ከዘካሪያስ አሳዬ( ኖርዌይ)
እንደሚታወቀው አገራችንን ሊጠብሳት እያዘጋጃት ያለው የ”ጎሳ ፖለቲካ” ደራሲውና ቀማሚው በሞት ቢለዩም
የሚያበርደው አስተዋይ መሪ አልተገኘም እንደውም እርዝራዞቹ የሳቸውን ህራይ እናስቀጥላለን በማለት አብሰውታል፡፡
በማስተዋል ማርከሻውን ለሚቀምሙም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በቂ ጆሮ አልተሰጣቸውም – ጩኸቱ እጅግ
ያደነቁራልና። ከውጪም ከውስጥም የሚረጨው የጎሳና የ”ደም” መርዝ ሳያንስ አሁን ደግሞ በሃይማኖት ተንተርሶ
የተጀመረው አለመግባባት አስደንጋጭ ይዘት እንዳለው አያጠያይቅም። ተወደደም ተጠላም ያስፈራል። ወያኔ/ኢህአዴግ
ባቀናበረው “የድርሰት” ፊልም መነሻ ሳይሆን በበርካታ መረጃዎች የተደገፈ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል።
የሚገርመው ግን እትብታችን በተቀበረችበት በአገራችን ሁለተኛ ዜጋ፣ ተሰደን ባለንበት አገር ሁለተኛ ዜጋ ! ተሰደን
በምንኖርበት አገር እንኳን የፖለቲካው ሁናቴ የወያኔን የቤት ስራ መቅረፍ ሲገባን እንደውም ያባስነው ይመስለኛል።
የኢህአዴግ/ ወያኔ በብሄር፣ በጎሣ፣ በዘረኝነት የከፋፈላትን አገር መታደግ ሲገባን ዛሬ ደግሞ ተሰደን እራስ በራሳችን
ተከፋፍለን በብሄር የፖለቲካ ድርጅት አቋቁመን እራስ በራሳችን መሻኮትና ለብሄራችን፣ለዘራችን ነፃነት እንታገላለን ስንል
የወያኔ ስራ ከማስፈፀም ምን ይለያል? ሁሉም የፖለቲካ ድርጅት አምባገነኑን ስርዓት ጥለን የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን
ባለቤት እናደርጋለን ብለን ካልን ምንድነው ችግራችን? አንድ የማንሆንበት! በእንደዚህ አይነት አካሄዳችን የመቶ አመት
ትግል እንዳያስፈልገን! በብሄር የታመነ ፖለቲካ የትም አያደርስም መጨረሻው ዋጋ ያስከፍላል ኢትዮጵያዊነትን ያልጠበቀ
ትግል ነው ምፃሜውም ያላማረ ነው።በብሄር ብቻ የተደራጀ ፖለቲካ እናትና አባትን የሚለያይ ፖለቲካ ውጤት ነው።
ማንም ሲወለድ ከዚኛው ብሄር ልወለድ ብሎ አልተወለደምና ብሄራችን ውበታችን ነው የመበላለጫ መለኪያ አይደለም!
ደማችን ኢትዮጵያዊነት ነው። ለእኔ ከዘር ቆጠራ እና ከብሔር ነፃ የሆነው የማንነት መገለጫ ኢትዩጵያዊነት ብቻ ነው፡፡
ዛሬ በአገር ቤት ውስጥ ሆነው በኢትዮጵያዊነት ስሜት እየታገሉ ያሉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ህዝቡም ዋጋ
እየከፈሉ ባሉበት ወቅት ውጪ ያለው መርዳት፣ ማታገል ሲኖርብን እኛው ውጪ ያለነው ተከፋፈልንና አገራችን ለበይ
ሰጠን! በቃላት ሽኩቻ አንባጓሮ ከፍተን መጣላት ወደድን!
ኢትዮጵያ ውስጥ የሐይማኖት፣ የፖለቲካ፣የጎሳ ችግርች ሲፈጠር እንደ እሳት አደጋ አላርም እየነፉና እየከነፉ መሮጥና
ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ብቻ ግን መሆን የለበትም፡፡መብቴው ማበጀት ያስፈልጋል።መብቴው ደግሞ ልዩነታችንን ወደ
ኋላ ትተን ህዝባችንን መታደግ ነው መሆን ያለበት! ያለበለዚያ ‹‹በአህያ ቆዳ የተሰራ ቤት፣ ይፈራርሳል ‹‹ጅብ የጮኸ
ዕለት…›› እንዳይሆን አንድነታችንም የዘይትና የውሃ አይነት እንዳይሆን ማንም ቢሄድ፣ ማንም ቢመጣ የማይነቃነቅና
መሰረተ ፅኑ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ሆኖ እንዲዘልቅ ወደ ታች ወርደን እናጥብቀው፡፡
“ዲሞክራሲ የሚሰራው አውሮፓ ውስጥ ነው፤ የአፍሪካ ባህል የተለየ ነው እንደተባለ፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ
ያለችበትን እንመልከት፡፡ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አምጥተናል ይላሉ፤ ነገር ግን በትክክል ያመጡት
ጎሰኝነትን ነው፤ሁሉም የተደራጀው በፓርቲ ሳይሆን በጎሳው ወይም በሃይማኖቱ ነው - በሁሉም ቦታ
እንደሚታየው፡፡ በዚህ የተነሳ ዓለም ከዚህ በፊት አይታው የማታውቀው ጦርነት በአፍሪካ ውስጥ መከሰቱ
አይቀርም ! በኢትዮጵያ ውስጥ አካሄዱም አያምርም ጠንቀቅ ብለን ብንመለከተው ጥሩ ነው አለበለዚያ አደጋው
የከፋ ነው፡፡ አስከፊ ነው የጎሳ ጦርነት!”
ህዝብ ውይይትና ለሚዲያ ፍጆታ ከሆኑት የሰሞኑ ወሬዎች መካከል ሁሉም ለግራ መጋባት የሚዳርጉ ሆነው
አግኝቻቸዋለሁ፡ ፡ አንዳንዱ ግልጽም፣ አስፈላጊም አልነበረም፡፡ ከአደረጃጀት ወሬዎች እንጀምር፡፡ ክላስተር የሚባል ነገር
መጥቷል፡፡ የሥራ ዘርፎችን ቡድኖችን መፍጠርና ተመሳሳይ ሥራዎችን እያሰባሰቡ የማስተባበር፣ የአደረጃጀት አይነት ነው
ፈልሳፊዎቹም ህውሃቶች ናቸው እራሳቸውን ብቻ ለመጥቀም የወጣ አሰራር ነው! መቼም ለህዝብ ሰርተው አያውቁም!
እውነት ነው ፡፡ ስለሁለቱ አዲስ ም/ጠ/ሚኒስትሮችና በድምሩ ሶስት መሆን ተገቢነትና አስፈላጊነት ግራ የተጋባው ዜጋ
ቁጥር ብዙ ነው፡፡ ምሁራን አይስማሙም፤ ተቃዋሚዎች አይደግፉም፡ ፡ የተቀረው ግራ ተጋብቶ መሃል (መስቀለኛ)
መንገድ ላይ ቆሟል፡፡ የተሿሚዎች አመጣጥ ከየትኛውም ብሄር ወይም ከየትኛውም የፖለቲካ ቡድን መሆኑ ፋይዳ
የለውም ብሄሩ ብቻ ሳየሆን ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል ።ካለበለዚያ ለእኔ ትርጉም አይሰጠኝም፡፡ ለእኔ ዋናው ጉዳይ
አስፈላጊ ነበር ወይ? የሚለው ነው፡፡ጉልቻው ቢለዋወጥ ለውጥ የለውም! አገሪቱ ራሷ ሶስት ም/ጠ/ሚኒስትር የሚሸከም
ትከሻ የላትም፡፡
የሌሎች አገሮችን ልምዶች መጠቃቀስ ብቻ አያዋጣም፡፡ እኛ ‹‹እፍ ቢሏት ብን›› በምትል በጣም ዝቅተኛ በጀት (ያውም
ግማሹ ከውጭና ከውስጥ ብድርና እርዳታ ከሚሰበሰብ የምንተዳደር ህዝቦች ነን፡፡ )
በቅርብ ግዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ በአልጀዚራ ቴሌቪዥን ቃለ_ምልልስ ባደረጉበት ወቅት ኤርትራው
መሪ ከኢሳያስ ጋር ለመነጋገር አስመራ ድረስ ለመሄድ መፈለግ በራሱ ግራ የገባ ነገር ነው፡፡አገር ቤት ካሉት የፖለቲካ
ድርጅቶች ጋር ምንም የሚያደራድረን ነገር የለም እያሉ ዲስኩር ሲያረጉም ይሰሙም እንደነበር የሚታወቅ ነው።
ከእነሱ ጋር መታረቅ ለምን ያስፈልገናል? ኢትዮጵያ ለኤርትራ ታስፈልጋታለች፡፡ ኤርትራ ግን ለኢትዮጵያ አታስፈልግም
ማለት ነው? መልሱን ለአንባቢ፡፡ ያው ወደቧ ነው ካላችሁኝ ደግሞ፡ ፡ እሱ ደግሞ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ በእርቅ ስም
መጥተው በለመዱት የበላይነት በተካኑበት እብሪት ሲጨፍሩብን ማየት አንፈልግም፡፡ በገዛ አገራችን የእነሱ መፈንጫ
መሆን አንፈልግም፡ ፡ ያለፈው ይበቃል፡፡ እዛው በጠበላቸው፡፡ አክራሪ (አልቃኢዳ አልሸባብ ወዘተ…) እንዳታስገባብን
ብንታረቅ ይሻላል የሚሉትም ከንቱ ስጋት ነው፡ ፡ የኢሳያስን ጉዳይ ለወያኔ እንጂ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አያሳስበንም ፡፡
ዛሬ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚኖር ማንኛውም መካከለኛ ገቢ ካለው ዜጋ ይልቅ ተንቀባሮ የሚኖረው የኤርትራ ስደተኛ
ነው፡፡ያግሩ ዜጋማ ሁለተኛ ዜጋ ነው። በእኛ ልጆች ኮታ እነሱ ኮሌጃችን ገብተው ይማራሉ፡፡ እኛ ግን ከእባብ እንቁላል
እርግብ ይፈለፈላል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ግራ የገባ ነገር ነው፡፡ ከጎረቤት ጋር ሰላም መፍጠር ተገቢ ቢሆንም ከኤርትራ ጋር
ስላለን ግንኙነት ግን ጊዜ ይፈታዋል ! ኧረ እኛ ማንንም መለየት አልቻንም እኮ ከኢትዮጵያዊነት ደም ይልቅ ሌላ ደም
ይሸታቸዋል ባለስልጣናቱ ተብዬዎች፡፡ የእኛ ችግር ድህነት እንጂ ኤርትራ አይደለችም፡፡ በሁለት ዝሆኖች መካከል ፀብ
ሲፈጠር የሚጎዳው ሳሩ ነው። በተጫረው የድንበር ፀብ ያለቁ ህዝቦቻችንንም እናስታውስ፡፡ መንግስት እያሳየ ያለው ከልክ
ያለፈ ትዕግስት ሊያመጣ የሚችለውን ችግር ከወዲሁ መገመትና መዘጋጀትም ያስፈልጋል፡፡ ውሻ በቀደደው ጅብ እንዳይገባ
አስቀድሞ መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ በእንቅርት ላይ… እንደሚባለው ማለቂያ ያጣው የወያኔ ግፍ ማለፊው መድረሱ አይቀር!!
ወያኔና ጀሌዎቹ በታላቋ ሀገራችን ኢትዮጽያ ላለፉት 21 ዓመታት የተንሰራፋው የዘር ጥላቻ በማስፈን ነፃ አውጭ ነኝ ባዩ
ቡድን ጠባብ ዓላማውን ለማሳካት ፍቅርን በሰበኩ፤ አንድነትን በመከሩ፤ ስለ እኩሌነት በተናገሩ የዲሞክራሲ ታጋዮችና
ሠላማዊ ዜጎች ላይ ማለቂያ የሌለው ስም በመለጠፍ በእንበለ ፍርድ በየእስር ቤቱ ያጎራቸው ዜጎች ቁጥር ለመጥቀስ
እስኪያዳግት ድረስ በግፍ ላይ ግፍ በበደል ላይ በደል ከመፈጸም ሊታቀብ ይቅርና ጭራሽ እየባሰበት ከመሄድ ሊገታው
የሚችል ሁኔታ ባለመፈጠሩ የጭቆና የብረት ቀንበሩን በሕዝብ ላይ በመጫን ሀገሪቱን በፍጥነት ወደ ታላቅ እስር ቤትነት
ለውጧታል።ኧረ ወገን ምንድን ነው የሚጠበቀው?
በመጨረሻም ወያኔ የዘራውን አይነት የዘር መንፈስ የበላይነትና የበታችነት ስር የሰደደውን የጎሣ ግጭት ማስፋፋት
ልንቃወመው፣ልንታገለውና ልንፋረደው ይገባል። ወያኔ/ህውሃት፣ብአዴን፣ኦህዴድ፣ ደኢሕዴን ወዘተ እያለ እየበታተነ
የዘራው መጥፎ የዘር መንፈስ ሊለያየን ሊበታትነን አይገባም። እናትንና አባትን ሊለያይ የሚችል ፖለቲካ ማለት በብሄር
ተመስርቶ ለብሄሬ ብቻ ነው የምሰራው ካልን ይህ መንፈስ ኢትዮጵያዊነትን አያመላክትም። አባቴ እናቴን ሲያገባት ዘርሽ
ምንድነው ብሎ አላገባትም እኔቴም እንዲሁ ! ኢትዮጵያዊነታቸው በቂ ነው! ዘሩን ለገበሬው እንስጠው! እናትን አባትን
የሚለያይ ፖለቲካ አንስራ !!
ድል በአንድነት ለሚያምኑ ኢትዮጵያውን ሁሉ !
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ከዘካሪያስ አሳዬ( edenasaye@yahoo.com)
No comments:
Post a Comment