Pages

May 11, 2013

ሠማያዊ ፓርቲና የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪው

SOURCE: ADDIS ADMAS

Saturday, 11 May 2013 11:37
ሠማያዊ ፓርቲና የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪው
Written by ናፍቆት ዮሴፍ

ሰማያዊ ፓርቲ ሠሞኑን በሠጠው መግለጫ፤ ከግንቦት 17 ጀምሮ መንግስት አልመለሳቸውም ባላቸው አራት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሠላማዊ ሠልፍ እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡ ሠልፉ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል በሚካሄድበት ጊዜና ቦታ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በተጠራው ሠላማዊ ሠልፍና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ከአቶ ይልቃል ጌትነት ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ ሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ መብት ቢሆንም እስከዛሬ እየተጠሩ ሳይካሄዱ የቀሩ ሠልፎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በቅርቡም ከግራዚያኒ ሀውልት መቆም ጋር ተያይዞ ያደረጋችሁት የተቃውሞ ሰልፍ አልተሳካም፡፡ እንደውም የሰልፉ መሪዎች ታስረው ነበር፡፡ አሁንስ የሚሳካላችሁ ይመስላችኋል? እንግዲህ እኛ ትግል ሥናደርግ መሠረታዊ መነሻችን መርሁ ነው፡፡ ሁለተኛ ህጉ ነው። በእነዚህ ሁለት ነገሮች ነው የምንመራው።

በሌላ በኩል ሠው በመሆናችን መሠረታዊ መብት አለን። ሀሣባችንን በነፃነት የመግለፅ መብታችንም በህጉ ተደንግጓል፡፡ ሥለዚህ ህገ-ወጦች የሚያደርጉትን ማስፈራራትና ዛቻ አይተን መብታችንን ከመጠየቅ ወደ ኋላ አንልም፡፡ ወደ ፖለቲካ ትግል የገባንበት ዋናው ነገር፣ ህገ ወጥ አሠራርን በመንቀፍና በመቃወም ህጋዊ ስርዓት እንዲመጣ ህዝብን እየመራን ለመታገል ነው፤ አላማችንም ይሄው ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ህገ-ወጥ ነገር ሲያደርግ ያንን ታግለን መቀየር እንጂ እሱ ስለማይፈቅድ ብለን መብታችንን አሣልፈን መስጠት የለብንም፡፡ እንደውም አለመፍቀዱ ነው የበለጠ እንድንታገል የሚያነሣሣን፡፡ ኢህአዴግ የሚሰራውን ህገ ወጥ ድርጊት በመታገል ህጋዊ አሠራር ለማስፈን እንጥራለን፡፡ ኢትዮጵያ የታሪክ፣ የነፃነት ተምሣሌት የሆነ፣ መንግስት የነበራት አገር እንደመሆኗ፤ እንዲህ አይነቱን ችግር በዚህ ጊዜና ዘመን ማስተናገድ እጅግ ነውር ስለሆነ ይህን ለማስተካከል ነው እንደ አማራጭ ሀይል ተደራጅተን ትግል የጀመርነው፡፡

ስለዚህ ምንም ጥርጥር የለውም እናደርገዋለን፡፡ እንደባለፈው አይነት እስርና መስተጓጐል አይገጥመን ብላችሁ ታስባላችሁ?

እኛ እንግዲህ እሱን አናውቅም፡፡ እኛ መብታችን ነው፤ ኢህአዴግ ወንበዴ ሆኖ ካሠረን ግን አንቺም መጠየቅ ያለብሽ እሱን ነው፡፡ እኔን መጠየቅ ያለብሽ ህገ-ወጥ ናችሁ ካልሽ ብቻ ነው፡፡ እኔ ህጋዊ ከሆንኩና የምጠይቀውም መብቴን ከሆነ፣ ያንን ህግ የሚጥሠውንና የህዝብን ሥልጣን ይዞ ያለአግባብ ሌላውን የሚበድለውን አካል ነው “ለምን እንዲህ ታደርጋለህ” ብለሽ መጠየቅ ያለብሽ፡፡ እኔ የሚገርመኝ ሚዲያዎች ለምን እንዲህ ዓይነት ጥያቄ እንደምትጠይቁን ነው፡፡ ምክንያቱም መብታችን እንደሆነ ታውቃላችሁ። ነገር ግን ለኢህአዴግ ጉልበተኝነት መብት ሠጥታችሁታል፡፡ ጥያቄዬን ግልፅ ላድርግልዎት፣ መብት የላችሁም ማድረግ አትችሉም እያልኩ አይደለም፤ ነገር ግን በቅርቡ የጠራችሁት ሠላማዊ ሠልፍ ተበትኗል፤ እናንተም ታስራችሁ ነበር፡፡

አሁንስ ከዚያ የተለየ በምን መልክ ልታካሂዱት አስባችኋል ማለቴ ነው…? እኔ እነዚህ ነገሮች የሚፈቱት በትግል ነው ባይ ነኝ፡፡ አንድ አምባገነን ፈቅዶ የሚሠጠው መብት አለ ብዬ አላስብም፡፡ በአለምም ታሪክ አምባገነን ለዜጐች ዴሞክራሲን ወዶና ፈቅዶ ሠጥቶ አያውቅም፡፡ ህዝብ በታሪኩ ለዘላለም ተሸንፎ የቀረበት አጋጣሚ የለም፡፡ ነገር ግን ይህ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ የተከለከሉ መብቶቻችንን ማረጋገጥ የምንችለው በትግል ነው፡፡ መብታችንን ማስከበር የምንችለው ትግሉን አጠንክረን ስንቀጥል እንጂ እጅ አጣጥፈን በመቀመጥ አይደለም፡፡ ለሠላማዊ ሠልፉ መነሻ ያደረጋችኋቸው አራት ነጥቦች የቆዩ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ሠልፉን ከአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር ጋር ያደረጋችሁበት ምክንያት ምንድን ነው? ቀኑን ለምን መረጣችሁት?

ይህን የበዓል አከባበር የመረጥንበት ዋናው ነገር ወቅቱ ዓለም በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ የሚያይበት ስለሆነ ነው፡፡ ያኔ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሚዲያዎች ለጉዳዩ ትኩረት የሚሠጡበት በመሆኑ እኛም በዚህን ወቅት ሠላማዊ ሠልፍ ማድረጋችን ድምፃችን ጐልቶና ከፍ ብሎ እንዲሠማልን ለማድረግ ብለን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የተለመደ ነው፡፡ በሌላውም ዓለም ትላልቅ ሥብሠባዎች በሚካሄዱበት ጊዜ እንዲሁ ድምፃቸውን ለማሰማት ሠልፍ ያደርጋሉ፡፡ ትኩረት ለመሣብ ነው? አቴንሽን ለመሣብ አይደለም (በቁጣ) ድምፅ ለማግኘት ነው፡፡ ትኩረት ለመሣብ የሚለው ቃል የእኛን ሀሣብ ያዛባዋል፡፡ ሠላማዊ ሠልፍ እንዳልኩሽ መብታችን ነው፡፡ ይሄንን መብታችንን ከህዝብ የምንጋራበትና ውጤታማ የምንሆንበት ጊዜ ነው፡፡ ለምሣሌ ኤርትራዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላማዊ ሠልፍ ያደርጋሉ፤ የተለያዩ ስብሠባዎች በሚካሄዱበት ወቅት፡፡ የመንግስት ሚዲያም ለጉዳዩ ሽፋን ይሠጣል፡፡ ይሄ መንግስት ለኤርትራውያን ሠልፍ ከፈቀደና፣ ግብር ከፋይ ለሆኑት ኢትዮጵያዊያንና በህጋዊ መንገድ እውቅና ለተሠጠን ፓርቲዎች የማይፈቅድ ከሆነ፣ ከኢትዮጵያዊያን በላይ ለኤርትራዊያን ይጨነቃል ያዳላል ማለት ነው፡፡ ሠላማዊ ሠልፉ የተጠራባቸው የኑሮ ውድነት፣ መፈናቀል፣ እስራትና የሀይማኖት ጉዳዮች የኢትዮጵያን መንግስት የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ለአፍሪካ ህብረት ተሠብሣቢዎች መናገሩ ለምን አስፈለገ? የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በተጨማሪም ሠማያዊ ፓርቲ አዲስ እንደመሆኑ በዚህ አጋጣሚ ራሱን ፕሮሞት ለማድረግ ሥለፈለገ እንጂ ሠላማዊ ሠልፉ ይሳካልኛል ብሎ አይደለም ይባላል፡፡

የእርስዎ ምላሽ ምንድነው? በመሠረቱ አስተያየት መስጠት መብት ነው፡፡ በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና ስራዎች ሠዎች አስተያየት መስጠት፣ መተቸት መብታቸው ነው፡፡ በዚህ ተቃውሞ የለኝም። ነገር ግን ፓርቲው ራሱን ለማስተዋወቅ ነው የሚለውን አልቀበልም፡፡ ምክንያቱም እስካሁን በአገሪቱ ውስጥም ሆነ በአለም ላይ ስለ ሠማያዊ ፓርቲ ያልዘገበ የለም፡፡ ሠማያዊ ፓርቲ፤ በዚህ አስቸጋሪና የፖለቲካ ደብዛው በጠፋበት ጊዜ መጥቶ፣ በዓለም አቀፍ ማህበረሠብም ሆነ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ አንድ የፖለቲካ ሀይል ሆኖ በመውጣት በኩል የተሣካለት ፓርቲ ነው፡፡ ራስን ለማስተዋወቅ የሠላማዊ ሠልፍን ስልት አንጠቀምም፡፡ ምክንያቱም ከበቂ በላይ የታወቅን ፓርቲ ነን፡፡ አሁን ጐግል ውስጥ ገብተሽ ሠማያዊ ፓርቲ ብትይ ታገኝናለሽ፡፡ እኛ ከምንለውም በላይ የታወቀ ፓርቲ ነው፡፡ ታወቅን የምትሉበት ምክንያት ምንድን ነው? ስለ ሠራን ይመስለኛል፡፡ ፖለቲካ ማለት የመርህ ትንተና ማለት አይደለም፡፡

አካዳሚ ስራም አይደለም፡፡ ለተጨባጭ ችግሮች ተጨባጭ መፍትሄ ማምጣት ነው፡፡ ስለዚህ ሠማያዊ ፓርቲ በአደረጃጀቱም በአመራር ብቃት፣ የህዝብ አጀንዳዎች ይዞ በመነሣት በኩል ያለው ተሠሚነትም ለትግሉ ያለውን ቆራጥነት የሚያሣይ ነው፡፡ ጉዳዩ የመንግስት ነው፤ በአፍሪካ ህብረት የስብሰባ ቀን ለምን ለተባለው እስከዛሬ የመንግስት ጉዳይ ነው ብለን ችግሮቹ እንዲስተካከሉ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሽ አልተገኘም። አሁንም የኑሮ ውድነት አለ፣ አሁንም ዜጐች ይፈናቀላሉ፡፡ አሁንም ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት ስም ወህኒ ነው ያሉት፣ አሁን መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ ገብነት የሀይማኖት ሥርዓታችን ይከበር ባሉት ሙስሊሞች ላይ እስርና እንግልቱን አላቆመም፡፡ ስለዚህ በህብረቱ በኩል ጫና ለመፍጠርና ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ ለማፈላለግ ነው ሠልፉ ከህብረቱ 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር ጋር እንዲገናኝ ያደረግንበት ምክንያት፡፡ ሠልፉ ተፈቀደና ተሣካ እንበል፡፡ ከዚያም የታሣሪ ቤተሠብ አለ፣ የሀይማኖቱ፣ የመፈናቀሉ፣ እንዲሁም የኑሮ ውድነቱ አንገፍግፎኛል የሚል ህዝብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ አገሩን ቢያጥለቀልቅ ሀላፊነቱን ትወስዳላችሁ፣ በምንስ ነው የምትቆጣጠሩት? የእኛ ፍላጐት ከላይ አንቺ እንደ ስጋት ያነሣሽው ነገር እንዲከሠትና ህዝቡ ግልብጥ ብሎ እንዲወጣ ነው የምንፈልገው፡፡

ህዝቡ ግልብጥ ብሎ ሲወጣ ደግሞ ይህንን የሚያረጋጋ ደሞዝ የሚከፈለው ደህንነትና ፖሊስ አለ። መጨረሻ ላይ ሠልፍ ልናካሂድ እንደሆነ ለሚመለከተው አካል የምናሣውቀው እኮ ይሄንን ነገር ጠብቆ ዝግጅት እንዲያደርግ ነው፡፡ ደሞዝ የሚከፈለው የፖሊስ ተቋም ዋናው ሥራው ከቁጥጥር ውጭ የሆኑና ያልተገቡ ነገሮች በግብር ከፋዩ ህዝብ ላይ እንዳፈፀም ነው፡፡ ሠላማዊ ሠልፍ እኮ መብት ነው፡፡ እኛም ለመንግስት አካል የምናሣውቀው በሠልፉ ጊዜ አላግባብ የሆነ አመፅና ሁከት የሚፈጥር ሠው ቢኖር ያንን ለይቶ ሥርዓት የሚያሲዝ እንዲመደብ ነው፡፡ ይሄ የመንግስት ግዴታ እንጂ የሠማያዊ ፓርቲ አይደለም፡፡ አሁን እናንተ ለሚመለከተው አካል አሳውቃችኋል? ማዘጋጃ ቤት ውስጥ የሚገኝ አንድ ቢሮ አለ፤ እንዲያውቀው የሚደረገው ሠልፉ ከመካሄዱ ከ48 ሠዓት በፊት ነው፤ እኛም ጊዜው ሲደርስ ግንቦት 15 አካባቢ እናሣውቃለን፡፡ አሁን ትኩረት ያደረግነው ለህዝቡ በስፋት የማስተዋወቅ የህዝብ ግንኙነት ሥራ ላይ ነው፡፡ ከሠልፉ ምን ትጠብቃላችሁ? ሠልፈኛው ጥቁር እንዲለብስ የፈለጋችሁበት ምክንያት ምንድነው? ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ የሠልፉ አላማ መንግስትን በተደጋጋሚ የጠየቅነው ነገሮች ነበሩ።

በመግለጫው ላይ እንዳመለከትነውም ችግሮቹ ዛሬ የተፈጠሩ አይደሉም፣ በተደጋጋሚ በግልጽ ደብዳቤ ጠይቀናል፣ አቋም ወስደንም በመግለጫ አውጥተናል፡፡ ነገር ግን መንግስት እኛን ከማጥላላት፣ ከማንኳሰስና ጆሮ ዳባ ልበስ ከማለት ውጭ መልስ አልሰጠም፡፡ ስለዚህ አሁንም አላማችን ጥያቄዎቻችን ጆሮ አግኝተው መፍትሔ እንዲሰጥ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የስራ አጡ ቁጥር የትየለሌ ነው፣ ኑሮ ውድነቱ አላፈናፍን ብሏል፣ ሙስና ተቋማዊ ሆኗል፣ ጋዜጠኞች እስር ቤት ናቸው፣ የሃይማኖት ጥያቄ የጠየቁ ሰዎች እስር ቤት ናቸው፤ መፈናቀሉን አሁንም አልቆመም፡፡ “ይህን ሁሉ ነገር መልክ አስይዝ” ነው የምንለው፡፡ ምክንያቱም መንግስት ግዴታ አለበት፡፡ ይህን እስኪመልስ አሁንም ግፊታችን ይቀጥላል፡፡ ሠላማዊ ሰልፉ የግፊቱ አንድ አካል ነው፡፡ ህዝቡ ግብር የሚከፍለው መንግስትም የህዝብን ስልጣን የያዘው እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ እኮ ነው፡፡ ይህንን ካላደረገ የማንን ጐፈሬ ሊያበጥር ነው፡፡ ስለዚህ “እባክህ ስማን” ነው እያልን ያለነው። መቼም ሟርት አይደለም፤ ግን ሠላማዊ ሰልፉ እንደከዚህ በቀደሙ ቢከለከል ምን ታደርጋላችሁ? እኔ አሁን ስለመከልከሉ አላስብም፡፡ መብቴ ስለሆነ ሰልፉ ይካሄዳል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ የእስከዛሬው የተከለከለው መብታችሁ ስላልሆነ ነው እንዴ? እንደሱ ማለት ሳይሆን ያንን አደረጉት ራሱ መንግስት ይወቀስበታል፡፡ ነገር ግን ገና ለገና እንከለከላለን እያልን እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም፡፡ እንደባለፈው መታሰር ቢመጣስ ለዚያ ዝግጁ ናችሁ? ያንን እነሱ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ይሠሩን፣ ይግደሉን፣ ወይም ከዚህ የተለየ ነገር ያድርጉ፤ ህገ-ወጥ ስለሆነ፣ በቃ ህገ-ወጥ ድርጊት ነው፡፡

ለምሣሌ አንቺ ሠላማዊ ሰው ነሽ፤ ከዚህ ስትወጪ ማጅራት መቼ ቢያገኝሽ ምን ትያለሽ? አንቺ መብት ያለሽ ዜጋ መሆንሽን በሠላም ወጥተሽ መግባት መብትሽ እንደሆነ ነው የምታምኚው፡፡ ነገር ግን እኔ ህጋዊ ስለሆንኩ ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ መብቴ እንደሆነ እኔ ብቻ ሳልሆን እናንተ ጋዜጠኞችም ታውቃላችሁ፤ ስለዚህ እኔ ህጋዊ መሆኔን እንጂ ህገ-ወጦች ስለሚሠሩት ላውቅ አልችልም። እኔ የማውቀው የተፈቀደውን እና ህጋዊውን እንጂ በህገ-ወጥና በውንብድና የሚደረገውን አላውቀውም፡፡ ሠማያዊ ፓርቲን ያፍርሰው፣ ሰብስቦ አመራሩን ይሰረው፣ እንደተለመደው ሌላ አይነት ፋይል ያዘጋጅ፤ ያ የእርሱ ፋንታ ነው፡፡ እንደተለመደው ሌላ አይነት ፋይል ያዘጋጅ ሲሉ ምን ማለትዎት ነው? ጓደኞቻችን ሽብርተኛ ተብለው በየእስር ቤቱ አይደለም እንዴ ያሉት! ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ማለቴ ነው፡፡ ለምሣሌ እነ አንዷለም አራጌና ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ የቅርብ ጓደኞቼ ናቸው፤ እስር ቤት እንዳሉ ታውቂያለሽ፤ የሽብርተኝነት ፋይል ተዘጋጅቶላቸው አይደለም እንዴ? እና እንዲህ ያለው ነገር ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። ነገር ግን ይህ እንዲለወጥ ነው ትግላችን፡፡ በሠላማዊ ሠልፉ ላይ ጥቁር ስለመልበስ ጠይቀሽኝ ነበር፡፡ ችግራችንን ሀዘናችንን፣ ያለንበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማመልከት ነው ጥቁር እንዲለበስ ያስፈለገው፡፡ ከአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ጋር አስታካችሁ ሠልፉን መጥራታችሁ ክብረ በዓሉን አይረብሽም ትላላችሁ? በምንም መንገድ አይገናኝም፡፡

ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ አንቺም እንደምታውቂው ይህ አይነቱ ብሶትን የማሰማት አሰራር በትላልቅ ስብሰባና ኮንፈረንሶች ላይ ይደረጋል፤ በአለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ ነው፡፡ ስለዚህ ሰላማዊ ሠልፉ ስብሰባውን ይረብሻል የሚለው ፍፁም የማይገናኝ ነገር ነው፡፡ ፓርቲው ራሱን ለማስተዋወቅ ሠላማዊ ሠልፍ አይጠራም፣ በሠራቸው ሥራዎች በአገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ታውቋል ብለዋል፡፡ እስቲ በዚህ አንድ አመት ውስጥ ምን ምን እንደሠራችሁ ይንገሩኝ…? እንግዲህ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ለመንግስት የአሠራር አቅጣጫ ነድፎ አይሰጥም። ሊያደርግ የሚችለው ፖሊሲውንና ፕሮግራሙን ለህዝብ ማስተዋወቅ፣ ድርጅታዊ ጥንካሬውን መፍጠር፣ አማራጭ ሀይል ሊሆን እንደሚችል ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ለሲቪክ ማህበረሰቡና ለሌሎች ቡድኖች ማሳወቅ፣ ፓርቲው አመራር መቀበል የሚችል አቅም ያለውና የኢትዮጵያን ችግሮች ሊፈታ የሚችል መሆኑን፣ በአሠራርም በአደረጃጀትም ሆነ በፖሊሲ ደረጃ ከአንድ ተቃዋሚ የሚጠበቀውን በማድረግ ረገድ ፓርቲው ከሚገባው በላይ ከፍተኛ ሥራ ሰርቷል። በተለያዩ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ የተለያዩ ውይይቶችን በቢሮው አድርጓል፡፡ ወሳኝ የሆኑ አገራዊ ጥያቄዎችን ይዞ ወደ ህዝብ ወጥቷል። ስለዚህ በእኔ እምነት እንደ አንድ ተቃዋሚና ስልጣን ያልያዘ ፓርቲ የምንችለውን ሁሉ ሠርተናል ብዬ ነው የማምነው፡፡ አዲስ እንደመሆናችሁ ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? በጣም ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ በተለያዩ ፓርቲዎች ያሉ ሰዎችንም እናውቃቸዋለን።

አብረናቸው ስንሰራም ነበር፡፡ ለምሣሌ የ33ቱ ፓርቲዎች ውስጥ አለንበት፡፡ ባለፈው ለሁለተኛ ጊዜ የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረምን በኋላ የመጀመሪያውን አብይ ኮሚቴው ስብሰባ ሲያደርግ በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ውስጥ ነበር፡፡ በአብይ ኮሚቴው በምክትል ፀሐፊነት የሚሠራው የፓርቲያችን ምክትል ሊቀመንበር ነው፡፡ ከአንድነትም ሆነ ከመኢአዶች ጋር መልካም ግንኙነት ነው ያለን፡፡ አሉ ከሚባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብረን እየሠራን ነው፡፡ በመጨረሻ የሚሉት ነገር ካለ …? እንግዲህ ሰልፉ እንደስሙ ሠላማዊ መሆኑን ደጋግመን ገልፀናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ሥራ ሃሳብ አመንጭቶ ስትራቴጂ ነድፎ ህዝቡን መምራት ነው፡፡ አንደበቱ ሚዲያ ሲሆን ጉልበቱ ህዝብ ነው፡፡ ውጤት እንዲመጣ ከተፈለገ ከላይ የተጠቀሱት ሶስት ነገሮች መተሳሰር መቻል አለባቸው፡፡ ሚዲያ አንደበት ነው፣ ፓርቲ አዕምሮና መሪ ነው፣ ህዝብ ጉልበት ነው፡፡

ይዘን የተነሳነው የህዝብ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ የግል ጥያቄ የለኝም ወይም ሰማያዊ የተለየ ጥያቄ የለውም፡፡ ነገር ግን የዚህ አገር ችግር የህዝብ ችግር ነው፡፡ ጥያቄውን ይዘን መጥተናል፤ ወደ ውጤት የምንመጣው በህዝብ ተሳትፎ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የኢህአዴግ አባላትን ጨምሮ ሁሉም በኑሮ ውድነት ውስጥ ነው፡፡ የተለየ ጥቅም የሚያገኙና ባለስልጣናት ካልሆኑ በስተቀር የኢህአዴግም አባል ሆኖ ብዙ የተቸገረ ሰው እንዳለ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ይመለከተናል የሚሉ ሁሉ በሰልፉ ተሣታፊ እንዲሆኑ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate