Pages

Dec 12, 2012

ኢሳት ዜና:-የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ50 ሺ ብር ዋስ በማስያዝ ክሱን በውጭ ሆኖ እንዲከራከር ትእዛዝ አስተላልፎአል።

ታህሳስ ፪(ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ50 ሺ ብር ዋስ በማስያዝ ክሱን በውጭ ሆኖ እንዲከራከር ትእዛዝ አስተላልፎአል።

ዳኛው በመዝገብ ቁጥር 123 ሺ 875 የተከሰሰው ጋዜጠኛ ተመስገን ከዚህ ቀደም ለብይን ተቀጥሮ እያለ አቃቢ ህግ ክሱን በማንሳቱ የተቋረጠ ቢሆንም አቃቢ ህግ እንደገና ክሱን በመቀስቀሱ ነው ለዛሬ የተቀጠረው ብሎዋል። የአቃቢ ህግን የክስ አስተያየት ያዳመጠው በዳኛ አይሸሹም ሽመልስ የተሰየመው ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ50 ሺ ብር ዋስ አልያም እስር ቤት ወርዶ ክሱን እንዲከራከር ውሳኔ አስተላልፎአል። የፍትህ ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት ተወካይም በሚቀጥለው ጊዜ ቀጠሮ እንዲቀርቡ በፖሊስ መጥሪያ እንዲደርሳቸው ውሳኔ አሳልፈዋል። የሚቀጥለው ጊዜ ቀጠሮም ለታህሳስ 24 ቀን 2005 ዓም ጠቃት ተቀጥሯል።
የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቆች የሆኑት አቶ አምሀ እና አቶ ስሜነህ ፍርድ ቤቱ የፌደራል አቃቢ ህግ በፈለገው ጊዜ መክሰስና ክሱን ማንሳት ስልጣን እንዳለው ብናውቅም ፣ ነገር ግን ዜጎችን ሰላማዊ ስራቸውን እየሰሩ እና እየኖሩ ሳለ በፈለገው ጊዜ ከሶ በፈለገው ጊዜ ክሱን በማንሳት ዜጎችን ማጉላላት የለበትም ፣ ስለዚህ ደንበኛችን ሲከሰስም ሆነ ዋስትና አስነፍጎት ካሳሰረ በሁዋላ ኪሱን አቋርጦ ሲፈታ ምንም ምክንያት ያልገለጸ ሲሆን ምክንያቱን እንዲያስረዳልን ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የፌደራል አቃቢ ህግ በበኩሉ ይርጋ እስካላገደው ድረስ ዜጎችን የመክሰስ እና ክሱን በፈለገው ጊዜ የማቋራጥ መብት እንዳለው ገልጾ ፣ የተመስገን ክስ የተቋረጠው ፍትህ ሚኒስቴር በቂ መረጃ ባለማሰባሰቡ ነው ብለዋል። ዳኛ አቶ አይሸሹም ለጠበቆች ክሱ ተቋርጦ ከማረሚያ ቤት በመውጣቱ የተጓደለበት መብት ምንድነው በማለት ጠበቆቹን ጠይቀዋል። ጠበቆቹም ደምበኛችን ያለበቂ ማስረጃ ክስ ሊቀርብበት አይገባውም ነበር፣ ክሱ ከተቋረጠም በሁዋላ ደንበኛችን ሰላማዊ ኑሮ እየኖረ ሳለ አሁን ድንገት የተጠረጠረበትን ምክንያት አቃቢ ህግ አላሳወቀም ፣ ሲፈታም ወጥተህ ወደ ቤትህ ሂድ ከመባል በቀር ምክንያቱ አልተነገውም ፣ ዜጎች ዝም ብለው አቃቢ ህግ ደስ ባለው ጊዜ ታስረው ደስ ባለው ጊዜ ይለቀቃሉ ወይ ብለው የጠየቁ ሲሆን ፣ ክሱ እንዲቋረጥም ጠይቀዋል።
አቃቢ ህግ ይህ የፍትህ ሚኒስቴር ስልጣን ነው ያለ ሲሆን ይርጋ እስካላገኘ ድረስ ክሳችንን መቀስቀስ መብት አለን፣ አሁን ምርመራችንን ጨርሰናል ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ በእርግጥ አሁንም ቢሆን ምንም የተጣራ ምርመራ አልተመለከተንም ፣ ክሱ ሲቋረጥም ገና ያስከስሳል አያስከስስም በሚለው ብይን ላይ ነበር፣ ቢሆንም አቃቢ ህግ ክሱን ሊቀሰቅስ የህግ ስልጣን አለው በማለት ለታህሳስ 24 ቀን 2005 ዓም ቀጠሮ ስጥቶ ችሎቱን አጠናቋል።

ጠበቃው አቶ አምሐ ለኢሳት እንደተናገሩት ጋዜጠኛ ተመስገን ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከራከር መፈቀዱ አወንታዊ ነገር መሆኑን ገልጸው ፣ ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን የኢኮኖሚ አቅም ሳይመረምር ቢወስንም ከወንጀሉ ፕሮፋይል አንጻር የ50 ሺ ብር ዋስትናው ብዙ የሚማረር አይደለም ብለዋል።

ጠበቃው አቶ አምሐ በተመስገን ላይ የቀረበው ክስ ከዚህ ቀደም ተከሶበት ክሱ ተቋርጣል የተባለው መሆኑን ገልጸው፣ ክሱ በወቅቱ ሲነሳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ ስለለተቋረጠበት ምክንያት አቃቢ ህግ ማስረዳት እንደነበረበት ገልጸዋል::

በተመሳሳይ ዜናም በእስር ላይ የምትገኘዋ ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ዛሬ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርባለች። ፍርድ ቤቱ የጋዜጠኛ ርእዮት አለሙን ጠበቃ የሆኑትን አቶ ሞላ ዘገየን መሰረታዊ የህግ ስህተት አለ ምትሉትን ተናገሩ በማለት የጠየቁ ሲሆን ጠበቃውም መልስ ሰጥተዋል። ጠበቃው ያቀረቡት መከራከሪያ ጋዜጠኛ ርእዮት ህገመንግስታዊ መብቷን ተጠቅማ ስራዋን ሰራች እንጅ፣ ከጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ ጋር የስልክ ንግግር አድርጋለች በመባል ብቻ ሽብረተኛ ተብላ ልተወነጀል አይገባትም የሚል ነው።

ችሎቱ እንደገና ጉዳዩን ለማየትና ትእዛዝ ለመስጠት ለታህሳስ 24 ቀን 2005 ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ርእዮት የ2012 የአለማቀፍ ሴቶች ሚዲያ ፋውንዴሽን ሽልማት አሸናፊ መሆኗ ይታወቃል

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate