ኤልያስ
እኔ የምላችሁ…ኢህአዴግ 9ኛውን የፓርቲውን ጉባኤ ያካሄደበትን እጅግ የተንቆጠቆጠ “ባለ 7 ኮከብ” (ኮከብ የመስጠት ኮፒራይቱ የራሴ ነው!) የስብሰባ አዳራሽ አይታችሁልኛል? (በኢቴቪ ማለቴ ነው!) በአካልማ ማን አስደርሷችሁ! (አዳራሹ ከ2ሺ ሰው በላይ አይችልማ!) ለነገሩ አዳራሹም ቢበቃ ሌላም የመግቢያ መስፈርት እንደነበረው ሰምቻለሁ። ምንጮቼ እንደነገሩኝ --- “ተራማጅ” ወይም “አብዮተኛ” ያልሆነ ግለሰብም ሆነ ፓርቲ ---- እንኳንስ በጉባኤው ሊሳተፍ ቀርቶ በአካባቢው ዝር ማለትም አይፈቀድለትም ነበር! (አሉ ነው እንግዲህ) በነገራችሁ ላይ አሁን ባልኩት ጉዳይ ዙርያ ማስረጃም ሆነ መረጃ እንደሌለኝ ከወዲሁ ለመግለፅ እወዳለሁ (እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር አሉ!) እናላችሁ ---- ኢህአዴግ ከውጭ አገር 13 “እህት ፓርቲዎች”ን ጋብዞ ከአገር ውስጥ አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ ያልጋበዘው አንዳንዶች እንደሚያስወሩት በ“ንቀት” ወይም “በአገር ውስጥ ምርት ስለማይኮራ”አይደለም ! (የሥጋ ዘመድ እንደሌለው በባዕድ ፓርቲዎች መታጀብ ምኑ ደስ ይላል?) በነገራችሁ ላይ ተጋባዥ የውጭ አገር ፓርቲዎቹ “እህት ፓርቲዎች”የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ እንደሆነ ከሁነኛ የገዢው ፓርቲ ምንጮች “ሁነኛ መረጃ” ማግኘቴን ስነግራችሁ በኩራት ነው፡፡ (የተርብ ካድሬ የፈጠራ ውጤት ነው ተብሏል!) በአሁኑ የኢህአዴግ ጉባኤ ምን እንዳስደሰተኝ ታውቃላችሁ? አንደኛ እንዳለፈው የአዳማ ጉባኤ ኢህአዴግ የሠላማዊ ሰልፍ መብታችንን ማረሳሳቱ ነው እንዴ? (አያደርገውም!)“ጓድ! ጓድ!” የሚል ነገር ብዙም አልሰማሁም (ጥሎብኝ ሶሻሊዝም አይመቸኝም!) ሁለተኛው ያስደሰተኝ ነገር ደግሞ የኢህአዴግ ግንባሮች በነፍስወከፍ (በፉክክር አልወጣኝም!) ያስገነቧቸውን ቄንጠኛ የጉባኤ አዳራሾች መመልከቴ ነው፡፡ (የአዳራሽን ችግር እነ “አንድነት”ፓርቲ ይንገሯችሁ!)አንዱ አሽሟጣጭ ወዳጄ ስለኢህአዴግ 9ኛው ጉባኤ ምን እንዳለኝ ልንገራችሁ አይደል---(አደራችሁን ኢህአዴግ እንዳይሰማ!) የዘንድሮ ጉባኤ የተካሄደው “አዳራሽ ከእኔ፤ ጉባኤ ከእናንተ” በሚል መርህ ነው ብሎኝ ቁጭ አለ፡፡ እኔ እንኳን በዚህ አልስማማም፡፡ ለምን መሠላችሁ? የአመራሩን “አድርባይነት”ችግር ያጋለጠውን “ታላቅ ጉባኤ” እኮ ነው አፈር ድሜ ያስበላው! እኔ የምለው ግን --- ጉባኤው በእንግሊዝኛም ሲካሄድ ነበር ልበል --- (የአማርኛው ሳያንስ እንግሊዝኛውንም?)ከሁሉም በላይ ቅር ያሰኘኝን ደግሞ ልንገራችሁ። በጉባኤው ላይ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አባላት መጋበዛቸው አልተመቸኝም፡፡ (ጠንቋይ ቤት ሄጄ ወይም አዋቂ ነግሮኝ ግን አይደለም) ቆይ እስቲ --- የቻይና ፖለቲከኞች ምን ሊፈይዱልን ነው የተጠሩት?የቀድሞው የአገራችን መሪ ጓድ (ኮሎኔል) መንግስቱ ኀይለማርያም ምን እንዳሉ ሰምታችኋል? የአገራችን የረዥም ጊዜ ወዳጅ የነበረችው የሶቭየት ህብረት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሚኻኤል ጎርባቾቭ፤ በ11ኛው ሰዓት ክህደት እንደፈፀሙባቸው በምሬት ተናግረዋል፡፡ (ፖለቲከኛ ወዳጅ የለውም ለማለት ነው!)አንዳንድ እውቅ የፖለቲካ ተንታኞች ስለቻይና ምን ይላሉ መሰላችሁ? “ቻይና የሚያምርባት ቀለበት መንገድ ስትሰራ ብቻ ነው!” በዚህ እንኳን እኔም ራሴ እስማማለሁ፡፡ ለዘመናት ከአንድ ኮሙኒስት ፓርቲ ውጭ የማታውቅ አገር፤ ለኢህአዴግ ምን ልታስተምርብን እንደምትችል መገመት አያቅተንም! (እሱ ለራሱ በቋፍ እኮ ነው!)የእኔን ዋነኛ ስጋት ብነግራችሁ ግን ደስ ይለኛል። ምን አለ በሉኝ --- የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አባላት እንዲህ እግር ካበዙ ስንት ታጋዮች የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉበትን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ከንቱ ያደርጉብናል፡፡ እዚህ አገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖራቸውን ሲሰሙ በድንጋጤ አፋቸውን መያዛቸው አይቀርም ብዬ እገምታለሁ፤ ከዚያም “ተራማጅ ፓርቲ በሚመራው ልማታዊ መንግሥት ውስጥ ተቃዋሚዎች ምን ይሰራሉ? ይሄ የተራማጅ ፓርቲ ተፈጥሮም ሆነ መርህ አይደለም” በማለት ኢህአዴግን ይሞልጩታል (የአቋም መግለጫ ሁሉ ሊያወጡ እንደሚችሉ ጠርጥሩ!) እኔ የምላችሁ ግን … ቻይና ውስጥ የምርጫ ቦርድ ኮሚሽን የሚባል ነገር አለ እንዴ? አረ አይመስለኝም!ፓርቲዎችና የምርጫ ፉክክር በሌሉበት አገር ምርጫ ቦርድ ምን ይሠራል? (የሥራ እድል ይፈጥራል ካልተባለ በቀር!)የፓኪስታን ጠ/ሚኒስትር አንድ ወዳጅ አገር ይሄዱና ባቡር ሳይኖር የሃዲድ መስመር ተዘርግቶ ያያሉ፡፡ በዚህ ተገርመውም የአገሪቱን ፕሬዚዳንት “ባቡር በሌለበት ሃዲድ ምን ይሰራላችኋል?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱም የዋዛ አልነበሩም “እናንተ አገር የፍትህ ሚኒስቴር አለ አይደለም እንዴ!” በማለት ዝም አሰኟቸው (ፍትህ ሳይኖር ፍትህ ሚ/ር--- ማለታቸው እኮ ነው!) ኢህአዴግ ሁልጊዜ በምን እንደሚያስገርመኝ ታውቃላችሁ? ራሱን ሲወቅስ ለነገ አይልም፡፡ የእሱ ችግር ምን መሰላችሁ? ወቀሳና ቅጣትን አይለይም። ወቅሶ ዝም ነው! (እንኳን ፓርቲ ህፃንም ቅጣት ያስፈልገዋል!) እናም--- “ችግሩን ሸፋፍነን ልናልፍ አይገባም!” ማለት ብቻውን ውጤት አያመጣም ለማለት ያህል ነው !እኔ የምላችሁ… ኢህአዴግ “የአመራሩ ችግር አድርባይነት ነው” ሲል ምን ለማለት ፈልጎ ነው?(አንዳንዴ እኮ በወፍ ቋንቋ የሚያወራ ነው የሚመስለው!) በነገራችሁ ላይ አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ በአሉ ግርማ በአንድ የሥነፅሁፍ ሥራው ላይ “ከአድርባይ ብዕር ባዶ ይሻላል” በማለት ፅፏል፡፡ የዘመኑ ደራሲ ደግሞ “ከአድርባይ አመራር ባዶ ፓርቲ ይሻላል” እንደሚል እገምታለሁ (ከሰሞኑ የኢህአዴግ ግምገማ በመነሳት) እናንተ አንባቢዎቼ እንደምታውቁት እስከዛሬ ድረስ በገዢው ፓርቲ የአመራር ጉዳይ ውስጥ ገብቼ “ፈትፍቼ” አላውቅም (ህገመንግሥታዊ መብቴ እንደሆነ ባውቅም!) አሁን ግን የአመራሩ ችግር አድርባይነትና ኪራይ ሰብሳቢነት መሆኑን ከራሱ ከኢህአዴግ ስለሰማሁ መፍትሄ ለመሰንዘር እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ ፈታኝ ወቅት እኮ ዝምታ ከ“ጠላት” እንጂ ከ”ወዳጅ” አይጠበቅም፡፡ (“ወዳጅ” እንጂ “አባል ነኝ” አልወጣኝም!) እናላችሁ… ኢህአዴግ የፓርቲውን አመራር ለውጭ ማኔጅመንት በኮንትራት ቢሰጠው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ አሃ… የኢህአዴግ አመራር ችግሮች ያለቅጥ በዙ እኮ! ይሄውላችሁ… በግልፅ እንነጋገር ከተባለ በዘንድሮው የኢህአዴግ ጉባኤ ፓርቲው የሰራው በጐ ነገር አለ ከተባለ፤ ቅድም እንዳልኩት ያስገነባቸው ቄንጠኛ የጉባኤ ብቻ ናቸው፡፡ ችግሩ ግን ምን መሠላችሁ?የጉባኤ አዳራሾች የመልካም አስተዳደር ችግርን ሊፈቱ አይችሉም፡፡ እንኳን የጉባኤ አዳራሾች የመንገድ እና የኮንዶሚኒዬም ግንባታዎችም ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄ አይሆኑም፡፡ በጉባኤው ላይ የህወሃት ሊ/መንበር “ልማቱ ሲቀላጠፍ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ይፈታሉ ” በማለት የሰጡት ሃሳብ የተሳሳተ መሆኑን የቀድሞው ምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ መናገራቸው አስደስቶኛል! (አንጋፋ የብአዴን ታጋይና በመተካካት ሥልጣን ያስረከቡ ግንባር ቀደም ባለሥልጣን መሆናቸው እንዳይዘነጋ!)ኢህአዴግ ራሱን “አድርባይ” ብሎ ሲገመግም ምን ሊል እንደፈለገ አልገባኝም ብያችሁ አልነበር ---- ስለዚህ ምን አደረግሁ መሰላችሁ --- “የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል” ያዘጋጀውን መዝገበ ቃላት አንስቼ ፍቺውን ማፈላለግ ጀመርኩላችሁ (ነገርዬው የአገር ጉዳይ ነዋ!) እናላችሁ እንዲህ ይላል- “አድርባይ አደራ ከሚለው ግስ የመጣ ሲሆን አድርባይ ሆነ ማለት ተስማምቶና መስሎ ኖረ ማለት ነው” ቆይ ግን --- የኢህአዴግ አመራር ከማን ጋር ነው ተስማምቶና መስሎ የኖረው? (እንወቀዋ!) ከተቃዋሚዎች? ከህዝብ? ከኪራይ ሰብሳቢዎች? ወይስ ከ”ሽብርተኛ”? (ይሄኔ ነው መሸሽ!) በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ህላዌ ዮሴፍ ደግሞ “የአመራራችን ቁንጮ የሚጠየቅበት አሰራር አለ ወይ?” ሲሉ መጠየቃቸው የመገረምና የመደነቅ ስሜት ነው የፈጠረብኝ፡፡ ኢህአዴግ ከ20 ዓመት በላይ ሲገዛን የተጠያቂነት ሥርዓት እንኳን አልዘረጋም ማለት ነው? (እንዲያ ከሆነ በመጪው ወር ምርጫ ያገናኘን!) ይቺን “አድርባይ” የምትል የፈረደባት ቃል ፍቺ ስፈልግ አዲስ ሃሳብ ብልጭ አይልልኝ መሰላችሁ … ለኢህአዴግ የአማርኛ ቋንቋ መፍቺያ መዝገበ ቃላት ማዘጋጀት!! እውነቴን ነው… የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሳያንሰን ኑሮአችንን የአማርኛ ቋንቋ ፈተና አደረገብን እኮ! ቆይ እስቲ--“የቀለም ” ማለት ምን ማለት ነው? “ተቸካይ” ማለትስ? “ጥገኝነትስ?” “ኪራይ ሰብሳቢስ?” የሰሞኑ “ተራማጅ”የሚል ቃልስ? (ደርግም ተራማጅ መሆኑን ያውጅ ነበር ብዬ እኮ ነው!) አሁን ለምሳሌ ተቃዋሚዎች ፈፅሞ ሊገባቸው ያልቻለ ኢህአዴግ የሚያዘወትረው አንድ አባባል አለው - “ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቤአለሁ” የሚል፡፡ እናላችሁ --- እነዚህንና ሌሎችንም አስቸጋሪ ቃላት ያካተተ መዝገበ ቃላት ለማሰናዳት ስፖንሰር እያፈላለግሁ ነው፡፡ (ምርጥ የቢዝነስ አይዲያ አይመስላችሁም?)አንድ ወዳጅ አለኝ - ተቃዋሚዎችን “ያሳዝኑኛልም ያናድዱኛልም” የሚል (ፈረንጆቹ love - hate relationship የሚሉት ዓይነት መሆኑ መሠለኝ) ይሄ ወዳጄ የኢህአዴግን 9ኛ ጉባኤ እንደ ልብ ሰቃይ ፊልም ቤቱን ቆልፎ በኢቴቪ ሲኮመኩምልኝ ሰነበተና በቀደም ዕለት ስልክ መታልኝ - “ሃሎ” አልኩት፡፡ “እቺ አገር እኮ ዜጐቿን በሁለት ሚዛን ነው የምትሰፍረው!” አለኝ - ተስፋ በቆረጠ የአነጋገር ቃና፡፡ “ምነው… ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?” አልኩት “የኢህአዴግ አድርባይ አመራሮች በተንቆጠቆጠ አዳራሽ ሲሰበሰቡ -- ተቃዋሚዎች አዳራሽ አጥተው በየቤታቸው ይሰበሰባሉ!” (ምህዳሩ ጠቧል ሲባል የት ነበረ?)“ግን እኮ ኢህአዴግም አምኗል!” አልኩት - ዝም ይሻላል ብዬ“ምኑን?” ተገርሞና ተቆጥቶ ጠየቀኝ“የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለበት!”የሚገርም ሳቅ በጆሮዬ እያንቆረቆረልኝ ሳለ ስልኩ ተቋረጠ (እድሜ ለቴሌኮም!)ዝም ብሎ በሸቀ እንጂ ኢህአዴጐችም ቢሆኑ እኮ በአንዴ “ባለ 7 ኮከብ” አዳራሽ ውስጥ አልተንፈላሰሱም፡፡ እስቲ አስቡት… 17 አመት ሙሉ በትግል ላይ ሳሉ የት ነበር ጉባኤያቸውን የሚያካሂዱት? ዛፍ ስር እኮ ነበር (ታሪክ ነው እንዳትሉኝ ብቻ!) ለነገሩ ተቃዋሚዎችም ዛፍ ስር ይሰብሰቡ ቢባል እኮ አያስኬድም (ኢህአዴግ “የትጥቅ ትግል” በኔ ይብቃ ብሏላ!) እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ … በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱ ይመስላችኋል? (የስልጣን ዘመኑ ስንት ነው ካላችሁኝ ግን እንኳን እኔ ባለቤቱም አያውቀውም) እናንተ ግርም ይላል እኮ ---- መልካም አስተዳደር እንደናፈቀን የ22 ዓመት ጐረምሳ አደረስንም አይደል! እግረ መንገዴን አንድ ነገር ጣል ላድርግ፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገመንግስታዊ መብታችንን ኢህአዴግ ሊያረሳሳን የፈለገ ይመስላልና እንደነቃንበት ለምን አንነግረውም? (በእልህ ሳይሆን በፒስ!) ወይ ይፈቀድ ወይ ይከልከል? (እዚህና እዚያ ማጣቀስ አይቻልም!) እርግጠኛ ነኝ--- ኢህአዴግ ህገመንግስቱ ያጎናፀፈንን መብታችንን መልሶ ይሰጠናል (“አድርባይነት”ቢያስቸግረውም 2 ሚ. ብር እየመዥረጠ ለተቃዋሚዎች የሚለግስ “ቸር ፓርቲ” እኮ ነው!)
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment