Pages

May 15, 2013

ዱላ መመከት ያቃተው አማራ (ይኸነው አንተሁነኝ)


ግንቦት 14 2013
ሕወሃት ሀገራችንን በገልበቱ መግዛት ከጀመረበት ግንቦት 1983 ዓ/ም ጀምሮ ለቁጥር የሚያታክቱ ለመስማት የሚያስጨንቁ ብዙ ቁም ስቅሎችን ፈጽሟል። የራሱን የሕወሃትን ፓርላማ አንቀጽ 39ን በመመርኮዝ ራስን የመቻል ጥያቄ አቅርባችሗል ወይም ልታቀርቡ አስባችሗል በሚል ሰበብ ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ የስቃይ ዘመናትን አሳልፏል። ከእኛ ጋር አልተባበራችሁም ሁሌ ትወጉናላችሁ እየተባሉ ያለቁት የኦጋዴን ህዝቦች የትየለሌ ናቸው። በጥቅሉ  የልማት እቅዳችንን ትቃወማላችሁ፣ እኛን እንደ መንግስት አልተቀበላችሁንም፤ የምንላችሁን ለመፈጸም ዝግጁነት ይጎድላችሗል፤ ታሪካችንን የኢትዮጵያ ታሪክ ለማድረግ በምናደርገው ጉዞ መሰናክል እየሆናችሁብን ነው በሚሉና በሌሎችም ምክንያቶች በመላ ሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ሊባል በሚችል መልኩ ሕወሃት ሰቆቃዎችን ፈጽሟል።
በተለይ ከሁሉም በለይ ሕወሃት ለያዘው የመከፋፈልና ሀገር የማጥፋት እንቅስቃሴ በተቃራኒው በመቆም፣ ስለ አንድነት በመስበክና ለዚህም በጽናት በመታገል ችግር ፈጥሯል በማለት ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት ጀምሮ የፈረጀውን አማራውን ባጠቃላይ ከጫወታ ውጭ ለማድረግ ወይም አማራው አቋሙን ቀይሮ ሕወሃት ባሰመረው መስመር ገብቶ እንዲጓዝ ለማስገደድ ወያኔ ሕወሃት በዙ ስቃዮችን በአማራው ላይ በመፈጸም ላይ ነው። ምንም እንኳ ሕወሃት ዋናዎቹን ሁለቱን የእምነት ተቋማት የኦርቶዶክስ ተወህዶ ክርስትናንና የእስልምናን ተከታዮች ያለ ርህራሄ ያጠቃ ቢሆንም በተለይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እየደረሰባት ያለው መጎሳቆል የአማራው መሸሸጊያ ዋሻ በሚል መሆኑ ሲታወስ ወያኔ ሕወሃት አማራውን ከሁሉም አቅጣጫ ለመመንጠር ምን ያህል እንደተዘጋጀና እየተገበረው መሆኑን ያሳያል።
ገና ወያኔ ስልጣን በያዘ ማግስት፤ በተለይ በአማራው ለይ የተፈጸመው የአርባ ጉጉና የበደኖ ጭፍጨፋ አንገብግቧቸው ጥያቄ ያነሱትና በሗላም የአማራው ድምጽ እንዲሰማ የፖለቲካ ድርጅት በማቋቋም አንቱ የሚያስብል ስራ የሰሩት እውቁ የህክምና ባለሙያ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፤ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ያለ አድሎ ሲሰጡት የነበረውን የህክምና አገልግሎት እሳቸው እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ባስፈለጋቸው ጊዜ በሕወሃት እንዳያገኙ ተነፍጓቸው የሞቱት ከአማራነታቸው በቀር ምን ምክንያት ሊሰጠው ይችላል።
ትምክህተኛና ነፍጠኛ የሚባሉ ቃላትን ከአማራው ሕዝብ ጋር በማያያዝ አማራው ለሚያቀርባቸው የመብት ጥያቄዎች ይህ የትምክህተኞች አመለካከት ነው። ወይም ደግሞ ነፍጠኛነት ነው በማለት ወያኔ ሕወሃት ቁጥራቸው የበዛ አማራዎችን መቷል አሳዷል የማሸማቀቅ ተስፋ የማስቆረጥና የተነገረውን ብቻ እንዲፈጽም የማስገደድ ከፍተኛ በደልም ሲፈጽም ቆይቷል።
የ1993ቱን የሕወሃት መሰንጠቅ ተከትሎ በወናነት ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር ሂደት ስጋቶቼ ናቸው፤ የስኬት መንገዶቻቸውንም ለሌሎች አማሮች ያሰለጥናሉ ያላቸውን ቱጃር ቱጃር አማሮች በሙስናና የዚህ ወያም የዚያ ደጋፊ በሚል ሰንካላ ምክንያት ከሶና ወህኒ አውርዶ ከጫወታ ውጭ ማድረጉ ሲታወስ ሕወሃት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣተር አማራውን ከዚህ የስራ ዘርፍ ማስወጣት ቀዳሚው መሆኑን በመገንዘብ መሆኑ አሌ ሊባል አይችልም። ይህ ስቃይ የደረሰባቸው ነጋዴዎችም ቢሆኑ አማራነታቸው ካልሆነ በቀር ሙስና የተባለው በሙሉ ሕወሃት ሲከወን የቆየ በመሆኑ እነሱ ብቻ ሊወነጀሉ ባልቻሉም ነበር። ላለፉት ሁለት አመታት ሳይቋርጥ የቀጠለው በጉራ ፈርዳ የሚኖሩ አማራ ገበሬዎችን ከኢኮኖሚ ይዞታቸው የማፈናቀል ሂደት ሳይቀዘቅዝ፤ በቤኒሻንጉል ክልል የሚኖረውን አማራ ገበሬ የማፈናቀሉ ሂደት በተመሳሳይ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ  ደን በማቃጠል ሰበብ በወያኔ ሹመኞች በስፋትና በተደራጀ መልኩ መቀጠሉ፤ የሕወሃት የማጣሪያ ወንፊት አማራውን ከየትኛውም የኢኮኖሚ ዘርፍ ለማስወጣትና ጥገኛ እንዲሆን ለማድረግ በተለይ ለአማራው ብቻ በልኩ የተሰራ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።
የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ ከመጣው መተረማመስ ጋር በተያያዘ የወያኔን ጦር ሰራዊት ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎችና በየትኛውም ምስሪያ ቤት ቅንጅትን ምክንያት በማድረግ ማሰጠንቀቂያ የደረሳቸው፣ ከስራ የተባረሩት፣ የታሰሩትና የተሳደዱት በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ አማራነታቸው ያመጣባቸው ጣጣ እንጂ ሌላ ምንም አልነበረም።
አማራው በልማት ከሌላውም የኢትኦጵያ ክልል  በከፋ ሁኔታ ላይ ያለ መሆኑ እየታወቀ ወያኔ ሕወሃት ግን በልማት ወደ ሗላ የቀሩና በጦርነት የተጎዱ በሚሉ ምክንያቶች አማራውን በማስወገድ አድሏዊ የእርዳታና በጀት ፍሰት ሲያከናውን መቆየቱ። ከዚህም በከፋ መልኩ ወያኔ በግል ፓርላማው አማካኝነት ለአማራው የሚመድበውን በጀት ለመቀነስ በማሰብ ባለፈው ሀገራዊ የሕዝብ ቆጠራ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማራዎች ሳይጠፉ ሆን ተብሎ እንዲተፉ ማድረጉ አማራውን ከምንም ጥቅማጥቅም በማስወጣት በአማራነቱ እንዲያፍርና እንዲሸማቀቅ ለማድረግ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል።
ከአራት ዓመታት በፊት ለሀገራችን ብርቅየ የተባሉ አማራ ጀነራሎችንና ባለሌላ መእረግ ወታደሮችን ጨምሮ፤ ብዙ የአማራ ምሁራንን ከግንቦት ሰባት የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ መመስረትና መንቀሳቀስ ጋር በማያያዝ፤ በአባልነትና በመንግስት ግልበጣ ያለ ማስረጃ ከሶ እስከ እድሜ ልክ እስራት በማስፈረድ የቀጣው በአማራነታቸው ስለመሆኑ ዘራቸው እየተጠቀሰ ሲሰደቡና ሲንቋሸሹ እንደነበር በወያኔው ፍርድ ቤት የተገኙት ፍርደኞች በሕዝብ ፊት የተናገሩት ጉዳይ ነበር። ይህ ሁሉ ሲፈጸም ታዲያ ግፉ እየወረደበት ያለው አማራውም ሆነ ሌለው ሰቆቃ ቀማሽ የሀገራችን ሕዝብ ገና ከጥልቅ እንቅልፉ አልነቃም የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ይህስ ካልሆነ የፍርሃት መንገዱ እስከ ምን ድረስ ነው? ብለው የሚጠይቁም ብዙዎች ናቸው።
የተለያዩ ምክንያቶችን በመጠቀም አማራው ከስልጣን፣ ከእርሻና ከንግድ ቦታው፣ ከስራና ከመኖሪያ ቤቱ፣ ከትምህርትና ከተለያዩ የአመራር ቦታዎች ገለል እንዲል የማድረጉ ሂደት ሰሞኑንም በወያኔ መንደር በስፋት እየተተገበረ ነው። በመሰረቱ አሁን ባለው የህወሃት አገዛዝ አንድን ባለስልጣን በሙስና መክሰስ ላፍ ካልሆነ በቀር ውሃ የሚቋጥር አይደለም። ምክንያቱም ትልልቅ የህወሃት ጀነራሎችና ዋና ዋናዎቹ ባለስልጣናት የእለት ከእለት ስራቸው ሙስና መከወን ነውና። ስለሆነም ሰሞኑን በሙስና ሰበብ ከስራ የተባረሩትም ሆኑ የታሰሩት የወያኔ ባለስልጣናት አንዳንድ አሯሯጮች ከተጨመረላቸው በቀር በአማራነታቸው ምክንያት የራሳቸው ድርጅት የበላቸው አማራ ወያኔዎች ናቸው።
ይህን ሁሉ ግፍ እየተቀበለ ያለው አማራ ታዲያ ሕወሃት በልኩ የሰራለትን የማጣሪያ ወንፊት የሚበጣጥሰው መቼ ይሆን? ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብስ ከወያኔ የተንኮል ወጥመድ ወጥቶ፣ እርስ ለርስ ከመወነጃጀልና ከመበላላት ጸድቶ ከከሕወሃት በተቃራኒ በመቆም የሀገር ተስፋነቱን ለመቼ ይቆጥበዋል? ሕወሃት እንደሁ የጥፋት እጁን አስረዘመ እንጅ አልመለሰም፣ ማስፈራራትና ድንፋታውን ቀጠለበት እንጅ አልበረደም፣ ጫካ እያለ በቀየሰው የእልቂት መልገድ ቀጠለ እንጅ የሕዝብ ጥያቄም ሆነ የሀገርና የዓለም ነባራዊ ሁኔታ እቅዱን እንደገና እንዲፈትሽ አላስገደዱትም። ስለሆነም አሁን በሀገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከቀጠልንና  አንዱ ሲጠቃ ሌላው ካልረዳ፤ በእኛ ጩኸት ወቅት ከጎናችን የሚቆም እንዳናጣ ያሰጋል። ከመቼውም ጊዜ በባሰ መልኩ ወቅቱ መተባበርንና አንድ ሆኖ መቆምን የሚጠይቅበት ወቅት ነውና በአንድነት እንነሳ።

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate