ግርማ ሞገስ (girma.moges@yahoo.com)
ቅዳሜ ሚያዚያ 6 ቀን 2005 ዓመተ ምህረት (Saturday, April 14, 2013)
ፌዴራል ስም የተሸፈኑ ህውሃት/ኢህአዴጎች እና በአቶ መለስ ራዕይ የተጠመቁ የክልል ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ የዘር ማጥራት (Ethnic Cleansing) ወንጀል ስለመፈጸማቸው መዘገብ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ይኽ ዜና በኢትዮጵያ ወዳጆች ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ዜጎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል። ኢትዮጵያ እንድትበተን የሚፈልጉ ግን አፍና እጃቸውን አስተባብረው ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከመንገዳቸው ላይ ተወግዳ ህልማቸው ወደሆኑት የቃል-ኪዳን አገሮቻቸው (Promised-land) ለመድረስ የጀመሩትን ጉዞ ፍጥነት እና ግልጽነት ሳያመቻቸው ዝቅ ሲያመቻቸው ደግሞ ከፍ ያደርጋሉ እንጂ አያቆሙም። የህውሃት ሕገ መንግስት (አንቀጽ 39) ግፉ በርቱ ይላል። ስለዚህ የቤንሻንጉል ጉምዝ አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ናስር ቀደም ብሎ በቪኦኤ አማርኛ ፕሮግራም ሲጠየቅ አፉን ሞልቶ ሞቅ ባለ ስሜት አማርኛ ተናጋሪውን ያፈናቀልነው መሬቱን ለልማት ስለፈለግነው ነው እንዳላለ ሁሉ ድንገት ተነስቶ ሰሞኑን ይቅርታ መጠየቁ ማጭበርበሪያ ድራማ እንጂ ሃቅ አይደለም። ይኽ ይቅርታ ከራዕይ እና ከፖሊሲ ለውጥ የመነጨ ሳይሆን የተለመደው የህውሃት ማዘናጊያ እና አቅጣጫ ማስቀሪያ ፕሮፖጋንዳ ነው። ለአንድ ደቂቃ እንኳን መዘናጋት የለብንም። ላብራራ።ቅዳሜ ሚያዚያ 6 ቀን 2005 ዓመተ ምህረት (Saturday, April 14, 2013)
በውጭ እና በአገር ቤት ያለው ኢትዮጵያዊ በአንድነት የዲፕሎማሲ ትግሉን ሙቀት ከፍ በማድረጉ ህውሃት ትኩሳቱ ሲፈጀው በተለየም የለጋሽ አገሮች የገንዘብ እርዳታ ሊቋረጥበት እንደሚችል ወለል ብሎ ሲታየው ስለተደናገጠ ቀውስ ለመቆጣጠር የተፈጸመ ትዕይንት ነው ይቅርታው። አለም አቀፍ የዘር ማጥራት ወንጀል እንዲፈጽም ያግባቡት ጌቶቹ ህውሃቶች እራሳቸውን ነፃ ለማውጣት አቶ አህመድ ናስር አደባባይ ወጥቶ ወንጀሉን ወደ ራሱ እና ወደ ወረዳ ሹሞቹ እንዲያስተላልፍ፣ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ የተፈናቀሉት ወደ ቀድሞ ስፍራቸው ይመለሱ ብሎ እንዲናገር አዘዙት። በጌቶቹ የታዘዘውን አቶ አህመድ ናስር ፈጸመ። በቅድሚያ እንደታዘዘው የፌዴራል ባለስጣኖች ከወንጀል ነፃ ለማድረግ ሞከረ። በሁለተኛ ደረጃ እራሱን እና ከወረዳ በላይ ያሉ የክልል ሹሞቹን ለማትረፍ ሞከረ። በቃ ይኼው ነው። ለህውሃት ጠቃሚ ከሆነ ድራማ ያለፈ ምንም ፋይዳ ያለው ነገር አተደረገም። ወንጀል ለተፈጸመበት ህዝብ ካሳ አልተከፈለም። ስህተት ተፈጽሟል ቢባልም የደረሰውን ኪሳራ ተፈናቃዩ ህዝብ እንዲወርስ ነው የተደረገው። ኢትዮጵያ ደሃ አገር በመሆኗ ወደቀድሞ ቦታችሁ ተመለሱ የተባሉት አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከመፈናቀላቸው በፊት የነበሩዋቸውን የቤት እንሰሳት እና ሌሎች ቅርሶች ግማሽ ያህሉን እንኳን መልሰው ሳያፈሩ በድህነት እና በበሽታ ይሞታሉ። የቀሩትም ከስጋት ሳይላቀቁ የቀረ ዘመናቸውን ይጨርሳሉ። በተጨማሪ በቤንሻንጉል ጉምዝም ሆነ በሌሎች ክልሎች ዜናው ላስደነገጣቸው ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዋስትና የሚሰጥ ህግ የፌዴራል መንግስት አላወጀም።
ካለአንዳች ሃፍረት አቶ መለስም ከመሞቱ በፊት አማርኛ ተናጋሪው ከጉራፈርዳ ወደ አገሩ እንዲመለስ የተደረገው አማርኛ ተናጋሪ በመሆኑ ሳይሆን ጫካ እየመነጠረ በማንደዱ ነው ብሏል። አቶ መለስ አማርኛ ተናጋሪው ወደ አገሩ እንዲመለስ ተደረገ ሲል በጭንቅላቱ ውስጥ ጉራፈርዳ ኢትዮጵያ መሆኗ አብቅቷል ማለት ነውን? ደቡብ ህዝቦች ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር የመገንጠል ሂደቱን ፈጽሟል ማለት ነውን? በሌላ ጊዜም በፓርላማ ብቸኛ ተቃዋሚ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ከጅጅጋ፣ ከደቡብ ህዝቦች እና ከቤንሻንጉል ጉምዝ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪው ህዝብ መፈናቀል ጥያቄን በማርላማ ሲያነሱ አቶ መለስ ተፈናቃዮችን ወንጀለኞች የሚያደርግ እንጂ እራሳቸውን (የፌዴራል ባለስልጣኖች) እና የክልል ባለስልጣኖችን ስተተኞች ወይንም ወንጀለኛ የሚያደርግ መልስ እንዳልሰጠ የቪዲዮ መረጃ ማቅረብ ይቻላል። ያም ሆነ ይህ በደቡብ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አቶ አህመድ ናስር፣ ከፈዴደራል አቶ መለስ ዜናዊ እና ምትኩ አቶ ኃለማሪያም ዘር የማጥራት ወንጀል ፈጽመዋል።
በተጨማሪ የጤና ምኒስትር ሳለ ከእንግሊዘኛ ተናጋሪ ለጋሽ አገሮች ጋር ቅርርብ ስለነበረው አቶ መለስ እንደሞተ አቶ ቴዎድሮስ አድሃኖም ቀደም ሲል አቶ ስዩም መስፍን ሲያደርግ እንደነበረው የኢትዮጵያን ሳይሆን የህውሃትን ጥቅም የሚያስቀድም የውጭ ጉዳይ ምንስትር ሆኖ በኢትዮጵያ ላይ መተከሉን እናውቃለን። ይኽ ግለሰብ ዛሬ ኢትዮጵያን ወክሎ በሚሄድባቸው ለጋሽ አገሮች በደቡብ ኢትዮጵያ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ስለተፈጸመው ዘር የማጥፋት ወንጀል ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ህውሃትን ከወንጀለኛነት ለማትረፍ በኢትዮጵያ የዘር-ማጥፋት ወንጀል አልተፈጸመም ማለት ከጀመረ ውሎ አድሯል።
እነዚህ ስማቸው የተጠቀሱት እና ሌሎች ወንጀለኞች በአለም አቀፍ እና ወደፊት የህዝብ መንግስት ሲመሰረት በአገር ቤት ከሚመሰረትባቸው ክስ በተጨማሪ ለጉብኝትም ሆነ ለስራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ የሚያስገባ ቪዛ እንዳያገኙ እና በውጭ ያስቀመጡት ሃብት እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ትግል ከግብ እስኪደርስ ድረስ ተጠናክሮ ሽቅብ እንዲጓዝ መደረግ አለበት። ከመረጃ እጥረት ይልቅ የመረጃ መብዛት ስለሚመረጥ መረጃ የማሰባሰብ ጥረትም እንደዚያው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ይኽን ጉዳይ አስመልክቶ በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በአውሮፓ የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ቁልፍ ናቸው። የሰላማዊ ሰልፈኛው ቁጥር ከፍ ማለት ደግሞ ተደማጭነትን እና ተጽዕኖን ከፍ ያደርጋል።
በአንድ አገር በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ላይ ዘር የማጽዳት ወንጀል (Ethnic Cleansing) መፈጸም ከተጀመረ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪም መጪ እጣ ምን እንደሆነ በየግድግዳው ላይ ተጽፎለታል ማለት ነው። በየግድግዳው ላይ የተጻፈለትን ማንበብ የቻለ ፈጠን ብሎ አካባቢውን መልቀቅ ማሰቡ አይቀርም። ምናልባትም ተወልዶ ያደገበትን ወይንም ለረጅም ጊዜ የኖረበትን የሚወደውን ቀየውን ለቆ ወደ ቀድሞ ዘመዶቹ ትውልድ ስፍራ መሄድን አሊያም ሌሎች እንዳደረጉት ወደ አረብ አገሮች ወይንም ወደ ምዕራቡ ዓለም ለመሰደድ ማውጣት ማውረድ ይጀምራል። የቀረው ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ደግሞ ጊዜው ሲደርስ (ለህውሃት ሁኔታው የተሟላ ሲመስለው ማለት ነው) ቀደም ሲል በሌላ ላይ የተፈጸመው የዘር-ማጥራት ወንጀል ይፈጸምበታል። ያም ሆነ ይኽ በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ላይ የተጀመረው የዘር ማጥራት ወንጀል የዜጎችን ኑሮ ቀጣይነት ያናጋል። ዜጎች እንደቀድሞው ባሉበት አካባቢ ተስፋ አይኖራቸውም። ልማት እና እድገትን ይቆማል። ለምሳሌ በቤንሻንጉል ጉምዝ እና በጎረቤቱ አማራ ህዝብ መካከል መቃቃር እየፈጠርክ እንዴት አድርገህ ነው በህዝብ ትብብር የአባይን ግድብ በቤንሻንጉል እየገነባሁ ነው የምትለኝ!? ባጭሩ የአቶ መለስ ራዕይ አብሮት እንዲቀበር ካልተደረገ በኢትዮጵያ ሁሉም በያለበት በተራ የዘር-ማጽዳት ወንጀልን እንደጽዋ መጎንጨቱ አይቀሬ ነው። ምርጫ 97ን ተከትሎ ድምጽ ይከበር የሚል ጥያቄ በተነሳበት ወቅት ይመስለኛል በአገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ከሚጫወተው እጅግ ጠቃሚ የፖለቲካ ሚና ባሻገር ቀልዱም የሚጥመኝን አቶ ጉዲናን አንድ ጋዜጠኛ “ለምን ድርጅትህ (ኦብኮ) ፈረሰ?” ብሎ ሲጠይቀው “የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ህውሃት/ኢህአዴግ የሁልሽንም በር ያንኳኳል” ማለቱ በወቅቱ ቢያስቀኝም ሃቁን የገለጸበት አባባል ግን እስከዛሬ ድረስ ከአዕምሮዬ አለ። በቃ እንደዚያ ማለት ነው። ዛሬ በጅጅጋ፣ በደቡብ ህዝቦች እና ቤንሻንጉል ጉምዝ በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ላይ የተጀመረው ዘር የማጥራት ወንጀል ነገ የሌሎችን በር ያንኳኳል። የሚገርመው ግን ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠር አባቱ አሜሪካዊ እናቱ ፊሊፒኖ ወይንም ኢትዮጵያዊት የሆነ አለም-አቀፋዊ የሰው ዘር እየተፈጠረ ባለበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ይኽን አይነት የዘር ማጥራት ወንጀል መፈጠሩ ነው። ስለሆነም ይኽ ዘር የማጥራት ወንጀል ፍጹም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።
የህውሃት/ኢህአዴግን የቅርታ ጥያቄ ድራማ ወደጎን በመተው በሰላማዊ ትግል የህውሃት/ኢህአዴግ መንግስት በህዝብ መንግስት እንዲተካ ማድረግ ላይ ማትኮር አለብን። በሰበብ አስባቡ የህውሃት/ኢህአዴግ የስልጣን ዘመን በተራዘመ ቁጥር አደጋው ይበልጥ እየገዘፈ እና ውስብስብ እየሆነ ይሄዳል እንጂ እያቆለቆለ እና እየቀለለ አይሄድም። እሬሳው በመታሰቢያ ተቋም (ፈውንዴሽን) ተቀምጦ ራዕዩ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ እና እንዲሰርጽ እናደርጋለን የሚለው የኢትዮጵያ መንግስት ወቅታዊ መዝሙርም የሚያሳየው ይኽ አደጋ ወደፊት ሊገዝፍ እና ሊወሳሰብ እንደሚችል እንጂ እየቀለለ መሄዱን አይደለም።
በመንግስት አዋጅ የተቋቋመው እና በመከላከያ ሚኒስቴር ጀነራል ሳሞራ የኑስ፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር አቶ ሱፊያን አህመድ፣ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ በፌዴሬሽን ም/ቤት አቶ ካሳ ተ/ብርሃን፣ በደቡብ ህዝቦች አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ በኦህዴድ ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ በህውሃት በአቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ በሶማሌ ክልል አስተዳዳሪ በአቶ አብዱ ዑመር መሐመድ እእና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አስተዳዳሪ በአቶ አህመድ ናስር የቦርድ አባልነት የሚመራው የአቶ መለስ መታሰቢያ ተቋም (ፋውንዴሽን) በሚቀጥለው ጽሑፍ በሰፊው ይተነትናል።
No comments:
Post a Comment