Pages

May 24, 2013

ዜና በጨዋታ አይነት ነገር፤ ሰማያዊዎች አምርረዋል፤ አምረዋልም!

253297_418646384899981_1037053069_nየሰማያዊ ፓርቲ አመራር ግንቦት 14 ለአዲሳባ ስብስባ እና ሰላማዊ ሰልፍ “አዋቂ” ጽ/ቤት (ሙሉ ስሙን ረስቼዋለሁ… በህገ መንግስቱ መሰረት ሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ አይጠየቅም እወቁልን ነው የሚባለው… ስለዚህ ስሙን ከተሳሳትኩ እንኳ እንዲህ ነው መሆን ያለበት የሚል መከራከሪያ ላነሳ ፈልጌ ነው ማለት ነው…) ብቻ ለማሳወቅ ደብዳቤ ይዘው ቢሄዱ የጽ/ቤቱ ሃላፊዎች ደብዳቤውን አንቀበልም ብለው… “ገግመው” ነበር፡፡ “ገገመ” ቃሏ ከአራዳ ስትሆን እምቢ ማለት ሳይገባው እምቢ አለ… ለማለት ታገለግላለች፡፡
የጽ/ቤቱ ሃላፊዎች ለምን ደብዳቤውን አንቀበልም እንዳሉ እንጃላቸው… ምናልባት እነርሱም በመንግስታቸው የተከፉበት ጉዳ ይኖራል፡፡ (ይቺ የግዳጅ ቦንድ ግዢ እኮ ሰራተኞች የስራ ተነሳሽነት ላይ ከባድ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ነው ያላት….) የምሬን ነውኮ… እነዚህ ሃላፊዎች በመንግስታቸው ላይ ቅሬታ ባይኖራቸው ኖሮ ደብዳቤውን ተቀብለው …
ለሰማያዊ ፓርቲ ባሉበት፤
ደብዳቤያችሁን በጥሞና ተመልክተነዋል፡፡ ጥያቄያችሁ ህገ መንግስታዊ እና ተገቢም ነው፡፡ የስብሰባ እና ሰላማዊ ሰልፍ “አዋቂ” ጽ/ቤትም ይህንን አይነት ጥያቄዎችን ያበረታታል፡፡ ነገር ግን በዕለቱ እንግዶች ስለሚበዙ እና የጥበቃ ሃይላችንም ስራ ስለሚበዛበት መልካም ፈቃዳችሁ ሆኖ ሰላማዊ ሰልፋችሁን ለሌላ ግዜ ብታዘዋውሩት ደስታችን ወደር የለውም፡፡
ከሰላምታ ጋር!
አባይ ይገደባል ሰልፍም ይፈቀዳል፡፡
የማይታይ ማህተም እና ፊርማ፡፡
አድርጎ በጨዋ ደንብ መሸኘት ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግንብዙዎቹ የመንግስት ሰራተኞች በተለይ ከዚህ የግዳጅ ለአምስት መረባዊ አደረጃጀት እና የግዳጅ አባይ መዋጮ በኋላ አድማ ላይ ናቸው እና ደብዳቤ አንቀበልም ይላሉ፡፡ ይሄ ከስራ ማቆም አድማ ተለይቶ አይታይም፡፡ ይሄ ፈቃድ ካልተጠየቀበት ተቃውሞ ካለይቶ አይታይም፡፡
የሆነ ሆኖ አሁን ሰማያዊ ፓርቲ ደብዳቤውን በእማኞች ፊት ጠረቤዛ ላይ አስቀምጦ ወጥቷል፡፡ በህጉ መሰረት ሰልፉን ከማድረግ ምንም የሚያግደው ነገር የለም ማለት ነው… ትላንት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ጥቁር ለብሰው ውለዋል፡፡ ዛሬም፡፡ ነገ ደግሞ የሚጠበቀውን ሰልፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ስለዚህም ሰማያዊዎች አምርረዋል… አምረዋልም!

No comments:

Post a Comment

Total Pageviews

Translate