Pages

May 23, 2013

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ ሰላማዊ ትግላችን ይቀጥላል!!!

ሰማያዊ ፓርቲ በመንግስት የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ድርጊቶች፣ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙና የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው ለመንግስት አካላት በተለያዩ ጊዚያት ጥሪ ቢያቀርብም ምላሽ ሊያገኝ ባለመቻሉ ጥሪውን ከፍ ባለ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ማሰማት እንዳለበት ወስኗል፡፡ በዚሁም መሰረት ሚያዚያ 29 ቀን 2005 ዓ.ም በሰጠው ጋዤጣዊ መግለጫ ፓርቲው ለመንግስት አካላት እስከ ዛሬ አቅርቦ ምላሽ አላገኙም ያላቸውን ጉዳዮች በመዘርዘር በመንግስት ላይ ያለውን ተቃውሞ ለመግለፅ ከግንቦት 15 እስከ 17 ቀን 2005 ዓ.ም ጥቁር ልብስ በመልበስ እንዲሁም ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ደግሞ በአፍሪካ ሕብረት ዋና ጽ/ቤት ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ተቃውሞውን ለመግለጽ የወሰነ በመሆኑ ፓርቲያችን ያነሳቸውን ጥያቄዎች የሚደግፍ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሲቪክ ማህበራትና ማንኛውም ኢትዮጵዊ ዜጋ በእነዚህ የሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፏል፡፡ 

ይህንን የፓርቲያችንን ጥሪ ለህዝቡና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እንዲዳረስ መገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ያደረጉት አስተዋፅዖ እጅግ የሚያስደንቅና የሚያስመሰግን ሲሆን ፓርቲው ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ ሕዝቡም በተጠቀሱት የሰላማዊ ትግል ስልቶች ለመሳተፍ ያለውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት በተለያዩ መንገዶች ለፓርቲያችን እየገለፀልን በመሆኑ ምስጋናችንን እያቀረብን አሁንም መረጃዎችን ሰው በሰው በማስተላለፍ ጭምር እያንዳንዱ ዜጋ በትግሉ እንዲሳተፍ መልዕክታችንን እናቀርባለን፡፡

ግንቦት 17 ቀን ቀን 2005 ዓ.ም በአፍሪካ ሕብረት ዋና ጽ/ቤት ፊት ለፊት የሚደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ በተመለከተ በህግ በተወሰነው መሰረት ሰልፉ የሚደረግ መሆኑን ማወቅ ላለበት አካል ግንቦት 14 ቀን 2005 ዓ.ም የማሳወቂያ ደብዳቤ የምናስገባ ሲሆን ለሰልፉም ሆነ ጥቅር ልብስ በመልበስ የሚደረገውን የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ የሚያስተባብረው ኮሚቴ ስራውን አጠናክሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በተቃውሞ እንቅስቃሴዎች የሚሳተፉ ሁሉ ፓርቲው የሚሰጠውን መመሪያዎች እንዲከተሉና ተቃዎሞአቸውን ሰላማዊ እና ህጋዊ በሆነው መንገድ ብቻ እንዲከናወኑና ጥሪያችንን እያስተላለፍን መገናኛ ብዙኃንም በዚህ በኩል ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን በድጋሜ እናቀርባለን፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

ግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate