ ትዕዛዝ እንዴት በግፍ ከመንበራቸው ተገፍተው እንደወረዱ፣ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ደብዳቤ ጽፈው ተቀባይነት እንዳላገኙ፣ ከዚያ በማስከተል ቀናኖ ቤተ-ክርስቲያን ተጥሶ  አቡነ ጳውሎስ እንዴት እንደተመረጡ እና  እርሳቸው በእንጦጦ ቤተክርስቲያን እንዴት በናይሮቢ በኩል እንደተሰደዱ በስፋት አብራርቷል።
ከሁሉም በላይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቁርጥ ቀን ልጆችን ከዳር በተስፋ ያነሳሳው የ እርቀ-ሰላም ሂደት ለመጨናገፉ ዋነኛ ተጠያቂዎቹ የአዲስ አበባዎቹ አባቶች መሆናቸውን የገለጠው በስደት ያለው ሲኖዶስ፤ የ እርቁ ሂደት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በስደት ያለው ሲኖዶስ እና ከአዲስ አበባ ተወክለው የመጡት ልዑካን  ድርድሩ እንዲሳካ በሙሉ ፍላጎትና ትጋት ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም የ አዲስ አበባዎቹ አባቶች ሰሞኑን ያወጡት መግለጫ አሳዛኝ ሆኗል ብሏል።
ከአዲስ አበባ የተወከለው  ተደራዳሪ ልዑክ እንደ መደራደሪያ ካቀረባቸው ነጥቦች መካከል ፦”በታሪክ አጋጣሚ የተከሰተውን የቀኖና ችግር ለማስተካከል የሁለቱም ፓትርያርኮች መዋዕለ ዘመን እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን በህይወት ያሉት ፓትርያርክ ወደ መንበራቸው በክብር ተመልሰው መዋዕለ ዘመናቸውን ይፈጽሙ>>የሚል እንደሚገኝበት ያወሳው የህጋዊው ሲኖዶስ መግለጫ፤<<አሁን ግን ከ አዲስ አበባ በወጣው  መግለጫ ላይ “ አምስት ብለን አራት አንልም የሚል”የቁጥር ጨዋታ ውስጥ መገባቱን አመልክቷል።
መግለጫው በማያያዝም፤የአገር ቤቶቹ አባቶች እየተከተሉት ያለው ሰፊውን ምዕመን ያሳዘነ አሠራር፤ ከቀኖና እና ከህገ ቤተክርስቲያን አኳያም ከመጀመሪያው አንስቶ እስካሁን ድረስ ስህተት እንደሆነ የነ ቅዱስ አትናቴዎስን፣የነ  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን እና የነ ቅዱስ ዲዮስቆርዮስን ህይወት ዋቢ በማድረግ በስፋት አስረድቷል።
<<ይህ ሁሉ የሆነው ለምንድነው ብለን ስንጠይቅ የወያነ-ኢህአዴግን አመራር ለማስፈጸም በገሀድ የፓርቲው አባላት የሆኑና ፦<እኛ ብንሾምስ >ብለው ደፋ ቀና የሚሉ ከ አምስት ያልበለጡ ጳጳሳት ከመጀመሪያው አንስቶ እርቀ-ሰላሙን በመቃወማቸው ነው ብሏል-ህጋዊው ሲኖዶስ።
እነዚህ ነጥቦች የሚያረጋግጡት አቢይ ጉዳይ ደግሞ ቀደም ሲል ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን መፋለስ ምክንያት የሆነውና ቅዱስ ፓትርያርኩን በግፍ ከመንበራቸው ያሳደዳቸው ሀይል፤አሁንም ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋትና ትውልዱንም ከመንፈሳዊ ህይወቱ ለማዳከም ቆርጦ በመነሳቱ ነው ሲልም ሲኖዶሱ በቤተ-ክርስቲያኒቱ ላይ እየሆነ ላለው ነገር ገዥውን ፓርቲ ዋነኛ ተጠያቂ አድርጓል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የ ኢትዮጵያ ፓትርያርክ እስከሆኑ ድረስ ይህን እውነት በመሰረዝ እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ የሚደረግን ማንኛውንም የሐዋርያዊ ወንበር ሽሚያ እንደማይቀበለውና እውቅና እንደማይሰጠው ያስታወቀው ሲኖዶሱ፤<<ከዚህም በላይ በ አባቶቻችን ቀኖና መሰረት ድርጊቱን አጥብቆ ያወግዛል” ብሏል።
እርቀ ሰላሙ እንዲሳካ ላለፉት ሶስት ዓመታት በራሳቸው ተነሳሽነት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ለቆዩት የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ጥልቅ ምስጋናውን ያቀረበው ሲኖዶሱ፤አሁንም የ ቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ከ አገር ጉዳይ ተለይቶ የማይታይ በመሆኑ ሀገርን የምትወዱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከሲኖዶሱ ጎን እንድትቆሙ ጥሪ እናቀርባለን ብሏል።
የብዙሀንን ድምጽ በማፈን ሊካሄድ የታሰበው ህገ-ወጥ የፓትርያርክ ምርጫ ተገትቶ ለሰላሙ ለሚደረገው ጥረት ሁሉ ህጋዊው ሲኖዶስ በሩን ከፍቶ እጁን ዘርግቶ በማለት አጠቃሏል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው ሲኖዶስ የያዘውን አቋም በተመለከተ የተለያዩ የህዝብ አስተያየቶችን ማቅረባችን ይታወሳል።

ኢትዮጵያ፤ የአፍሪካ ህብረትን ፕሮቶኮል ጥሳለች ተባለ


ጥር ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ በሚካሄደው 50ኛው የአፍሪካ ህ ብረት ስብሰባ ኢትዮጵያ የሊቀ-መንበርነቱን ቦታ እንደምትረከብ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰጠው መግለጫ በህብረቱ አገራት ዘንድ ጥ ያቄ ማስነሳቱ ተዘገበ።

የደቡብ አፍሪካ የውጪ ፖሊሲ ኢኒሺየቲቭ (ሳፍፒ) እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበርነቱን ቦታ ከቤኒን እንደሚረከቡ በ ኢትዮጵያ የተሰጠው መግለጫ የህብረቱን ፕሮቶኮል የጣሰ እና ጊዜውን ያልጠበቀ በመሆኑ አባል አገራቱን አስገርሟል።
ኢትዮጵያ የሊቀ-መንበርነቱን ቦታ ለመውሰድ የፈለገችው ተራዋ ሆኖ ሳይሆን ፤ወቅቱ የህብረቱ 50ኛ ዓመት ኢዩቤልዩ የሚከበርበት በመሆኑ በዚህ ታሪካዊ በዓል ሊቀመንበርነቱን ለመውሰድ ከመሻት ነው የሚል ትችትም ተሰንዝሯል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግን አቶ ሀይለማርያምን በሊቀመንበርነቱ ቦታ መምረጥ- ከህብረቱ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ጋር እንዲያያዝ ሆን ተብሎ የተደረገ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።
አምባሳደሩ ይህን ቢሉም የሊቀመንበርነቱ ምርጫ የሚደረገው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር የፊታችን ጃንዋሪ 27 በሆነበት ሁኔታ-ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት ሊቀመንበርነቱ የሷ እንደሆነ የሰጠችው መግለጫ የህብረቱን ፐሮቶኮል ጥሷል ተብሏል።
ቃል አቀባዩ ዲና ሙፍቲ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ የህብረቱ ሊቀመንበር ለመሆን ተራው የምስራቅ አፍሪቃ መሆኑን በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ ቦታውን ከቤኒን ለመረከብ ቅድመ-ዝግጅት አጠናቃለች ማለታቸው ይታወሳል።
በ ኢትዮጵያ አቋም ተቃውሞ ያሰሙት የህብረቱ አገራት እነማን እንደሆኑ በግልጽ ባይመለከትም አምባሳደር ዲና ሙፍቱ ፦”አቶ ሀይለማርያም የሊቀመንበርነቱን ስፍራ ሲረከቡ ዋነኛና ቀዳሚ ተግባራቸው በሁለቱ ሱዳኖች መካከል ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲመሰረት እና ለአዲሱ የሶማሊያ መንግስት ጠንካራ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ነው”ማለታቸው፤ምናልባት ተቃውሞው ከምሥራቅ አፍሪካ ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄ ያጭራል።
ጃንዋሪ 27 ቀን የህብረቱ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል በሚከበርበት ጊዜ በሚካሄደው ምርጫ ኢትዮጵያ እንዳለችው የሊቀመንበርነቱን ቦታ ታገኝ ይሆን ወይስ ሌላ ውዝግብ ሊነሳ ይችላል? የሚለው ከወዲሁ ማነጋገር ጀምሯል

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አንድ ነን አንከፋፈልም አሉ

ኢሳት ዜና:-በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን “አንድነን አንከፋፈልም” በማለት የሰደቀና የአንድነት ፕሮግራም አዘጋጅተው ውለዋል።ጥር ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በአዲስ አበባ በኑር መስጊድ በተካሄደው የሰደቃና  የአንድነት ስነስርአት ላይ ተካፍለዋል። ድርጊቱ ገዢው ፓርቲ ሙስሊሞችን ከሁለት ለመክፈል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመቃም የታለመ መሆኑን በስነስርአቱ ላይ የተካፈሉ ሙስሊሞች ገልጸዋል።
ተመሳሳይ ዝግጅቶች በሻሸመኔ፣ በጅማ እና በመቱ መካሄዱን ለማወቅ ተችሎአል።
ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ካለፈው  አመት ጅምሮ ድምጻችን ይሰማ በማለት ተቃውሞአቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።
በመንግስት በኩል የተያዘው ፖሊስ ” በትግስት እንያቸው” የሚል መሆኑን አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ተናግረዋል። ሙስሊሞቹ “ተቃውአቸውን ከጊዜ መርዘምና ከመሰላቸት አንጻር ያቆማሉ ተብሎ በመንግስት የተያዘው እሳቤ ትክክል አለመሆኑን በየሳምንቱ በሚደረጉ ተቃውሞዎች እንዲሁም መንግስት ሙስሊሙን በመክፈል እርስ በርሳቸው እንዲጣሉ በሚያደርገው እንቅስቃሴ መረዳት ይቻላል ” በማለት አንድ የእምነቱ አስተማሪ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል።

Jan 18, 2013

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንቱን የሚተካ ሰው ጠፍቷል ተባለ


በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንቱን የሚተካ ሰው ጠፍቷል ተባለ

ኢሳት ዜና:- የኢሳት የኦህዴድ ምንጮች እንደገለጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ከ3 አመት በፊት የተመረጡት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ከተመረጡበት ማግስት ጀምሮ በህመም ምክንያት በስራቸው ላይ ለመገኘት ባይችሉም እርሳቸውን ለመተካት በኦህዴድ ባለስልጣናት መካከል ስምምነት በምጥፋቱ ተተኪ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ አልተቻለም።ጥር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

አቶ አለማየሁ አቶምሳ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በሁዋላ አንዳንድ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚናገሩት በምግብ መመረዝ ሳቢያ በተነሳ ችግር እስካሁን ድረስ ስራቸውን በተገቢው ሁኔታ ለመፈጸም አልቻሉም።
በአቶ መለስ ዜናዊ የቀብር ስነስርአት ላይ ህክምናቸውን ሳይጨርሱ እንዲገኙ ተጠርተው የነበሩት አቶ አለማየሁ፣ የቀብር ስነስርአቱ ከተፈጸመ በሁዋላ ብዙም ሳይቆዩ አቋርጠውት የነበረውን ህክምና ለመከታተል ወደ ታይላንድ አቅንተዋል። ዜናውን እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ አቶ አለማየሁ በታይላንድ ህክምናቸውን እያደረጉ ሲሆን፣ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ካለፈው ምክር ቤት ስብሰባ ጀምሮ እሳቸውን ለመተካት በተደጋጋሚ ቢሰበሰቡም ስምምነት ላይ ለመድረስ ባለመቻላቸው ምክትላቸው እሳቸውን ተክተው በመስራት ላይ ናቸው።

በክልሉ ምክር ቤት ህገደንብ አንድ ፕሬዚዳንት በህመም ወይም በሌላ ምክንያት በቦታው ላይ ለአመታት ካልተገኘ ስለሚወሰድበት እርምጃ የተደነገገ ነገር አለመኖሩን የኦህዴድ አባሉ ምንጫችን ገልጿል። በዚህም የተነሳ አቶ አለማየሁ በጽህፈት ቤታቸው ሳይገኙ ቀጣዩ ምርጫ ከሁለት አመት በሁዋላ ይከናወናል በማለት ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ በሙሉ ጤንነት ወደ ስልጣናቸው ይመለሳሉ ብለው እንደማያምኑ ምንጫችን ገልጸዋል።

በአቶ አባዱላ ገመዳ የሚመራው ቡድን የአቶ አለማየሁን  በስልጣን መቆየት የማይደግፍ ሲሆን፣ አቶ አባዱላ ተመልሰው የክልሉ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ለማድረግ ደጋፊዎችን እያሰባሰቡ ነው። በአቶ አለማየሁ ዙሪያ የተሰባሰቡ ሰዎች በበኩላቸው የአቶ አባዱላን ቡድን በሙስና በመክሰስ ተመልሰው ወደ ስልጣን እንዳይመጡ አስፋላጊውን ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች መካከል  የተፈጠረው አለመግባባት በክልሉ ውስጥ ለሚታየው ሙስና ከፍተኛውን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አባሉ ገልጸዋል። “ሙስና ወረርሽኝ ሆኗል” ያሉት አባሉ ” በሙስና ኔት ውርክ ውስጥ ያልገቡ አባሎች እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ከስራ እየተባረሩ መሆኑን” ገልጸዋል። የአፈ ጉባኤ የአባዱላ ደጋፊዎች በአንድ በኩል ስልጣናችንን ብናጣ በሚል በዘረፋ ውስጥ ሲሰማሩ፣ የአቶ አለማየሁ ቡድኖችም እንዲሁ የአባዱላ ቡድን አሸንፎ ስልጣን ቢይዝ ከስራ ይቀንሰናል በሚል ከፍተኛ ዘረፋ እየፈጸሙ መሆኑን ገልጿል።

በክልሉ ስለሚፈጸመው ሙስና የጸረ ሙስና ኮሚሽንን ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

Total Pageviews

Translate