ጥር ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ብሄራዊ ቡድኑ ዛሬ ከአምናው ሻምፒዮን ዛምቢያ ጋር ተጫውቶ አቻ ተለያይቷል። ዋልያዎች ጀግንነታቸውን አስመሰከሩ
በ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ቀትር ላይ ከዓምናው ሻምፒዮን ከዛምቢያ ቡድን ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ 10 ሰው ተጫውቶ 1ለ1 ተለያዬ።
በሺዎች በሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው የእልታ ዜማ ታጅበውና ከላይ እስከ ታች በቢጫ አሸብርቀው ወደሜዳ የገቡት ዋልያዎች ፤በባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዎና በዛምቢያ ላይ በግልፅ የበላይነታቸውን እያሳዩ የመጡት ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ነው።
ጨዋታው ከመጀመሩ ዋልያዎች በማራኪ አጨዋወት አንድ ሁለት በመቀባበል ጫና ፈጥረው ቆዩ።
ከዚያም 10ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰይድ ብቻውን ኳስ ሲገፋ ከነበረው የዛምቢያ ተከላካይ በፍጥነት ኳሷን በማስጣል ወደፊት ሊያመራ ሲል በተከላካዩ ተጠለፈ። ዳኛውም የመጀመሪያውን ቢጫ ለዛምቢያ ተከላካይ አሳዩ፡፡
ሳላዲን እንደገና በ16ኛው ደቂቃ ከአዳነ ግርማ የተሻገረችለትንና ሁለቱን የዛምቢያ ተከላካዩች አልፉ እየነጠረች እግሩ ሥር የገባችለትን ኳስ የበረኛውን መውጣት በማየት ከፍ አድርጐ በረኛውን በመስቀል በአናቱ ላይ ቢያሣልፋትም መሬት ላይ በመንጠር ለጥቂት የአግዳሚውን ብረት ታክካ ወደ ውጪ ወጥታለች። ብዙዎችን ቁጭ ብድግ ያደረገች የመጀመሪያዋ ሙከራ ነበረች፡፡
ብዙም ሳይቆይ ዋልያዎች አንዱ ሁለት እየተቀባበሉ ከሁዋላ እየገፉ ያመጧትን ኳስ አዳነ ግርማ በፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ላይ ራሱን ነፃ አድርጎ ለቆመው ሳልሀዲን ሰይድ አቀበለው። ሳልሀዲን ኳሷን የሚመታ በመምሰል አጠገቡ የነበረውን የዛምቢያ ተከላካይ አታሎ ወደ ጎል ሊያመራ ሲል በዘምቢያ ተከላካይ ጥፋት ስለተፈፀመበት ዋልያዎች የፍጹም ቅጣት ምት አገኙ፤ ሆኖም ሳልሀዲን ረጋ ብሎ የመታትን ኳስ የዛምቢያው በረኛ በቀላሉ አድኗታል
ከዕረፍት በፊት በተደጋጋሚ በግራ በኩል በተደጋጋሚ ሲያጠቁ የታዩት ዛምቢያዎች አልፎ አልፎ ወደ ጐል በመድረስ ጫና መፍጠራቸው አልቀረም፡፡
በዚህ ሁኔታ 26ኛው ደቂቃ ላይ የዛምቢያው አማካይ በመሀከል ሰንጥቆ ያሣለፋትን ኳስ ለማግኘት፤ የዛምቢያው አጥቂና የኢትዮጵያው ጐል ጠባቂ ጀማል ጣሰው ወደ ኳስ ሲሮጡ ፤ጀማል ከኳስ ውጪ በዛምቢያው አጥቂ ላይ አደገኛ ጨዋታ በመጫወቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡
ከ26ኛው ደቂቃ ጀምሮ ሙሉ 90ደቂቃው በ10 ሰው ለመጫወት የተገደደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጀማልን መውጣት ተከትሎ የተፈጠረበት ጫና፤ የጨዋታ የበላይነቱን እንዳሳጣው በግልፅ ታይቷል፡፡
ጀማል መውጣቱን ተከትሎ ብዙም ሣይቆዩ ዛምቢያዎች ጐል አስቆጠሩ፡፡ የመጀመሪያው ግማሽ ጨዋታ በዛምቢያ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ፡፡
እጅግ አስገራሚው ነገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 1-0 እየተመራ ቢሆንም፣ 1 ተጫዎች በቀይ ካርድ ቢወጣበትም፤ ደቡብ አፍሪካ የተገኘው ደጋፊ ስሜቱና ድጋፉ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱ ነው፡፡
በ10 ሰው ለመጫወት የተገደደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዕረፈት በኋላ መጠነኛ የአሰላለፍ ለውጥ በማድረግ ባሳየው ብስለት የተሞላበት ጨዋታ (ከብዙዎች ግምት ውጪ)ኳስ በመቆጣጠርም ሆነ ጥሩ ጨዋታ በማሣየት ከዛምቢያዎች ልቆ ታይቷል፡፡
ዋልያዎች የተፈጠረባቸውን የአንድን ሰው ክፍተት ለመሸፈን ይመስላል አብሮ በመከላከልና አብሮ በማጥቃት የተመሠረተ የካውንተር አታክ አጨዋወት ስልት በመከተልና የተቆጣጠሯትን ኳስ በድንቅ ቅብብል አፍጥኖ በመጫዎት የአምናውን ሻምፒዎና አስጨንቀውት ውለዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ 64ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አዲስ ህንፃ በመሀል ሰንጥቆ ለሳልሀዲን ያደረሰለትን ኳስ ፤ሳልሀዲን በቀኝ በኩል ለገባለት ለአደነ ግርማ በጥሩ ሁኔታ አቀበለው፡፡ የጨዋታው ኮከብና እውነተኛ ግርማ ሆኖ ያመሸው አምበሉ አዳነ ግርማም ኳሷን የሚመታ መስሎ- ሊደረብ ተጠግቶ የቀረበውን የዛምቢያ ተከላካይ ካስተኛው በኋላ ፤በረኛው ባጠበበትና ባልጠበቀበት በግራ በኩል አክርሮ መሬት ለመሬት የመታት ኳስ የግራውን ቋሚ በረት በመምታት ከመረቡ ተወህዳለች። አዳነ ግርማ ከጓደኞቹ ጋር ደስታቸውን ሊገልፁ ወደ ደጋፊዎቻቸው ሲያመሩ፤ የወደቁት የዛምቢያ ተከላካይና በረኛው ከመሬት አልተነሱም ነበር፡፡
ስታዲየሙ ዳር እስከ ዳር በጭፈራ አስተጋባ። ውሃ ሰማያዊ ሱፍ ከነጭ ሸሚዝና ከቀይ ክራቫት ጋር የለበሱት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በደስታ በመስፈንጠር ሽቅብ ዘለሉ፡፡ የራሳችንን አርሰን ቬንገርና አሌክስ ፈርጉሰን በታላቅ ውድድር ላይ ሲዘሉ አየን። በዚሁ 1ለ1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቀቀ፡፡
ከሌሎች አገሮች ደጋፊዎች በተለየ መልኩ ቡድናቸውን ለመደገፈ በስታዲየም ዙሪያ የተገኙት ውቦቹ ኢትዮጵያውያን፤ ለቡድናቸው ካበረከቱት ታላቅ አስተዋፅኦ በተጨማሪ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን አድምቀውትና ውበት አለብሰውት ታይተዋል፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment